ግብረ ታሪክ፤
ከተግባር ስህተት የታሪክ ስህተት ይከፋል:: ደረጃው የተለያየ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ በተግባር ስምሪት ወቅት የሚፈጸም የአንድ አጋጣሚ ስህተት ወይ በእርማት ይስተካከላል አለያም ጉዳቱ እንዲቀንስና እንዳይደገም ጥንቃቄ እየተደረገ ለህፀፁ መፍትሔ ይፈለጋል:: የዕለት ተዕለት የሕይወት እንቅስቃሴ የሚያስተምረንና የሚያሳየን ይህንኑ እውነታ ነው:: የታሪክ ስህተትና ውጤቱ ግን እንደዚህ ቀላል የሚባል አይደለም:: አንድን ታላቅ ወንዝ ለሁልጊዜውም ከትሮ ለማቆም እንደማይሞከርና እንደማይቻል ሁሉ በሀገርና በሕዝብ ላይ የሚፈጸም ስህተትንም እንዲሁ ገድቦ ወይንም ሸሽጎ ማቆም አይቻልም:: ወንዝ ጠቃሚም ይሁን ጎጂ፤ ብቻ አሰስ ገሠሡን ይዞ እንደሚፈሰው ሁሉ የታሪክ ጉዞና ሸክምም ከዚህ ምሳሌ ጋር ይቀራረባል::
ባለማወቅም ይሁን ይሁነኝ ተብሎ በዜጎችና በሀገር ላይ የሚፈጸም ክህደትና ወንጀል ወይንም በጎነትና መልካምነት ከትውልድ ትውልድ የሚሸጋገረው ልክ እንደ ወንዝ ፍሰት ባለማቋረጥ ነው:: ከቃል ወደ ቃል፣ ወይንም በጽሑፍ፣ አለያም በተለያዩ የኪነ/ሥነ ጥበባት ዘውጎች እየተነገረ፣ እየቀለመና እየተከሸነ የሚተላለፍ የታሪክ ውርስ ጥቂት የመደብዘዝና አንዳንዴም የመከለስ ባህርይ ይስተዋልበት ካልሆነ በስተቀር ለትውልድ የሚደርሰው ፍንጩ ሳይጠፋ ነው:: ከዘመን ዘመን ቅብብሎሹም እንዲሁ::
ስለዚህም ነው በመልካሙ የሀገራችን ታሪኮች የምንኮራው፣ የምንደምቀው፣ በተፈጸሙት ስህተቶች የምንቆዝመውና በወይ ነዶ ቁጭት የምንንገበገበው:: አስረግጦ መናገር የሚቻለው ታሪክ ክስተት መዝጋቢ ብቻ ሳይሆን ፈራጅና ዳኛ ጭምር መሆኑን ነው:: በጎነትን ሲዘክር ስሜትን በሀሴት አግሎ የመንፈስን ቆፈን ይገፋል:: ስህተትን ሲያወሳ ደግሞ አሸማቆ አንገትን ያስደፋል:: ከዚህ ወዲያ ክብረት ከዚህ ወዲያ ክስረት ምን የበረታ ጉዳይ ይኖራል:: ዛሬ ኢትዮጵያን የገጠማት ሀገራዊ ዘርፈ ብዙ ፈተና የሚመደበው በዚህን መሰሉ እውነታ ሥር ነው:: በኢትዮጵያና በሕዝቧ የታሪክ ሰሌዳ ላይ በጥቁር ቀለም የሚታተም ጥቁር ጠባሳ ለማኖር የሚንፈራገጡት የጠላት ኃይላት የግፍ ዋንጫ ጨብጠው “ሉዓላዊ ክብሯን” ለመዳፈርና ለግላጭ ፍልሚያ አደባባይ ላይ መዋላቸው በአንድ ወገን፣ ይህንን ከአዳፋ ምኞት የመነጨ የታሪክ ጭቅቅት ለማጽዳት የሚደረግ የልጆቿ የደም አሻራ ትንቅንቅ በሌላ ወገን፤ “የመሆን ወይንም ያለመሆን” ተጋድሎው የተፋፋመው በዚሁ ምክንያት ነው::
ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት፤
እኛ ዜጎቿ “ኢትዮጵያ ምሥጢር ነች” ብለን የምናውጀው ራስን ለማንቆለጳጰስ ተፈልጎ ሳይሆን የፀና እውነትና መራሔ ታሪካችን ስለሆነ ነው:: ይህንን ጥልቅ ሃሳብ ከአካዳሚያዊ ትንተና ይልቅ ብዙው ሕዝብ ሊረዳው በሚችለው የአዘቦት ቋንቋ ለማብራራት እንሞክር:: አንዳንድ የቃላት አጠቃቀሞች ለሃይማኖትም ሆነ ለሳይንሳዊ ሙግት እንዳይዳረጉ የመቅድም አቤቱታ በማኖር ወደ ዋናው መነሻ ጉዳይ እናዝግም::
ኢትዮጵያ በዘመናት ውስጥ አንቱታን አትርፋ የኖረችው በድንግልና ክብሯ ነው:: ትናንት የነበረው የትውልዶቿ ፍሰትና ዛሬም ያጀቧት የማህኗ ፍሬዎች የተገኙትም ከድንግልናዋ አብራክ ነው:: ጥቂት የእንግዴ ልጆች መብቀላቸው ግን ሊዘነጋ አይገባም:: በግልጽ ምሳሌ እናብራራው:: የታላቋ ዓለማችንን የፖሊስነት ማዕረግ ለመንጠቅ የሚፋለሙትና “ታላቅ ነን!” በማለት የሚኩራሩት በርካታ ሀገራት እንደ ሀገር የተፈጠሩትበወራሪዎችና በተስፋፊዎች “ድንግልናቸው ተገስሶ” እና ደምና ታሪካቸው ከጠላቶቻቸው ወይንም ከወራሪዎቻቸው ጋር ተወራርሶ ነው:: አለያም በራሳቸው ጀብደኝነት የሌላውን ድንግልና ደፍረው “በመዋለዳቸው” ነው:: የብዙ ሀገራት የታሪክ መዛግብት የሚያስነብቡን ይህንን እውነታ ነው::
ጥቂት ዘለቅ ብለን እውነታውን እናፍታታው:: የበርካታ የዓለማችን ሀገራት ታሪክ የሚተርክልን ብጫዎቹ የሰው ዘሮች ከነጮቹ ጋር ወይንም ነጮቹና ጥቁሮቹ ከቀያዮቹ ጋር የተዛመዱትና የተዋለዱት በጦር ሜዳ ፍልሚያ ገባሪ ወይንም አስገባሪ በመሆን ነው:: የድንበራቸው ስፋትና ጥበት የተከለለውም በወረራ፣ በመስፋፋት አለያም በርስት ግዢ ጭምር የመሆኑ እውነታ ያስገርማል::
ለዚህን መሰሉ ዓለም አቀፍ እውነታ በጥሩ አብነት የምትጠቀሰው ዛሬ በራሳችን የሉዓላዊነት ጉዳይና በህልውናችን ወጭት ውስጥ እጇን እየሰደደች ካልፈተፈትኩ እያለች የምትታከከንና የምትሞግትን አሜሪካ ይሏት ሀገር ነች:: ይሁዳ ጌታውን ለመሸጥ ተዘጋጅቶም እንኳን ቢሆን እጁን ከኢየሱስ ጋር በወጭት ውስጥ ነክሮ አብሮ ማዕድ እንደቆረሰው መሆኑን ያስታውሷል::
ይህቺ “ከእኔ በላይ ታላቅ ሀገር ለአሳር!” እያለች የራሷን ክብር ሽቅብ እያጎነች የሌሎችን የምታንኳስሰው አሜሪካ አፈጣጠሯን በተመለከተ ከላይ በትክክል ለገለጽነው “በመደፈር የመፀነስና የመወለድ” ታሪክ ጥሩ ማሳያ መሆን የምትችል ናት::
እናብራራው:: አሜሪካ በአሥራ ሦስት የብሪቲሽ ኮሎኒ (የቅኝ ግዛት ስብስብ) ጁላይ 4 ቀን 1776 ዓ.ም “ተፈጥራና ነፃ ሀገር ተብላ” እውቅና ቢሰጣትም በቅኝ ገዢዋ በታላቋ ብሪታኒያ ተባርካ ጎጆ የወጣቸው ከ1783 ዓ.ም የፓሪሱ ስምምነት (Treaty of Paris) በኋላ ነበር:: ስለዚህም ነው አሜሪካ ተፀንሳ የተወለደችው “ድንግልናዋን በደፈሩ” ወራሪዎችና ጉልበተኞች ነው ለማለት የተበረታታነው:: ከዚሁ ታሪክ ጎን ለጎንም ግዛቶቿን ማስፋፋት የጀመረችው ዶላሯን ሆጨጭ አድርጋ ርስት በመግዛት ጭምር መሆኑ ሌላው መለያዋ ነው::
ልቡ እንዳበጠ የሠፈር ጎረምሳ “ሳትጠራ አቤት! ሳትላክ ወዴት!” ለማለት መደላድል የሆናትን የጀብደኝነት ታሪኳን በጥቂቱ እናስታውስ:: አሜሪካኖች ራሳቸውን የሚያስተዋውቁት “Melting Pot” እያሉ ነው:: ጽንሰ ሃሳቡ በቀላሉ ይብራራ ከተባለ ዜጎቿ የተሰባሰቡት ከልዩ ልዩ ሀገራት ልዩ ልዩ ባህል፣ ቋንቋና የሕይወት ተሞክሮ ኖሯቸው በተከማቹ የአዳም ዝርያዎች ነው ማለት ነው:: ወይንም የቋንቋችንን ዘይቤ በመጠቀም “Melting Pot” የሚለውን ጽንሰ ሃሳብ አቅልለን እንግለጸው ከተባለ በለማኝ አኩፋዳ ውስጥ በተጠቀጠቀ ድብልቅልቅ የምጽዋት የእህል ዓይነቶች ልንመስው እንችላለን:: ብስልና ጥሬ፣ ቂጣና ቆሎ፣ ፍትፍትና ፍርፍር፣ ሽሮና ቅቅል ወዘተ. የተቀላቀለበት እንደማለት ነው::
ጉዳዩን በአንድ አስገራሚ ታሪካቸው እናብራራው:: 49ኛው የሀገሪቱ ስቴት ሆኖ ለቤተሰብነት የበቃውና በተፈጥሮና በቱሪዝም ሀብቱ የናጠጠው፣ በወታደራዊና በኢኮኖሚ ትሩፋቱ የሚያስጎመጀው የአላስካ ግዛት ለሀገረ አሜሪካ አባል ስቴት ሆኖ የተመዘገበው በጃንዋሪ 3 ቀን 1959 ዓ.ም ነበር:: ይህ የቴክሳስን፣ የካሊፎርኒያንና የሞንታናን ያህል ስፋት ያለው ታላቅ ስቴት ከቀድሞዋ ሩሲያ በግዢ ወደ አሜሪካ የተላለፈው በካሬ ሜትር ሁለት ሳንቲም ሂሳብ ሆኖ በጠቅላላው 7.2 ሚሊዮን ዶላር ተከፍሎበት ነበር::
ይህንን ገንዘብ በ2020 ዓ.ም የገንዘብ አቅም ልክ እንመዝነው ከተባለ ስሌቱ 133 ሚሊዮን ዶላር ግድም ይሆናል:: በአጭር አገላለጽ በሰሜን ምዕራብ የአሜሪካ ግዛት ተንጣሎ የሚገኘው ያ ማህፀኑ በተፈጥሮ ሀብት የተባረከው ምድር የተገዛው ዛሬ ታላላቆቹ የዓለም የእግር ኳስ ክለቦች አንድን መለስተኛ የእግር ኳስ ተጫዋች በሚገዙበት ዋጋ ያህል እንደሆነ መገመት አይከብድም::
ከኢትዮጵያ ድንግል ማህፀን የተፈጠረው ትውልዷ ሀገሩን የአንድ ብዙ “ምሥጢር ነች!” እያለ የሚገልጻት አለምክንያት አይደለም:: ኢትዮጵያን በዘፍጥረት ታሪኳ ያበጃጃት አምላክ በልዩ ጥበብና የተፈጥሮ ፀጋ አስውቧት ነው:: ገነትን ከሚከቡት ከአራቱ ታላላቅ ወንዞች ጋር የግዮን ሚና መጠቀሱም ተረት ሳይሆን በመለኮታዊ ምሥጢር ተወስኖ ነው:: ሦስቱን የዓለም ታላላቅ ሃይማኖቶችን (ይሁዲ፣ ክርስትናና እስልምና) አክብራ መቀበሏና አከባብራ ማኖሯ ሌላው የመንፈሳዊ ምሥጢሯ ታላቅ መገለጫ ነው::
በዘመናት ውስጥ ጉልበታቸውን የፈተሹባትን ወራሪዎች ውርደት አከናንባ መመለሷና በነፃነቷ ክብር ፀንታ መቆሟ ሌላኛው የምሥጢራዊነቷ ማመላከቻ ነው:: ይህ ታሪኳ ከእርሷም አልፎ የተገፉ የዓለም ዜጎች ኩራት መሆኑ በራሱ እጅግ ያስደንቃል:: እኒህን መሰል የታሪክ ሃብቶቿን ያካበተችውና የትውልዷን ቁጥር እያበዛች የኖረችው በድንግልናዋ እንደተከበረችና እንደ ታፈረች “አንቱ” በመሰኘት ነው:: የሉዓላዊነቷ ክብር ተጠብቆ የኖረችውም በልጆቿ የደምና የአጥንት ቅጥር ታጥራ መሆኑ ሌላው የምሥጢሯ ፍቺ ነው::
ባለቅኔው ዮሐንስ አድማሱ “ከወዴት ዘረፍሽው” በሚል ርዕስ ሀገሩን በገለጸበት ረጅም ቅኔያዊ ግጥሙ ውስጥ ለማመልከት የሞከረው ይህንንው ምሥጢራዊ ባህርያዋን ነው:: ጥቂት ስንኞችን እንዋስ::
“ያን መሰል ተፈጥሮሽ የፍጥረት ይባቤ፣
ያን መሰል ተፈጥሮሽ ያካል ቅርጽ ይባቤ፣
ያን መሰል ውበትሽ የውበት ይባቤ፣
ከኅቱም ምድር እንጂ አይገኝ ከሩካቤ::”
[የቃላት ፍቺ፤ ይባቤ፡- ዕልልታ፣ ምሥጋና፣ መዝሙር:: ኅቱም፡- ድንግል:: ሩካቤ፡- ፍትወተ ሥጋ]
ኢትዮጵያ ለኢትዮጵያዊያን የዕድሜን ኮንትራት ያህል ተፈራርመው የሚኖሩባት ጊዜያዊ መኖሪያ ብቻም አይደለችም:: ከድንግል ማህፀኗ ለተገኙት ልጆቿ ትርጉሟ የላቀ ነው:: ሀገር የቆመችው በጀግኖች ልጆቿ ደምና አጥንት ተገንብታ መሆኑ ታሪኳ ምስክር ነው:: “እምዬ!” የምንላት እናት ኢትዮጵያ ሥረ ታሪኳ ተተርኮም ሆነ ተመንዝሮ የሚያልቅ አይደለም:: በቃላት ፍቺ ሊብራራ የማይችል የረቀቀ ምሥጢርም ነው::
ቀዳሚ ነገሥታቶቻችን ኢትዮጵያን የመሰሉት በበርካታ የተለመዱ አገላለጾች መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ የሁሉንም ሃሳብ ሊያጠቃልል በሚችለው በሚከተለው ገለጻ መደምደሙ የተሻለ ይሆናል:: ኢትዮጵያ ምሥጢር ነች:: የተፈጠረችውም ሆነ የፈጠረችን በድንግልናዋ ነው:: ተፈጥሮ የምትለግሰንና ስትለግሰን የኖረችው በረከት የሚገኘውም ከድንግልናዋ ማህፀን ውስጥ በሚገኘው ትሩፋት ነው:: የእናት ፍቅር፣ የእናት ርህራሄ፣ የእናት ምገባ፣ የእናት አለኝታነት ወዘተ. ይሄ ሁሉ መገለጫ የሚውለው የአንድ ብዙ ለሆነችው ኢትዮጵያ ነው:: ጠላቶቻችን ያላወቁት ምሥጢር ይህ ነው:: የአሸናፊነታችን ምሥጢሩም ይሄው ነው:: የአምላኳ ተራዳኢነት፣ የልጆቿ ጀግንነት፣ የሰላም ተምሳሌት መሆኗ:: ይሄው ነው:: ሰላም ይሁን!
(ጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን መስከረም 12/2014