ኢትዮጵያውያን ከጥንት ከጠዋቱ በሀገራቸው ጉዳይ ቀልድ አያውቁም። የሀገራቸውን ሉአላዊነት ሊዳፈር ለመጣ በአገራቸው ላይ እጁን ላነሳ፣ ሰይፍ ለመዘዘ፣ ጥይት ለተኮሰው ሁሉ አራስ ነብር ናቸው። በቁጣ ይነሳሉ። በቁጣ ይተማሉ። እንቢን ለሀገሬ ብለው ይዋደቃሉ፤ ይቆስላሉ ይሞታሉ።
ከጥንት ጀምሮ የሚታወቁትም በዚሁ የአልበገር ባይነትና የጀግንነት ታሪካቸው ነው። ለአገራቸው ሉዓላዊነት በሚሰሩት ጀበዱና በሚፈጽሙት ድል ነው። የሀገራችንን ነፃነት አስከብረው ፤ ዳር ድንበሯን ጠብቀውና አስጠበቀው ለዛሬው ትውልድ ያስረከቡት ለጠላት አንንበረከክም በሚል ተጋድሎ እና አሸናፊነት ነው።
ታዲያ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣውን ጀግንነት የአሁኖቹ ወጣቶችም ዳግም ሊደግሙት ተነስተዋል። አስቀድመው በተፃፈ የጀግንነት ታሪክ ብቻ ሳይሆን በታሪክ ሰሪነት የዘመናቸውን ታሪክ ሊጽፉ በፊታውራሪነት ለህልውና ዘመቻ ከፊት ተሰልፈዋል። ለእናት ሀገራችን ይፈሳል ደማችን ፤ይከሰከሳል አጥንታችን፤ ይሰዋል ህይወታችን ብለው በቆራጥነት የህልውና ዘመቻውን ተቀላቅለዋል ፤አሁንም በመቀላቀል ላይ ናቸው።
ኢትዮጵያውያን ክብር ለሀገሬ፤ ክብር ለኢትዮጵያ ፤እኔ እያለሁ በማንም አትደፈርም ሀገሬ በሚል ቆራጥነት ነው በየዘመኑ ሀገርን ለመውረር ዳርድንበሯን ለመድፈር የሚመጣን ጠላት ለመመከት ሆ ብለው የሚተሙት። ሀገርን ሊደፍርና ሊያስደፍር ለሚመጣ ጠላት ምሱን ሰጥቶ የሚመልሱትም። ኢትዮጵያውያን በታሪካቸው የማንንም አገር ሉዓላዊነት ተዳፍረው አያውቁም። በየዘመኑ ሀገርን ለማዳን ለሚቀርብላቸው የክተት ዘመቻ አንዴም ጨርቄን ማቄን ብለው አያውቁም።
ሁሉም ኢትዮጵያዊ ለአገር ነጻነትና ሉአላዊነት ሲጠራ አቤት ሲላክ ወዴት ብሎ በዓለም ላይ በቀኝ ያልተገዛች ብቸኛዋ ሀገር ለመሆን አብቅቷል። ዛሬም ይሄንኑ ከቀኝ ከግራ ከውስጥና ከውጭ ተሰናስሎ ሀገርን ለማፍረስ የመጣን ጠላት በጀግንነት ለመደምሰስ ተነሳስቷል።
አሸባሪው ህወሓት በጥቅምት 2013 ዓ/ም በሀገራችን ላይ ታሪክ የማይረሳው፤ ጭካኔ የተሞላውና ዘግናኝ ተግባራት ፈጽሟል። የህ ከሃዲ ኃይል ከውጭ ጠላት ጋር አብሮና ተባብሮ በሀገር ላይ ጥቃት ቢከፍትም ኢትዮጵያውያን በዝምታ አላዩትም። አጸፋውን ሊመልሱ ለህልውና ዘመቻው ከዳር እስከ ዳር በቁጣ አስገምግመው ተነሱ እንጂ። የዘመቻቸው መሰረት አውነትና ፍትህ ነበርና በየተሰማሩበት የድል ካባ እየተጎናጸፉም ይገኛሉ።
ወጣቱ ትውልድ በአጭር ጊዜም ከሃዲን ለመደምሰስና ትግሉን በድል ለመቋጨት እየተጋ ከሚገኘው፣ የሀገሩን ሉአላዊነት ለማስከበር በየዱሩ፣ በየሸንተረሩ ዝናብና ቁር ሳይበግረው እየተጋ ላለው፤ ማንኛውም መሰናክል ሳይበግረውና ቤት ንብረቴና ቤተሰቤ ሳይል ሀገር ከሚጠብቀው የመከላከያ ሰራዊት ጎን ተሰልፏል።
አሸባሪው ህወሓት ከፍጥረቱ አንስቶ በአሰቃቂ ሁኔታ የሀገር መከላከያ ሰራዊትን ከኋላው በመውጋት አሰቃቂ ተግባር እስከፈጸመበት ጊዜ ድረስ የእናት ሀገር ጡት ነካሽ ሆኖ ቆይቷል። ሀገርን ለማፍረስ ህዝብን ለመጨረስ ከውጭ ጠላቶች ጋር ሆኖ ታሪክ የማይረሳው ተግባር በመፈጸም ላይ ነው።
አሸባሪው ህወሓት ሀገርን ለጠላት አሳልፎ መስጠት ብቻም ሳይሆን በመንግሥታዊ አገዛዝነት በቆየባቸው 27 ዓመታት ሀገር በኢኮኖሚ እንዳታድግና ህዝቡም ተጠቃሚ እንዳይሆን በአንድ ቡድን የበላይነት ሁሉንም ጠቅልሎ ኪሱን ሲያደልብና ሀብትና ንብረት ሲያሸሽና በውጭ ሲያከማች ቆይቷል።
ይሄም አልበቃ ብሎ አሁን ደግሞ ‹‹ ሀገር እናፈርሳለን ፣ ሂሳብ እናወራርዳለን ፣ ያጣነውን ስልጣን ዳግም እንቆናጠጣለን ›› በሚል ቀቢጸ ተስፋ በሁሉም ሀገሪቱ ክፍል ሰላም ለማደፍረስ በመስራት ላይ ነው። በተለይም በአፋርና በአማራ ክልልና ህዝብ ላይ በከፈተው ወረራና ጦርነት የበርካታ ንጹሀን ዜጎች ህይወት ተቀጥፏል ሀብት ንብረት ወድሟል። ትምህርት ቤቶችና የጤና ተቋማት ተቃጥለዋል። ልጆች ያለወላጅ አዛውንቶች ያለ ጧሪ ቀርተዋል። ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ፣ ለተለያየ ችግር የተዳረጉት ደግሞ በርካቶች ናቸው።
ታዲያ ይህን የግፍ ግፍ እየፈጸመና ለውጪው ጠላት ተላላኪ ሆኖ ጠላት ሆኖ የሚሰራውን የሽብር ኃይል በመደምሰስ ህዝቦችን በነጻነት ለማኖር ለተጠራው የህልውና ዘመቻ የክተት ድምጽ መላው ኢትዮጵያውያን ሴት ወንድ፣ ወጣት አዛውንት ሳይል ሁሉም በየአቅጣጫው በተባበረ ክንድ መነሳቱ ተገቢና የሚጠበቅ ነው።
ወጣቱ በትልቅ አገራዊ ፍቅርና የጀግንነት ወኔ እናት ሀገሬን አላስደፍርም ብሎ የሀገር መከላከያ ሰራዊቱን ለመቀላቀል ሆ ብሎ ተሟል። ይሄ ደግሞ አዲስ ሳይሆን ከቀደመው ዘመን የቀጠለ ታሪካዊ ሂደትና ለዘመናት በወርቅ ቀለም ተጽፎ የሚዘከር ገድል ነው። ህይወቱን ሰጥቶ ሀገሩን ከወራሪዎች ሊጠብቅ በቆራጥነትና የጀግንነት ስሜት ተነስቷል። በአንድነት እንደመነሳቱም በአጭር ጊዜ የድል ብስራቱን ማብሰሩ አየቀሬ ነው።
አዲስ ዘመን መስከረም 12 ቀን 2014 ዓ.ም