በጎጥ በረት ውስጥ የተፈለፈለውና የጎሳ ጡጦ ጠብቶ ያደገው አሻባሪው የህወሓት ቡድን የማዕከላዊ መንግስቱን ስልጣን በተቆጣጠረበት ሃያ ሰባት አመታት ውስጥ አረመኔና ጨካኝ መሆኑን የሚያስመሰክሩ በርካታ ጥፋቶችን ፈፅሟል::
በኢትዮጵያ ህዝብ የጋራ ትግል ስልጣኑን ከተነጠቀ በኋላም የስልጣን አባዜ የሚያመጣው እብደት ከእኛ በላይ ላሳር በሚል ትእቢት ተወጥሮ እኩይ ምግባሩን ሲያስቀጥል ቆይቷል:: በተለይም ኢትዮጵያን መምራት የሚችለው ብቸኛ ድርጅት ‹‹እኔ ነኝ›› በሚል መረጃ እያምታታና በሚዲያ የበላይነት ራሱን ኢትዮጵያ ከምታክል አገር ይልቅ ለምእራባውያን ፍላጎት የተሻለ አድርጎ ሲያቀርብ ቆይቷል::
ቡድኑ ከዚህ የባንዳ ተግባሩ ባሻገር ኢትዮጵያን የሚፈልጋት እርሱ እስከ ገዛትና የትግራይ ብሄርተኝነት የበላይነትን ይዞ እስከቀጠለ ብቻ በመሆኑ የኢፌዲሪ መከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት በመሰንዘር ኢትዮጵያ ላይ በገሃድ ጦርነት ከፍቷል:: ኢትዮጵያም በቡድኑ እብሪትና ጥቃት ምክንያት ሳትፈልግ ጦርነት ውስጥ ለመግባት ተገዳለች::
ይሕ ሲሆን የአለም የዲሞክራሲና የሰብዓዊ መብት ጠበቃና አርአያ እንደሆኑ አድርገው የሚያስቀምጡት ምእራባውያንና አንዳንድ መገናኛ ብዙሃን በአንፃሩ የሽብር ቡድኑ የእብደት ተግባር እና ጥፋት አልታያቸውም:: ቡድኑ በማይካድራ ከተማ በንጹሃን ዜጎች ላይ የፈጸመው ጭፍጨፋና አስከፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት አላስደነገጣቸውም::
ቡድኑ የሚፈፅማቸውን በደሎች ሰምተው እንዳልሰማ፣ አይተው እንዳለየ፣ ገብቷቸው እንዳልገባቸው ሆነዋል:: አምነስቲ ኢንተርናሽናል የተሰኘው ተቋም በተጠናና በተቀነባበረ መልኩ የሽብር ቡድኑን የጭካኔ ጥግ የሚያስመሰክሩ ጭፍጨፋዎችን ከማጋለጥ ተቆጥቧል::
በተለይ የኢትዮጵያ መንግስት ለትግራይ ህዝብ በማዘንና የጥሞና ጊዜ ለመስጠት የአንድ ወገን የተኩስ አቁም ውሳኔ ሲያስተላልፍ በቅጡ ማመስገንም ሆነ ማድነቅ አልሆነላቸውም:: ከመንግስት በተቃራኒ የሽብር ቡድኑ ተኩስ ማቆም ፍላጎት እንደሌለው በተግባር ሲያሳይ አንዴም በቅጡ አልኮነኑትም::
ይሕን ተከትሎም አሸባሪው ቡድን በጦርነቱ ገፍቶበት በአዲስ መልክ ሂሳብ አወራርዳለሁ ብሎ መጥቷል:: ጦርነቱን ወደ አፋርና ወደ አማራው ክልል በመግፋት ለበርካቶች እልቂት፤ ምክንያት ሆኗል:: ወጣት፣ ሴቶች፤ ህጻናትና አዛውንቶች ጨፍጭፏል። ደፍሯል:: የእምነት ተቋማትን አቃጥሏል። ለመተካት የማይቻሉ ቅርሶች ሰርቋል:: አውድሟል። በድሃ ህዝብ የተሰሩ ክሊኒኮች፤ ሆስፒታሎች ዘርፏል:: አቃጥሏል። በርካቶችን ከቀያቸው እንዲፈናቀሉ ብሎም ሰው ሰራሽ እርሃብ እንዲከሰት አድርጓል::
ለቢራቢሮ ነፍስ ሁሉ ተቆርቋሪ ነን የሚሉን ምእራባውያን እና አንዳንድ መገናኛ ብዙሃን በአንፃሩ በሽብር ቡድኑ ጥፋት የሚሞተው ወገን፤ የሚባክነው ሃብት፤ የሚወድመው መሰረተ ልማት አልታያቸውም:: መሰል ተግባር ሲፈፅም መኮነን ቀርቶ አስተያየት ሲሰጡበት አላስተዋልንም::
ሌላው ቀርቶ በአለም አቀፍ ደረጃ ህፃናትን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ለጦርነት መመልመል፣ ማስታጠቅም፣ ሰላይነት መጠቀም እና ተሳታፊ ማድረግ በአለም አቀፍ ወንጀል የሚያስጠይቅ ሆኖ ሳለ አሸባሪው ቡድን ህፃናትን ለጦርነት እያሰለፈ መሆኑ በግልፅ አደባባይ እያስተዋሉ እንኳን የሚመለከታቸው አለም አቀፍ ተቋማት ዝምታን ሲመርጡ እያስተዋልን እንገኛለን::
ምእራባውያኑ ኢትዮጵያን ሉአላዊነት በመዳፈር ነፍስ እንዳላወቀ ህፃን ልጅ በሞግዚት አስተዳደር የማስተዳደርና የመጠበቅ ህልማቸውን ለማሳካት እየተውተሩ ናቸው:: ፍጹም ምክንያታዊ ባልሆነ መልኩ የግል ፍላጎትን ብቻ መሰረት በማድረግ የኢትዮጵያ መንግስት ከአሸባሪው ህወሓት ጋር የሚያደርገውን ፍልሚያ እንዲያቆም ግፊት በማድረግ ተጠምደዋል::
ኢትዮጵያ በየቦታው የቁጥጥር ኬላ አስቀምጣ እንቅስቃሴውን አጓተተችብን እያሉ በየትዊተሩ እና ዓለምዓቀፍ መድረክ ላይ እርግማን የሚያዘንቡ ተቋማትና ባለስልጣናት የአሸባሪው ቡድን ጭካኔ ብሎም ብልግና ለመናገር አፋቸው ተለጉሟል::
አሸባሪው ቡድን የጭካኔ ድርጊት ከማውገዝ ይልቅም በሰብዓዊነት ስም ለአሸባሪው ቡድን መተላለፊያ ኮሪደር ስለሚከፈትበት መንገድ ብዙ ሲጨነቁና ሲደክሙ እያየናቸው ነው:: ለፖለቲካ ሸሪኮቻቸው ሲሉ ኢሰብዓዊነትን እንደሚያበረታቱ እያሳዩን ይገኛሉ::
በዳይ እያለ ተበዳይን የሚቀጣውና በግል ፍላጎት እና በቡድን ይሁንታ ላይ መሰረት ያደረገ የካንጋሮ ፍርድ በመፍረድ ላይ ናቸው:: በእነርሱ ቡድናዊ የካንጋሮ አድሎአዊ ፍርድ አሸባሪው ህወሓት እያጠፋ፣ የሚቀጣው መንግስት ሆኗል። አሸባሪው ህወሓት እየገደለ፣ የሚወነጀለው መንግስትን፤ ቡድኑ እየዘረፈና ሀገር እያተራመሰ፣ የማዕቀብ ዛቻው የሚጎርፈው ኢትዮጵያ ሆኗል።
ይሕ ሁሉ ኢትዮጵያን እንደ ሃገር እንዳትቀጥል የማድረግ ሴራ ነው። ቢያውቁ ኢትዮጵያ ሰላሟ የተረጋገጠና አንድነቷ የተጠበቀ ሲሆን ጥቅማቸው ይከበራል::በአላስፈላጊ ጫና ኢትዮጵያ ላይ አደጋ ቢጋረጥ ጥቅማቸውን የሚያጡት እነሱ ናቸው::
ኢትዮጵያውያን በታሪካቸው ለማንም ጥገኛ ሆነው አያውቁም:: የጥገኝነት አስተሳሰብና ስነ ልቦና የሌለው ህዝብ በታሪክ ያጋጠሙትን ፈተናዎች ያለፈውም በጠንካራ አንድነቱና ህብረቱ ነው:: የተለያዩ የፖለቲካ አቋሞች ወይም ፍላጎቶች ቢኖሩ እና ተቃርኖ ያላቸው ወገኖች ጭምር በአገር ጉዳይ አቋማቸው ተመሳሳይ ነው::
ኢትዮጵያዊ በጠላት ፊት ያለ መንበርከክ ትልቅ የሞራል ልዕልና አለው:: ለጠላት በር አይከፍትም:: ለሃሳብ ልዕልና እንጂ ለጉልበት ቦታ አይሰጥም:: በሃሰተኛ ወሬ ሳይደናገር እውነትን ማረጋገጥ ላይ ያተኩራል:: በተጣራ ማስረጃ እንጂ በግርድፍ መረጃ አይበይንም:: ለፍትሕ፣ ለነፃነትና ለእኩልነት እንጂ ለአምባገነንነት አያጎበድድም::
ኢትዮጵያዊያን በሀገራቸው ክብር አይደራደሩም:: አይፈሩም:: አይደፈሩም:: አገራቸው መኩሪያቸውና መከበሪያቸው ናት:: ዜጎችዋ እናት አገራቸውን የመከራ ቋት አያደርጉም:: ባዕዳን ፍርፋሪ ሲሉ የአገራቸውን ሚስጥር አሳልፈው አይሰጡም:: ስለ ፍቅር እጅ ስለ ጠብ ከሆነ ነፍጥ ያነሳሉ:: ከአገራቸው ህልውና በላይ ምንም የሚበልጥበት ነገር እንደሌለም ታላቁን የዓድዋ ድል ጨምሮ በርካታ ተጋድሎዎቹ ህያው ምስክር ናቸው::
በየዘመናቱ የተነሱ ጠላቶቿን በህዝቦቿ አንድነት እና የጋራ ክንድ እያሳፈረች ዘመናትን የተሻገረችውና ለጥቁሮች የነፃነት ምልክት የሆነችው ኢትዮጵያ፣ ዛሬም እንደ ትላንቱ የገጠማትን ወቅታዊ ፈተና በብቃት ትወጣዋለች:: ዳር እስከ ዳር አንድ በመሆን በኢትዮጵያዊነት ስሜት ከመከላከያና ከመንግስት ጎን መሆኑን እያሳየ ይገኛል::
ይሕን ወቅታዊ ችግር ለመሻገርም ከበፊቱ በተሻለ መልኩ እጃችንን ልንሰበስብ ይገባናል:: ‹ድር ቢያብር አንበሳ ያስር› እንዲሉ እኛ በኢትዮጵያና በኢትዮጵያዊነት የምናምነው ሁሉ ለአገራችን ክብር እና ሞገስ እንዲሁም ብልጽግና በጋራ መረባረብ ይኖርብናል::
የውስጥ ችግራችንን ተጠቅመው ለከፋ ችግር እንዳይዳርጉን የውስጥ ችግሮችን መፍታት እና ለጊዜው በጋራ ጉዳይ ላይ ማለትም ብሔራዊ_ክብራችን አሳልፎ ባለመስጠትና በብሔራዊ_ጥቅማችን አለመደራደር ግድ ይለናል:: ሉአላዊነታችን ካላስደፈርን ሌላው እዳው ገብስ ነው። አንድነታችን ካጠናከርን አገራችንን ለመታደግ አንቸገርም:: ለጠላትም መጠቀሚያ አንሆንም።
ዓለምን ሁሉ እኛ ላይ የሚያደባና ከእኛ ጥቅም በተፃራሪ የቆመ አድርጎ ማሰቡም ስህተት መሆኑን መረዳት ይኖርብናል:: በአጠቃላይ አሁን ያሉት ችግሮች እንዳሉ ሆኖ ወርቃማ እድሎችን በጥንቃቄ በመጠቀም ትልቅ ታሪክ መስራት እንችላለን::
ታምራት ተስፋዬ
አዲስ ዘመን መስከረም 12 ቀን 2014 ዓ.ም