በኦሊምፒክ መድረክ የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳሊያ በአስር ሺ ሜትር ለአገሯና ለአፍሪካ ያስመዘገበችው ኮማንደር አትሌት ደራርቱ ቱሉ በአዲስ አበባ በተለምዶ አያት አደባባይ ተብሎ የሚጠራው አደባባይ በስሟ ተሰይሞ እንደሚመረቅ ታውቋል። በምረቃው ዕለትም ‹‹እኔም ለኢትዮጵያ ወታደር ነኝ›› በሚል መሪ ሃሳብ የሩጫ ውድድር የሚደረግ መሆኑን የለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ አስታውቋል።
በአዲስ አበባ ከተማ ካሉት አደባባዮች መካከል አንዱ በአዲሱ ለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ የሚገኘው አያት አደባባይ ተጠቃሽ ነው። ይኸው አደባባይም በጀግናዋና የብዙዎች ተምሳሌት በሆነችው ኮማንደር ደራርቱ ቱሉ ተሰይሟል። በባርሴሎና ኦሊምፒክ በ10ሺ ሜትር ለአፍሪካና ለአገሯ የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳሊያ ያጠለቀችው ደራርቱ፣ በጥቁር የሴት አትሌቶች ታሪክም በፈርቀዳጅነቷ ትጠቀሳለች። በርካታ ሴት አትሌቶችም እርሷን እንደ አርዓያ በመመልከት ወደ ስፖርቱ ገብተው ውጤታማም ሊሆኑ ችለዋል። ከአትሌትነት እስከ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አመራርነት እንዲሁም በማህበራዊ ጉዳዮች ላይ በምታደርገው ንቁ ተሳትፎ ጀግንነቷን በማስመስከርም ዘልቃለች። በመሆኑም የለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ቀድሞ ‹‹አያት›› በሚል የሚታወቀውን አደባባይ ‹‹ደራርቱ አደባባይ›› በሚል ሰይሞታል። በመጪው እሁድ መስከረም 16/2014 ዓ.ም አደባባዩ የሚመረቅም ይሆናል።
የለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ሻምበል ትዛዙ ውብሸት በኦሊምፒክ 10ሺ ሜትር የመጀመሪያዋ አፍሪካዊት ባለድል በመሆኗ እንዲሁም በተደጋጋሚ በረጅም ርቀት ሩጫ በማሸነፍ እንቁ የሆነችው ደራርቱ፤ ለአፍሪካ እንዲሁም ለኢትዮጵያም ቀንዲል ሆና የምትታይ መሆኗን ገልጸዋል። ይህቺን አትሌት ለማድነቅና ለማክበር እንዲሁም ለሌሎችም አርዓያ ሆና እንድትኖር አደባባዩ በስሟ ይጠራል። ይህም ክፍለ ከተማው እንዲሁም ከተማ አስተዳደሩ የወሰደው እርምጃ እጅግ የሚያስደስት መሆኑን ጠቁመዋል።
በዕለቱ ከሚደረገው የአደባባይ ምረቃ መርሃግብር ባሻገር የሩጫ ውድድር የሚካሄድ መሆኑንም ትናንት በክፍለ ከተማው ጽህፈት ቤት በተሰጠው መግለጫ ተጠቁሟል። ሩጫው የሚካሄደው ‹‹እኔም የኢትዮጵያ ወታደር ነኝ›› በሚል መሪ ሃሳብ ሲሆን፤ ለአገር መከላከያ ሰራዊት፣ ልዩ ኃይል እና የሚሊሻ አባላት ድጋፍ ለመግለጽ እንዲሁም ገንዘብ በማሰባሰብ ድጋፍ ማድረግንም አላማው አድርጓል። መነሻና መድረሻውን ደራርቱ አደባባይ የሚያደርገው ሩጫው 5ኪሎ ሜትር የሚሸፍን መሆኑም ታውቋል።
በሩጫው ላይ 3ሺ የሚሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ለመከላከያ ሰራዊት ደጀን መሆናቸውን ለማሳየት የሚሳተፉ ሲሆን፤ በአዲስ አበባ ከሚገኙ ክለቦች የተወጣጡ ታዋቂ አትሌቶች እንዲሁም አንጋፋ ስፖርተኞችም ይካፈላሉ። በሩጫው አሸናፊ የሚሆኑ አትሌቶች፣ አንጋፋ ስፖርተኞች እንዲሁም የህብረተሰብ ክፍልም በድምሩ የ100ሺ ብር ሽልማትም መዘጋጀቱን በክፍለ ከተማው ስፖርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አበባ አንሙት ገልጸዋል። ከኮሮና ቫይረሽ ስርጭት እንዲሁም ከጸጥታ ጋር በተያያዘም አስፈላጊው ቅድመ ጥንቃቄ ተደርጓል። በሩጫው ተሳታፊ ለመሆን የሚያስችለው የቲሸርት ሽያጭ በአዲስ አበባ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን፣ አዲስ አበባ ስታዲየም እንዲሁም በክፍለ ከተማው ባሉ ወረዳዎች በ500 ብር ማግኘት የሚቻል መሆኑም ተጠቁሟል። ከቲሸርት ሽያጭ የሚገኘው ገንዘብም ለሰራዊቱ ድጋፍ እንዲሆን በአዲስ አበባ ከተማ ስፖርት ኮሚሽን የታቀደው አካል እንደሚሆንም ታውቋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ለሩጫው ቴክኒካዊ ድጋፍ በማድረግ ተሳታፊ ሆኗል። የፌዴሬሽኑ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ እታፈራሁ ገብሬ ክፍለ ከተማው አዲስ ከመሆኑ አንጻር በፍጥነት ተደራጅቶ የአገር መከታ የሆነውን የአገር መከላከያ ሰራዊት ለመደገፍ ላደረገው እንቅስቃሴ አመስግነዋል። ፌዴሬሽኑ በአጭር ጊዜ ተቋቁሞና በጀትም ይዞ ቀድመው ከተቋቋሙት ፌዴሬሽኖች ቀድሞ መገኘቱ እንዲሁም አንጋፋ አትሌቶችን ማበረታቱ የሚያስመሰግነው ነው። በቀጣይም ቴክኒካዊ ድጋፍ በማድረግና አብሮ በመስራት የሚቀጥል መሆኑንም አብራርተዋል።
የለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ኤሊያስ መሃመድ፤ ክፍለ ከተማው ለአገር መከላከያ ሰራዊት የገንዘብ እገዛ ለማድረግ በሚካሄደው መርሃ ግብር ከከተማው አትሌቲክስ ፌዴሬሽን እንዲሁም ከክፍለ ከተማው በተወጣጣ ኮሚቴ እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል። ከእነዛ መካከል አንዱ በሆነው ሩጫ ‹‹እኔም ለኢትዮጵያ ወታደር ነኝ›› በሚል ለአገሩ ህይወቱን ለሚሰዋው መከላከያ ሰራዊት ድጋፍ ለማዋል በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን መስከረም 11 ቀን 2014 ዓ.ም