‹ገዴ› ‹ቢሰጠኝ› እና ‹የፍቅር ግርማ› የተሰኙ ሶስት አልበሞችን በግል አውጥታለች።ከ‹ስለ ኢትዮጵያ› አልበም በፊት ሶስት አልበሞችን ከሌሎች ድምጻዊያን ጋር በህብረት ሰርታለች።‹እወድሀለሁ› በሚለው ነጠላ ዜማዋ እ.አ.አ. በ2004 በምስራቅ አፍሪካ ምርጥ የሴት ድምጻዊያን ዘርፍ ከኢትዮጵያ የመጀመሪያዋ የኮራን ሽልማት ማግኘት የቻለች ድምጻዊ ናት።በ2008 ዓ.ም ‹የት ብዬ› በተሰኘው ለ‹ሀሪየት› ፊልም ማጀቢያ በተሰራው ሙዚቃዋ የአፍሪማ የጉማ እና የለዛ ሽልማቶችን አሸንፋለች።በሀገር እና ማህበራዊ ኃላፊነትን በመወጣት ወደኋላ የማትለው ድምጻዊቷ በኤች አይ ቪ ኤድስ ዙሪያ ‹ማለባበስ ይቅር›፣ ‹መላ መላ› እና ‹መታመን ማመን› የተሰኙ ነጠላ ዜማዎች ላይ ተሳትፋለች።በእናቶች ላይ በወሊድ ጊዜ የሚደርስ ሞትን ለመቀነስ እና በህጻናት የምግብ አመጋገብ ላይ ያተኮሩ በፌስቱላ ግንዛቤ ለማስጨበጥ ባለመ እና በህዳሴ ግድብ ላይ በተሰሩ ሙዚቃዎች ላይ ተሳታፊ ነበረች።በአዲሱ ‹ስለኢትዮጵያ› አልበም ላይ ‹የኔ ቀለም› የሚል ሙዚቃ አበርክታለች።ስለ ኢትዮጵያ አልበም እና ስለ ጀግኒት ንቅናቄ ጠይቀናታል።
አዲስ ዘመን፡- በቅርቡ “ስለ ኢትዮጵያ” የሚል አዲስ አልበም አውጥታችኋል፤ ለመሆኑ ይህ አልበም እንዲሰራ ምክንያት የሆናችሁ ምንድነው?
ድምጻዊ ጸደኒያ፡- ሀገራዊ ሙዚቃዎች ሁሌ ይሰራሉ፤ ግን ለምን በአንድ ላይ አናደርገውም ብለን ነው ያሰብነው።የእኔ እንኳን ቀደም ብሎ ለራሴ አልበም ሀገራዊ ዜማ እንዲሆን ከዓመት በፊት የሰራሁት ሙዚቃ ነበር።ከጓደኞቼ ለምን እንደአልበም አብረን አንሰራውም የሚል ጥያቄ ሲመጣ ሙዚቃውን ሰጠኋቸው።በአንድ አልበም ላይ ‹ስለኢትዮጵያ› በሚል ርዕስ ሰራነው።ሁልጊዜ ስለሀገር ይሰራል፤ እንደ ኢትዮጵያ ስለሀገር እና ስለሰላም የተዘመረበት ሀገር የለም እዚች ምድር ላይ።ስለዚህ ያንኑ ነው ያደረግነው።ለአዲስ ዓመት ስጦታ ብለን ለኢትዮጵያ ያቀረብነው ስራ ነው።ሁሉም በቅንነት በህብረት ሀገርን በማሰብ የሰራው ስራ ነው።ሀገራችን መቼም እንደታሸች እፎይ ሳትል አትቀጥልም።እንደሀገር እፎይ የምትልበትን ጊዜ ከወዲሁ መልካም ምኞት ለመግለጽ የሰራነው ስራ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- በአልበሙ ላይ እነማን ተሳተፉ?
ድምጻዊ ጸደኒያ፡- “ስለ ኢትዮጵያ” ከ110 በላይ ባለሙያ ተሳትፎበታል።ሙዚቀኛ፣ አቀናባሪ፣ የግጥምና ዜማ ደራሲም በአጠቃላይ ከ110 በላይ ባለሙያ ተሳትፎበታል።ነብሱን ይማረው እና ጋሽ አለማየሁ እሸቴም የመጨረሻ ስራውን የሰራው እዚህ አልበም ላይ ነው።በሁለት አልበም ሁለቱም አልበም 14 ሙዚቃዎች ባጠቃላይ 28 ሙዚቃዎች የያዘ ሲዲ ነው የተሰራው፡፡
አዲስ ዘመን፡- በአልበሙ ላይ የተካተቱ ስራዎች በጋራ የሚታዩበት ሂደት ነበረው ወይስ ሁሉም ያለውን ነው የሰጠው?
ድምጻዊ ጸደኒያ፡- የሚበዛው እንዳውም ለዚህ አልበም ታስበው አዲስ የተሰሩ ናቸው።አብዛኛው ግጥምና ዜማው ሙዚቃ ቅንብሩ፤ ማስተር እና ሚክስ ተደርጎ በ20 ቀን ውስጥ ነው ያለቀው።በጣም ጥቂቶቹ ናቸው ቀድመው የተሰሩት፤ እነሱም ቢሆን የተጀመሩትም ያላለቁ ገና በጅምር ላይ ብቻ ያሉ ናቸው።የኔ ብቻም ሳይሆን አይቀርም አልቆ የነበረው እና አብዛኛው ስራ በ20 ቀን ውስጥ ተጀምሮ የተጠናቀቀ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያዊነት በእጅጉ እንዲቀጭጭ ተደርጓል የሚሉ አሉ፤ በቅርቡ ግን ይህ ሁኔታ ተቀይሮ ኢትዮጵያዊነት በአዲስ መልኩ እያንሰራራ ነው፤ ለመሆኑ ኢትዮጵያዊነትን አንቺ እንዴት ትገልጪዋለሽ? አልበሙ ውስጥ የተካተተው ያንቺ ዘፈንስ መልዕክቱ ምንድ ነው?
ድምጻዊ ጸደኒያ፡- ‹ስለኢትዮጵያ› አልበም ላይ እኔ የሰራሁት ‹የኔ ቀለም› የሚል ነው።ሀሳቡ በዋናነት ለሀገር ስለሚከፈል ውለታ ነው።
እርምጃሽን ተከትዬ ከፍ ዝቁን ልችልልሽ
ዝማሜሽን የሚያቀና ያሰብኩትን ልሰፍርልሽ
ውለታሽን ልመልስ ስል የምሰጠው አጣሁልሽ
ሀገሬ ሆይ አበድሪኝ ሀገር ስሆን የምከፍልሽ—-ሀገሬ ይላል።
ሀገራዊ ስሜትን ለመፍጠር ለራሴው በፈለኩት ተነሳሽነት ነው ይሄንን ሙዚቃ ልሰራ የቻልኩት።ሀገርን እንዲህ ብለሽ የምትገልጪው ነገር አይደለም።ሁሉም ለየሀገሩ ክብር አለው።ሁሉም ለያለበት እና ለተወለደበት ሀገር ክብር አለው።ከኢትዮጵያ ውጪ ያሉትም ሰዎች ለሀገራቸው ክብር አላቸው።እኔም ለተወለድኩበት ሀገሬ የምሰጠው ቦታ እና ክብር አለ።ለኖርኩበት ለእናት ሀገሬ መሆን መድረስ ነው።ሀገር ደግሞ ሁሉም ላደገበት እትብቱ ለተቀበረበት ለሚያቀው ማንነትም የሚመሰረተው ሀገር ላይ ነው።ስለዚህ ማንነት ነው ብዬ ነው የማስበው።የኔ ማንነት ሀገር ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- በተለያዩ ወቅቶች አርቲስቶች ስለሃገራቸው አዚመዋል፤ ስለሃገራቸው ከሃገር መከላከያ ሰራዊት የማይተናነስ ጀብድ ፈጽመዋል፤ ሀገር ችግር ውስጥ በምትሆንበት ጊዜ የአርቲስቶች ሚና ምን ያህል ሃያል ነው ትያለሽ?
ድምጻዊ ጸደኒያ፡- ለሀገር ይሄ የእከሌ ይሄኛው የእንትና የሚባል ነገር የለውም።እኛም ለሀገር ካለን የሀገር ፍቅር ስሜት እና ለሙዚቃችን ካለን ክብር ስለሀገራችን በመዝፈን አስተዋጽኦ አደረግን።ይሄ የእከሌ ድርሻ የምትይው አይደለም፤ ሁሉም እንደሙያው እንደችሎታው እና እንደአቅሙ ያደርጋል።ይሄ የእኛ ስራ ብቻ አይደለም።ሁሉም እያደረገ ነው፤ እናንተም እንደጋዜጠኝነታችሁ ታደርጋላችሁ።የምንኖረው እዚች ምድር ላይ እስከሆነ ድረስ ለማንም ስንል ሳይሆን ለራሳችን ስንል ነው የምንችለውን እያደረግን ያለነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ማህበራዊ ሚዲያ ላይ ተጠቃሚ ነሽ፤ በተለይ ትዊተር ላይ የህዳሴ ግድብን ስትደግፊ እናያለን።ከዚህ በተቃራኒው ኢትዮጵያዊ ሆነው በማህበራዊ ሚዲያ አፍራሽ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ አሉ፤ እነዚህ ወገኖች ከዚህ ድርጊታቸው እንዲወጡ ምን መልዕክት አለሽ?
ድምጻዊ ጸደኒያ፡- አይ ስራቸው ያውጣቸው፤ ምን አስበው እንደሆነ አላውቅም።ጀርባቸው ከምን በመነሳት እንደሆነ ስለማላውቅ እንዲህ ነው እንዲህ ነው ልል አልችልም።ግን ስራቸው ያውጣቸው ከማለት በስተቀር ጊዜም የለኝም ለእንደዚህ አይነት ነገሮች።እውነቱን ንገሪኝ ካልሽ ለመጥፎ ሀሳብ ብዙም ቦታ አልሰጠውም፤ ስራቸው ያውጣቸው።ምናልባት የኢትዮጵያዊነት ስሜት የማይሰማቸው ሰዎች ሊሆኑ ይችላሉ።የኢትዮጵያዊነት ስሜት የማይሰማቸው ሰዎች ስለሆኑ ከምን አጀንዳ ተነስተው እንደሚቃወሙ ስለማላውቅ እንዲህነው ልልሽ አልችልም።በደፈናው የኢትዮጵያዊነት ስሜት የማይሰማቸው ሰዎች ናቸው።
አዲስ ዘመን፡- በጀግኒት ንቅናቄ አምባሳደር ነሽ፤ሴቶች በወር አበባ ምክንያት ከትምህርት ቤት እንዳይቀሩ ስትንቀሳቀሱ ነበር።ይህ እንቅስቃሴአችሁ ምን ውጤት አስገኘ? አሁንም የትምህርት ቤት መከፈቻ ወቅት ላይ ነንና ያሰባችሁት ነገር ካለ?
ድምጻዊ ጸደኒያ፡- ያለፈው ዓመት ለ3ሺ ተማሪዎች ነበር የወር አበባ ንጽህና መጠበቂያ አሰባስበን የሰጠነው።አሁን ደግሞ 50ሺ ብለን ተነስተናል።ካለፈው የሚለየው ያኔ 3ሺ የሰጠነው ሞዴስ አንዴ ተጠቅመው የሚጥሉት ነበር።በአሁኑ ግን ያዘጋጀነው የሚታጠብ ነው።ምክንያቱም ካለው ሁኔታ አንጻር ዋጋውም አስተማማኝ አይደለም።ከዋጋ እና አካባቢንም ከመበከል አንጻር ስናየው አንዴ ተጠቅሞ የሚጣለው ብዙ አያዋጣም።ስለዚህ ብርቄ የሚል ፓኬጅ አዘጋጅተናል።
ብርቄ ማለት ትንሽዬ ባልዲ ውስጥ የውስጥ ሱሪ አራት የሚታጠብ የንጽህና መጠበቂያ ሞዴስ፣ የሞዴስ ማጠቢያ ፈሳሽ ሳሙና እና ፊሽካ የያዘ ነው።ፊሽካው እንግዲህ አደጋ እንኳን ቢደርስባት ፊሽካውን በመንፋት የሚያስጥላትን ሰው ለመጥራት እንዲያስችላት ነው። ይሄን ያዘጋጀነው የገጠሪቷን ኢትዮጵያን እያሰብን ነው፤ በእግራቸው ብዙ ኪሎ ሜትሮች ሄደው የሚማሩ ልጃገረዶች ስላሉ ለደህንነታቸው ነው።ለአንድ ልጅ የመደብነው 220 ብር ነው።አንድ ልጃገረድ በ220 ብር ለ18 ወር እንድትጠቀም ማድረግ ይቻላል።
አንዴ ተጠቅሞ የሚጣለው ቢሆን ኖሮ በጣም ውድ ስለሚሆን አዋጪ አይሆንም።ግባችን ለአንድ ሚሊየን ልጃገረዶች ይሄን አገልግሎት ማድረስ ነው።ምን ያህል ጊዜ ይፈጅብናል የሚለውን አናውቅም።ግን ያለፈው 3ሺ ነበር፤ አሁን 50ሺ ብለናል።እንዲህ እያለ እየጨመርን እንሄዳለን።ትምህርት ከመጀመሩ በፊት ለሴት ተማሪዎች ይሄንን ለማዳረስ እቅድ ላይ ነን፤ ለዚህም ዘመቻው ተጀምሯል፡፡
ልጃገረዶች በንጽህና መጠበቂያ እጥረት ከትምህርት ገበታቸው እንዳይቀሩ ማገዝ የሚፈልጉ ሰዎች በንግድ ባንክ፣ በህብረት ባንክ እና በኦሮሚያ ህብረት ስራ ባንክ አካውንት አለ፤ በዛ በኩል መርዳት ይችላሉ።በነዚህ አካውንቶች በሚገኘው ብር እኛ ገዝተን እናቀርባለን።ገንዘብ መላክ ያልፈለጉ እና እራሳቸው በአካል ሄደው መግዛት የሚፈልጉም ለገጣፎ አደይ ፓድ የሚባል ፋብሪካ አለ። ከዛ በመግዛት ለሚያስፈልጋቸው አካላት በእኛም በኩል በግላቸውም ማድረስ ይችላሉ።እኛ በጀግኒት ለ50ሺ ሴቶች ለማዳረስ አቅደን እየሄድን ነው፤ የሚፈልጉ አካላት ከእኛ ጋር በጋራ በመሆን ወይም በግላቸው እንዲደርስ ማድረግ ይችላሉ፡፡
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ በዝግጅት ክፍሉ እና በአንባቢያን ስም አመሰግናለሁ!
ድምጻዊ ጸደኒያ፡- እኔም እድሉን ስለሰጠሽኝ አመሰግናለሁ!
ቤዛ እሸቱ
አዲስ ዘመን መስከረም 11 ቀን 2014 ዓ.ም