ሴትነት በብዙ ነገር ፈተና የሚደርስበት ቢሆንም ታግለውት ከወጡበት ግን መጽሐፍ እንደሆነ እሙን ነው።እንደ መጽሐፍ የሚነበብ ብዙ ነገሮችን የሚያስተምር ነው።በተለይም ጥሩ አንባቢ ካገኘ የህይወትን ውጣ ውረድ ከእነስኬቱ ቁልጭ አድርጎ ያሳያል።የነገ መንገድንም ይመራል።በእሳት ያልተፈተነ ወርቅ ስለሌለ በህይወት የተፈተነ ሴትም እንዲህ እንደወርቁ ውድ መሆኑ አይቀርም።ይህንን ደግሞ በተግባር የሚያሳዩ ብዙ ሴቶችን እናገኛለን።ዛሬ የምናቀርብላችሁም ሴት ከእነዚህ መካከል አንዷ ነች።የህይወት መምህርነቷ ደግሞ ከትምህርት ጋር የተያያዘ ነው።
እንግዳችን ወይዘሮ ቱሩፋት በላይነህ ትባላለች።የፌደራል ፍርድ ቤት ረዳት ዳኛና ጠበቃ ነበረች።ዛሬ ደግሞ በአምቦ ዩኒቨርሲቲ የህግ አማካሪ በመሆን እየሰራች ሲሆን፤ ከዲፕሎማ ተነስታ ሁለተኛ ዲግሪዋን የሰራች ነች።በዚህ ጉዞዋ ብዙ ፈተናዎችን ያሳለፈች ሲሆን፤ በተለይ ልጅ እያጠቡ መማርን በተሞክሮዋ ታስተምራለች።እናም ከህይወቷ ትማሩ ዘንድ ጋበዝናችሁ።
አስተዳደግ ለእርሷ
ቤተሰብ ልጅን ይሰራል፤ ለቁም ነገርም ያበቃል።በተለይም ጥንካሬ፣ ጀግንነትና ተስፋ አለመቁረጥን ያስተምራል።ይህ የሚሆነው ግን ብዙ መንገዶችን በማሳያት ነው።የመጀመሪያው ደግሞ ሆኖ ማሳየት ሲሆን፤ የቅርብ ተጠሪና አርአያ እናቶች፣ አባቶችና ታላላቅ ልጆች ናቸው።በዚህም የቀጣይ የልጆች የወደፊት እጣ ፋንታ በእነዚህ አካላት ላይ ይሆናል።በተለይም የሴት ልጅ ህይወት የሚመሰረተው በእነዚህ እድል ወሳኝ አካላት መሆኑን ከራሷ የህይወት ተሞክሮ ተነስታ ታስረዳለች።የእርሷ ቤተሰቦች የዛሬ ህይወቷን እንደሰጧትም ታምናለች።
የቱሩፋት ቤተሰቦች በህይወት ብቻ ሳይሆን በቀለምም መምህሮቿ ነበሩ።በዚህም በሁለቱም የተሳለ ሰይፍ ሆና እንድታድግ አድርገዋታል።በተለይም ሴት ልጅ ማደግና ራሷን መቻል የምትችለው ስትማር ብቻ ነው የሚለው አቋሟ እንዲጸና ያደረጋት ይህ የቤተሰቦቿ ስሪት እንደሆነ ትናገራለች።ቤተሰብ ብቻ ለልጁ ስኬታማነት መልፋት እንደሌለበትም ታምናለች።በዚህም የሚሰጧትን መመሪያ ፍንክች ብላ አታውቅም።ይልቁንም ጨምራበት፣ አጎልብታው ትገኛለች።ይህ ደግሞ በትምህርቷም ሆነ በህይወቷ ስኬታማ ሆና እንድትቀጥል አድርጓታል።
‹‹እናቴ ለዛሬ እዚህ መድረሴ መሰረቴ ናት።የትምህርትን ዋጋ ራሷ ሆና አሳይታኛለች።ተስፋ ሳይቆርጡና ልጅ ኖሮ መማር እንደሚቻል ምሳሌዬ ሆናለች።በተለይም ያሰቡበት ላይ ለመድረስ የማያስችሉ ፈተናዎችን እንዴት ማለፍ እንዳለብኝ በሚገባ አስተምራኛለች።ሴትነት ከወንድ ብቻ ሳይሆን ከተፈጥሮም ፈተና የሚግጥምበት መሆኑን በእርሷ አይቻለሁ።ስለዚህም እናት እናት ብቻ አይደለችም።የህይወት መምህር፤ የወደፊት ተስፋ ሰጪና ቀጣይን መንገድ አስተካካይ ሆናልኛለች፡፡›› የምትለው ወይዘሮ ቱሩፋት፤ ሴቶች ወደፊት መሆን የሚፈልጉት ነገር ካላቸው ዛሬ ላይ ከእናታቸው ጋር እየተመካከሩ ነጋቸውን ማብራት እንዳለባቸው ትመክራለች።
አስተዳደግ ኑሮ ነው።በተለይም ለሴት ልጆች።ምክንያቱም የልጅነት አዕምሮ ውስጥ የሚቀመጥ ማንኛውም ባህል፣ ወግና ልማድ እንዲሁም የቤተሰብና የጎረቤት ቦታ ሰጪነት ማንነትን የሚያስቀምጥ ነው።እያሸማቀቁና እየገፉን ካኖሩን ወደፊት መገስገስን አናስብም።ስለሆነም ይህንን መጋፈጥ ላይ መስራት የግል ተግባራችን መሆን አለበትም ትላለች።ነገን የምናየው ዛሬ ባለምነው ልክ እንደሆነም ማመን ይኖርብናል ባይ ናት።አስተዳደጋችን ነጋችንን በሚያነጋ መልኩ ልናደርገው የምንችለው እኛው ነን የሚል አቋምም አላት።
ትምህርትና ሴትነት
የእርሷ የትምህርት ሀሁ የጀመረው በተወለደችበት ቀዬ ሰሜን ሸዋ ዞን ፍቼ ከተማ ግራጃርሶ ወረዳ ሲሆን፤ የመምህር ልጅ ብትሆንም መጀመሪያ ደረጃ ላይ ጎበዝ ተማሪ ግን አልነበረችም።መካከለኛ ላይ ትቀመጣለች።ነገር ግን የእናትና አባቷ ሥራ ማቅለልና ትምህርቷ ላይ እንድታተኩር መገፋፋት ራሷን ከጊዜ ወደ ጊዜ እንድታይ አድርጓታል።ከዘጠነኛ ክፍል በኋላ መነሳሳቱ የመጣውና የደረጃ ተማሪ የሆነችውም ለዚህ ነው።ውጤቷ እስከ 12ኛ ክፍል ያስቀጥላት ነበር።ይሁን እንጂ ይህም ሆኖ ከ10ኛ ክፍል ትምህርቷን በማቋረጥ በአቋራጭ የልጅነት ህልሟን ፍለጋ ገብታለች።እዚህም ላይ ቢሆን ማንም አላስቆማትም።መሰረቱ የጸናን ማን ይንደዋል።
ከአስረኛ ክፍል ትምህርቷን አቋርጣ ዲፕሎማ ነጆ የግብርና ትምህርት ቤት የገባችው ወይዘሮ ቱሩፋት፤ በግብርና የትምህርት መስክ በከፍተኛ ውጤት መመረቅ የቻለች ነች።ከዚያ ዓመት ከሰራች በኋላ የመጀመሪያ ዲግሪዋን በዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ በህግ የትምህርት መሰክ በክፍያ መማር ችላለች።በከፍተኛ ውጤትም ተመርቃለች።ይህ ደግሞ የተሻለ ቦታ ላይ ተቀምጣ እንድትሰራ አድርጓታል።ሆኖም ለትምህርት ቅድሚያ ትሰጣለችና ይህንን ትታ ሁለተኛ ዲግሪዋን ለመማር በአምቦ ዩኒቨርሲቲ ትምህርቷን ለመከታተል ገባች።በኮሜርሽያል ሎው (የንግድ ህግ) ትምህርቷን 3 ነጥብ 7 በማምጣት አጠናቃለችም።በዚህ ጊዜ ውስጥ በእርሷ ባች ብቸኛ ተመራቂ ነች።ምክንያቱም ተመራቂዎቹ በኮሮና ምክንያትና በሌሎች ችግሮች ሳቢያ የዛሬዋን ቀን ማየት አልቻሉም።በተጨማሪም ከ10 ተማሪዎች ውስጥ በውጤት እየመሩና እስከመጨረሻው የቀጠሉ ሁለት ሴት ተማሪዎች ውስጥ አንዷ ነበረች።ለዚህ ደግሞ ቆራጥ መሆኗ አግዟታል።
ከትምህርቷ ጋር በተያያዘ በጣም የሚያስገርመውና ጥንካሬዋን የሚያሳየው ሁለተኛ ዲግሪዋን ስትማር የነበረባት ፈተናና የእርሷ ውጣ ውረዱን የመቋቋም ሁኔታ ነው።በዩኒቨርሲቲው የህግ አማካሪ ነች።ህጻን ልጅም አላት።የቤት ውስጥ ሥራውም ቢሆን የእርሷ ነው።ይህ ሆኖም ግን የስኬቷ መሰረት ትምህርት ነውና ልታቆመው አልወደደችም።እየሰራች፣ ልጇን እያጠባች፤ ሰራተኛዋ ስትሄድባት ደግሞ ክፍል ውስጥና ሥራ ቦታ ጭምር ህጻኗን ይዛ እየሄደች የዛሬውን ሁለተኛ ዲግሪ በጥሩ ውጤት ማጠናቀቅ ችላለች።
ወይዘሮ ቱሩፋት ሴት ልጅ በተለይም የገጠር ልጅ ስትሆን ጠቃሚነቷ የሚታየው ከመማር ይልቅ ከቤት ውስጥ ሥራ ጋር በተያያዘ ብቻ ነው።ይህ ደግሞ ብዙ እድሎችን ይዘጋባታል።ከዚያ ስታልፍም ቢሆን ሁሉም ሰው ይቀናባታል።ሴቶች ሳይቀሩ እንዴት አደረገችው የሚሏት ናት።ይህ ሁሉ ግን በአንድ ነገር ድባቅ ይመታል።በትግዕስትና ተስፋ ባለመቁረጥ።ያሰቡት ላይ ደርሶ በማሳየት።ይህንን ቢተገብሩትና ባህሪያቸው ቢያደርጉት ለውጣቸውና ስኬታቸው ሩቅ እንደማይሆንም ታስረዳለች።
ከዚህ ጋር ተያይዞ አንድ ነገር አጥብቃ ትናገራለች።‹‹ሴቶች ልጅ ስለማሳድግ ትምህርቴን መማር አልቻልኩም፤ እንዴት ይህ ይሆንልኛል፤ የልጅ እናት ነኝ ወዘተ የሚል ሰበብ ካበዙ መቼም ቢሆን ያሰቡት ላይ አይደርሱም።ልጅ ሲመጣ ጉልበት ይሆናል።ምክንያቱም የነገ ተስፋ የምንሰጠው፤ የተሻለ ነገር ከእኛ የሚፈልግ አካል እንዳለ ያሳስበናል።የተሻለ ገቢ ማምጣት እንዳለብን ያስጠነቅቀናል።ካልተማሩና ካልተለወጡ ደግሞ ይህንን ማሳካት በፍጹም አይታሰብም።እናም ያንን እያሰቡና የተሻለውን እያለሙ ለልጆቻችን የነገ እድል ሰጪዎች ለመሆን እንተጋለን።እኔም ያደረኩት ይህንን ነው፡፡›› ብላለች።
እንግዳችን ሴት ልጅ ስትማር የሚገፋት ብዙ ነገር አለ።በተለይም የተማረው ሀይል ከእኔ እኩል መሆን የለባትም፤ ልትበልጠኝም አይገባትም ብሎ ያስባታል፤ ያደናቅፋታልም።መምህራንም ቢሆኑ እንዲሁ ብዙ ፈተና የሚያደርሱባት ነች።በተለይም የመጀመሪያ ዲግሪ ተማሪዎች ላይ የሚታየው ነገር በጣም አሳዛኝ ነው።መምህራን ሴት ልጅ ላይ ጥቃት ፈጽመው ህግም ሆነ ተፈጻሚነት ስለሌለው ነገሮች ይደባበቃሉ።በዚህም ሴቶችም መናገር ይፈራሉ።ይህ ደግሞ የሥነልቦና ጫና ጭምር እየደረሰባቸው እንዲማሩ ይሆናሉ።ፍራቻም በዚያው ልክ ስኬታማ እንዳይሆኑ ያደርጋቸዋል።ስለዚህም ሁሉም ላይ እንዲገኙ ከተፈለገና አቅማቸውን እንዲያሳዩ ከታሰበ የህግ ባለሙያዎችም ሆኑ መንግስት እዚህ ላይ ትልቅ ሥራ መስራት እንዳለበት ታስገነዝባለች።
ሥራና ሴትነት
ሴት ልጅ ባትቀጠርም ሁልጊዜ ሰራተኛ ናት።ከተቀጠረች ደግሞ የበለጠ ሰራተኛ ትሆናለች።ምክንያቱም የቤቱም የመስሪያ ቤቱም ሀላፊነት በእርሷ እጅ ላይ እንዳለ ይሰማታል።በዚህም ለሁለቱም እኩል የምትሰራና የምትኖር፤ የምትሞት ጭምርም እንደሆነች ማንም ያምናል።እርሷ ባለችበት የሚጎድል ነገር አይኖርም።በትንሹ እንኳን ብንወስድ ሴት የምትመራው ተቋምና ወንድ የሚመራው ተቋም ንጽህናው እኩል አይደለም።አሰራሩና ቅልጥፍናውም እንዲሁ።ስለዚህም ሴት ልጅ ቦታው ሁሉ የሚያምርላትና ሁሉን ነገር የምታጣፍጥ ጨው ነች።ለዚህም በለውጡ መንግስት የተመረጡና በአመራርነት ቦታ ላይ የተቀመጡ ሴቶችን ብቻ ማየት በቂ ነው፡፡
እነርሱ ባሉበት ሁልጊዜ ድልና ብስራት ይሰማል።እንባም ይታበሳል።መሆንና መስራት ጭምር የሚታየው በእነርሱ ሥራ ነው።አሁን ላይ በሚታዩ ሴቶች ዝም ያሉና አይሆንልኝም የሚሉ ሴቶች ሲነሱ አይተናል።ለዚህም ሌላ ሳልጠቅስ ራሴን ማንሳት እችላለሁ የምትለው ቱሩፋት፤ ለእኔ የአገራችን ፕሬዚዳንት ክብርት ሳህለወርቅ፣ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት መአዛና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አዳነች አርአያዎቼ ናቸው።እነርሱን በማየቴ ዲግሪ ይበቃኛል ብዬ የተቀመጥኩትን አንቅተውኛል።ሁለተኛ ዲግሪዬን መማር እንድችል መሪ ሆነውኛል።ስለሆነም በእነዚህና መሰል አርአያ ሴቶች አማካኝነት ብዙዎች መማር ልጅ መውለድ አይገድበውምን፤ መማር እድሜ አይገድበውምን፤ መማር እስከዚህ ድረስ የሚባል መስፈርት አይሰጠውምን ተምረዋል ብዬ አምናለሁም ብላናለች።
ቱሩፋት በስራ ህይወቷ በግብርና በተመረቀችበት ሙያ ነጆ በግብርናው ዘርፍ ባለሙያ ሆና ዓመት ያህል ማህበረሰቡን በባለሙያነት አገልግላለች።ከዚያ የመጀመሪያ ዲግሪዋን ስትይዝ ደግሞ በፌደራል ፍርድ ቤት ረዳት ዳኛና ጠበቃ በመሆን አራት ዓመት ሰርታለች።በመቀጠል ለትምህርት አምቦ ዩኒቨርሲቲ በመግባቷ ሥራዋን ወደዚያ በማዞር የህግ አማካሪ በመሆን መስራት ችላለች።በእርግጥ አምቦ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በቆየችባቸው ጊዜያት ውስጥም ከህግ አማካሪነቷ ጎን ለጎን ብዙ የሰራቻቸው ተግባራት አሉ።እንደውም በዓመት ቆይታዋ ይህንን ያህል ከሰራች ከዚያ በላይ መስራት እንደምትችል ያየችበት እንደሆነም አጫውታናለች።
ሴትን የሚመለከት ጉዳይ የእኔ ነው እምነቷ ነው።በዚህም የሴቶች ዳይሬክቶሬቱን በማገዝ የትምህርት ቤቱ ሰራተኞችና ተማሪዎች በህይወታቸው ላይ ምክክር እንዲያደርጉ የተለያዩ መድረኮችን ትፈጥራለች።በተመሳሳይ ለውጥ የሚባለው ምን አይነት ነው የሚለውን እንዲያውቁ ልዩ ዝግጅት በማድረግም ላይ ትሰራለች።ከእነዚህ መካከል አንዱ ሰራተኞቹ አካባቢያቸውን እንዲያውቁ እንጦጦ ፓርክ ድረስ በመውሰድ ያዘጋጀችው የህይወት ውይይት ልዩ ቦታ የሚሰጠው ነበር። እንደ እነመአዛ አሸናፊ አይነት ትልልቅ እንግዶች የተጋበዙበት በመሆኑም ብዙ ልምድ ተቀስሞ የተመለሱበት እንደነበር ታስታውሳለች።
ዛሬም፣ ነገም እስከ ህይወት ፍጻሜ ድረስ ሴቶች ይችላሉ የሚለውን እያንዳንዱ ሴት ሆኖ ማሳየት አለበት እምነቷ የሆነው ቱሩፋት፤ እርሷም አርአያ ለመሆን እንደምትሰራ ታስረዳለች።ቀጣይ ህልሟም ሁለት ነገር እንደሆነ ነግራናለች።መጀመሪያው የልጅነት ህልሟ የሆነው ሰዎችን መርዳት ሲሆን፤ ለዚህም ትልቅ ፕሮጀክት ነድፋ እየተንቀሳቀሰች ነው።በተለይም እንደአበበች ጎበና አይነት የአገር ባለውለታ ሰዎችን ማስታወስ ላይ ፍላጎቷ ነው።የእርሳቸውን ታሪክ የያዘ ፊልም ለመስራትም ብዙ ነገሮቿን የጨረሰች እንደሆነ ገልጻልናለች።ይሁንና አንዳንድ እገዛዎች ስለሚያስፈልጓት ሀሳቡን የወደደው ሁሉ እንዲረባረብ ጥሪ አቅርባለች።
ሌላውና ሁለተኛው እቅዷ ሴት ልጅ ካልተማረች የፈለገችውን አታገኝም የሚለውን እምነቷን እውን የምታደርግበት ሲሆን፤ ይህም ሶስተኛ ዲግሪዋን መማር ነው።ስለዚህም ጊዜ ሳትሰጥ እንደምታደርገው አውግታናለች።ለዚህ ደግሞ ባለቤቷና ቤተሰቦቿ እንደሚያግዟት እምነቷ ነው።ለሴቶች እናት አባት እንዲሁም ባለቤቶች መልዕክቷም የእኔን ቤተሰብ እድል ስጥዋቸው ነው።ምክንያቷም ሴት ልጅ የአገር፣ የቤተሰብ፣ የኑሮ ማገር ነች።ግለሰብና አገር ብቻ ሳይሆን ዓለምን ጭምር ትለውጣለች።ስለሆነም ማንኛውም ሰው ለራሱ ካሰበ ለሴቶች ይስራ እምነቷም፤ አቋሟም በመሆኑ ነው።
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን መስከረም 11 ቀን 2014 ዓ.ም