ከወደ ቻይና የወደፊት የሳይንስና ቴክኖሎጂ ተስፋ የሆኑ ኢትዮጵያውያን ብቅ ማለታቸውን ሰምተናል። እነዚህ አምስት ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች በቻይና ቤጂንግ በተካሄደው የዓለም ሮቦት ቴክኖሎጂ ውድድር ሻምፒዮና የወርቅ፣ የብርና የነሐስ ሜዳሊያ በማምጣት ማሸነፋቸውን ተሰምቷል። በቻይናዋ ርዕሰ መዲና ቤጂንግ እ.ኤ.አ የ2021 የሮቦት ቴክኖሎጂ ውድድር መካሄዱን የአገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።
በዚህም በቻይና ቲያን ጂን ዩኒቨርሲቲ የሚማሩ አምስት ኢትዮጵያውያን በውድደሩ አምስት ሜዳሊያ እንዳሸነፉ በቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄኔራል ዉ ፔንግ ተገልጿል። ዳይሬክተር ጀነራሉ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያውያኑ የሮቦት ውድድሩን ያሸነፉት አንድ ወርቅ፣ ሁለት የብርና ሁለት የነሐስ ሜዳሊያ በማምጣት ነው “ለመላው ኢትዮጵያውያንና ለአሸናፊዎቹ ከፍተኛ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት ማስተላለፍ እፈልጋለሁም” ብለዋል።
በዓለም አቀፉ የሮቦት ቴክኖሎጂ የፈጠራ ክህሎት ውድድር ኢትዮጵያን የወከሉ ወጣት ተማሪዎች አሸናፊ መሆናቸው ትርጉሙ ከፍ ያለ ነው። አገራችን ከዘርፉ የሚገኘውን ጥቅም ለመቋደስና በኢኮኖሚና በስልጣኔ እድገት ላይ ያለውን ትርፋት ለመጠቀም እነዚህን መሰል ወጣቶች ያስፈልጓታል። በተለይ መሰል ውድድሮች ላይ የሚሳተፉና ለድል የሚበቁ ጀግኖች መኖራቸው በዚህ ዘርፍ ላይ አዳዲስ የፈጠራ ስራዎች ላይ ለመሰማራት ለሚፈልጉ በርካታ ታዳጊዎች ተስፋን የሚፈነጥቅ ነው።
የቴክኖሎጂ ዘርፍ አሁናዊ ገፅታ
ዓለማችን በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ በላቀ ሁኔታ ዘምናለች። የሰው ልጅ አእምሮውን ተጠቅሞ የእለት ተእለት ኑሮውን ከማቀላጠፉም በላይ በእጅጉ የረቀቁ ቴክኖሎጂዎችን በመፍጠር ለማመን የሚከብዱ የፈጠራ ውጤቶችንን እያስተዋወቀ ይገኛል።
በቴክኖሎጂው ዘርፍ ጊዜን፣ ጉልበትንና ጥራትን በየጊዜው ከማሻሻሉም በላይ በምድራችን ላይ ያልተገለጡ ሚስጢራትን ለመገንዘብ እንዲያስችለው አግዞታል። ነግቶ በመሸ ቁጥር የሰውን ልጅ ድንቅ የማሰብና የመተግበር አቅም ልህቀት የሚመሰክሩ የቴክኖሎጂና ሳይንሳዊ ፈጠራዎች ይፋ ሲሆኑ እንሰማለን።
ወጣቶች የግል ክህሎታቸውን ተጠቅመው ችግሮች የሚፈቱና ኑሮን የሚያሻሽሉ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ውጤቶችን ይፋ ያደርጋሉ። የትምህርት ተቋማት በየጊዜው ችግሮችን በመንቀስ፣ ጥናትና ምርምር በማድረግ በግብርናው፣ በትራንስፖርቱ፣ በመሰረተ ልማት እንዲሁም በመሰል ጉዳዮች ላይ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ያስተዋውቃሉ። የልህቀት ማእከል ይገነባሉ።
ይህ ብቻ አይደለም ዘርፉ ከፍተኛ ፉክክርና ውድድር የሚታይበት ነው። ሃብታም አገራት የበላይነታቸውንና ጡንቻቸውን የሚያሳዩት በቴክኖሎጂ አቅማቸው ነው። ወታደራዊ አቅማቸውን የሚያጠናክሩት፣ ግብርናቸውን ኢኮኖሚያቸውንና የከተሞቻቸውን ስልጣኔ የሚገነቡት የሳይንስና ቴክኖሎጂ የፈጠራ ውጤቶቻቸው ላይ ተመስርተው ነው።
ኢትዮጵያ-አርቴፊሻል ኢንተለጀንት
የኢትዮጵያ መንግስት “በሮቦት ሳይንስ” እንዲሁም በአጠቃላይ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ የሚታየውን ክፍተት ለመሙላት የተለያዩ የምርምር ማእከላትን ይፋ ለማድረግ ቁርጠኝነቱን እያሳየ ይገኛል። በተለይ በዘርፉ ብሩህ አእምሮ ያላቸው ወጣቶች ምቹ ሁኔታ እንዲፈጠርላቸው በመስራት ላይ ነው። ይህን ሃላፊነት የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት እየተመራ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚገኙ ተማሪዎች ውጤታማ እንዲሆኑ ለማድረግ እንደሚሰራ ይታወቃል። ከዚህ በተጓዳኝ በግል ጥረት የማህበረሰብ ችግር ይፈታሉ ተብሎ የሚታሰቡ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ለማስተዋወቅ የሚተጉ ወጣቶችን በመንግስት ክትትል ስር እንዲሆኑና የተሻለ ድጋፍ እንዲያገኙ ለማድረግ የሚሰራው ስራ የሚበረታታ ነው።
አሁን አሁን ከሙከራ የምርምር ስራ ባሻገር በተግባር ተሞክረው ውጤት ማሳየት የቻሉ የቴክኖሎጂ ፈጠራ ስራዎችን ያስተዋወቁ በርካቶች ናቸው። ለምሳሌ ያህል “ሶፊያ” የተሰኘች በዓለማችን የሮቦት ቴክኖሎጂዎች እውቅናዋ ከፍተኛ የሆነ አርቴፊሻል ኢንተለጀንት ዘርፍ የፈጠራ ውጤት ላይ እውቋ ቤተልሄም ደሴ ቀዳሚ ተሳታፊ እንደነበረች የሚዘነጋ አይደለም።
የተለያዩ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ናይጄሪያ፣ጋና፣ ኬኒያ እና ደቡብ አፍሪካ በአርቴፊሻል ኢንተለጀንትና በተለያዩ ዘርፎች ላይ ህይወትን የሚያቀሉ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በማስተዋወቅ ከአፍሪካ ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛሉ። የኢትዮጵያ መንግስት “የአራተኛው ትውልድ” የቴክኖሎጂና ሳይንስ አብዮትን መቀላቀል አስፈላጊነት ላይ በማመኑ የተለየ ትኩረት አድርጎ እየሰራ ነው። በቅርቡ ሳተላይት ከማምጠቅ ጀምሮ የግብርናውንና መሰል ዘርፎችን ለማዘመን የሚሰራውን ስራ መጥቀስ አስፈላጊ ነው።
በተጨማሪ በግል ጥረታቸው እጅግ አስደናቂ የፈጠራ ውጤቶችን የሚያስተዋውቁ ወጣቶችን በኢትዮጵያ ውስጥ ብቅ ብቅ እያሉ ይገኛሉ። ከነዚህ መካከል ደግሞ በመግቢያችን ላይ የጠቀስናቸው ሰላሙ ይስሃቅ፣ አባኩማ ጌታቸውና ፀጋዬ አለሙ ተጠቃሽ ናቸው። ይህን ስንመለከት ኢትዮጵያ በቴክኖሎጂው ዘርፍ የላቀ ውጤት ለማምጣትና ወደ በለፀጉት አገራት ተርታ ለመሰለፍ የምታደርገው ጉዞና ራዕይ ሩቅ አለመሆኑን ነው።
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን መስከረም 11 ቀን 2014 ዓ.ም