አሮጌው ዓመት ጓዙን ጠቅልሎ ሲወጣ፤ አዲሱ ዓመት ሲመጣ ሁሉም ሰው እቅድ ያቅዳል። ዲፕሎማ ያለው ዲግሪ፣ ዲግሪ ያለው ማስተርስ፣ ማስተርስ ያለው ዶክትሬት ለመስራት፤ ቤት የሌላው ቤት ለመግዛት (ለመስራት)፤ ያላገባ ለማግባት፤ ያልወለደ ልጅ ወልዶ ለመሳም፤ ነጋዴው በሃብቱ ላይ ሃብት ለመጨመር ብቻ ምን አለፋችሁ ሁሉም እንደ አቅሙ አዲስ ዓመት ሲመጣ በዓመቱ ውስጥ ምን መሥራት እንዳለብን ማቀድ የተለመደ ነው፡፡
ነገር ግን “የሺህ ፍልጥ ማሰሪያው ልጥ” እንደሚባለው፤ እቅዳችን ተሳክቶ ያለምንበት ለመድረስ አገር ጸንታ መቆም አለባት። አገር ሰላሟ መጠበቅ አለበት። አገር ሰላሟና ሉአላዊነቷ ካልተጠበቀ በታቀደው እቅድ ተመርቶ፣ በተሰጡት መክሊት ወርዶ ወጥቶ ማትረፍ ይቅርና በህይወት መኖር በራሱ ጥያቄ ምልክት ውስጥ እንደሚገባ ማንም ቢሆን የሚያውቀው ሃቅ ነው።
ያለፈው ዓመት ለኢትዮጵያዊያን ከባድ ዓመት ነበር። እንደ ሀገር ብዙ ተግዳሮቶች የተፈጠሩበት፤ ብዙ ጉዳት የደረሰበት፤ ደግሞም ብዙ ድል የተገኘበት ዓመት ነው። የጁንታው የሰሜን እዝ ጥቃት እና እሱን ተከተሎ የተፈጠሩ ወታደራዊ፤ ፖለቲካዊ፤ ዲፕሎማሲዊ፤ ኢኮኖሚያዊ፤ ማህበራዊ ውጥንቅጦች የ2013 ታሪክ ዋነኛ አካል ነበሩ። እነዚህ በተግዳሮትነት ሊጠቀሱ ቢችሉም የህዳሴ ግድብ ሙሊት እና 6ኛው ብሔራዊ ምርጫ በሰላም መጠናቀቅም የአገሪቱ የዓመቱ የስኬት ታሪክ ሆኖ አልፏል፡፡
የጥፋት ቡድኑ ስልጣን ላይ በነበረበት 27 ዓመታት አራቁቷት ባዶዋን ያስቀራትን አገር “እኛ የበላይ ሆነን እንደለመድነው ፈላጭ ቆራጭ ካልሆን፣ ሲኦልም ቢሆን ወርደን እናፈርሳታለን፤ ኢትዮጵያን ለማፍረስ አይደለም ከሰው ጋር ከሰይጣን ጋርም ቢሆን እንተባበራለን፤ ታላቋን አገር አፍርሰን የጎጥ አገር እንመሰርታለን” በሚል በጀመረው የሞት ሽረት ትግል የኢትዮጵያን ህዝብ አገር አልባ ለማድረግ እየተሟሟተ ይገኛል።
ይህ ብቻ አይደለም በ21 ክፍለ ዘመን አጀብ የሚያሰኝ ጋብቻ ከአሸባሪው የሸኔ ቡድን ጋር በመፈጸምም አገሪቱን እንደ የመን፣ ሊቢያ እና ሶሪያ የጦር አውድማ ለማድረግ፤ እንደሶቬት ህብረት ለመበታተን ቋምጠዋል። ለዚህም ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር ሳይቀር ህብረት ፈጥሯል።
ዛሬ ከመቼውም ጊዜ በላይ ኢትዮጵያ እጆቿን ዘርግታ የልጆቿን ብርቱነት ትሻለች። ልጆችዋ በጋራ እንዲጠብቅዋት እና ከተጋረጠባት አደጋ እንዲታደጓትም ትፈልጋለች። ወቅቱ ከመቼውም ጊዜ በላይ፤ ዜጎች በአንድነት ቆመው ለሀገር ያላቸው ፍቅር ከምንም በላይ መሆኑን በተግባር የሚያሳዩበት ነው። ወቅቱ እያንዳንዱ ዜጋ አገሬ ምን አደረገችልኝ ሳይሆን እኔ ለአገሬ ምን አደረግኩ ብሎ ራሱን ሊጠይቅ የተገባበት ነው፡፡
ዛሬ በአሸባሪው ህወሓት የተስፋ መቁረጥ ተግባር ብዙ ኢትዮጵያዊያን ተወልደው አድገው ለዘመናት ከኖሩበት ቀያቸውና አድባራቸው ተፈናቅለዋል። ኢትዮጵያን ሊንዱ ባቀዱ ቡድኖች በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ሰዎች ነፍሳቸው ተጨንቋል። ሁሉም በተሰጠው መክሊት ወጥቶ ወርዶ አገሩን ከመፍረስ አደጋ መታደግ፤ የወገንን እንባ ማበስ ወቅቱ የሚጠይቀው አስገዳጅ ተግባር ነው፡፡
የኢትዮጵያ የውስጥና የውጭ ታሪካዊ ጠላቶች አገሪቱን ለማፍረስ ትናንትም ዛሬም ያልፈነቀሉት ድንጋይ፤ ያልገቡበት ጉድጓድ የለም። ትልቁ በእውነታ ግን ኢትዮጵያን አገሬ ምን አደረገችልኝ ሳይሉ፤ “ከሀገሬ እኔ ልቅደም” በሚለው አብሯቸው ዘመናት በተሻገረው ማንነታቸው ሀገሪቱ እንደ ሀገር አስከብረው ኖረዋል። በታሪክ ከብረው ስማቸውን ከሰማይ በላይ አስቀምጠዋል።
ኢትዮጵያን ያሉ ፈራሽ ገላ ሰጥተው የማትፈርስ አገር አቆይተዋል። ኢትዮጵያን ያሉ የአሸናፊነት ዝማሪን አቆይተውልን አልፈዋል። ኢትዮጵያን ያሉ የነጻነት ቀንዲል አድርገውን በሰላም አሸልቧል። ኢትዮጵያን ያሉ የተከበረች፣ የተፈራችና ያልተሸነፈች ሀገር አቆይተዋል። ሀገርን በፅኑ መሠረት ላይ አቁመው የዘመናት ትርክት ሆነው አንቀላፍተዋል።
ኢትዮጵያዊነት ምስጢሩ ብዙ ነው። የኢትዮጵያዊነት ስሜት እናዳፍንህ ቢሉት የማይዳፈን፣ እናፍንህ ቢሉት የማይታፈን፣ ልርሳው ቢሉት የማይረሳ ረቂቅ ነው። ለዚህም ነው፤ ጠላቶች ኢትዮጵያን ሊያጠፏት ባሰቡ ቁጥር የምትጎላባቸው፤ ሊጥሉት ሲከጅሉ የምትጠነክረው። ዛሬም እንደቀደሙት ዘመናት ኢትዮጵያን ለመናድ የሚፍጨረጨሩ ሀይሎች በራሳቸው ክፋት እየከሰሙ ሲሄዱ እያየናቸው ነው።
አሁን ላይ እንደሀገር የሚያስፈልገን ፤ እኔ ለሀገሬ ምን ሰራሁ እንጂ “እነእገሌ ሀገሬን ጉድ ሰሯት” በሚል እጃችንን አጣጥፈን መቀመጡ አይደለም፡፡ እንደአባቶቻችን ቀፎው እንደተነካ ንብ ‹‹ሆ›› ብለን በህብረት ወጥተን በኢትዮጵያ “በአይናችን” የመጡ ጠላቶቻችን ታሪክ ለማድረግ ከመቼውም ጊዜ በላይ በአንድነት የምንሰለፍበት ጊዜ አሁን ነው።
አገራችን ከውጭና ከውስጥ የተጋረጠባትን አደጋ በተባበረ ክንድ ለመመከት ሁሉም “እኔ ለአገሬ ምን አደረግሁላት” በሚል በተሰማራበት የስራ ዘርፍ አገሩን አሁን ከገባችበት ውጥንቅጥ ወጥታ ዛሬም እንደትናንቱ ታፍራና ተከብራ እንድትኖር የበኩሉን አስተዋጽኦ ሊያበረክት ይገባል። በዚህም የአባቶቻችን ልጆች መሆናችንን በተጨባጭ ማሳየት አለብን።
ወታደሩ በተሰለፈበት የጦር ግንባር የአገሩን ማተብ አጥብቆ እንደጀመረው ጠላትን ማንበርበሩን፣ ዱቄት ማድረጉን አጥብቆ መቀጠል አለበት። ወቅቱ ነግደን የምናተርፈበት ሳይሆን የምንተጋገዝበት በመሆኑ ነጋዴው አውቆ ገበያውን በማረጋጋት አገሪቱ የተከፈተባትን የኢኮኖሚ አሻጥር መመከት አለበት።
ባለሀብቱ ገንዘብ በባንክ ቤት አስቀምጦ ባንክ የሚያጨናንቅበት ጊዜ ሳይሆን በዱር በገደል ለሚጋደለው ወንድም እና እህቱ ድጋፍ የሚያደርግበት ሊሆን ይገባል። ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ወገኖቹን ለማቋቋም ያለ ማንም ጎትጎች ሊንቀሳቀስ የተገባበት፤ በጥፋት ኃይሎች የወደሙ መሰረተ ልማቶችን መልሶ ለመገንባት የበኩሉን ድጋፍ የሚያደርግበት ወቅት ነው።
እንዲሁም የመንግስት ሰራተኛው ወገኑን አጎንብሶ የሚያገለግልበት እንጂ የሚያንጓጥጥበትና የእጅ መንሻ የሚሻበት ወቅት አይደለም። በጥቅሉ ነጻነት፣ ሰላም፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ያለመሰዋእትነት አይገኝምና ለአገሪቱ ሰላም፣ ፍትህና ዴሞክራሲ መረጋገጥ ሁሉም የበኩሉን አስተዋጽኦ ሊያደርግ ይገባል። ዛሬ ኢትዮጵያችን በተሰማራንበት መስክ ሁሉ ጠንክረን እንድንሰራ ያለንን ሁሉ ለእርሷ እንድንል አጥብቃ የምትፈልገን ጊዜ ላይ ናት።
በአዲሱ ዓመት ሁሉም “እኔ ለአገሬ ምን ሰራሁላት” በሚል እራሱን በመፈተሽ በሚችለው አገሩ ከተጋረጠባት አደጋ መመከት አለበት። በአዲሱ ዓመት አዲስ ማንነት እንቀምር፤ አዲስ ህይወት እንጀምር፡፡ ከአቧራ ምኞት ከአቧራ ህይወት እንውጣ፡፡ ወደ ብርሃን እንውጣ፤የተጀመረውን አገራዊ ለውጥ በአንድነት አቀጣጥለን ዳር እናድርስ፡፡
ጥበብን እንካፈል፣ ግኝት እንፈልፍል፡፡ ህሊናን እናድስ፣ ኑሮን እናወድስ፡፡ በአዲሱ ዓመት ለመናቆር ሳይሆን ለመፋቀር ቦታ እንስጥ፡፡ እንደ ግለሰብ መቋሚያ የሚያሲይዝ እምነት ብቻ ሳይሆን እንደ ማህበረሰብ መቋቋሚያ የሚሆን እውነት እንጨብጥ፡፡ በርቀት መነቋቆር ሳይሆን በቅርበት መነጋገር ባህል ይሁን፡፡ አዲስ ዓመት ሲመጣ ከአሮጌ ማንነት እንውጣ፡፡ ሰላም!
ከራማአ ማዶ
አዲስ ዘመን መስከረም 11 ቀን 2014 ዓ.ም