የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን በኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ውድድሮችን የማስተናገድ አቅም ያላቸው ሜዳዎች ባለመኖራቸው የአገሪቱ ስታዲየሞች ጨዋታ እንዳይካሄድባቸው ማገዱ ይታወሳል። በገደብ ጨዋታዎች እንዲደረጉበት የፈቀደው ብቸኛው የባህርዳር ስታዲየም ሲሆን፤ እርሱም በሂደት አሁን ካለበት ሁኔታ ለውጥ የማያሳይ ከሆነ የእገዳው ሰለባ ሊሆን እንደሚችል ካፍ ማስጠንቀቁ አይዘነጋም። በመሆኑም የኢፌዴሪ ስፖርት ኮሚሽን ስታዲየሞች ሜዳቸውንና የተጫዋች የመልበሻ ክፍሎች እንዲሁም ሌሎች መሰረታዊ ነገሮች በካፍ መስፈርት መሰረት ተሟልተው አገሪቱ በድጋሚ ጨዋታዎችን እንድታካሂድ ለማድረግ በእንቅስቃሴ ላይ ይገኛል።
ዓለም አቀፍና አህጉር አቀፍ ጨዋታዎችን እንዳያካሂዱ እገዳ ከተጣለባቸው ስታዲየሞች መካከል አንድ ለእናቱ የነበረው የአዲስ አበባ ስታዲየም የሚጠቀስ ነው። ለረጅም አስርት ዓመታት ያህል ስፖርታዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ሌሎች ጉዳዮችን ሲያስተናግድ የቆየው ይህ ስታዲየም በእርግጥም እርጅና እየጎበኘው ይገኛል። ሜዳውና የውስጥ ክፍሎቹ በአገልግሎት ብዛት እንደ ቀድሞ ምቹ ካለመሆናቸውም ባለፈ የተመልካች ስፍራውም ወንበሮች መሰባበራቸው ስታዲየሙ ጥገና እንደሚያስፈልገው ያሳብቁ ነበር። በመሆኑም የኢፌዴሪ ስፖርት ኮሚሽን ከሁለት ወራት በፊት ስታዲየሙ እንዲታደስ ውል ገብቷል። እስካሁን ባለበት ሂደትም እድሳቱ ምን ያህል ደርሷል የሚለውን የኮሚሽኑ አመራሮች እንዲሁም የክልል ስፖርት ኮሚሽነሮች በተገኙበት የመስክ ምልከታ ተደርጓል።
በዚህም የተጫዋቾች መልበሻና የመታጠቢያ ክፍሎች ግንባታ ተጠናቆ የልስን ሥራ መጀመሩ ታውቋል። በካፍ ግብረመልስ መሰረት የመጫወቻ ሜዳውን ለማደስ በማሰብ የሜዳው ቁፋሮ ተከናውኖ እንደ አዲስ ሙሌት ከተደረገ በኋላ ሥራዎቹ ቆመዋል። ለዚህም ምክንያት ወቅቱ ክረምት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ እንዲዘገይ የተደረገ መሆኑ ተገልጿል። ነገር ግን ከቀጣይ ሳምንታት ጀምሮ የሜዳ ሥራው ይጀመራል፤ በጥቂት ወራት ውስጥም ሳሩ ይበቅላል ተብሎ ይጠበቃል። እስካሁን ያለው የግንባታ አፈጻጸምም 11 ነጥብ 5 በመቶ ነው። ይህ አፈጻጸም ዝቅተኛ ሊሆን የቻለውም የሜዳ ሥራው ከፍተኛውን ድርሻ ስለሚይዝ እንደሆነ ከኢፌዴሪ ስፖርት ኮሚሽን የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
የእድሳት ሥራውን ፍሬንድስ ኢንጅነሪንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ የያዘው ሲሆን፤ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅም ውል ገብቷል። ይሁን እንጂ እድሳቱን በማፋጠን ፕሪሚየር ሊጉን ጨምሮ በቀጣይ ለሚካሄዱ ሌሎች ጨዋታዎች ለማድረስ ከውሉ ባጠረ ጊዜ ውስጥ አጠናቆ ለማስረከብ ርብርብ እየተደረገም እንደሚገኝ ታውቀል። በጉብኝቱ ወቅት ማብራሪያ የሰጡት የኢፌዴሪ ስፖርት ምክትል ኮሚሽነር አቶ ዱቤ ጂሎ፤ የስታዲየሙ እድሳት ጥራቱን ጠብቆ በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ ኮሚሽኑ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል።
ምክትል ኮሚሽነሩ አክለውም ካፍ ባስቀመጠው መስፈርት መሰረት ስታዲየሙን ለማደስ እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው። በዋናነትም የመልበሻ ክፍሎች እና የመጫወቻ ሜዳው ላይ ትኩረት ተደርጎ ከደጋፊዎች መቀመጫ ጋር ሥራዎች በመከናወን ላይ ይገኛሉ።በመሆኑም እድሳቱ እስከ የካቲት አልያም መጋቢት ወር ድረስ ተገባዶ ወደ ግልጋሎት እንደሚገባም ጠቁመዋል።
ከዚህ ጎንለጎንም የባህር ዳር እና የሀዋሳ ስታዲየሞችም መስተካከል ያለባቸው ጉዳዮች እየተሰሩ ነው። የብሔራዊ ስታዲየም ግንባታም በመልካም ሁኔታ እየተጓዘ ይገኛል።፡ በተጨማሪ ከክልሎች ጋር የምንሰራቸው የማዘውተሪያ ስፍራዎች አሉ። ይህም ለወጣቶች እና ታዳጊዎች በቂ የመጫወቻ ስፍራዎች እንዲኖሩ ያደርጋል። በአጠቃላይ በሚቀጥሉት ዓመታት ከ3 በላይ ዓለም አቀፋዊ ጨዋታዎችን የሚያስተናግዱ ስታዲየሞች እንዲኖር እየተሰራ መሆኑን ምክትል ኮሚሽነሩ አብራርተዋል።
ከዕድሜ ጠገቡ የአዲስ አበባ ስታዲየም ባሻገር እጅግ ዘመናዊና ግዙፍ ስታዲየም በከተማዋ በመገንባት ላይ መሆኑ ይታወቃል። ይህ የብሔራዊ ስታዲየም ግንባታም የመጀመሪያ ዙር ተጠናቆ ሁለተኛና የማጠቃለያ ሥራዎች ላይ ይገኛል። በዚህ ስታዲየምም ጉብኝት የተደረገ ሲሆን፤ የጣራ ተሸካሚ የመጨረሻ ሥራ የሆነው የኮንክሪት ሙሌት (Ringbeam) ሥራ በመከናወን ላይ ይገኛል። ይህ ሥራ ከተጠናቀቀ በኋላም፤ በቀጥታ ወደ ብረት ሥራ እና የጣራ ማልበስ ሥራ እንደሚገባም ኮሚሽኑ አረጋግጧል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን መስከረም 10/2014