የአሸባሪው ህወሓት ታጣቂዎች በአማራ ክልል በፈፀሙት ወረራ ንፁሃንን ከመግደል ባሻገር በርካታ የሕዝብ ሀብቶችን አውድመዋል። ካወደሟቸው የሕዝብ ሀብቶች መካከል በዋግኽምራ ዞን ፃግብጂ ወረዳ ሕፃናትን ከዳስና የድንጋይ መቀመጫዎች ያላቀቀው የአትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ ትምህርት ቤት ይገኝበታል። ሕዝብን ሰላም በማሳጣት ሀገር ለማፍረስ ቆርጦ የተነሳው አሸባሪው ህወሓት በፈፀመው እኩይ ተግባር ከፍተኛ ውድመት የማድረሱ ዜና ብዙዎችን አስቆጥቷል። የሕፃናቱ የደስታ እምባ ሳይደርቅ በአሸባሪው ቡድን ትምህርት ቤቱ መውደሙም መከፋትን ፈጥሯል።
አሸባሪው ቡድኑ በትምህርት ቤቱ ላይ የፈፀመው ጥቃትም ለሕፃናት፣ ለሕዝብ ብሎም ለእውቀትና ለትምህርት መስፋፋት ደንታ እንደሌለው ያሳያል። በእርግጥም ከጫካ ጀምሮ ገንጣይ አስገንጣይ እቅዱን አንግቦ ወደ አራት ኪሎ ሲገባ፤ እኩይ ተግባሩን ለማስፈፀም የትምህርቱ መስክ ዋነኛ ኢላማው ነበር። ሀገር አፍራሽ ህልሙን ለማሳካት ባለፉት 27 ዓመታት በትምህርቱ ዘርፍ ላይ በተለያየ መልኩ የጥፋት በትሩን አሳርፏል።
አሸባሪ ቡድኑ እንዲህ እንደ ዛሬው በመሣሪያ ሳይሆን በፖሊሲ አስደግፎ በትምህርት ዘርፍ ላይ ሲፈፅም ከነበራቸው ጥቃቶች ከብዙ በጥቂቱ ለማስታወስ እንሞክር። ወያኔ በትምህርቱ ዘርፍ ሲፈፅማቸው ከነበሩት ጥቃቶች መካከል አንዱና ዋነኛው በራሱ የቀረፀው ትውልድ ገዳዩ የትምህርት ፖሊሲ ነው።
ሀገር አፍራሹ ትህነግ የትምህርት መስኩን ለማኮላሸት የመጀመሪያው እርምጃ ያደረገው፤ በ1984 ዓ.ም ትውልድ ገዳይ የትምህርት ፖሊሲ ቀርፆ ተግባራዊ በማድረግ ነበር። በወቅቱ የፖሊሲውን ተግባራዊነት ተከትሎ ብዙዎች ቅሬታ ማሰማት የጀመሩት ማልደው ነበር። ፖሊሲው የትምህርት ጥራት ከቀን ወደ እያሽቆለቆለ ጭራሽ በራሱ የማይተማመን ደካማ ትውልድ እንዲፈጠር ያለመ መሆኑን ብዙዎች አስቀድመው ሞግተዋል።
የኢትዮጵያ ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ምሁራን፣ ወላጆች፣ መምህራን፣ በጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው ተማሪዎች የወያኔ የትምህርት ፖሊሲ ያለበትን ችግርና በትውልዱ ላይ ዕዳ የጫነ መሆኑን በመረጃ አስደግፈው ጥያቄ አቅርበው ነበር። ነገር ግን ወያኔ በማንአለብኝነት ተነሳስቶ ጥያቄ ያነሱትን አገር ወዳድ ኃይሎች በሙሉ እስራት፤ ሞትና ስደት እንዲገጥማቸው በማድረግ ጥያቄውን ለማዳፈን ነበር የሞከረው።
ወያኔ ሀገሪቱን ወደሚፈልገው አቅጣጫ ለመውሰድ ያመቸው ዘንድ በኢትዮጵያ የዘመናዊ ትምህርት ጉዞ ውስጥ ለዘመናት ደምቆ የተጓዘውን የግብረ ገብ ትምህርትን ደብዛውን ማጥፋት ነበረበት። ይህን በማድረጉም የትምህርት ተቋማቶች ሥነ ምግባሩ የተመሰገነ ትውልድ ማፍራት እንዲሳናቸው ሆኗል። ይህም ወያኔ በትምህርት ተቋማት ላይ የሚፈፅመው ጥቃት እንዲህ እንደ ዛሬው በመሣሪያ ሳይሆን፤ የትምህርት ሥርዓቱን በመጠቀም እንደነበር ቁልጭ አድርጎ ያሳየናል።
አሸባሪ ቡድኑ በትምህርቱ ዘርፍ ላይ ሲፈፅማቸው ከነበሩ በርካታ ጥቃቶች ውስጥ ከመምህርነት ሙያ ጋር ተያይዞ ያሉትን ነጥቦች እንመልከት። በኢትዮጵያም የመምህርነት ሙያ ትልቅ ክብር ይሰጠው እንደነበር ይታመናል። ለዚህ ደግሞ ከሁለት ዓመት በፊት ሕይወታቸው ያለፈው የማይክሮሊንክ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ኮሌጅ መሥራች እና የኢትዮጵያ ነፃ-ፕሬስ አለኝታ በሚል የሚታወቁት አቶ ዳኛቸው ይልማ ሲናገሩ፤
«ከ1966 ዓ.ም በፊት መምህር ለመሆን የምርጦች ምርጥ መሆንን (cream of the cream) ይጠይቅ ነበር። በዚህም መሠረት ወደ መምህራን ማሠልጠኛ ይገቡ የነበሩት ከየትምህርት ቤቶቻቸው የላቀ ውጤት ያመጡት ነበሩ። መምህራኑም ከተማሪዎቻቸው አልፈው ለአካባቢው ኅብረተሰብ ጭምር አርአያ (role models) ነበሩ። በኋለኛው ዘመን ግን የመምህርነት ሙያ መኩሪያ ሳይሆን ማፈሪያ እስከመሆን ደርሷል»ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ የሙያዎች ሁሉ አውራ፣ አባት፣ መሰረት ከክብሩ እንዲወርድ ‘ወያኔ’ በግልፅ ሲሰራ ነበር። የአራት ኪሎ ዘዋሪ የነበረው እና ዛሬ በአሸባሪነት የተፈረጀው ቡድን፤ የመምህራንን ማሕበራዊ ዋጋ እንዲያሽቆለቁል በማድረግ ሀገሪቱ አለኝታ አልባ አድርጎ የማቆየት ፍላጎቱን ያለከልካይ ለማድረግ አስቦ ሰርቷል፡፡ በሌላ በኩል መምህራንን ከማንኛውም ለውጥ ለማግለል ሆን ብሎ የሰራቸው ሥራዎች በመኖራቸው ሙያው ክብሩን እንዲያጣ ያደረገ መሆኑን ብዙዎች ያነሳሉ፡፡
ወያኔ የመምህርነት ሙያን እና መምህራን የነበራቸውን ክብር እንዲያጡ ማድረጉ በሽፍታነት ዘመኑ ብቻ ሳይሆን ወንበር ላይ በነበረበት ወቅት ፀረ – ትምህርት፣ እውቀት ጠል፣ አዋቂን የማያከብር እንደነበረም ያመላክታል።
ከትምህርት ሚኒስቴር በወጡ መረጃዎች መሰረት አሸባሪ ቡድኑ ህወሓት በሰሜን እዝ የመከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት ከሰነዘረበት ጊዜ አንስቶ መንግሥት የተናጠል የተኩስ አቁም አድርጎ መቀሌን ለቆ እስከወጣበት ድረስ በትግራይ አጎራባች በሆኑ የአማራና የአፋር አካባቢዎች ላይ ባደረጋቸው ትንኮሳዎች ከሰባት ሺ በላይ የሚሆኑ ትምህርት ቤቶች ሙሉ በሙሉ ወድመዋል፡፡
የሽብር ቡድኑ በተለይ በአማራ ክልል በፈፀመው ጥቃት 2ሺ903 ትምህርት ቤቶች ሙሉ በሙሉ የወደሙ ሲሆን ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ሕፃናት ከትምህርት ገበታ ውጪ ሆነዋል፡፡ በግጭቱ ከ4ሺህ በላይ መምህራን ከሥራ ገበታ ውጪ እንደሆኑም መረጃዎቹ ያሳያሉ፡፡
በተመሳሳይ በአፋር ክልልም በርካታ ትምህርት ቤቶች መውደማቸውንና ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሕፃናትና ተማሪዎች በዚሁ ግጭት ምክንያት ከትምህርታቸው መስተጓጎላቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
የትምህርት ሚኒስቴርም በአማራ ክልል በሽብርተኛው የህወሓት ቡድን ለወደሙና ለፈረሱ ትምህርት ቤቶች መልሶ ማቋቋሚያ የሚሆን የ100 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ከሰሞኑ ማድረጉ ይታወሳል፡፡
ዳንኤል ዘነበ
አዲስ ዘመን መስከረም 10/2014