ዩኒቨርሲቲዎች በተለያዩ የትምህርት መስኮች ብቁ ምሩቃንን ለሀገር ልማት ከማበርከት ባሻገር በውስጥ የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች መለየትና መፍታት የሚያስችሉ ችግር ፈቺ ምርምሮችና አገልግሎቶች በስፋት ማከናወን እንዳለባቸው ይጠቆማል። በዚህ ረገድ በርካታ ዩኒቨርሲቲዎች በተለያዩ ጊዜ ወቅታዊ ችግሮች ሲፈጠሩ ተማሪዎቻቸውን የሚያገለግሉበትን መንገድ በመቀየስ የመማር ማስተማር ሥራው ሳይቆራረጥ እንዲቀጥል በማድረግ አበረታች ውጤት እያስመዘገቡ ይገኛሉ።
ዛሬ ከኮሮና ወረርሽኝ ስርጭት ጋር ተያይዞ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት እና በተለያዩ አካባቢዎች በተከሰቱ ግጭቶች ሳቢያ የተፈጠሩ ጫናዎችን ለማስወገድ በአምቦ ዩኒቨርሲቲ እየተደረጉ ያሉ እንቅስቃሴዎችን በተመለከተ የዩኒቨርሲቲው የአስተዳደርና የተማሪዎች አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ሰለሞን አለሙ ለአዲስ ዘመን የሰጡትን አስተያየት ይዘን ቀርበናል። መልካም ንባብ።
ምክትል ፕሬዚዳንቱ እንደተናገሩት ከኮሮና ጋር በተያያዘ በመላው ሀገሪቱ እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ የነበረው የትምህርት ሂደት ተስተጓጉሎ ነበር። ለተወሰነ ጊዜም ሁኔታዎች እስኪመቻቹ ድረስ ትምህርት ቤቶች ሙሉ ለሙሉ ተዘግተው ቆይተውም ነበር። ቁጥጥር እየተደረገ ለማስተማር ተወስኖ ተመልሰው እንዲገቡ ሲደረግ ደግሞ ወረርሽኙን ለመከላከል ጠቃሚ የሆኑ ለመላው ሠራተኛ ሳኒታይዘር የማምረት፤ ሁለት ሁለት ታጣቢ ማስክ የማዘጋጀት፤ ከንክኪ የጸዳ የእጅ መታጠቢያ በላይብረሪና መመገቢያ ቦታዎች የማስቀመጥ ሥራ ለክረምት ተማሪዎችም ጭምር ተተግብሯል።
በላይብረሪ በመኝታ ቤት ስድስት የነበረውን የተማሪ ቁጥር ወደ አራት እንዲቀንስ ተደርጓል። በክፍል ውስጥ የሚገኙ ተማሪዎችን ቁጥር የመቀነስ እና ሌሎች ቅድመ ዝግጅቶችም ተከናውነዋል። በአምቦ ዩኒቨርሲቲ የተፈጠረውን ክፍተትና የባከነውን ጊዜ ለማካካስ የመርሃ ግብር ማስተካከያ ተደርጓል፤ መምህራን ተጨማሪ ሥራዎችን እንዲሰሩ ተደርጓል። የማስተርስ ተማሪዎችንም በቴክኖሎጂ በመጠቀም ሲያስተምር ቆይቶ ከኮሮና በኋላ ሁለት ጊዜ አንዱን ዙር በጥር አንዱን ደግሞ ለሁለተኛ ጊዜ አሁን እያስመረቀ እንደሚገኝም ምክትል ፕሬዚዳንቱ ይገልፃሉ።
በመምህራን፣ በተማሪና በአስተዳደር ዘንድ በቂ መረጃ ስላልነበር ስጋቱ ነበር። ከኮሮና ጋር በተያያዘ ከሠራተኞች የተያዙም ሕይወታቸው ያለፈም ቢኖሩ በተማሪዎች ላይ ግን የተፈጠረ ነገር አልነበረም ብለዋል።
እንደ ምክትል ፕሬዚዳንቱ ገለፃ፤ ኮሮና ከፍተኛ ጉዳት ባለማድረሱ አሁን ላይ መዘናጋት አለ፤ ይህም በመምህራንና በሠራተኛው በኩል ይታያል። በዚሁ የሚቀጥል ከሆነና አዲሱ ኮሮና ከተስፋፋ የባሰ ችግር ሊገጥመን ይችላል። በአሁኑ ወቅት ያለው የተማሪ መምህራን ጥምርታም እንደመደበኛው ጊዜ ነው። ይህ የተደረገው ደግሞ በርካታ ተማሪዎች ትምህርቱ እንዳያልፋቸው በማለት ነው። በመሆኑም እንደ አዲስ ጥንቃቄ የማድረግ ሥራ የምንሰራ ይሆናል። በካምፓሱ የኮሮና መመርመሪያም ለአምቦ ሪፈራል ሆስፒታልና በአካባቢው ላሉት የኦክሲጅን ማምረቻም ከአምስት ወር በፊት አስመርቆ በሥራ ላይ ይገኛል።
ሃያ አምስት በመቶ የሀገራችን ሕዝብ ከድህነት በታች በሆነበት ሁኔታ በጦርነት መቆየቱ ብዙ ዋጋ ያስከፍለናል። ጦርነቱም እርስ በእርስ የሚካሄድ ነው፤ በመሆኑም የጦርነትን ሀሳብ በሰላም ማሸነፍ ይቻላል። የሕዝቡም ፍላጎት ከዚህ የዘለለ አይሆንም። ጦርነቱ የኢኮኖሚ ብቻ ሳይሆን በሕዝቦች መካከል ያለውን አብሮ የመኖር ግንኙነትም የሚያሻክር ነው ሲሉ ምክትል ፕሬዚዳንቱ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
ወቅታዊ ሁኔታንም አስመልክቶ ተማሪዎች ተረጋግተው እንዲማሩ ዩኒቨርሲቲው በርካታ ሥራዎችን ሲሰራ እንደቆዬ ተናግረዋል። በመጀመሪያ በነበረው ሀገራዊ ሁኔታ ኅብረተሰቡ ውስጥ በተፈጠረው ስጋት ቀላል የማይባል ተማሪ ከሚኖርበት አካባቢ ርቆ ላለመማር በመወሰኑ አንደኛ ዓመት ሆነው ተመድበው ሳይመጡ የቀሩ በርካታ ተማሪዎች አሉ። ሲማሩ የነበሩትም አንዳንድ ረብሻዎች ሲፈጠሩ አቋርጠው ይሄዳሉ። ሲመለሱ ማካካሻ ትምህርት ተሰጥቷቸው ቀጥለው እንዲያጠናቅቁ ተደርጓል።
በሌላ በኩል ጦርነቱ ከሚካሄድባቸው አካባቢዎች የመጡ ተማሪዎች የሥነ ልቦናና ማህበራዊ ጫና እንደሚገጥማቸው ይታወቃል። ከትግራይ ለመጡት የባንክ አገልግሎት በመቋረጡ የኢኮኖሚ ችግር እንደገጠማቸውና በተለይ ተመራቂ ተማሪዎች የመመረቂያ ልብስ እንደሌላቸው አሳውቀዋል። ዩኒቨርሲቲው ግን ትምህርታቸውን ጨርሰው መሄድ በሚፈልጉበት ወቅት ትራንስፖርት ወደ አማራ፣ ትግራይ፣ አፋር፣ ቤኒሻንጉል፣ ወለጋ አካባቢ ወጪ ይሸፈናል። ይህ ነገር ቁጥሩ ባይበዛም በፊትም የኢኮኖሚ ችግር ላለባቸው ሲደረግ የነበረ ነው። መሄድ የማይችሉ ካሉም ለተወሰነ ጊዜ እዚያው መቆየት የሚቻልበት ሁኔታ እየተመቻቸ ይገኛልም ብለዋል።
እንደእሳቸው ማብራሪያ፤ ተማሪዎች የተጠሩት ከጦርነቱ በፊት በመሆኑ ያን ያህል ችግር አልነበረም፤ በመሀከል የነበረው እረፍትም አጭር ጊዜ በመሆኑ ርቀው ባለመሄዳቸው ያን ያህል የጎላ ችግር አልታየም። ነገር ግን የክረምት ተማሪዎች ሆነው መቀሌ፣ አክሱም፣ አዲግራት መማር የነበረባቸውን የአሁኖቹ ከተመረቁ በኋላ ትምህርታቸውን በዩኒቨርሲቲው የሚቀጥሉ ይሆናል። ከእነዚህ ሁለት ዓመትም ያቋረጡና አራት፣ አምስት ዓመት የተማሩ በመሆናቸው መንግሥት ለሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች ባቀረበው ጥያቄ መሰረት አንድ መቶ ስንጠብቅ የነበረ ቢሆንም አምስት መቶ ተማሪዎች ተቀብለናል።
ለቀጣይም ከኮሮና አንጻር ችግሩ እንዳይባባስ ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ እየተሰራ ይገኛል። መጀመሪያ ሲከሰት ከነ ጋዋናችን በየመንደሩ በመዞር ስንሰራ ነበር። ይህን የምንደግመው ይሆናል። በፕሬዚዳንቱ በሚመራ በወሎ ለተፈናቀሉ በቀረበልን ጥያቄ መሰረት ድጋፍ ለማድረግ የአልባሳት፣ የምግብ፣ የእህልና የመሳሰሉትን የሚያካትት ሁለት ሚሊዮን ብር የሚገመት ድጋፍ ከምረቃ በኋላ የሚደረግ ይሆናል ብለዋል።
ወያኔ ተደምስሶ በአገሪቱ ሰላም መፈጠሩ አይቀርም። በዚህ ጊዜ ዩኒቨርሲቲው ጦርነቱ ከተቋጨ በኋላ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግና የሕዝብ ለሕዝብ ትስስር እንደቀደመው እንዲመለስ ሥራ ይሰራል። ከእነዚህ አካባቢዎች የሚመጡ ተማሪዎች የተለያዩ ችግሮች ውስጥ ቆይተው የሚመጡ በመሆኑ የኑሮ ውድነቱም በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ በመሆኑ እነሱንም የመደገፍና የመንከባከብ ሥራ የሚሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ፅጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን መስከረም 10/2014