(ክፍል ሁለት)
(በክፍል አንድ ጽሁፍ አሸባሪው ህወሓት ሌብነትን በኢዮጵያ እንዴት እንዳስፋፋና ያስከተለውን ጉዳት ለመጥቀስ ተሞክሯል። ቀጣዩ ክፍል ደግሞ ዛሬ እንዲህ ተሰናድቶ ቀርቧል) ፖለቲካውና የፖለቲካ መሪዎች ከሌብነት ካልተላቀቁ፣ የሰው ኃይል ምደባቸው፣ ሕግና መመሪያቸው፣ የሕግ አፈጻጸማቸው ለሌብነት ክፍት ከሆነ በሂደት እንደ ሥርዓት ሌብነት ውስጥ መገባቱ አይቀርም። ሌብነት ስርዓት ከሆነ ደግሞ ነጻውና ጨዋው ዜጋም ሳይወድ መብቱን በገንዘብ ለመግዛት ይገገዳል።
ለሌባው የማይገባውን በመክፈል የሌብነት ተባባሪ ይሆናል። ሌብነት በዚህ መልክ በዜጋው አሰተሳሰብ ከተጋባና የተከታታይ ትውልዶች ልምምድ ወደመሆን ከተሸጋገረ ሌብነት ባሕል ወደመሆን ያድግና አገር በምዕተ-ዓመታት ከማትወጣበት የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የሞራል ድቀት ውስጥ ትገባለች። እንደ አገርም እንፈርስና በምድር ላይ አሻራ አልባ አገርና ሕዝብ እንሆናለን ማለት ነው።
የሕዝቧን ሰላምና ደሕንነት ከማስጠበቅ ባሻገር የአገርን ልማት ለመምራትና ለማፋጠን ኃላፊነት የተጣለበት የመንግስ መዋቅር በፖለቲካዊ ሌብነት ውስጥ ከተዘፈቀ ዋና ዋና የሀብት ምንጭ የሆኑ የአገር ሀብቶች በሌቦች ቁጥጥር ስር የሚገቡበት እድል ከፍተኛ ነው። በአገራችን ከፍተኛ ሌብነት ከሚፈጸምባቸው ዘርፎች መካከል የከተማና የገጠር መሬት አስተዳደር አንዱና ዋነኛው ነው። በሕወሐት ዘመን እንደ ጋምቤላና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ በመሳሰሉ ክልሎች የገጠር መሬት በሌብነት ሰንሰለት በተሳሰሩ የመንግስት ባለስልጣናትና ሸሪኮቻቸው በሚሊዮኞች የሚገመት ሄክታር መሬት ተዘርፏል።
ዘረፋና ሌብነቱ በመሬት ሀብት ላይ ብቻ አልተገደቡም። መሬትን በዋስትና በማስያዝ ባንኮችም እንዲዘረፉ በተለይም የኢትዮጵያ ልማት ባንክ እርቃኑን እንዲቀር ተደርጓል። በከተሞች በተለይም በአዲስ አበባና በዙሪያው የነበረው ዘረፋም ከዚህ የተለየ አልነበረም። ዜጎች ከቀያቸው በልማት ስም እየተፈናቀሉ ኑሯቸው ሲመሰቃቀልና ለከፋ ድህነት ሲዳረጉ ቆይተዋል። ችግሩ እየከፋ ሄዶም ለሕዝባዊ አመጽ መቀጣጠልም ዋና ምክንያ ሆኗል።
እነዚህንና መሰል በደሎችን ለማረም ተብሎ በአዲስ አበባ አካባቢ በልማት ሰበብ የተፈናቀሉና የሚፈናቀሉ ዜጎችን ኑሮ ለማሻሻል በሚል መንግስት ለገበሬ ቤተሰቦች የፈቀደው በከተማ ውስጥ የመኖሪያ ቦታ ባለቤት የመሆን መብት በከተማ አስተዳደሩ በየደረጃው በተሰገሰጉና በድለላ ስም በሚንቀሳቀሱ ሌቦች ጥምረት ሐሰተኛ ሰነድና ሰው ሰራሽ ባለቤቶች እየተሰየሙ የአዲስ አበባ መሬት ዳግም መቸብቸቡን ቀጥሏል።
ይህም በልማት ተነሺ ስም የተፈናቀሉ ዜጎችን ለመታደግና ሌብነትን ለመግታት ሲባል የተወሰደ በጎ እርምጃ ለሌላ ዓይነት ሌብነት በር መክፈቱን ያሳየናል። ድርጊቱ በመላው የከተማ ነዋሪዎችና በእውነተኛ የልማት ተነሺዎች ላይ ከፍተኛ ቅሬታ አሳድሯል። የማዕድን ዘርፉም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መነቃቃት እየታየበት ቢሆንም አዳዲስ የውስጥና የውጭ ሌቦች መሰባሰቢያ እየሆነ በመምጣቱ እንደ ኮንጎና ሊቢያ ከመሆናችን በፊት አፋጣኝ መፍትሔ ሊበጅለት ይገባል።
የንግዱ ዘርፍም ሥር የሰደደ ሌብነት የሚታይበት በመሆኑና ሌቦች ገበያን በማመሰቃቀል አደገኛ ሴራ የሚፈጽሙበት የኢኮኖሚ ክፍል ሆኖ ቆይቷል። መንግስት ገበያን ለማረጋጋትና ስርቆትን ለመከላከል የወሰዳቸው እርምጃዎች ተመልሰው ለስረቆትና ለሌቦች መበልጸጊያነት ሲሆኑና የገበያ አለመረጋጋቱን ሲያባብሱና ዜጋውን ሲያማርሩ እያስተዋልን ነው። ለምሳሌ መንግስት በግንባታው ዘርፍ የሚስተዋለውን በተለይም የሲሚንቶን ዋጋ ለማረጋጋት በልማት ድርጅቶች በኩል ለተወሰኑ ባለሃብቶች ውክልና እየተሰጠ እንዲያከፋፍሉ ተዘርግቶ የነበረው አሰራር ችግሩን ይበልጥ አወሳቦትና የሲሚንቶን ዋጋ ከነበረው በሁለትና ሶስት እጥፍ በላይ እንዲንር በማድረግ በሌብነት መስመር የተመለመሉ ወኪሎች እንዲያከፋፍሉ ግዴታ ለገቡለት አካባቢ ሳያደርሱ ከፋብሪካ ግቢ ሳይወጣ እንዲቸበቸብ ተደርጓል።
ይህም ለመንግስት የሚገባው ገቢ ወደሌቦች ኪስ እንዲገባና የግንባታ ስራ ተቋራጮች ደረሰኝ ከተቆረጠላቸው ሁለትና እና ሶስት እጥፍ ዋጋ እንዲከፍሉ በመገደዳቸው በርካቶች ለኪሳራ እንዲዳረጉ ሆነዋል። አሰራሩ ዘርፉን በአጭር ጊዜ ውስጥ በከፍተኛ ደረጃ ከጎዳውና ጥቂት ሌቦችን ያለአግባ ካበለጸገ በኋላ በአጭር የቴሌቪዝን መግለጫ አሰራሩ እንዲቆም መደረጉን ስንሰማ ከጅምሩ አንድን አይነት ሌባ በሌላ ዓይነት ከመቀየር ያለፈ ፋይዳ እንዳልነበረው ተገንዝበን ነበር።
በአገራች ላይ አሁን የሚስተዋለው የኑሮ ውድነት በንግድ ስም ሳይሰሩ ለመክበር የሚጥሩ ሌቦች ውጤት ነው። ሌቦች በአገር ውስጥ ንግድ ብቻ ሳሆን የወጪ ንግዱን በመቆጣጠርና ከአለማቀፍ ሌቦች ጋር በመመሳጠር የሚልኩትን የአገር ምርት ከሚሸጡበት ትክክለኛ ዋጋ እጅግ በማሳነስ ለመንግስት ያሳውቃሉ። ልዩነቱንም ምርቱ በተላከበት አገር በውጭ ምንዛሬ ያከማቻሉ። የአርሶ አደራችን ምርት በዶላር ተመንዝሮ በባዕድ አገር እንዲቀር ያደርጋሉ። በዚህም ምክንያት አገራዊ የንግድ ሚዛናችን በከፍተኛ ደረጃ ይዛባል። ከፍተኛ የውጪ ምንዛሬ እጥረት ያጋጥመናል። ክፍተቱን ለመሙላት መንግስት እርዳታ ይለምናል፤ይበደራል። ሌቦች ዘርፈው በውጪ አገር ላከማቹት የአገር ሐብት መላው የኢትዮጵያ ደሃ ሕዝብ እዳ ከፋይ ይሆናል። ሌብነቱ አንድ ቦታ ካልቆመ የድህነት አዙሪቱ ውስጥ እንቀጥልና እዳውም ለመጪው ትውልድ የሚተላለፍ ይሆናል።
ሌላው የአገራችን የኢኮኖሚ ዕድገትና የንግድ ስርዓቱ ነቀርሳ ሆኖ የቆየው የኮትሮባንድ ንግድ ሲሆን የጦር መሳሪያን ጨምር ተገቢው ታክስ ሳይከፈልባቸውና ጥራታቸው ሳይረጋገጥ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ ሸቀጦች ግብር ከፋይና ሕጋዊ ነጋዴውን በማሽመድመድ በአንጻሩ ሕገ-ወጦች በአቋራጭ እንዲከብሩ ሲያደረግ ቆይቷል። በሌላ በኩል ደግሞ ሌቦች ኬላ ክፍት እየተደረገላቸው ከፍተኛ የውጪ ምንዛሬ ማስገኘት የሚችሉ የአገር ምርቶችን በድብቅ ከአገር በማስወጣት ከዚህ የሚገኘው ከፍተኛ የውጪ ምንዛሬ በባዕድ አገር እንዲቀርና የአገር ኢኮኖሚ እንዲደቅ ያደርጋል።
ሌብነት ከኢኮኖሚ ጉዳቱ ባለፈ ለሰዎች ህይወት በከንቱ መቀጠፍ ምክንያት ነው። በአገራችን ባለው ከፍተኛ የትራፊክ አደጋ ምክንያት የሚያልቀው ዜጋ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከሌብነት ጋር የተያያዘ ነው። አሽከርካሪዎች በአግባቡ ሰልጥነውና ተፈትነው ብቃታቸው ተረጋገጦ መንጃ ፈቃድ ስለማይሰጣቸው፤የተሽከርካሪዎች ብቃት ማረጋገጫ ምርመራ በአግባቡ ስለማይከናዎንና በሌብነት ምክንያት ብቃት የሌላቸው አሽከርካሪዎችና ተሽከርካሪዎች አገልግሎት እንዲሰጡ በመደረጋቸው የትራፊክ አደጋ እየተበራከተና የዜጎች ህይወትም በከንቱ እየተቀጠፈ ንብረትም እየወደመ ይገኛል።
ከሌብነት አንጻር የሚወጡ ሕጎችን በተመለከተ የኢህአዴግ መንግስት ህግ በማውጣት የሚታማ አልነበረም። ላለማክበርና ላለመተግበር ወስኖ የሚያወጣቸውና ለማሕበረሰቡ ሚስጥር የሚመስሉ ህጎች ግን በርካቶች ነበሩ። ለዜጎች በሚገባ ግልጽ ያልተደረገውና የተወሳሰበው የአገራችን ቢሮክረሲ ለዜጎች ሚስጥር የሆኑ ሕጎች ለሌብነት እጅግ የተመቹ ናቸው። ከቀበሌ መታወቂያ አሰጣጥ ጀምሮ፣ የመንጃ ፈቃድ አሰጣጥ፣ የንግድ ፈቃድ አወጣጥና እድሳት፣ በፍርድ ቤቶችና በፍትሕ ተቋማት፣ በመንግስት ግዢ፣ በግብር ውሳኔ በኢንቨስትመንት ፈቃድና ቦታ አሰጣጥ ወዘተ ያሉ ሕጎችና መመሪያዎች እጅግ የተንዛዙና ለዜጋው ግልጽ ያልተደረጉ በመሆናቸው ለሌብነት ክፍት የሆኑ ናቸው።
በአሁኑ ወቅት ሌብነትን መዋጋት ለኢትዮጵ የስነምግባር፣ የሞራል ወይም የሀብት ብክነት ጉዳይ ሳይሆን የህልውናና እንደ አገር የመቀጠልና ያለመቀጠል ጉዳይ ነው። ሌብነት ካለ አገራዊ መረጋጋት፣ ሰላም እንዲሁም በመንግስትና በሕዝብ መካከል መተማመን ሊኖር አይችልም። ሁሉም ዓይነት ሌብነቶች የልማት እንቅፋት ከመሆናቸውም በላይ ለድህነት ስር መስደድ፣ ለዜጎች የሀብት ክፍፍል ልዩነትና ለማሕበራዊ ፍትሕ መጓደል አብይ ምክንቶች ናቸው። ስለሆነም ሙስናን መዋጋትና ሌብነትን ማዳከም ማለት መልካም አስተዳደርን ማስፈን፤ የሕግ የበላይነት ማረጋገጥ፣የዴሞክራሲ ባሕል መጎልበትና ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ ማለት ነው። ይህም ለብልጽግናና ለዜጎች ኑሮ መሻሻል መሰረት መጣል ማለት ነው። ስለሆነም በብልጽግና ፓርቲ ለሚመራ መንግስት ከዚህ በላይ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ተግባር ይኖራል ተብሎ አይገመትም።
ቀጣዩ መንግስት ሌብነትን ለማዳከምና የአገር እድገት እንቅፋት መሆን ከማይችልበት ደረጃ ላይ ለማድረስ አልሞ መስራት አለበት። በቅድሚያ በገዢው ፓርቲ ውስጥ ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት ሊኖረውና አባላቱንና አመራሩን በዚሁ ማዕቀፍ ውስጥ ሊያጠራና ሊያሰማራ ይገባዋል። ገዢው ፓርቲ ጠንካራ የአባላት የሥነምግባር ደንብ በማውጣት መላ አባላቱ እንዲገነዘቡትና እንዲተገብሩት ሊያደረግ ይገባል። በየደረጃው በሌብነት የተጨማለቁ አመራሮችንና ቢሮክራቶችን ገምግሞ ያለ ምሕረት ማጥራት የመጀመሪያው ቁልፍ ሥራ ሊሆን ይገባል። ያፈራውን ንብረት ለማስመዝገብ የሚያንገራግር የመንግስት ኃላፊና ሠራተኛ በምን ሞራል ሌብነትን ሊያወግዝና ሊታገል ይችላል? መሪነት አርአያነት ነው።
የአርአያነት ቁጥር አንድ መለኪያው ደግሞ በዝንባሌም በተግባርም ከሌብነት መጽዳት ነው። ብቁ፣ በስነምግባራቸው የተመሰገኑ፣ ውጤታማና ከፖለቲካ ስልጣን ውጭ ቢሆኑ እንኳን ሰርተው መኖር የሚችሉ ስልጣንን መኖሪያቸው ያላደረጉ ሰዎችን ወደ አመራርነት የማምጣት አስፈላጊነት ሊተኮርበት ይገባል። የመንግስት ቢሮክራሲ በተለይም ዋናዋና ለሌብነት ተጋላጭ ዘርፎች አካባቢ የሰው ኃይል ስምሪቱ ለብቃትና ለስነምግባር ከፍ ያለ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል።
የአገር ኢኮኖሚ በፈቀደ መጠን የመንግስት ባለስልጣናትና የመንግስት ሰራተኞች ራሳቸውንና ቤተሰቦቻቸውን ለማኖር የሚያስችልና ከስልጣን በተነሱ ጊዜ የኑሮ ዋስትናቸው እንዳይናጋ የሚያደርግ ደመወዝና ጥቅማጥቅም ሊጠበቅላቸው ይገባል። ስለ ነገ የቤተሰቡ እጣ ፋንታ እየተጨነቀ ዛሬን በውጤታማነትና በንጽህና ለማገልገል የሚፈቅድ የመንግስት ባለስልጣንና ሠራተኛ ማግኘት ከባድ እንደሆን በመገንዘብ መንግስት ተገቢውን ማስተካከያ ሊያደርግ ይገባል፡፤
ሌብነትና ሙስናን ለሚፋለሙ አካላትና ዜጎች ማበረታቻ መስጠት እጅግ አስፈላጊ ነው። ለምሳሌ የተጭበረበረ ታክስን በኦዲት ወይም በምርመራ ወይም በጥቆማ ተሳትፈው ለሕግ በማቅረብ እንዲከፈል የሚያደርጉ ኃላፊዎች፣ ባለሙያዎች፣ ዜጎች ለአገር ካስመለሱት ገንዘብ በተወሰነ መጠን እንዲከፈላቸው ማድረግ አንድ አማራጭ ሊሆን ይችላል። የወቅቱ ዋናው ጠላታችን ሌብነት በመሆኑ ሌብነትን የሚጋፈጡ ዜጎች የሚያስፈልጋቸው የኢኮኖሚ ማበረታቻ፣ የህግ ከለላና ዋስትና ብቻ አይደለም። የጀግንነት ሜዳሊያም ሊሸለሙ ይገባል።
የመንግስት አሰራርና መረጃዎች ለዜጎች፣ ለሲቪክ ማህበራትና ለመገናኛ ብዙሃን ተደራሽ መሆን አለባቸው። መገናኛ ብዙሐንም በጥብቅ ዲሲፕሊንና ስነምግባር እንዲሰሩ በማድረግ በጸረ-ሌብነት ትግሉ አወንታዊ ሚና እንዲጫወቱ ማድረግ ተገቢ ነው። የመንግስት ግዢዎች፤ የንግድ ፈቃድ አሰጣጥና እድሳት፤ የግብር ማሳወቅና መክፈል ሂደቶችና ሌሎች አገልግሎቶች አሁን ያለው ጅምር ተጠናክሮ በቴክኖሎጂ እንዲደገፉ በማድረግ የሰዎችን ንክኪ መቀነስ ሌላው አማራጭ ነው።
የመንግስት ኃላፊዎች ለመረጣቸው ህዝብ ተጠያቂ የሚሆኑበት ህዝቡም በስፋት የሚሳተፍበት ግልጽ፣ ቀላልና መላው ሕዝብ የሚረዳቸውና የሚያከብራቸው የአሰራር ደንቦችና መመሪያዎችን ማውጣት፣ ያሉትን ማሻሻልና ስራ ላይ ማዋል፤ በየተቋማቱ የሥራ አፈጻጸም ሂደቱና ውጤታማነቱ በግልጽ በሚታወቅ ስርዓትና ህዝቡን ባሳተፈ መልኩ ክትትል የሚደረግበትን ሥራዓት መዘርጋት ያስፈልጋል። ከፍተኛ በጀት ተመድቦላቸው የሚከናወኑ የልማት ፕሮጀክቶች ከጥራት፣ ከጊዜ፣ ከዋጋና ከአገልግሎት አንጻር ኦዲትና ክትትል የሚደረግበት አሰራር ሊዘረጋላቸው ይገባል። የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብና በርካታ የስኳር ፕሮጅክቶች ከአስር ዓመት በላይ በተንከባለሉባት አገር በቅርቡ በመዲናችን የተከናወኑ ድንቅ የሸገር ልማት ፕሮጅክቶችን እንደ ሞዴልና መልካም ተመክሮ ወስዶ በማስፋት ውጤታማነትን ማጎልበት ይገባል።
አገራችን በውጭ ምንዛሬ እጥረት እየተቸገረች ባለችበት በአሁኑ ወቅት አንጡራ ሀብቷን በጥቁር ገበያና በሀሰተኛ የወጪ ንግድ እየተዘረፈች ሀብቷም እንደ ዜጎቿ እየፈለሰ የሚገኝ በመሆኑ የወጪና ገቢ ንግዱ የሕግ ማዕቀፍና ቢሮክራሲ ምንም ያህል ውስብስብና አታካች ቢሆን እያራቆተን ያለውን የሀብት ፍልሰት ሊገታው አልቻለምና ሊፈተሸ ይገባል። ሌቦች በአግባቡ ክትትል ተደርጎባቸው በሕግ ተጠያቂ የሚሆኑበት አሰራርና ይሕን የሚያስፈጽም ጠንካራና ገለልተኛ የህግና የፍትህ አደረጃጀት መፍጠርና የተሻለ ስነምግባር ባለው ብቁ አመራና የሰው ኃይል ማሟላት ያስፈልጋል። ከረጅም ጊዜ አንጻር ለህጻናትና ለወጣቶች በትምህርት ስርዓቱ ሌብነትን የሚጸየፍ የግብረገብነት ትምህር እንዲሰጥ በማድረግ የሌብነትን አሰተሳብ ከትውልዱ አእምሮ መንቀል ያስፈልጋል።
አባቡሌ ከጉለሌ
አዲስ ዘመን መስከረም 10/2014