ከሐምሌ ወር መባቻ ጀምሮ የሰብዓዊ እርዳታ ጭነው ወደ ትግራይ ክልል ከገቡ 466 ተሽከርካሪዎች መካከል የተመለሱት 38 ብቻ መሆናቸውን፣ እንዲሁም ባለፈው ሳምንት መቐለ ከደረሱት 146 መኪናዎች መካከል አንዳቸውም እንዳልተመለሱ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስታውቋል፡፡ ሁኔታውን ‹‹አሳሳቢ›› ሲል የገለፀው ድርጅቱ፤ ‹‹ሕይወት አድን የሆኑ ሰብዓዊ እርዳታዎችን ለትግራይ ክልል ለማቅረብ ተሸከርካሪዎች ያስፈልጉኛል›› ብሏል፡፡
የኢ.ፌ.ዲ.ሪ መንግሥትም ቀደም ሲል ጉዳዩን አስመልክቶ ይፋ ባደረገው መረጃ፣ ሰብዓዊ እርዳታዎችን ለማቅረብ ወደ ትግራይ ክልል የሄዱ ተሸከርካሪዎች እንዳልተመለሱና ተሽከርካሪዎቹ ከተፈቀደላቸው ዓላማ ውጭ ላለመሰማራታቸው ማረጋገጫ እንደሌለ አስታውቆ ነበር፡፡ የመንግሥታቱ ድርጅት ይፋዊ መረጃም ይህንን የመንግሥት መረጃ የሚደግፍ ሆኖ ተገኝቷል፡፡
ጉዳዩ ከሌሎች አካላት በበለጠ በቅርበት የሚመለከተው የዓለም የምግብ መርሃ ግብር (World Food Program – WFP) መኪኖቹ አለመመለሳቸውን አምኗል፡፡ አስገራሚው ጉዳይ ግን ተሽከርካሪዎቹ ያልተመለሱበትን ምክንያት ለመጥቀስና ‹‹ሰብዓዊ እርዳታዎች ያስፈልጋሉ›› የሚለውን የራሱን ተደጋጋሚ ማሳሰቢያ ውሃ እንዲበላው የሚያደርግ ክስተት ሲፈጠር ክስተቱን አለማውገዙ ነው፡፡
ድርጅቱ በቃል አቀባዩ ጄማ ስኖውደን በኩል ባወጣው መግለጫ፣ 38 መኪናዎች ብቻ እንደተመለሱና ሰብዓዊ እርዳታዎችን ለማቅረብ የተሽከርካሪ እጥረት እንዳጋጠመው አስታውቋል፡፡ ‹‹በአሁኑ ወቅት ሰብዓዊ እርዳታዎችን ለትግራይ ክልል ለማቅረብ ዋነኛ እንቅፋት የሆነብኝ የተሽከርካሪ እጥረት ነው›› ብሏል ።፡ የድርጅቱን መግለጫ ይበልጥ አስገራሚ የሚያደርገው ደግሞ ‹‹ተሽከርካሪዎቹ የት እንደሆኑ አላውቅም›› ማለቱ ነው፡፡ ሰብዓዊ እርዳታዎችን በማከፋፈል ግንባር ቀደም ሚና ይዞ የሚገኝ ድርጅት እርዳታ የጫኑ መኪናዎች የት እንደሚገኙ አያውቅም ቢባል ማን ያምናል?
‹‹ትግራይ እየተራበች ነው … የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት በመንግሥት ኃይሎች እየተስተጓጎለ ነው …›› የሚሉ አያሌ ክሶች እየቀረቡ ባሉበት በዚህ ወቅት ድርጅቱ ለትግራይ ክልል የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት የሚያደርሱ ተሽከርካሪዎች ከትግራይ አለመመለሳቸውን በመግለጽ ፤ ለምን እንዳልተመለሱ ምክንያቱን ለመናገር ግን ፈቃደኛ አይደለም ፤ይባስ ብሎም ‹‹ተሽከርካሪዎቹ የት እንደሆኑ አላውቅም›› የሚል ምላሽ መስጠቱ ሁንታውን የበለጠ ግራ አጋቢ ያደርገዋል። ተቋሙ የአሸባሪውን ቡድን ተግባር ከማውገዝ ይልቅ እንዲህ ዓይነት ሀላፊነት የጎደለው ምላሽ የመስጠቱ እውነታ ብዙ ጥያቄ የሚያስነሳ እንደሆነ ይታመናል ፡፡
የዓለም የምግብ መርሃ ግብር የሰብዓዊ እርዳታ አቅራቢ ተሽከርካሪዎች አለመመለስን አለማውገዙም ሆነ ‹‹ተሽከርካሪዎቹ የት እንደሆኑ አላውቅም›› ማለቱ ፤ ከሁሉም በላይ ድርጅቱ የአሸባሪውን ህ.ወ.ሓ.ት ወንጀል እየደበቀ ነው ለሚሉ ሰፊ አስተያየቶች እያጋለጠው ይገኛል ፡፡ ከዛም ባላይ ከቡድኑ ጋር ያልተገባ ግንኙነት አለው ለሚሉም ወገኖችም ጠንካራ ትችት ተጋላጭ እያደረገው ይገኛል ።
አሸባሪው ህወሓት የደርግ መንግሥትን ለመጣል የበረሃ ትግል ላይ በነበረበት ወቅት የዓለም የምግብ መርሃ ግብርን ጨምሮ ከሌሎች ድርጅቶች ጋር ምን ሲያደርግ እንደነበርና በሰሜን ዕዝ ላይ ከፈፀመው ክህደት በኋላ ከእርዳታ ድርጅቶች ጋር ስለነበረው ግንኙነት ለሚያውቅ ሰው ይህ ዓይነቱ አጋጣሚ ከአጋጣሚ የዘለለ ሊሆን እንደሚችል ለመገመት አያስቸግረውም ፡፡
ለመሆኑ የዓለም የምግብ ድርጅት የአሸባሪው ህ.ወ.ሓ.ት ታጣቂዎችን በገፍ ጭነው ስለታዩት ተሽከርካሪዎች ፎቶ መረጃ የለውም ? በተቋሙ በኩል ለቡድኑ አመራሮች የሳታላይት ስልኮች እየቀረበ ነው የሚለውን ክስ ሳይሰማ ቀርቶ ነው ? ይህ ሁሉ እየሆነ ባለበት ድርጅቱ አሸባሪውን ህ.ወ.ሓ.ትን የወንጀል ተግባር በአደባባይ ለማውገዝ ምን ቸገረው ?
ይህ ብቻ አይደለም ከሳምንታት በፊትም አሸባሪው ህ.ወ.ሓ.ት የአሜሪካ ዓለም አቀፍ ልማት ኤጀንሲ (USAID) የእርዳታ መጋዘኖችን መዝረፉን የኤጀንሲው የኢትዮጵያ የበላይ ኃላፊ ሾን ጆንስ ቢናገሩም የኤጀንሲው ዋና አስተዳዳሪ ሳማንታ ፓወር ግን ስለድርጅታቸው መዘረፍ ምንም ሳይሉ ቀርተዋል፡፡
የኢትዮጵያን መንግሥት በመክሰስ ግን ሴትዮዋን ማንም አይቀድማቸውም፡፡ የሰብዓዊ እርዳታ የያዙ የድርጅታቸው መጋዘኖች በአሸባሪው ህ.ወ.ሓ.ት ተዘርፈው ሳለ እርሳቸው ግን አሁንም ‹‹የኢትዮጵያ መንግሥት እርዳታ ወደ ትግራይ እንዳይገባ እያደረገ ነው …›› የሚለው የተለመደ ክሳቸው ላይ ናቸው ፡፡
ሌላም ጉድ አለ … በስደተኛ መታወቂያ የቡድኑ ተዋጊ ሆነው የተገኙ ሰዎችም እንዳሉ የሚያሳዩ መረጃዎችንም ተመልክተናል፡፡ ጉዳዩ የሚመለከተው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን (UNHCR) ስለታጣቂ ስደተኞች ተጠይቆ ‹‹ … ጉዳዩን አጣራለሁ … እየተከታተልኩት ነው …›› የሚል የፌዝ ምላሽ ሰጥቷል፡፡
የዓለም የምግብ መርሃ ግብርን ጨምሮ ሌሎች ‹‹በሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት ላይ ተሰማርተናል›› የሚሉ ድርጅቶች ጓዳቸው ሲፈተሽ የሚታየውና የሚሰማው ነገር እጅን አፍ ላይ የሚያስጭን እንደሆነ ለድርጅቶቹ ቅርበት ያላቸው አካላት በተደጋጋሚ ለአደባባ ያበቁት ሃቅ ነው፡፡
የምዕራባውያን ‹‹የእርዳታና የመብት ተሟጋች ድርጅቶች›› በሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት እና በመብት ተሟጋችነት ሽፋን የፖለቲካ ሴራዎችን በማቀነባበር እንደሚታሙ ከዛም ባለፈ እንደሚከሰሱ የሚታወቅ ነው ፡፡
ይህ ሴረኛነታቸው በቀደሙት የንጉሳዊውና ወታደራዊ ዘመነ መንግሥታት በግልጽ ታይቷል፡፡ እርዳታን ከሰብኣዊነት ይልቅ ፖለቲካዊ ገፅታ በማላበስ ተጠምደው እንደነበር ይታወቃል። እርዳታን በቀጥታ ለአማፂያን ከመስጠት ጀምሮ የውሸት መረጃዎችን በመፈብረክ ፖለቲካዊ ዓላማቸውን ሲያስፈፅሙ ነበር። የአሸባሪው ህ.ወ.ሓ.ትን የዘረፋ ወንጀል መሸፋፈንና ለማውገዝ አለመፈለግም የዚሁ ሴረኛ አካል ሊሆን እንደሚችል አሁን አሁን ብዙዎች እየተስማሙበት ያለ እውነታ ነው፡፡
‹‹ትግራይ እርዳታ እንዳታገኝ ተከልክላለች፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ተፈፅመዋል … ብለው ሲጮሁ የከረሙት የአውሮፓና የአሜሪካ ሹማምንት የቡድኑን የአደባባይ ከባድ የዝርፊያሆነ የሰብዓዊ እርዳታ አቅራቢ ተሽከርካሪዎችን አግቶ የመያዝ ወንጀሎችን ማውገዝ አልፈለጉም፡፡ አንዳንዶቹ እንኳንስ ዝርፊያውንና እገታውን ሊያወግዙ ይቅርና ወንጀሉን ሕጋዊ ለማድረግ ሲጥሩ ታይተዋል፡፡
የዓለም የምግብ መርሃ ግብር ‹‹እርዳታ ለማቅረብ ተሽከርካሪ አነሰኝ›› ብሎ ‹‹ለምን አነሰህ? ተሽከርካሪዎቹ የት ሄዱ?›› ቢባል ለችግሩ ተጠያቂ የሆነውን አሸባሪው ህ.ወ.ሓ.ትን ላለማውገዝ ሲል ትክክለኛውን ምክንያት እንደማይናገር ሁሉ የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብዓዊ እርዳታ ማስተባበያ ቢሮ (OCHA) ‹‹ … በትግራይ ያለው የእርዳታ እህል እያለቀ ነው፤መንግሥት እርዳታ እንዳይገባ መሰናክል እየሆነ ነው …›› ብሎ የተለመደ ውንጀላውን ቢያሰማም ‹‹እርዳታው እንዴት አለቀ?›› ተብሎ ቢጠየቅ ግን እውነተኛውን ምክንያት መናገር የሚፈልግ አይመስልም፡፡
እነዚህ ተቋማት ‹‹ስለአሸባሪው ህ.ወ.ሓ.ት ወንጀል ለምን አትናገሩም?›› ተብለው ሲጠየቁ ‹‹ … ማስረጃ የለንም፤በአካባቢው ባለው አስቸጋሪ የፀጥታ ሁኔታ ምክንያት ጉዳዩን ለማጣራት አልቻልንም፤ጉዳዩን ለማረጋገጥ የኢትዮጵያ መንግሥት ያቋረጣቸውን የስልክ፣ የመብራትና የባንክ አገልግሎቶች ማስጀመር አለበት …›› በማለት የተለመደውን ምክንያታቸውን ያስተጋባሉ፡፡
‹‹የሰብዓዊ መብት ጥሰት እየተፈፀመ ነው … የሰብዓዊ እርዳታ ተከልክሏል …››ለሚለው ውንጀላቸው ግን ምንም ማጣሪያና ማስረጃ አያስፈልጋቸውም፤ያለበቂ ማስረጃ የኢትዮጵያን መንግሥት መክሰስና መወንጀል ምንም አይመስላቸውም፤እንዲያውም ይህን ኢ-ፍትሐዊ ድርጊታቸውን የሰብዓዊነት መግለጫ አድርገው ይቆጥሩታል፡፡
የእርዳታ ድርጅቶችን የአሸባሪው ህ.ወ.ሓ.ትን ድብቅ ፍቅር የሚያውቁ ሰዎች ስለዚህ ጉዳይ የተናገሩት ሃሳብ እንደዋዛ የሚታይ አይደለም ብዬ አምናለሁ፡፡ ነገሩ ይህን ይመስላል … የዓለም የምግብ መርሃ ግብር ‹‹የሰብዓዊ እርዳታ አቅራቢ ተሽከርካሪዎች ከትግራይ አልተመለሱም … የተሽከርካሪ እጥረት ገጠመኝ …›› ብሎ ሲናገር ቡድኑ በቃል አቀባዩ በኩል ‹‹መኪኖቹ ያልተመለሱት በነዳጅ እጥረት ምክንያት ነው›› የሚል ምላሽ ሰጥቷል፡፡
የዓለም የምግብ መርሃ ግብር ‹‹የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት ለትግራይ በፍጥነት ማድረስ አለብኝ፤ይህን ለማድረግ ደግሞ ተሽከርካሪዎች ያስፈልጉኛል፤ነዳጅ ወደ ትግራይ ይግባና መኪናዎቹ ይመለሱልኝ …›› የሚል አቤቱታ አሰምቷል ፡፡
መቼም ለማንም ባለ አእምሮ የእርዳታ አቅርቦት ጭነው የሄዱት መኪኖች ወደ ትግራይ ሲገቡ መመለሻ ነዳጅን ታሳቢ አድርገው እንደሚሰማሩ ይታመናል ። መሬት ላይ ካለው ችግር ጋር በተያያዘም በመኪኖቹ የመጠባበቂያ ነዳጅ ማከማቻዎች ውስጥ አስፈላጊውን ነዳጅ ይዘው እንደሚጓዙም ይታመናል ። መኪኖቹም ከዚህ አንጻር ችግር ያለባቸው አይደሉም ፣ከዚህ ውጪ መኪኖቹ ትግራይ ከገቡ ቦኋላ ስለነዳጅ ማሰብ ተገቢ አይደለም። ይህ አይነቱ አሰራር ለብዙ ትዝብት የሚያጋልጥ ጭምር ነው ፡፡
በአጠቃላይ የዓለም የምግብ መርሃ ግብርን ጨምሮ ሌሎች ‹‹በሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት ላይ ተሰማረናል›› የሚሉ ድርጅቶች የአሸባሪው ህውሓትን ከባድ ወንጀሎች ባለማውገዝ እራሳቸውን ከፍ ላለ ትዝብት እየዳረጉ የመገኘታቸው እውነታ የአደባባይ ሚስትር እየሆነ ነው!
አዲስ ዘመን መስከረም 10/2014