በሰው ልጅ ህይወት ውስጥ ተስፋ መቁረጥን የመሰለ የከፋ ርግማን የለም።አንድ ሰው በህይወቱ ተስፋ ከቆረጠና ይህንኑ ከራሱ ጋር መምከር ከጀመረ እንኴን ለሌላው ለራሱም የሚሆንበት እድል የለውም።ፍጻሜውም እጅግ የከፋ እንደሚሆንም ብዙ የህይወት ተሞክሮዎችን ይመሰክራሉ።
የተስፋ መቁረጥ እውነታ ቡድናዊ ገጽታ ሲኖረው ደግሞ ነገሩ አስከፊ ከመሆኑም በላይ ሊያስከትል የሚችለውም አደጋ ለወሬ የሚመች አይደለም። ተፈጥሯዊ የሆነውን የሰው ልጁ ነገሮችን በሃላፊነት የመረዳትና የመተግበር ማንነትን በማጥፋት ፍጹም አውሪያዊ ባህሪ የሚያላብስ ክስተት ጭምር ነው።
ይህ አውሬያዊ ባህሪ በጊዜ ካልተገራ ፍጥረታዊ የሆነውን ሰብአዊ ስብእናን ከማጥፋት ባለፈ ከሰብአዊነት ያፈነገጡ ተግባሮችን ለመስራትም ሆነ ተግባራቱን ሌሎች እንዲደግፉና እንዲተገብሩ በሀይል ጭምር ግፊት በማድረግ አጥፍቶ ወደ መጥፋት ፍጹም ሰይጣናዊ ተግባር መሸጋገሩ የማይቀር ነው።
በእኛም ሀገር በትግራይ ክልል ዛሬ ላይ የሚታየው እውነታ ከዚህ የስብእና ቀውስ የሚመነጭ ነው። ይህንን ችግር በአግባቡ መረዳት ካልተቻለ ሀገርን ሊያስከፍል የሚችለው ዋጋ ከፍ ያለ ስለመሆኑ ለመገመት የሚቸግር አይደለም። እንደ አገር በዚህ ችግር ምክንያትም እየከፈልነው ያለው ዋጋ ቀላል አይደለም።
አሸባሪው ህወሓት ገና ከፍጥረቱ የተነሳበት የተሳሳተ የፖለቲካ አስተሳሰብና ለዚሁ አስተሳሰብ ሕይወት ለመስጠት የሄደበት የሴራ መንገድ የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር መልሶ ራሱን ዋጋ እንደሚያስከፍለው ለመገመት ኢትዮጵያንና ኢትዮጵውያውያንን በአግባቡ ለሚረዳ ብዙም የሚከብድ አይደለም።
የቡድኑ አመራሮች ራሳቸውም ሆኑ በዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ በገመዷቸው ውስብስብ ሴራዎች በተፈጠረ ድል አዲስ አበባ ገብተው ስልጣነ በትሩን የመያዛቸው እውነታ በፈጠረባቸው ትዕቢትና እብሪት ራሳቸውን አልፋና ኦሜጋ አድርገው እንዲያዩ ሆነዋል። ከዚያም በላይ ለራሳቸው ያልተገባ ማንነት በመፍጠር ይህንኑ ወደ ማምለክ ገብተዋል ።ይህንኑ የሚሸከሙ ትርክቶችንም ፈጥረው እሱኑ በማዳመጥ ዝለዋል።
ባስልጣን ላይ በነበሩባቸው 27 ዓመታት ከዚህ መንፈስ በተቀዳ ስብእና በሀገርና በህዝብ ላይ ከፍ ያሉ በደሎችን መከራ እና ስቃዮችን አድርሰዋል። ዜጎች እንደ ሀገር ባለቤትነታቸው ስለሀገራቸው በኃላፊነት እንዳያስቡ፤ በገዛ ሀገራቸው ጉዳይ ባይተዋር እንዲሆኑም አድርገዋል።
የሀገሪቱን እና የሕዝቦቿን ሀብት የቡድኑ ሀብት አስኪመስል ድረስ ኃላፊነትና ተጠያቂነት በጎደለው መልኩ በግልጽ ዘርፈዋል። በዚህም ሀገርና ህዝብን ቀጣይነት ላለው ዕዳ ዳርገዋል። ከፍ ያለ የሀገር ሀብትም በአንድም ይሁን በሌላ ባልተገባ መልኩ በእጃቸው እንዲገባና ከሀገር እንዲወጣም አድርገዋል።
ራሳቸው በፈጠሩት ያልተገባ የማንነት ትርክት የጦዙት የቡድኑ አመራሮች ተጨባጭ የሆነውን እውነታ ለመቀበል ፈቃደኝነት ባጡ መጠን ፣ በተፈጠሩ የህዝብ አመጾች ያለ አንዳች የጥይት ድምጽ ባልገመቱትና ባልጠበቁት መንገድ ከስልጣን ተባረው መቀሌ ለመክተም በቅተዋል።
የቡድኑ አመራሮች በመቀሌ ቆይታቸው ራሳቸው ስተው እንወክለዋለን ያሉትን ህዝብ ባሳቱበት የተዛባ ትርክትና ትርክቱ በፈጠረው ሞቅታ ተመልሰን ወደ ስልጣን እንመጣለን፤ የቀደሙትን ያልተገቡ ጥቅሞች እናስጠብቃለን በሚል የከሰረ ህሳቤ የትግራይን ህዝብ ሲጠብቅ በነበረው የመከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት በመሰንዘር በታሪካቸው ትልቁን ስህተት ፈጽመዋል።
ይህንንም ተከትሎ በተካሄደው የህግ ማስከበር ዘመቻ ምኞታቸው ቅዥት እስኪሆን ድረስ ከፍ ያለ ኪሳራ ደርሶባቸዋል። ኪሳራው የፈጠረውን የስነ ልቦና ቀውስ ለማከም የትግራይ ህጻናትና እናቶችን ሳይቀር ወዳልተገባ ጦርነት በማስገባት ተጨማሪ ታሪካዊ ስህተት ፈጽመዋል።
የቡድኑ አመራሮች ከአንድ ስህተት ወደ ሌላ ስህተት እየተሸጋገሩ ፤ ከስህተቶቻቸው ከመማር ይልቅ ያልተገቡ የማንነት ትርክቶች በፈጠሩት መታወር ዕድሜያቸውን በሚያሳጥሩ የተንሰላሰሉ ስህተቶች ለማለፍ ተገደዋል።
በቅርቡ የቡድኑ አፈቀላጤ አሸባሪው አቶ ጌታቸው ረዳ የግብጹ ፕሬዚዳት ንብረት እንደሆነ ከሚነገርለት የቴሌቪዥን ጣቢያ ጋር ባደረገው ቃለ መጠይቅ የቡድኑ አመራሮች ፖለቲካ ስብእና ወደ አጥፍቶ መጥፋት የተስፋ መቁረጥ ደረጃ መድረሱን አሳይቷል ። በግልጽና በአደባባይ ሀገር ለማፍረስ የግብጽን መንግስት ተማጽኗል።
ይህ ፍጹም በተስፋ መቁረጥ የተሞላ ቃለ መጠይቅ ከሁሉም በላይ ለትግራይ ህዝብ ከፍ ያለ መልእክት የሚያስተላልፍ ነው። የህ የወረደ ተግባር የትግራይ ህዝብ በሀገረ መንግስት ግንባታ ውስጥ የነበረውን ከፍ ያለ ተሳትፎ እና የመስዋእትነት ታሪክ የሚያጠቁርና ለሀገር ክብር የሞቱ የትግራይ ሰማዕታትን ዳግም የገደለ የአደባባይ የባንዳነት ተግባር ነው።
ቃለ መጠይቁ ቡድኑ በመጨረሻው የታሪክ ምእራፉ ላይ ከፍ ባለ የተስፋ መቁረጥ እርግማን እየተቅበዘበዘ እንደሚገኝም ያመላከተ ነው። ቡድኑ በዚህ ሁኔታ ውስጥ የመገኘቱን እውነታም የትግራይ ህዝብ በአግባቡ ሊገነዘበው እንደሚገባም መልእክት ያስተላለፈ ነው።
አሸባሪው ህወሓት ራሱ ጠፍቶ የትግራይን ህዝብ የዚህ ጥፋት አካል ለማድረግ እየባዘነ መሆኑን በተጨባጭ ያሳየ፤ የትግራይ ህዝብ እራሱን ከዚህ ቡድን እንዲለይ ፤ የራሱን እጣ ፈንታ እራሱ መወሰን ወደ ሚያስችለው መንገድ እንዲመለስ የሚጠይቅ የማንቂያ ድምጽ ጭምር ነው!
አዲስ ዘመን መስከረም 10/2014