የሴቶች እግር ኳስ ልክ እንደ ወንዶቹ በዓለም ላይ እኩል ትኩረት ይሰጠዋል ማለት ቅጥፈት ነው። የሴቶች እግር ኳስ እንኳን እንደ አፍሪካ ባሉ ያላደጉ አገራት ባደጉት አገራትም ከወንዶች እኩል ትኩረት እንደማይሰጠው አያከራክርም። ያም ሆኖ ለሴቶች እግር ኳስ ቀና አስተሳሰብ ባላቸው ጥቂት ግለሰቦች ይህ አስተሳሰብ እየተሰበረ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተሻለ ትኩረት እያገኘና እያደገ ስለመምጣቱ መካድ አይቻልም።
ለዚህም የተለያዩ ግለሰቦች እልህ አስጨራሽ ትግል ማድረጋቸው ዛሬ ላይ እንዲመሰገኑ አድርጓቸዋል። እንደ ኢትዮጵያ ባሉ የወንዶች እግር ኳስ እንኳን ባላደገባቸው አገራት በሴቶች እግር ኳስ ላይ ጊዜ፣ እውቀትና ገንዘብን ለማባከን አርቆ አሳቢነትንና ትልቅ ተስፋን መሰነቅ ይጠይቃል። አሰልጣኝ ብርሃኑ ግዛው ለዚህ ትልቅ ምሳሌ መሆኑ ብዙዎችን ያስማማል። በሴቶች እግር ኳስ ላይ ተስፋ ሳይቆርጥ ረጅም ዓመት ሰርቶ ለታላላቅ ስኬቶች ከመድረሱም በላይ ወደ ስኬት የተሸጋገረበት የሕይወት ውጣውረድ ለብዙዎች ትምህርት ይሆናልና በዛሬው የስፖርት ማህደር አምዳችን ከጋዜጠኛ ታምሩ አለሙ ማስታወሻ የተወሰደውን የአሰልጣኝ ብርሃኑ ግዛውን ሕይወት ለመዳሰስ ወደድን።
ከሳምንት በፊት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሴቶች ክለብን በማሰልጠን በኬንያ በተካሄደው የመካከለኛውና ምሥራቅ አፍሪካ (ሴካፋ) የክለቦች ቻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታ አስደናቂ ጉዞ ያደረገው አሰልጣኝ ብርሃኑ ቡድኑ በተጋጣሚዎቹ ላይ በአራት ጨዋታዎች ከሁለት ደርዘን በላይ ግብ አስቆጥሮ ለፍፃሜ መድረሱ ይታወቃል። በፍፃሜው ጨዋታ ግን ግልፅ በሆነ የዳኝነት በደል የዞኑን ዋንጫ ሳያነሳ በመቅረቱ በቀጣይ ዓመት በግብፅ በሚካሄደው የአፍሪካ ክለቦች ቻምፒዮንስ ሊግ ውድድር በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የመሳተፍ ተስፋው ሳይሳካ ቀርቷል። ያም ሆኖ በሴካፋው ፍልሚያ እስከ ፍፃሜ የተጓዘበት መንገድና የገነባው ቡድን ትልቅ ተስፋ የታየበትና አድናቆትን ያተረፈለት ሆኗል።
አሰልጣኝ ብርሃኑ በ1972 ዓ.ም የተወለደው ሰሜን ሸዋ ዞን ከሸኖ ከተማ ወጣ ብላ በምትገኘው መኑሻ የገጠር መንደር ውስጥ ነው፤ ለቤተሰቡ ደግሞ የመጀመሪያ የበኩር ልጅ ነው። ገና በስድስት ዓመቱ እናትና አባቱ በመለያየታቸው ከአያቶቹ ጋር ለመኖር የተገደደው የያኔው ታዳጊ የዛሬው የኢትዮጵያ ሴቶች እግር ኳስ መሪ፤ ወላጆቹ ወደ አዲስ አበባ ሄደው ለየብቻ አዲስ ኑሮ ሲመሰርቱ እሱ ከአያቶቹ እርሻ፣ አያቶቹ ቀዬ ውስጥ ቀረ።
በአስራ አንድ ዓመቱ የእናትና የአባቱ ናፍቆት ሲበረታበት ወላጆቹን ፍለጋ ከቤት ጠፍቶ በክፍት መኪና ተደብቆ ወደ አዲስ አበባ መጣ። የመኪናው መዳረሻ መሀል መርካቶ ነበር። ብርሃኑ ከመነሻው እንዳሰበው ወላጆቹን አዲስ አበባ ላይ በቀላሉ ማግኘት ባለመቻሉ ጎዳና መውደቅ ዕጣፈንታው ሆነ፤ ሰው ከሞላው የገበያ ሰፈር የሰው ናፍቆቱን ይዞ ትንሹ ብላቴና መንገድ ላይ ዋለ፤ በረንዳ ላይ ተኛ።
ከሁለት ቀን በኋላ አዲስ አበባ የሚኖረው ነጋዴው አጎቱ ያመጣውን ሸጦ ሲመለስ ታዳጊው ብርሃኑ ደግሞ ጎጃም በረንዳ አካባቢ ምግብ ፍለጋ ሲዞር ድንገት ተገናኙ፤ ለሁለቱም የዕድልና የገድ ቀን ሆነ። አጎቱ የገበያ ገድ ሞላለት፤ እሱ ደግሞ ዕድለኛ ሆኖ በአጋጣሚ የስጋ ዘመድ አጉራሽ አልባሹን አገኘ፤ ወደ ቤቱ ይዞት ሄደ፤ አብረው መኖርም ጀመሩ። ብርሃኑ ትምህርት እየተማረ ጎን ለጎን አጎቱን ያግዛል፤ ቅቤና እንቁላል ይሸጣል።
በአንዱ ቀን የተሰጠውን እንቁላልና ቅቤ ሸጦ ጨርሶ 140 ብር ይዞ ወደቤቱ ሊመለስ ሲል አንድ ሰው አስቆመው። «ጋዝ ግዛልኝ» ብሎ 11 ብርና ጄሪካን ሰጠው፤ ለሚላክበት ደግሞ አምስት ብር ጉርሻ ሸጎጠለት፤ ሰውየው መያዣ እንዲሆን ግን 140 ብሩ እኔ ጋር ይቀመጥ ብሎ ወሰደበት፤ ታዳጊው በአምስት ብሩ የሚበላውን ቀይ ወጥ እያሰበ ጄሪካኑን ይዞ ሄደ፣ ከማደያ ጋዙን ገዝቶ ሲመለስ ሰውየው የለም፤ ብሩን ይዞበት ጠፍቷል፤ የአጎቱን ቁጣና ዱላ ፈርቶ ምን ይዤ ልመለስ ወደ አጎቴ ቤት ብሎ ድጋሚ ጎዳና ወጣ፤ አስር ቀን ውሎና አዳሩ ጎዳና ላይ ሆነ፤ በአስራ አንደኛው ቀን በፍለጋ ተገኘ፤ ተመክሮ ወደ ቤቱ ተመለሰ፤ አጎቱን በሥራ እያገዘ ትምህርቱን ቀጠለ።
ከልጅነቱ ጀምሮ ያደረበትን የኳስ ፍቅር ለመወጣት ጃንሜዳ መዋል አዘወተረ፤ ግብ ጠባቂ ለመሆን ወሰነ። በአንድ ክለብ የሲ ቡድን በረኛ ምልመላ ላይ ከብዙዎች አንዱ ሆኖ ተወዳደረ፤ ከመጨረሻዎቹ አምስት ዕጩ በረኞች መካከል አንዱ እሱ ነበር። መልማዩ አሰልጣኝ ግን «እጅ ውርወራ» አትችልም አለው፤ እሱን ለማስተካከል ጃንሜዳ ላይ በርትቶ ሰራ፤ መጨረሻ ላይ ግን «እጅ ውርወራ» የተባለው ገንዘብ አምጣና ወደ ክለቡ ላስገባህ መሆኑን ተረዳ፤ ሳይመረጥ ቀረ።
1987 ዓ.ም እግርኳስ ተጫዋችነቱ አልሳካ ሲለው ለተሻለ ሕይወት ስደትን መረጠ፤ ከአስር ጓደኞቹ ጋር ሆኖ በሱዳን በኩል ግብፅን አልፈው እስራኤል ድንበር ደረሱ። አራቱ ጓደኞቹ ግን የሲና በረሀ ሲሳይ ሆነው ሕይወታቸው አለፈ። አንዱ የበረሀ ወዳጁ እጁ ላይ ነው የሞተበት፤ እሱን ጨምሮ በሕይወት የተረፉት ስድስቱ እስራኤል ድንበር ላይ ተይዘው አንድ ዓመት ከስድስት ወር ታስረው ወደ ሀገር ቤት ተመለሱ።
ከዚህ ሁሉ የሕይወት ውጣውረድና ተስፋ አስቆራጭ ፈተና በኋላ 1989 ዓ.ም አዲስ ሕይወት ልጀምር ብሎ የሰፈር ወጣቶችን እኩዮቹን ሰብስቦ በተለይ በቡድን ፀብ አካባቢውን ያሰለቹ ጎረምሶችን ይዞ ጃንሜዳ ላይ ማሰልጠን ጀመረ፤ ይህንን ያየው የወረዳው አስተዳዳሪ የወረዳውን ቡድን እንዲያሰለጥን ዕድል ሰጠው፤ ከተጫዋቾቹ ጋር ሆኖ ዋንጫ አመጣ፤ ጃንሜዳን ይበልጥ ወደደው፤ አሰልጣኝነትም እየጣፈጠው መጣ።
1990 ዓ.ም ብዙ ትኩረት የማይሰጣቸውን ሴቶችን ማሰልጠን ጀመረ፤ ቀዳሚዎቹ የምኒልክ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ሲሆኑ ጃንሜዳ የሚሰሩ ሌሎች ሴት ተጫዋቾችም ተቀላቀሉት። 1992 ዓ.ም የቡድኑን ገቢ ለማጠናከር መላ ዘየደ፤ ተጫዋቾቹ እንደ ወንድ ለብሰው ሆያሆዬ እየጨፈሩ ለአዲስ ዓመት ደግሞ ቀሚስና ሻሽ ለውጠው አበባዮሽ እያሉ ፍራንካ ይሰበስቡና ኳስ ይገዙበታል፤ ለውድድር ምዝገባ ይከፍሉበታል።
ለገና እና ለፋሲካ ደግሞ ዶሮ እያጫረቱ እየሸጡ ማሊያ ይገዙበታል። የቡድኑ ጅማሬ ጥሩ ባይሆንም ብዙ ጎል እየገባበት ቢሸነፍም ተስፋ አልቆረጠም፤ ሴቶችን ከማጀት ወደ ሜዳ እያስወጣ የወቅቱ የአስተሳሰብ ትችትና መገፋትን ችሎ ሙሉ ትኩረቱን እንስት ኳስ ተጫዋቾች ላይ አደረገ፤ ነገ የብርሃን ቀን እንደሚሆንም አመነ። ሙሉ ቡድኑን የሚወስድ ተገኘ። የካ ክፍለ ከተማ ለአምስት ዓመት ተረከበው፤ ሁለት ዋንጫዎችን ሳመ። ቀጥሎ ይህንኑ ቡድን ለሴቶች እግርኳስ ታላቅ አስተዋፅኦ ያደረገው አቶ አብነት ግርማይ በባለቤትነት የሚመሩት ሴንትራል ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በተሻለ ክፍያ ወሰደው። የመጀመሪያ ደመወዙ 100 ብር ነበር፤ ቡድኑ በአምስት ዓመት ውስጥ ሦስት ዋንጫዎችን አሸነፈ፤ ደመወዙም 1ሺህ 200 ብር ደረሰ።
በአንድ አጋጣሚ ምግብ ቤት ውስጥ የተመለከታት ቆንጆ ልቡን ወሰደችው፤ ተዋደዱ፤ ተጋቡ፤ የእሱ ገቢ ብቁ ባለመሆኑ ባለቤቱ ወደ አረብ ሀገር ሄዳ ለሁለት ዓመት ሰርታ ተመለሰች፤ እሱም በአሰልጣኝነቱ ቀጠለበት። ከጃንሜዳ ወደ የካ ክፍለ ከተማ፣ ከየካ ወደ ሴንትራል ኮሌጅ የተሸጋገረው ቡድኑ ከአምስት ዓመት የሴንትራል ቆይታ በኋላ ንግድ ባንክ ገዛው። ልጆቹን ይዞ ዕድሜና ልምዱን አካብቶ እስካሁን ለ10 ዓመት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን አሰልጥኖ 11 ዋንጫዎችን ከባንክ ቡድን ጋር መጎናፀፍ ቻለ።
በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሴቶች ቡድን አሰልጣኝነት ከሰሞኑ ለሁለት ዓመት ውሉን ያራዘመው አሰልጣኝ ብርሃኑ፣ ለፊርማ ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ ተቀበለ፤ በ100 ብር ደመወዝ የተጀመረው የብርሃን ጉዞ አሁን ከ50ሺህ ብር በላይ የወር ተከፋይነትን አልፏል። እሱ ሴቶችን በ1992 ማሰልጠን ሲጀምር ብሔራዊ ቡድኑ ግን በ1994 ነበር የተቋቋመው፤ ሉሲዎችን ከአራት ጊዜ በላይ እየተመላለሰ አሰልጥኗል፤ አሁንም የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ እሱ ነው።
እስካሁን በአጠቃላይ 22 ዋንጫዎችን ወስዷል፤ በአገር ውስጥና በውጪ ሥልጠናዎችን ተከታትሎ ኤ ላይሰንስ (የመጀመሪያ ደረጃ) ላይ ደርሷል፤ በስደት የረገጣትን ግብፅ የብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ ሆኖ ተመላልሶባታል፤ አንድ ክለብን ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ብቻ ለአስር ዓመት በማሰልጠን በአገራችን ረዥም ዓመት የቆየ አሰልጣኝ የሚል ክብረወሰንን ይዟል፤ አሁንም እዚያው ነው፤ በግሉ ብዙ ፈተናዎችን አልፎ ከስኬት ጫፍ ደርሷል፤ አብራው ኑሮን ከታገለችው ባለቤቱ ጋር በፍቅር የታጀቡ ዓመታትን አሳልፎ ሦስት ልጆችን አፍርቷል።
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኬንያ የሴካፋ ቻምፒዮንስ ሊግ ቆይታው የፍፃሜውን ጨዋታ ሳይጨምር አራት ጨዋታዎች አከናውኖ ሁሉንም አሸንፏል፤ 25 ጎሎችን አስቆጥሮ 3 ጎል ብቻ ገብቶበት ለፍፃሜ የደረሰ ቢሆንም ግልፅ በሆነ የዳኝነት በደል ዋንጫ ሳያነሳ ቀርቷል። የቡድኑ ፊውታራሪዎቹ ሎዛ አበራና መዲና አወል የውድድሩ ክስተት ሆነዋል፤ ቡድኑ ካስቆጠራቸው 25 ጎሎች ሃያ አንዱን ሎዛና መዲና ናቸው ከመረብ ያሳረፉት፤ ሎዛ 13 መዲና 8 ግቦችን አስቆጥረው ታሪክ ሲሰሩ ከተጫዋቾቹ ስኬት ጀርባ አሰልጣኝ ብርሃኑ ይገኛል።
ይህ ሰው ለጨለማው እጁን አልሰጠም፤ መንጋትን እያሰበ ብርሃን እንደሚተካ እያመነ ዓመታትን በፈተና አሳልፏል። ከመነሻ እስከ እስራኤል ድንበር፥ ከጎዳና እስከ ተንጣለለ ቪላ፥ ከስደት እስከ ዓለምን እስከመዞር፥ ከእስር ቤት እስከ ቤተመንግሥት፥ ከመቶ ብር ደመወዝ እስከ ሚሊዮን ብር የፊርማ ተከፋይ፥ ከእንቁላልና ቅቤ ነጋዴ እስከ ዘመናዊ እርሻ ባለቤት፥ ከጃንሜዳ እስከ ብሔራዊ ቡድን የደረሰ የብርሃን ጉዞ ተምሳሌት ነው።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን መስከረም 9/2014