ወላጆች ልጆቻቸው በቂ ምግብ ያልበሉ ሲመስላቸው የሚጨነቁት ጭንቀት ልጆቹም አልበላም ማለታቸውን የሚያቆሙት ነገር ሁሌም የወላጆች መወያያ ርእስ ነው።
ልጆቻችን ምግብ እንዲበሉልን ማድረግ የምንችልባቸው 20 ዘዴዎች በሚል የህፃናት ሀኪሞች በቴሌግራም ገፃቸው ያካፈሉንን እነሆ ብለናል፤ መልካም ንባብ።
ህፃናት ገና በአእምሮም በአካልም ያልዳበሩ የቤተሰባችን አካል ናችው። ታዲያ ምግብ አዘጋጅተን ቁጭ ብለን ተጨንቀን ስናበላቸው ለእኛ ብለው የሚበሉ ይመስላቸዋል። በዚህ የተነሳ ለወላጆች ልጆቻቸውን ማብላት ከባድ ስራ ይሆናል።
አንዳንድ ህፃናት ገና ምግብ ሲያዩ ሊያለቅሱ ወይም ተነስተው ሊሮጡ ይቺላሉ። ይህ ነገር ሲደጋገም ለወላጆች አስጨናቂ ይሆናል እድሜያቸው ከ 1 – 3 ዓመት ያሉ ልጆች የእድገታቸው ፍጥነት ከመጀመርያ ዓመት ሲነፃፀር ቀነስ ስለሚል በዛው ልክ የምግብ ፍላጎታቸው እና አወሳሰዳቸው ትንሽ ቀነስ ሊል ይችላል፤ ይሄም ፍፁም ተፈጥሯዊ ነው።
ይሄን ተፈጥሯዊ ነገር ማወቅ እና መረዳት ከሁሉም ወላጆች ይጠበቃል። በዛሬው ጽሁፋችን ሙሉ ጤነኛ ሆነው ምግብ አልበላም ብለው ለሚያስቸግሩ ህፃናት በምን መልኩ የምግብ ፍላጎታቸውን ማስተካከል እንደሚችል እና እንዴት አድርገን መመገብ እንደምንችል እናያለን። እነዚህ 20 ዘዴዎች ለሁሉም ህፃናት በተመሳሳይ መልኩ ላይሰሩ ይችላሉ። ላንዱ ውጤታማ የሆነ ሌላው ውጤታማ ላይሆን ይችላል።
1. አዲስ ምግብ ለማስለመድ ሲያስቡ 20 ጊዜ ይሞክሩ ልጅዎ አዲስ ምግብ ለመጀመር አስቸግሮት ሊሆን ይቺላል። እየቀመሰ ሊተፋውም ይችላል፤ ሆኖም በትእግስት በየቀኑ ቢያንስ ለ20 ቀን ይሞክሩ። ይሄ ሙከራ ብዙ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ከሆነ የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ በመጨረሻ ላይ ውጤታማ ሆኖ ታይቷል።
2. ልጆች አንድን ምግብ እምቢ ስላሉ ቶሎ ሌላ ተለዋጭ ምግብ ለመስራት እና ለማቅረብ አይቸኩሉ። ደጋግመው ያቅርቡላቸው። ልጅዎ እንደ ምግብ ቤት ምግብ እንዲያዝ እና እንዲቀያይር አይፍቀዱለት።
3. ልጆች ምግብ አልበላም ሲሉ በምትኩ ወተት ወይም ጁስ አይስጡ ከዛ ይልቅ ከትንሽ ቆይታ በኋላ ራሱ ምግቡን ያቅርቡለት። አሁንም እምቢ የሚል ከሆነ ምግቡን ያንሱት ይሄንን በተደጋጋሚ ካደረጉ ልጅዎ እምቢ ስላለ ብቻ የሚቀየር ነገር እንደሌለ ቀስ በቀስ ይረዳል።
4. ቋሚ የምግብ ሰዓትን ያስለምዱ፤ ይህን ሲያደርጉ የምግብ ሰአትን እና ስርዓትን ለልጅዎ ያስተምሩታል።
5. ጣፋጭ ነገሮችን ከልጅዎ የምግብ አይነት ውስጥ ይቀንሱ። ጣፋጭ ነገር ካስፈለጋቸውበሚመገቡበት ጊዜ ወይም መጨረሻ ላይ ጣፋጭ ፍራፍሬዎችን ይመግቧቸው።
6. ትኩረትን የሚወስዱ ነገሮችን ያስወግዱ ለምሳሌ፡- መጫወቻዎች፣ የቤት እንስሳት፣ ተንቀሳቃሽ ምስሎች ወይም ቴሌቪዥን ያሉ ነገሮች የሕፃን ልጅዎን ትኩረት ከምግቡ በላይ ሊወስዱ እና በዚህም የተነሳ በትንሹ በልተው እንዲያበቁ ያደርጋቸዋል። ስለዚህ ልጅዎ ከምግብ ጋር ጤናማ ግንኙነት እንዲኖረው ሲመግቡት ሙሉ ትኩረቱ ምግብ ላይ እንደሆነ ያረጋግጡ።
7. አይን የሚይዙ ምግቦችን ማዘጋጀት “ሲያዩት ያላማረ… ” አይደል የሚባለው? ልክ እንደ አዋቂዎች ሁሉ ሕፃናትም በዓይናቸው ይመገባሉ። የሚያዩት ነገር በጣም ይስባቸዋል። ለህፃናት ምግባቸውን ሲያቀርቡ በቀለማት ያማረ የሚስብ እና አስደሳች ሆኖ እንዲታይ ማድረግ ይኖርቦታል። ፈጠራ የታከለበት የኮከብ የአበባ የአሻንጉሊት ቅርፅ ያላቸውን ፍራፍሬዎች አትክልቶችን ወይም ፓንኬኮች ይስሩ።
8. ልጅዎን ምግብ ለምን አትበላም/አትበይም ብለው አያስጨንቋቸው በምግብ ሰአት አንዳንዴ ለብቻቸው እንዲሆኑ እና ነፃነትን እንዲለማመዱ ያደርጉ። ሕፃናት አንዳንድ ጊዜ በምግብ ሰአት ብቻቸውን እንዲበሉ ሲደረጉ የተሻለ ነው። በምግብ ሰአታቸው ላይ የእራት ጠረጴዛቸውን ከጎንዎ ካዘጋጁ በኋላ ትንሽ ማንኪያ እና ሳህን ይስጧቸው። ከዛም በቅርብ ርቀት ሆነው ይከታተሏቸው።
የተቀሩትን ክፍሎች በቀጣይ ሳምንት እትማችን ይዘን አንመጣለን፤ ተከታተሉን።
አስመረት ብስራት
አዲስ ዘመን መስከረም 9/2014