አዲስ አበባ፡- በሁሉም እርከን ላይ ያለው የኢትዮጵያ ሥርዓተ ትምህርት ዓለም አቀፋዊ ተወዳዳሪነትን መሰረት ያደረገ አለመሆኑን የትምህርት ሚኒስትሩ አስታወቁ፡፡
በኢትዮጵያ ያለው የትምህርት ሥርዓት እና የትምህርት ግብዓት በተለይም የመማሪያ ክፍሎች ጥራት ለ 21ኛው ክፍለ ዘመን የማይመጥኑ በመሆናቸው ችግሩን ለማስተካከል የጋራ ጥረት እንደሚያስፈልግ የኢፌዴሪ ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።
የኢፌዴሪ ትምህርት ሚኒስቴር ከትያትር ጥበባት ባለሙያዎች ጋር በመተባበር ስለትምህርት ፍኖተ ካርታ ዝግጅት እና ጥናቶች ላይ ያተኮረ ውይይት ባካሄደበት ወቅት የኢፌዴሪ ትምህርት ሚኒስትር ዶክተር ጥላዬ ጌቴ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚሰጠው ትምህርት እና የትምህርት ግብዓት ለ21ኛው ክፍለ ዘመን የማይመጥን ነው። ትምህርቱም ተግባር ላይ ከማተኮር ይልቅ በንድፈ ሃሳብ የታጨቀና ለፈተና በማዘጋጀት መርህ ላይ የተመረኮዘ ነው።
እንደ ዶክተር ጥላዬ ከሆነ፤ በሁሉም እርከን ላይ ያለው ሥርዓተ ትምህርት ዓለም አቀፋዊ ተወዳዳሪነትን መሰረት አላደረገም። ከዚህ በተጨማሪ በመላ አገሪቷ በሚገኙ አካባቢዎች እጅግ አሳሳቢ የሆነ የትምህርት ክፍሎች መጎሳቆል አለ። በተለይ በታዳጊ ክልሎች ውስጥ አሁንም ድረስ ዛፍ ስርና በሰብል ተረፈ ምርት በተሰሩ መጠለያዎች ውስጥ የሚማሩ ተማሪዎች አሉ። ይህ ሁኔታ ደግሞ ተማሪዎቹ በንፋስ፣ በአቧሯና በጸሃይ እንዲቸገሩ አድርጓል።
ኢትዮጵያ ከበጀቷ አንድ አራተኛውን ለትምህርት ዘርፈ እንዲሁም ከአጠቃላይ ዓመታዊ ገቢዋ አራት ነጥብ አምስት በመቶውን ለትምህርት እያዋለች ነው ያሉት ዶክተር ጥላዬ ይህን ያህል ችግር መስተዋሉ ግን ጉዳዩ የበለጠ አሳሳቢ እንዲሆን አድርጎታል። ችግሩንም በጋራ ማስተካከል ያስፈልጋል።
የኢትዮጵያ ሰዓሊያንና ቀራጺያን ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ አክሊሉ መንግስቱ በበኩላቸው፤ የትምህርት ሥርዓቱ ደካማ ተማሪንም ቢሆን ከክፍል ክፍል እንዲያልፍ የሚረዳ በመሆኑ ሊታሰብበት እንደሚገባ ተናግረዋል። በተለይ ተማሪው በዕውቀት ደካማ ቢሆንም መንግስት በተማሪው ላይ ያፈሰሰው ሀብት በማስላት መንግስት ከሚከስር ተማሪውን ደግፎ ማሳለፍ ይገባል የሚል አሰራር አገሪቷን እየጎዳት መሆኑንም አብራርተዋል።
የኢትዮጵያ ደራስያን ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ አበረ አዳሙ እንደገለጹት፤ የሚዘጋጀው የትምህርት እቅድ እንደ እስከዚህ ቀደሙ ከክፍል ወደክፍል መዘዋወርን ሳይሆን ዕውቀትን መሰረት ያደረገ ሊሆን ይገባል። ትምህርት በፈጠራ፣ በስነምግባር ቀረጻ እና በዕውቀት ላይ እንዲመሰረት በማድረግ ትውልዱን ማስተማር እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።
እንደ አቶ አበረ ከሆነ፣ የትምህርት ሥርዓቱ ዕውቀትን እና ፈጠራን መሰረት ማድረግ አለበት ሲባል ኪነጥበቡንም ማካተት ያስፈልጋል። አሁን የሚሰጠው ትምህርት ለኪነጥበቡ ጀርባ የሰጠ በመሆኑ የታላላቅ ኢትዮጵያውያን ጸሃፍትን ስራዎች በትውልዱ ውስጥ ማስረጽ አልተቻለም። በመሆኑም ይህንን ማስተካከል ለተማሪው ገንቢ ዕውቀትን ማስተላለፍ ይገባል።
በመድረኩ የተሳተፉ የተለያዩ የኪነጥበብ ሙያተኞች የኢትዮጵያውያን ኪነጥበባዊ ስራዎች በትምህርት ፍኖተ ካርታው በቂ ቦታ ተሰጥቷቸው ሊካተቱና ግብዓት ሊሆኑ እንደሚገባ ገልጸዋል።
አዲስ ዘመን የካቲት 19/2011
በጌትነት ተስፋማርያም