አሸባሪው ህወሓት በህዝብ ላይ የሰራው ግፍ መቼም ተቆጥሮ አያልቅም። ይህ አሸባሪ ቡድን በየቀኑ በሚዘራው የጥላቻ ችግኝና በሚያዘጋጀው የእልቂት ድግስ ሰዎችን ከመኖሪያ ማፈናቀል፣ ህፃናትንና አረጋውያንን ለጦርነት ማሰለፍ፣ ሴቶችን መድፈር እና ሌሎች የፈፀማቸው አሳፋሪ ድርጊቶች የሀገር ጠላት እንደሆነ የሚያሳዩ ምልክቶች ናቸው። አሸባሪ ቡድኑ በዋነኛነት ሲሰብክ የኖረው አንድነት ላይ ሳይሆን ልዩነት ላይ ነው። አንዱ ብሄር በሌላው ላይ እንዲነሳ፤ አንዱ ብሄር በሌላው ብሄር ላይ ጥላቻን እንዲያሳድር የሆነ ያልሆነ ትርክት በመፍጠር ዜጎች በጠላትነት እንዲተያዩና ጣት እንዲቀሳሰሩ ጭምር አስቦ ሲሰራ መቆየቱ ገሃድ እየወጣ መጥቷል። ይሄን በእያንዳንዱ ዜጋ ልብ ውስጥ የተዳፈነን እሳተ ገሞራ ደግሞ ዛሬ በመቆስቆስ አሁን ለሴራው ማሳለጫ እየተጠቀመበት ይገኛል።
በቅርቡ የብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ለአዲስ ዘመን በሰጠው መግለጫ በአሁኑ ወቅት በደቡብ ወሎ ላይ 183ሺ 404 ተረጂዎች ያሉ ሲሆን እነዚህም በደሴ ዙሪያ በዘጠኝ ጣቢያዎች ላይ የሚገኙ መሆናቸው ታውቋል። አሁን በቅርቡም 60ሺ ተፈናቃዮች መጨመራቸውንና ለሁሉም አስፈላጊው የሰብዓዊ ድጋፍ ሁሉ እየተደረገላቸው መሆኑን ምክትል ኮሚሽነሩ ተናግረዋል። በቅርቡ ይህ አጥፊና ፅንፈኛ የህውሓት ቡድን በአማራና በአፋር ክልሎች በሴቶችና ህፃናት ላይ የግፍ ግፍ ማድረሱ ይታወሳል። አሁን ባለው ሁኔታ ዜጎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው በተለያዩ አካባቢዎች ተጠልለዋል።
ይህን ተከትሎ ሰሞኑን የሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ሚኒስቴር በአማራና በአፋር ክልሎች በአሻባሪው ህውሓት ጉዳት የደረሰባቸውን ሴቶችና ህጻናት ከመደገፍ አንጻር የተሰሩ ስራዎችን አስመልክቶ ለጋዜጠኞች ማብራሪያ ሰጥቶ ነበር። ማብራሪያውን የሰጡት የሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ሚኒስትር ክብርት ወ/ሮ ፊልሰን አብዱላሂ እንዳሉት፤ በአሸባሪነት የተፈረጀው አጥፊው የህወሓት ቡድን እየፈጸመ ባለው ትንኮሳ ምክንያት በአማራና በአፋር ክልሎች ቤት ንብረታቸው ለወደመባቸውና ከቀያቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች አገልግሎት የሚውል አጠቃላይ ግምቱ 24 ሚሊዮን 909 ሺህ 600 ብር የሚሆኑ ሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረግ የሚያስችል ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛል።
በተለይ በአፋር ክልል መጠለያ ጣቢያዎች የሚገኙና ድጋፍ የሚሹ 76,525 ተፈናቃይ ወገኖች የሚኖሩ ሲሆን 39,793 (52%) ህጻናት፣ 3,061 ነፍሰ ጡር እናቶች፣ ለአቅመ ሄዋን የደረሱ ሴቶች 19,130 (25%)፣ እንዲሁም 15,304 (20%) ለአቅመ አዳም የደረሱ የህብረተሰብ ክፍሎች መሆናቸው መረጃዎች ያሳያሉ። ከእነዚህ መካከል 459 የተለያዩ ችግሮች / በተለይም ከወሊድ በኋላ በደረሰባቸው ጉዳት ተጋላጭ እንደሆኑ፤ እንዲሁም ደግሞ 16,836 (22%) ያህሉ የስነ ልቦና ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው ለማወቅ ተችሏል።
ከዚህ መነሻነት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከገቢዎችና ጉምሩክ ሚኒስቴር ጋር በመነጋገር ያሰባሰባቸውን የተለያዩ አልባሳት እንዲሁም ከምግብ ነክ ግብዓቶች ስኳር፣ ፓስታ፣ ሩዝ እና ምስር በአፋር ክልል ለሚገኙ ተፈናቃይ ወገኖች ግልግሎት እንዲውል የቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል።
በአሁኑ ወቅትም ለተፈናቀሉ ወገኖች አገልግሎት የሚውል አጠቃላይ ግምቱ 24 ሚሊዮን 909 ሺህ 600 ብር የሚሆኑ ሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረግ ቁሳቁሶቹ ከድሬዳዋ፣ ጅግጅጋ፣ በአዋሽና ከአዋሳ ከሚገኙ የጉምሩክ ቅርንጫፍ ጣቢያዎች ወደ ክልሎቹ በመጓጓዝ ላይ ናቸው።
በዚሁ መሰረት 8 ሚሊየን ብር የሚገመት 8500 ኪሎግራም አልባሳት ወደ አማራ ክልል በመጓጓዝ ላይ የሚገኝ ሲሆን ቀሪው 16 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት አልባሳትና ምግብ ነክ ቁሳቁስ ለአፋር ክልል ተልኳል።
በሌላ በኩል በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በተለይ በመተከል፣ በሰሜን ሸዋ እንዲሁም ከትግራይ ክልል ጋር በተከሰተው ግጭት ምክንያት የተፈናቀሉ ዜጎች 1 ሚሊየን እንደሚጠጋ ከምግብ ዋስትና ስጋት መከላከልና ስራ አመራር ኤጀንሲ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
በተመሳሳይ በቢሮው በኩል ለማጣራት የተሞከረው ተጨባጭ መረጃ እንደሚያሳየው በአጠቃላይ አሁን ላይ 605,300 (314,096 ሴ) ያህል ሰዎች ተፈናቅለው በችግር ላይ እንደሚገኙ ከእነዚህም መካከል የህጻናት ቁጥር 230,447 (135,072 ሴ) በተለያዩ መጠለያዎች የሚገኙ 131,721 (57,065 ሴ) የህብረተሰብ ክፍሎች በከፋ ችግር ውስጥ እንዳሉ ሲሆን ከነዚህም ውስጥ 55,477 (24,173 ሴ) ያህል ህጻናት እንደሆኑ ለማወቅ ተችሏል።
በመሆኑም በቀጣይ ለሴቶች እና ህጻናት የሚያስፈልጉ መጠለያ ድንኳን፤ የመኝታ ፍራሽ፤ የመኝታ እና የግል አልባሳት፤ ከወላጅ ለተነጠሉ፣ ወላጆቻቸውን በሞት ላጡና በጊዜያዊ ማቆያ የሚገኙ ህጻናትን ከቤተሰባቸው ጋር የማቀላቀልና የማዋሃድ ስራዎች ማስፈጸሚያ የሚሆን የበጀት ድጋፍ፤ በጣም ለተጎዱ ህጻናት፣ ለነፍሰ ጡር እና ለወለዱ እናቶች የሚሆኑ ሀይል ሰጪ እና አልሚ ምግቦች፤ ለሴቶችና ህጻናት ግልጋሎት የሚውሉ የንጽህና መጠበቂያ ኪቶች እንዲሁም ደግሞ የምግብ ማብሰያ እና መመገቢያ እቃዎች አስፈላጊ ተብለው የተለዩ የእርዳታ ቁሳቁሶች ማድረስና እና መልሶ ማቋቋም ስራን ጨምሮ በትኩረት ከወዲሁ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
በሌላ በኩል ጥቃት ለደረሰባቸው ህጻናት እና ሴቶች አስፈለጊ የስነ-ልቦና ድጋፍ እና የስነ-ልቦና ቁሳቁስ ድጋፍ (ለምሳሌ የህጻናት መጫዎቻዎች) ለማሟላት ጥረት እንደሚደረግ ተነግሯል።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከዚህ ቀደም ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ በሆኑ ክስተቶች ሳቢያ ጉዳት ለደረሰባቸው፣ ንብረታቸው ለወደመባቸውና ከመኖሪያቸው ለተፈናቀሉ ሴቶች፣ ሕጻናት፣ ወጣቶች፣ አቅመ ደካሞችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ሰብዓዊና ቁሳዊ ድጋፎችን በማይካድራና መተከል ዞን ማድረጉንም አስታውቋል።
የሴቶች ህጻናትና ወጣቶች ሚኒስቴር የተናጥል ተኩስ ማቆም እርምጃ ውሳኔ በፊት በትግራይ ክልል ከዳሰሳ ጥናት ጀምሮ ልዩልዩ ስራዎች ዕቅድ በማውጣት መተግበራቸውን አንስተው። በዚህም የስነልቦና ድጋፍ ለሚሹ ማህበረሰቦችን በ5 ከተሞች የአንድ መስኮት አገልግሎት በተሟላ ግብዓት ማደራጀት፣ የማገገሚያ ማዕከላት ማደራጀት፣ በሁሉም ቦታዎች ባለሙያ መመደቡ እና የቢሮና የውስጥ ቁሳቁስ የማሟላት ስራ ሲሰራ መቆየቱን አስታውሰዋል።
በቀጣይም ከሚመለከታቸው ባለድርሻና አጋር አካላት ጋር በመተባበር እና ሀብት በማሰባሰብ መሰል ድጋፎችን አጠናክሮ የሚቀጥልና ማህበራዊ ኃላፊነቱን የሚወጣ ይሆናልም ተብሏል።
ሚኒስትሯ ክብርት ወ/ሮ ፊልሰን አብዱላሂ በዚህ አጋጣሚ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የሴቶችና ወጣቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንዲሁም የህጻናትን መብትና ማህበራዊ ደህንነት ለማስጠበቅ እያከናወናቸው ያሉ ዘርፈ ብዙ ተግባራት ስኬታማ እንዲሆኑ የገንዘብ፣ የቁሳቁስ፣ የቴክኒክና ሌሎች ድጋፍ ሲያደርጉ ለቆዩና አሁንም ከጎናችን ላልተለዩን ባለድርሻና አጋር አካላት በሙሉ ድጋፉን ባገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ስም ላቅ ያለ ምስጋናቸውን አቅርበዋል። ወደፊትም የተቋሙን ጥረት በንጹህ ወገናዊነት በመደገፍ የጀመሩትን እገዛና ድጋፍ ይበልጥ አጠናክረው እንዲቀጥሉ አገራዊ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
በመጨረሻም የ2013ዓም የበጀት ዓመት በርካታ ፈተናዎች የበዙበት ቢሆንም መላው ህዝብ በኢትዮጵያዊ ወኔ በጋራ በመቆም፣ በአንድነትና የመደጋገፍና የመረዳዳት እሴቶቻችንን ተግባራዊ በማድረግ የገጠሙንን ፈተናዎች በአሸናፊነት የተወጣንበት ዓመት ነበር ሲሉ ሚኒስትሯ አስታውሰዋል። የሴክተሩ አብይ የትኩረት አቅጣጫ በአስር ዓመቱ የልማት እቅድ መሰረት ትውልድን በማብቃት፣ የሴቶች፤ ሕፃናትና ወጣቶችን ውክልና እውን በማድረግና የዜጎችን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት በማስጠበቅ እና መብታቸው መከበሩን ማረጋገጥ ነውም ብለዋል።
በአዲሱ የበጀት ዓመት በእቅድ ከያዝናቸው መካከል – ሁሉን አቀፍ የህጻናት የገንዘብ ድጋፍ ፈንድን፣ የህጻናት ማህበራዊ አገልግሎት ኤጀንሲን፣ የአፍሪካ ሴቶች የአመራር ማዕከልን በማቋቋም እና በቅርቡ የመሰረትነውን የወጣቶች ካውንስልን ጨምሮ ሁሉንም ወደ ተግባር ለማስገባት እንዲሁም ሌሎች በበጀት ዓመቱ በእቅድ የተያዙ ተግባራት በተቀመጠላቸው የጊዜ ገደብ በስኬት ለማጠናቀቅ እየተሰራ ሲሆን፤ ሌሎች በ10 ዓመቱ መሪ ዕቅድ የተያዙ አዳዲስ አሰራሮችን ተግባራዊ ለማድረግ በ2014 በወሳኝ መልኩ እንቀሳቀሳለን ነው ሲሉ ሚኒስትሯ ክብርት ወ/ሮ ፊልሰን አብዱላሂ አስታውቀዋል።
በተመሳሳይ በቅርቡ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ያወጣው መግለጫ እንደሚያሳያው አሸባሪው የህወሓት ቡድን ረሃብን እንደ ጦርነት መሳሪያና ሐሰተኛ ፕሮፖጋንዳ ማሳለጫ አድርጎ ቀጥሏል። ይህ አሸባሪ ቡድን በአንድ በኩል ለተጎጂዎች የሚላከውን ሰብአዊ እርዳታ እየዘረፈ በሌላ በኩል በረሃብ ምክንያት ሰዎች እየሞቱ ነው የሚል እርስ በእርሱ የሚጣረስ ፕሮፖጋንዳ እያሰራጨ ይገኛል። ሆኖም መንግሥት በትግራይም ሆነ በአማራና አፋር ክልል በአሸባሪው ህወሓት ምክንያት ለተፈናቀሉና ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ሰብአዊ እርዳታ እየደረሰ መሆኑም ተነግሯል። በዚህም ከተለያዩ የሰሜን ወሎ አካባቢዎች ተፈናቅለው በደሴ ተጠልለው ለሚገኙ አረጋውያን፣ ሴቶች፣ ወጣቶችና ህፃናት ድጋፍ እየቀረበ መሆኑን እና በተጨማሪም በተለያዩ የአማራ አካባቢዎች በተለይም በዋግምራ ዞን ሰቆጣ ወረዳ እና በጎንደር ፈጥኖ ደራሽ ሰብአዊ እርዳታ የማድረስ ሥራ እየተከወነ መሆኑን ከፅህፈት ቤቱ የተገኘው መረጃ ያሳያል።
በአጠቃላይ ሁሌም የመከራ ገፈት የሚቀምሱትና የበደል ጫና አንገት ያስደፋቸው ሴቶች በሀገራቸው ኮርተው አንገታቸውን ቀና አድርገው እንዲሄዱ ማድረግ የሁሉም ባለድርሻ አካላት ሚና የጎላ ነው። በዚህ ወቅት ከመቼውም ጊዜ በላይ አንድነታችንን ማጠናከር፤ በችግር ላይ ያሉትን መደገፍና የተፈናቀሉትን ማቋቋም ያስፈልጋል። መፈናቀል ብርቱ ፈተና ሆኖ እንዳይቀጥል ከወዲሁ ቅድመ ዝግጅት ማድረግ ተገቢ ነው። የተፈናቀሉትን ማቋቋም ሳንችል ተጨማሪ ዜጎች ከተፈናቀሉ ሁኔታውን ከባድ ያደርገዋል። በመሆኑም ለእነዚህ ዜጎች በተለይም ለሴቶችና ህፃናት ለመድረስ ኢትዮጵያውያን የሚችሉትን ያህል ማድረግ ይኖርባቸዋል። በርካታ ዜጎች ሰብዓዊ መብታቸው ተጥሶ ለእንግልት እየተዳረጉ በመሆናቸው ማኅበረሰቡን በማስተባበር እነዚህን ዜጎች ለማገዝ በየትኛውም የሀገሪቷ ክፍል የሚገኝ ዜጋ በቁርጠኝነት መሰለፍ ይኖርበታል።
ዘላለም ግርማ
አዲስ ዘመን መስከረም 9/2014