በኢትዮጵያ ወርሃ መስከረምን ተከትለው በአደባባይ ከሚከበሩ በዓላት መካከል የገዳ ሥርዓት አንዱ አካልና የኦሮሞ ሕዝብ የአንድነት፣ የመተሳሰብና የምስጋና በዓል የሆነው ኢሬቻ ነው። ኢሬቻ እሳቤው ፍቅርና መተሳሰብ ሆኖ የኦሮሞ ሕዝብ በዓይኑ ማየት የማይችለውን አምላክ በሥራው በተገለጠበት ወቅት ለአምላኩ ያለውን ፍቅር የሚሳይበት፣ ለተደረገለትም የሚያመሰግንበትና ለቀጣዩም የሚፀልይበት የጋራ በዓል ስለመሆኑም ይነገራል።
ከጊዜ ወደ ጊዜ እየደመቀ የመጣው የኢሬቻ በዓል በ2012 ዓ.ም ከብዙ ጊዜ በኋላ ለቁጥር የሚታክት የኦሮሞ ማህበረሰብና ሌሎችም ኢትዮጵያውያን በተገኙበት በአዲስ አበባ በድምቀት ተከብሯል። በዓሉ በ2013 ዓ.ም በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት በብዙ ቁጥር ባይከበርም ዘንድሮ ግን ባልተገደበ ቁጥር የበዓሉ ታዳሚያን አስፈላጊውን ጥንቃቄ አድርገው በዓሉን እንዲያከብሩ በኦሮሞ አባገዳዎች ህብረትና በኦሮሚያ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ በኩል ውሳኔ ተላልፏል።
በዚሁ መሰረትም የ2014 የኢሬቻ በዓል የኮቪድ ፕሮቶኮልን በጠበቀ መልኩ ባልተገደበ የሰው ቁጥር መስከረም 22 በአዲስ አበባ እንዲሁም መስከረም 23 በቢሾፍቱ እንደሚከበር የኦሮሞ አባገዳዎች ህብረትና የኦሮሚያ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ በጋራ አስታውቀዋል። ከዚሁ ጎን ለጎንም በዓሉን በሚመለከት ከሀገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ ጋር አስታከው አባ ገዳዎችና ሀደ ስንቄዎች ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ሃደ ስንቄ ቱለማ አፀዱ ቶላ የአዳማ ከተማ ነዋሪ ናቸው። የኢሬቻ በዓል በገዳ ሥርዓት ለረጅም ዓመታት ሲከበር የቆየ መሆኑንና በዓሉ የኦሮሞ ባህልና ከትውልድ ወደትውልድ ሲሸጋገር የመጣ መሆኑን ይገልፃሉ። ይህንኑ በዓል በትልቅ ሥርዓት ለማክበር መዘጋጀታቸውንም ይናገራሉ።
ኢሬቻ የፀሎትና የምስጋና በዓል ነው የሚሉት ሃደ ስንቄ ቱለማ አፀዱ በዋናነት የኦሮሞ ሕዝብ ከጨለማው አውጥቶ ወደ ብርሃን ያመጣውን አምላክ የሚያመሰግንበት፣ ለኢትዮጵያ ሰላም የሚመኝበትና የሚፀልይበት ብሎም የተጣላው እንዲታረቅ ፈጣሪውን የሚለምንበት መሆኑን ይገልፃሉ።
በዓሉ በርካቶች ተሳትፈውበት የሚከበርና የእርቅ እንደመሆኑ ዘመኑ የሰላም፣ የፍቅርና የመተሳሰብ እንዲሆንና ኢትዮጵያም ያጋጠማት ችግር እንዲቃለልላት ፀሎት የሚደረግበት መሆኑንም ይጠቁማሉ። በዓሉን የሚያከብረው መላው የኦሮሞ ሕዝብም በሀገሪቱ ሰላም እንዲመጣ እምነቱ መሆኑንም ይገልፃሉ።
ሀደ ስንቄዎች የፀሎትና አስታራቂ ሰዎች በመሆናቸው ፈጣሪያቸው ለሀገራቸው ኢትዮጵያ እርቀሰላሙን እንዲያወርድላቸው እንደሚለምኑና ፈጣሪያቸው ሕዝባቸውን አንድ እንዲያደርግላቸው እንደሚፀልዩም ይናገራሉ። ‹‹እኛ ኢትዮጵያውያን አንድ በመሆናችንና የተከሰተው ጦርነትም የእኛው በመሆኑ እኛ ሀደ ስንቄዎች ፈጣሪ ጦርነቱን እንዲያበርድ እንፀልያለንም›› ይላሉ።
በዓሉ በኦሮሞ ዘንድ ብቻ የሚከበር ባለመሆኑና ሁሉም የሚያከብረው በመሆኑ ሁሉም ኢትዮጵያውያን የበዓሉ ታዳሚ እንዲሆኑና በዓሉም በሰላም እንዲከበር ፈጣሪቸውን እንደሚለምኑም ይገልፃሉ። የሰላም ዘመን እንዲሆንም ተመኝተው በዓሉን በጋራ እናክብር ሲሉ ሃደ ስንቄ ቱለማ አፀዱ ጥሪያቸውን ያቀርባሉ።
ሃደ ስንቄ ቱለማ አየሉ ሂርቱ ደግሞ ነዋሪነታቸው ጫንጮ ነው። በዓመት አንድ ጊዜ የሚከበረው የኢሬቻ በዓል አስደሳችና በርካቶችም ለማክበር የሚጓጉት ነው ይላሉ። በዓሉ የኦሮሞንና ሌሎች ኢትዮጵያውያን ሕዝቦችን ብቻ ሳይሆን የመላውን ዓለምን ትኩረት የሚስብ ስለመሆኑም ይመሰክራሉ። በበዓሉ አከባበር ወቅት ፍቅር፣ አንድነት፣ ትብብርና መተሳሰብ እንዳለም ይጠቁማሉ።
በዓሉ የፍቅር፣ የአንድነት፣ የመተሳሰብና የአንድነት በመሆኑ ኢትዮጵያ የገጠማትን ወቅታዊ ፈተና ለማለፍ ሀደ ስንቄዎች በዚሁ የበዓሉ እሴት መሰረት ሀገራችን ሰላም እንድትሆን እንፀልያለን፤ ፈጣሪያችንንም እንለምናለን ሲሉ ይናገራሉ።
ኢትዮጵያውያን ቋንቋችንና እምነታችን የተለያየ ቢሆንም ተቻችለን በጋራ ነው የምንኖረው የሚሉት ሀደ ስንቄ ቱለማ አየሉ፤ ሀገሪቷ የገጠማትን ጦርነት በጋራ መመከት ይገባናል ሲሉም መልዕክታቸውን ያስተላልፋሉ። በዘመን ውስጥ ደስታም ሆነ ኀዘን የሚያጋጥም በመሆኑ ዘር፣ ቀለምና ሃይማኖት ሳንል የገጠሙንን ችግሮች በጋራ ሆነን እንደአመጣጡ ማሳለፍ ተገቢ መሆኑንም ይናገራሉ።
ሀደ ስንቄዎችም ፈጣሪያቸውን አብዝተው የሚለምኑት ክፉ ነገሮችን እንዲያበርድላቸውና በምትኩ ጥሩ ነገር እንዲያመጣላቸው፤ ጦርነቱም እንዲቆም ነው ይላሉ። በዓሉ በጋራ ስለሚከበርና ሁሉም የሚሳተፍበት በመሆኑ ኢትዮጵያ ያጋጠማትን ችግር በጋራ መፍታት አለብን ሲሉ ምክራቸውን ይለግሳሉ።
የሜጫ አባገዳና የኦሮሚያ አባገዳዎች ህብረት አባል አባገዳ ወርቅነህ ተሬሳ በበኩላቸው፤ ኢሬቻ ማለት ሰላም፣ አንድነት፣ መፈቃቀር፣ መተሳሰብ መሆኑን ይገልፃሉ። የኦሮሞ የማንነቱ መገለጫ መሆኑንም ይጠቅሳሉ። ሰዎች በፖለቲካ አስተሳሰባቸው፣ በሃይማኖታቸው፣ በቋንቋቸውና በጎሳቸው ሳይለያዩ በጋራ የሚያከብሩት በዓል መሆኑንም ይመሰክራሉ።
ሰላም ከሌለ ደግሞ ሰውም ሆነ ኢሬቻ የሌለ በመሆኑ ለሰላም ሲባል ሁሉም ሰው መረባረብና በጋራ መስራት አለበት ይላሉ አባገዳ ወርቅነህ። በሀገሪቱ ሰላም እንዲሰፍን አባገዳዎች እንደሚፀልዩና መልካም ነገሮች እንዲመጡ እንደሚማፀኑም ይጠቁማሉ።
በአሁኑ ጊዜ በአማራ ክልልና በአፋር ክልል አካባቢዎች እየተካሄደ ያለው ጦርነት ለኢትዮጵያ የማያስፈልግ ነበር የሚሉት አባ ገዳ ወርቅነህ፤ ጊዜው የለውጥ ዘመን ከመሆኑ አኳያና ጦርነት የሀገርን እድገት የሚገታ በመሆኑ ጦርነቱን በጊዜ መቋጨት እንደሚገባም ያመለክታሉ።
እንደአባገዳ ወርቅነህ አስተያየት ደግሞ ለሀገሪቱ ሰላም እንዲፈጠር፣ አንድነትና ፍቅር እንዲመጣ፣ የተጣላ እንዲታረቅ ፈጣሪያቸውን እየለመኑ እንደሚገኙ ይናገራሉ። ሕዝቡ ደግሞ አባገዳዎችና የሃይማኖት አባቶች የሚሉትን መስማት እንዳለበትና ሰምቶም ተግባራዊ ማድረግ እንደሚጠበቅበት ያሳስባሉ።
አባገዳ ወርቅነህ ‹‹ጦርነቱ እንዲበርድ ፈጣሪያችን ከእኛ ጋር ይሁን፤ ሁላችንም ፈጣሪያችንን እንለምን›› ይላሉ። በተለይ ሰላም ለሁሉም መሰረት ከመሆኑ አኳያ ሁሉም ለሰላም ዘብ መሆን እንዳለበት ይጠቁማሉ። ኢሬቻ የአንድነት፣ የፍቅር፣ የሰላም፣ የብልፅግና፣ የመነፋፈቅ በመሆኑ የኦሮሞ ሕዝብን ጨምሮ ሁሉም ኢትዮጵያውያን በዓሉን በጋራ እንዲያከብሩም ጥሪያቸውን ያስተላልፋሉ።
የአባገዳ ቱለማና የኦሮሞ አባገዳዎች ህብረት ፀሐፊና የሆራ ፊንፊኔና ሆራ አርሰዴ አስተባባሪ አባገዳ ጎበና ወላሬሶ እንደሚሉት፤ የሀገሪቷ ሁኔታ ከተፈጥሮ ጋር የተያያዘ ነው። በዚህ የተፈጥሮ ሂደትም አንድ ትውልድ ሲተካ ሌላኛው ቦታውን ይለቃል። በዚያው ልክ አንድ ዓመት አዲስ ሆኖ ሲመጣ አሮጌው ዓመት ቦታውን ለአዲሱ ያስረክባል። ይኸው መተካካትም ከተፈጥሮ ጋር ይያያዛል።
በእነዚህ ክንውን ውስጥ ታዲያ በርካታ ክስተቶች ይፈፀማሉ። ደስታና ኀዘን ይኖራል። ባሳለፈው የ2013 ዓመትም በኢትዮጵያ ልዩ ልዩ ችግሮች አጋጥመዋል። አስደንጋጭና ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታዎችም ተከስተዋል። ከዚህ ውጪ ደግሞ አስደሳችና የሀገሪቱን ብሩህ ተስፋ የሚያሳዩ ሁኔታዎች ተፈጥረዋል። በዚህ ሂደትም ትውልድ ዛሬ ላይ ደርሷል።
ኢትዮጵያ ከ80 በላይ የሚሆኑ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ያሏት ሀገር እንደመሆኗ እነዚሁ ሕዝቦች ለፈጣሪያቸው ምስጋናን የሚያቀርቡበት የራሳቸው የሆነ ባህልና ሃይማኖታዊ ሥርዓት አላቸው ። ለፈጣሪ፣ ለመሬት፣ ለአካባቢ፣ ለእፀዋትና ለአዝርቶቻቸውም ምስጋና የማቅረቢያ ቀኖች አሏቸው።
ከነዚህ ብሔረሰቦች ውስጥ ደግሞ አንዱ የኦሮሞ ሕዝብ ሲሆን ሕዝቡ በኢሬቻ በዓል አማካኝነት ምስጋና ያቀርባል። ይህ የኢሬቻ በዓል በሁለት ተከፍሎ የሚታይ ሲሆን አንደኛው ‹‹አብራሳ›› የሚባልና የበልግ ዝናብ በሚዘንብበት ወቅት በተራራ ላይ የሚደረግ ምስጋና ነው። ሁለተኛው ደግሞ የክረምቱ ወቅት አልፎ ፀደይ ሲመጣ ‹‹በመልካ›› ላይ የሚደረግ የምስጋና በዓል ነው።
የኦሮሞ ሕዝብ ማንኛውም ዓይነት እምነት ይኑረው በየእምነቱ የክረምቱ ወቅት አልፎ ፀደይ ሲመጣ በመልካ ላይ አልያም በቤቱ ውስጥ ሆኖ ለፈጣሪው ምስጋና ያቀርባል።
እንደ አባ ጎበና ገለፃ፤ ጦርነት ለሰው ልጅ መጥፎ በመሆኑና ሰላም እንዲሰፈን፤ ፈጣሪ ሰላምን እንዲመልስ የሁሉም ፀሎት ያስፈልጋል። ከጥንት አባቶችና እናቶች እንዲሁም አያቶች የተወረሰውን ጥሩ ባህሎችና የኦሮሞን መልካም ገፅታ የሚያንፀባርቁትን ማስቀጠል ያስፈልጋል።
ከጦርነት ብቻ ሳይሆን ከዘመኑ ገዳይ ከሆነው የኮሮና ቫይረስ ራስንና ቤተሰብን መጠበቅ ያስፈልጋል። ከዚሁ ጎን ለጎንም በሀገሪቱ እያጋጠመ የመጣውን የኢኮኖሚ ችግር ከመንግሥት ጋር በመሆን መታገል ይገባል። ተስፋ ባለመቁረጥ ይህ ጊዜ ያልፋል በሚል በተስፋ አባቶች ያወረሷቸውን መልካም ባህሎችንም ማስቀጠል ይገባል። ጦርነቱ እንዲረግብም ለፈጠሪ ፀሎት ማድረግ ከመላው የኦሮሞና የኢትዮጵያ ሕዝብ ይጠበቃል።
በዚህ ሁሉ ጊዜ ውስጥ ኢትዮጵያን እንደዚህ ዓይነት የእርስ በእርስ ጦርነት ገጥሟት አያውቅም። በእርስ በርስ ጦርነትም የሚደቀው የሀገር ኢኮኖሚ ነው። የሚሞተውም ኢትዮጵያዊ ነው። እነዚህ ችግሮች ቢኖሩም ታዲያ ከ2013 ዓ.ም ወደ 2014 ዓ.ም ሽግግር ሲደረግ የተሻለ ሰላም እንደሚመጣ ይጠበቃል።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን መስከረም 9/2014