
ኢትዮጵያ በውል ያልተለዩ እና ያልታወቁ እምቅ የገጸ ምድር እና ከርሰ ምድር የቱሪዝም ሀብቶችን በእቅፏ የያዘች ሀገር ናት፤ ይሁንና እነዚህን ሀብቶቿን በተገቢው መጠን ሳትጠቀምበት ኖራለች። በዚህም ከፍተኛ ቁጭት ተፈጥሮ ቆይቷል፡፡
ከቅርብ አመታት ወዲህ ግን የለውጡ መንግሥት በተከተለው አቅጣጫ ነባር የቱሪስት መስህቦች ይበልጥ እንዲጎበኙ የሚያስችሉ መሰረተ ልማቶችን ከመገንባት፣ ቅርሶችን ከማደስና አዳዲስ የቱሪስት መዳረሻዎችን ከማልማት አኳያ በስፋት እየተሠራ ይገኛል።
ከዚሁ ጎን ለጎንም ቱሪስቶች ሀገሪቱን እንዲጎበኙ ሲደርግበት የኖረውን መንገድ በማስፋት አዳዲስ የቱሪስት ምርቶችን ይዞ መቅረብ ላይ እየተሠራ ነው። ለእዚህም የኢትዮጵያ አየር መንገድ በትራንዚት የሚያጓጉዛቸውን መንገደኞች በአየር መንገዱ ቆይታ በሚያደርጉበት ወቅት የሀገሪቱን በተለይም በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ መስህቦች እንዲጎበኙ ለማድረግ አየር መንገዱ፣ ቱሪዝም ሚኒስቴርና የኢሚግሬሽን መስሪያ ቤት በቅርቡ ስምምነት የደረሱበትን ሁኔታ በማሳየት መጥቀስ ይቻላል።
የቱሪዝም ሚኒስቴር በተናጠል ከሚደረጉ ሥራዎች ባሻገር ከአለም አቀፍ እና ሀገር አቀፍ ተቋማት ጋር በቅንጅት በመሥራት ከተለመደው ነባር አሰራር በመውጣት የዘርፉን አማራጭ ምርቶችን በማስፋት ተወዳዳሪነትን ለማሳደግ በቁርጠኝነት እየሠራ እንደሚገኝ ሰሞኑን በተሰጠ አንድ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይም አስታውቋል።
ይህን ከግምት ውስጥ በማስገባት ባለፉት አመታት በርካታ ተግባሮች ሲከናወኑ መቆየታቸው የተጠቆመ ሲሆን፣ ይህ እንቅስቃሴ ተጠናክሮ ቀጥሎ ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት የሳይንስና የባህል ድርጅት(ዩኔስኮ) ጋር በመተባበር ‹‹ የዩኔስኮ ዓለም አቀፍ ጂኦፓርኮች እና ጂኦቱሪዝም ለዘላቂ ልማት ያለውን ሚና በተመለከተ ከነገ ግንቦት 4 እስከ 7 ቀን 2017 ድረስ አንድ ወርክሾፕ እንደሚካሄድ ተመላክቷል።
በመግለጫው ላይ እንደተጠቆመው፤ የዩኔስኮ ጂኦፓርኮች ነጠላና የተዋሃዱ ጂኦግራፊያዊ አካባቢዎች ሲሆኑ፣ አለም አቀፍ የጂኦሎጂካል ጠቀሜታ ያላቸው ቦታዎች እና መልክአ ምድሮች ከሁለገብ የጥበቃ ጽንሰ ሀሳብ ጋር የሚተዳደሩበት ነው። ዩኔስኮ ከጂኦፓርኮች ጋር ተቀናጅቶ መሥራት የጀመረው ከ1993 ነበር። የዩኔስኮ ግሎባል ጂኦፓርኮች መለያም ህዳር 7 ቀን 2008 አም በ195 አባል ሀገሮች በ38ኛው የድርጅቱ ጠቅላላ ጉባኤ ጽድቋል።
የዩኔስኮ ዓለም አቀፍ ጂኦፓርኮች ዓለም አቀፍ የጂኦሎጂካል ጠቀሜታ ያላቸው ቦታዎች እና መልከዓ ምድሮች በሁለንተናዊ የጥበቃ፣ የትምህርትና የዘላቂ ልማት ጽንሰ ሀሳብ የሚተዳደሩበት ነው። በ50 ሀገሮች ከሚገኙ 229 የዩኔስኮ ግሎባል ጂኦፓርኮች መካከል በአፍሪካ ውስጥ የሚገኙት ሁለት ብቻ ናቸው።
ኢትዮጵያን ጨምሮ በአፍሪካ የዩኔስኮ አለም አቀፍ ጂኦፓርኮች ቁጥር ዝቅተኛ እንዲሆን ካደረጉ ቁልፍ ምክንያቶች መካከል አንዱ ስለ ጂኦፓርኮች ያለው ግንዛቤ አነስተኛ መሆን ነው።
ከነገ ጀምሮ በአዲስ አበባ የሚካሄደው ወርክሾፕም ለዘርፉ ተዋንያን ግንዛቤ መፍጠር እና የዩኔስኮ ዓለም አቀፍ ጂኦፓርክ ፕሮጀክቶችን በኢትዮጵያም ይሁን በሌሎች የምስራቅ አፍሪካ ሀገሮች ማስጀመር እና የጂኦፓርኮችን ጽንሰ ሀሳብ በአህጉሪቱ ማስተዋወቅን ዓላማው አድርጓል።
የቱሪዝም ሚኒስቴር የፖሊሲ አናሊስት የሆኑት ጌታነህ አዲስ (ዶ/ር)በጉዳዩ ላይ በተለይ ከአዲስ ዘመን ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳሉት፤ ዩኔስኮ ግሎባል ዓለም አቀፍ ቅርሶችን በሶስት አይነት መልኩ ይመዘግባል። መጀመሪያ ላይ የዓለም ቅርስ ወይም ደግሞ ዓለም አቀፍ እሴት ያላቸው ሰው ሰራሽ እና ተፈጥሮአዊ ቅርሶች ተመርጠው የሚመዘገቡበት መንገድ ሲሆን፣ ሁለተኛዎቹ ደግሞ ባላቸው ባዮ ዳይቨርስቲ (ብዝሀ ህይወት) ዩኔስኮ በሚሰጠው እውቅና የሚመዘገቡ ናቸው።
ሶስተኛው እና በቅርቡ በፈረንጆቹ 2015 መተግበር በተጀመረው የዘላቂ ልማት ግቦች ላይ ለመድረስ ትኩረት ማድረጉ ነው። ይህም ከሌሎቹ ለየት ይላል። ይህም ያለውን የመልከዓ ምድር አቀማመጥ እና ዓለም አቀፍ ፋይዳ ግምት ውስጥ በማስገባት በዩኔስኮ እንደሚመዘገብ ጠቅሰው፣ በዩኔስኮ ተመራጭ ሆኖ ለመመዝገብ መልከዓ ምድሩ ወሳኝነት ቢኖረውም በውስጡ ያለው ብዘሀ ህይወት፣ ባህላዊ ሀብቶች፣ የአካባቢው ማህበረሰብ ጥያቄ ውስጥ የሚገቡ ጉዳዮች ናቸው ሲሉም አብራርተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ባሏት መልከዓ ምድሮች እና በተፈጥሮ ሀብቶቿ ለተፈጥሮ ቅርብ መሆኗን የፓሊሲ አናሊስቱ ጠቅሰው፣ ይህም በዘርፉ የተሻለ መሥራት እንደሚገባ አመላካች መሆኑን ጠቁመዋል። የሰሜን ተራሮች እንዲሁም የባሌ ተራሮች ብሄራዊ ፓርኮች አካባቢዎች፣ የአፋር ስምጥ ሸለቆ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያስመዘገብናቸው ሰው ሰራሽ እና የተፈጥሮ ቅርሶቻችን ዋጋ እንዳሰጡን ሁሉ ያልታዩ ሌሎች ጸጋዎቻችንን መግለጥ ተጨማሪ ዕድል ይሰጣል ሲሉም አስታውቀዋል።
‹‹ባህላዊ እና መንፈሳዊ ቱሪዝሞች እንዳሉን ሁሉ በመልከዓ ምድሩ ላይ ብንሰራ ተጨማሪ ጥቅም በማግኘት ከሀገር አልፈን ለአካባቢው ማህበረሰብ መትረፍ የምንችልበት መንገድ ሰፊ ነው›› ሲሉም አመልክተው፣ እንደዚህ ያሉ ቅርሶች እንዲጠበቁ ዕድል መስጠት በቱሪዝም ዘርፉ ላይ መነቃቃትን እንደሚፈጥር ጠቁመዋል።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ይሄን ከግምት ውስጥ በማስገባት ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ ዩኔስኮ ጋር በመተባበር ‹የዩኔስኮ ዓለም አቀፍ ጂኦፓርኮች እና ጂኦቱሪዝም ለዘላቂ ልማት ያላቸው ሚና› በሚል መነሻ ሀሳብ ከግንቦት 4 አስከ 7 ቀን 2017 ዓ.ም የሚቆይ ዓለም አቀፍ ወርክሾፕ መዘጋጀቱን አስታውቀዋል፡፡
በመድረኩ ከምስራቅ አፍሪካ ሩዋንዳን፣ ጅቡቲን ታንዛኒያን፣ ኡጋንዳን ኬንያን ጨምሮ ሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት እንደሚሳተፉ ገልጸው፣ ከሳውዲ አረቢያ፣ ከፈረንሳይ፣ ከሲውዘርላንድ፣ ከቦትሶዋና የተውጣጡ የዘርፉ ታዋቂ አሰልጣኞች እንደሚታደሙበትም ተናግረዋል። ከዘርፉ ተጠቃሚ እየሆነች ያለችው የታንዛኒያ ተወካዮች በቦታው በመገኘት ልምድ እንደሚያካፍሉ አስታውቀዋል፡፡
እሳቸው እንደተናገሩት፤ በመድረኩ የመጀመሪያው ቀን 120 ለሚደርሱ ባለድርሻ አካላት ወሳኝ የግንዛቤ መፍጠሪያ ተዘጋጅቷል፤ በቀሪዎቹ ሶስት ቀናት ደግሞ ለተመረጡ ባለሙያዎች (ከዩኒቨርስቲ፣ ከክልል፣ ከባህልና ቱሪዝም፣ ከቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን፣ ከኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣን) በተመረጡ ሳይቶች ላይ ተግባር ተኮር ስልጠና ይሰጣል። ስልጠናውን ጨርሰው ሲመለሱ ወሳኝ የሚባሉ የቱሪዝም ቦታዎችን ለይተው ለጂኦፓርክ እና ለጂኦ ቱሪዝም ልማት እንዲውሉ፣ በዩኔስኮም እውቅና እንዲያገኙ የሚያስችሉ ሥራዎችን እንዲሠሩ ያለመ ነው፡፡
በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎች የሚሳተፉበት እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታወቁ ምሁራን ሥልጠና የሚሰጥበት ይህ ወርክሾፕ እንደ ሀገር በቱሪዝም ዘርፉ እየተከናወነ ላላው ተግባር ሌላ ሰፊ በር እንደሚከፍት ገልጸዋል። በቀጣይ ሊከናወኑ የታቀዱ ሌሎች የትብብር ሥራዎች እንዳሉም ጠቁመዋል።
ከግንዛቤ ማስጨበጥና አካባቢን በጥልቅ ከመረዳት እንቅስቃሴ በኋላ እንደየአስፈላጊነቱ የቅርስ ልየታ ቦታ እንደሚደረግ፣ አዳዲስ ጂኢፓርኮች እና ጂኦ ቱሪዝሞች የማስመዝገብ እንቅስቃሴ እንደሚኖር ጌታነህ አዲስ (ዶ/ር) አመላክተዋል፡፡
የራስን ሀብት በዓለም አቀፍ ደረጃ በማስተዋወቅ የራስ ሚና ከፍተኛ መሆኑን አስታውቀው፣ ቦታዎችን በመለየት፣ የተጣራ መረጃ በማቅረብ፣ ግንዛቤ ያለው ማህበረሰብ በመፍጠር ሂደቱን ማቀላጠፍ እንደሚቻል ጠቁመዋል። አብዛኛው በሀገር ውስጥ ቅርሶች ላይ በራስ ሚና እንደሚሰራ ገልጸው፣ ድንበር ዘለል በሚሆኑበት ጊዜ ከሌሎች ሀገራት ጋር አብሮ መሥራት ሊኖር እንደሚችል አመላክተዋል፡፡
ጂኦፓርኮችን እና ጂኦቱሪዝምን ለዘላቂ ሀገራዊ ልማት ለማዋል ወሳኝ ትግበራዎች እንደሚያስፈልጉ ያስገነዘቡት አናሊስቱ፣ ለአብነትም ማህበረሰቡን ያማከለ፣ ተጠቃሚነቱን ያረጋገጠ አሠራር ግድ እንደሚል፣ ቦታውን መለየት፣ ማስተዋወቅ፣ አስፈላጊ ሰነዶችን ማዘጋጀት፣ መሰረተ ልማቶችን ማስፋፋት ወሳኝ እንደሆኑ አመላክተዋል፡፡
የዩኔስኮ ግሎባል ጂኦፓርክ በቅርስ ጥበቃ ላይ ከሚሠሩት ሌሎች አካላት የተለየ መሆኑን ጠቅሰው፣ ለእዚህ እንደምሳሌ ያነሱትም በነባሩ የቅርስ ምዝገባ ሥርዐት ሰው ሰራሽ እና ተፈጥሮአዊ ቅርሶች ሲመዘገቡ ጥብቅ ቦታ በሚል ከማህበረሰብ መገለላቸው፣ ተጠብቀው እና ተከልለው መገኘታቸው እንደ ቀዳሚ መስፈርት የሚነሳ መሆኑን ነው።
በግሎባል ጂኦፓርክ ይሄ እንደሌለ፣ በተቃራኒው ማህበረሰብ ወሳኝ እና አስፈላጊ መሆኑ የታየበት ነው ብለዋል። ‹‹ የዩኔስኮ ጂኦፓርክ ማህበረሰብ ከሌለ ጂኦፓርክ አይኖርም›› በሚል መስፈረት እየሠራ እንደሚገኝ አመልክተው፣ ይህንንም የአፋር ክልሉን ኤርታሌን በምሳሌነት አንስተው አብራርተዋል።
ኤርታሌን በጂኦፓርክነት እናስመዝግብ ብለን ብንነሳ የኤርታሌ ዙሪያ ማህበረሰብ ሊኖር ግድ ይላሉ ሲሉ ጠቁመው፣ ማህበረሰብ በሌለበት ግሎባል ጂኦፓርክ እንደማይኖር፣ በተወሰነ ኪሎ ሜትር የአካባቢው ማህበረሰብ ተጠቃሚ የሚሆንበት ሁኔታ ከሌለ ዩኒስኮ እውቅና እንደማይሰጥም ገልጸዋል፡፡
‹‹ሀገራችንን የሰው ልጅ መገኛ፣ የተፈጥሮ እና የሰው ሰራሽ ሀብቶች ማዕከል፣ በስነምህዳር እና በመሰል ጸጋዎቿ ቀዳሚ እያልን እንጠቅሳለን›› ሲሉ አስታውቀው፣ ‹‹በጂኦፓርኩ እና በጂኦቱሪዝሙ ላይ እውቅና ተሰጥቶን መመዝገብ ስንችል ተጨማሪ እድሎችን በመፍጠር በቱሪዝም ዘርፉ ላይ የተሻለ ለውጥ ማምጣት እንችላለን›› ብለዋል፡፡
የጎብኚዎችን ቀልብ በመሳብ የሀገሪቱን ጸጋዎች ወደ ገንዘብ መመንዘር፣ መንግሥትም ሆነ ባለድርሻ አካላት ተጨማሪ ገቢ በማግኘት ከዘርፉ የበለጠ ተጠቃሚ መሆን እንዲችሉ፣ ከገጽታ ግንባታ እና ከተወዳዳሪነት አኳያ ላቅ ያለ ሚና እንዳለው አመልክተዋል፡፡
አናሊስቱ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ በዘርፉ በአፍሪካም ሆነ በአለም አቀፍ ደረጃም ብዙ ሀብት አላት። ከአጠቃቀም አኳያ ግን የሚገባውን ጥቅም እያገኘች አይደለችም። ከኢትዮጵያ ያነሰ የተፈጥሮ ሀብት ያላቸው ሀገራት የተሻለ ተጠቃሚ እየሆኑ ይገኛሉ። ለአብነትም ከአፍሪካ ግብጽ እና ኬንያ ይጠቀሳሉ።
እንደ ግብጽ እና ኬንያ ያሉ ሀገራት በአንድ እና በሁለት የተፈጥሮ ጸጋዎች በቱሪዝሙ ላይ ተጽዕኖ መፍጠር ችለዋል። ለዚህ ተጠቃሚነት ያበቃቸው የተፈጥሮ ሀብታቸውን መለየት፣ ማስተዋወቅ እና መጠቀም መቻላቸው በዋናነት ይገለጻል።
በተፈጥሮ እና በባህል ቅርሶቿ ዓመቱን ሙሉ የምትጎበኘው ኢትዮጵያ ግን ከዘርፉ ተጠቃሚ አለመሆኗ ቁጭት መፍጠሩን አስታውቀው፣ በዚህ የተነሳም በተለየ እንቅስቃሴ ለውጥ ለማምጣት እየተሠራ መሆኑን ጌታነህ አዲስ (ዶ/ር) አመልከተዋል፡፡
በግሎባል ጂኦፓርክ ከአፍሪካ ሞሮኮ እና ታንዛኒያ የጂኦፓርክ እና ጂኦቱሪዝም ሀብቶቻቸውን ማስመዝገባቸውን ጠቅሰው፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ግን 229 የሚሆኑ ሀገራት እነዚህን ሀብቶቻቸውን ማስመዝገባቸውን ገልጸዋል።
ከአንድ ነጥብ አራት ቢሊየን በላይ የህዝብ ብዛት ያላት እና በጸጋዎቿ ከሌሎቹ አህጉራት የምትለየው አፍሪካ በሁለት ሀገራት ጂኦፓርክ መጠራቷ ቁጭት እንደሚፈጥር ተናግረዋል።
ግሎባል ጂኦፓርክ ዘርፈ ብዙ ፋይዳ አንዳለው ጠቅሰው፣ በተለይ ዘርፉን ከማሳደግ እና ሀገርን በዓለም አቀፍ ደረጃ ከማስተዋወቅ አኳያ ሚናው ትልቅ መሆኑን አመልክተዋል። ይህን ፋይዳም አብነት ጠቅሰው ሲያብራሩ በቤልጅየም እና በስፔን ከተማ በነበራቸው ጉብኝት ጂኦፓርኮች ተጠብቀው ለጉብኝት፣ ለቱሪስት አገልግሎት፣ ለማስተማሪያነት ሲውሉ መመልከታቸውን ጠቅሰዋል።
ከአጸደ ህጻናት ጀምሮ እስከ ዩኒቨርስቲ ድረስ ያሉ ተማሪዎች በቦታው በመገኘት ስለአካባቢ ስነ ምህዳር፣ ስለቅርስ እና ተፈጥሮ ሀብት ተጨባጭ እውቀት እንዲኖራቸው ማድረግ እንደሚያስችል ተናግረው፤ በሌላ መልኩ ለቦታው ጎብኚዎች በሚደረግ የምግብ አቅርቦት፣ በግብይት ቦታ ገቢዎች ማግኘት እንደሚያስችል ገልጸዋል። ባለሙያው አያይዘውም ከአካባቢው እጽዋቶች የሚዘጋጅ ጂኦፉድ የሚባል ምግብ በማዘጋጀት ለቱሪስቶች በማቅረብ ለአካባቢው ማህበረሰብ የሥራ እድል እስከመፍጠር የቻሉበትን አጋጣሚ አንስተዋል፡፡
እስከ አሁን በዚህ ተጠቃሚ ያልተሆነበት ዋነኛ ምክንያት የግንዛቤ እጥረት መሆኑን ጠቅሰው፣ ጥቂት ግንዛቤ ያላቸው ሰዎች ለውጥ ለማምጣት ሞክረው በሚፈለገው መልኩ ለውጥ እንዳልመጣ አንስተዋል። ይሄ ችግር እንደአንድ ትልቅ ክፍተት ተወስዶ ከተቋማት ጋር በመነጋገር ከዚህ ላቅ ሲልም በፖሊሲ ደረጃ በማካተት እየተሰራበት እንደሚገኝ የፖሊሲ አናሊስቱ ገልጸዋል፡፡
እሳቸው እንዳብራሩት፤ ከውሳኔ ሰጪ እና ፖሊሲ አውጪ አካላት በተጨማሪ ባለስልጣናት እና የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ሃላፊዎች የሚገኙበት ይህ ወርክ ሾፕ ግንዛቤ ከማስጨበጥ ጎን ለጎን በቀጣይ ስለሚሠሩ ሥራዎች አቅጣጫ ይቀመጥበታል ተብሎ ይጠበቃል። ኢትዮጵያ በዩኔስኮ መስፈርት መሰረት በፓርኮች ጥበቃ እና ልማት ጥሩ ስም አላት፤ 12 የሚዳሰሱ ቅርሶችን በዩኔስኮ በማስመዝገብ በአፍሪካ ቀዳሚ ከሆኑ ሁለት ሀገራት አንዷ መሆን ችላለች።
በተለይ ለጂኦፓርክ ምዝገባ ምቹ ሁኔታዎች መኖራቸው ወደፊት የተሻሉ ዕድሎች መፈጠር እንደሚችሉ አመላክተዋል። ሌሎች ከዚህ ጋር የሚያያዙ ቅርሶችን የመጠበቅ፣ የመንከባከብ፣ ለዘላቂ ልማት የማዋል እንቅስቃሴዎች በጂኦፓርክ እና ጂኦቱሪዝም ላይ ዓይነተኛ ለውጥ ለማምጣት እንደሚያስችሉም ጠቁመዋል፡፡
ዘላለም ተሾመ
አዲስ ዘመን እሁድ ግንቦት 3 ቀን 2017 ዓ.ም