
በቱሪዝም ሀብታቸው ከሚታወቁ የሀገራችን ክልሎች መካከል የሀረሪ ክልል ይጠቀሳል። በክልሉ ዋና ከተማ ሀረር ከሚገኘውና በዩኔስኮ ከተመዘገው የጀጎል ግንብ በተጨማሪ ክልሉ የአያሌ ቅርሶች ባለቤት ነው። ሸዋ ሊድ ሌላው በዩኔስኮ የተመዘገበ የክልሉ ቅርስ ነው። ሀረር በውስጧ አቅፋ በያዘቻቸው በርካታ ቅርሶች ሳቢያ የጎብኚዎች ቀልብ በእጅጉ ያረፈባት ከተማ ለመሆን በቅታለች።
የክልሉ ባህል ቅርስ ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ ተወለደ አቡዱሽ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንዳሉት፤ የሀረር ከተማ በአለም አቀፍ ደረጃ በፈረንጆቹ 2003 የሰላም እና የመቻቻል ከተማ በሚል በዩኒስኮ እውቅና ተሰጥቷል። በሀረር ከተማ የሚገኘው የጀጎል ግንብ በ2006 በአለም አቀፍ ቅርስነት ተመዝግቧል። ክልሉ ለቱሪዝም በሰጠው ልዩ ትኩረት ከተማዋ በእደጥበብ ባለቤትነት የብራንድ ባለቤትነት የብቃት ማረጋገጫ አግኝታለች።
የሀረር ከተማ የአለም ቅርስ ከተሞች ድርጅት እንዲሁም የአለም ቱሪዝም ከተሞች ፌደሬሽን አባል ሆና መመረጧን ጠቅሰው፣ እነዚህ ሁሉ ለአለም አቀፍ እውቅናዋ እንዲሁም ለቱሪዝሙ ዘርፍ እድገት የበኩሉን ኣስተዋጽኦ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅትም እነዚህን ስኬቶችና ከተማዋ በቱሪዝም ዘርፍ ይዛ የቆየቻቸውን ሀብቶ በመልካም እድልነት በመጠቀም የቱሪዝም ዘርፉን ልማት አጠናክሮ ለማስቀጠል ብርቱ እንቅስቃሴ እየተደረገ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡
ሀረር በቱሪዝሙ ዘርፍ ህያዊቷ ሙዚየም በሚል በአለም መድረክ ካሉ አቻ ከተሞች ጋር በብራንድነት እንድትጠራ የማድረጉ ሥራ ተጠናክሮ መቀጠሉን ኃላፊው ተናግረው፣ ከቅርስ ጋር ተያያዥ የሆኑ ቦታዎችን ለመስህብነት ለማዘጋጀት እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል። በዚህም ጀጎል አካባቢ ተከልሎ ያለውን ቦታ ክፍት በማድረግ ማህበረሰቡ ከቅርስነት ባለፈ ለኢኮኖሚያዊ ጥቅም ያለውን ሚና እንዲረዳ ለማድረግም እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
የቢሮ ኃላፊው እንዳስታወቁት፤ አካባቢው ተመራጭ የቱሪስት መናፈሻ እንዲሆን በትኩረት እየተሰራ ነው፤ ቅርሱን በጠበቀ ሁኔታ ከገጠር እስከ ከተማ፣ ከከተማ እስከ ዲያስፖራ እንደዚሁም የተለያዩ ድርጅቶችን ባቀፈ መልኩ ለኑሮ እንዲሁም ለጉብኚዎች ምቹ ያልነበሩ ቦታዎችን ውብ እና ምቹ ለማድረግ እየተሰራ ይገኛል።
በተለይ ከ2015 ወዲህ በተከናወኑ ተግባሮች ቱሪስቶች ጀጎልን ብቻ ጎብኝተው እንዳይመለሱ ሰፊ እድሎችን በመፍጠር የቱሪዝም አማራጮች መስፋታቸውን ኃላፊው ጠቁመዋል። በጀጎል ግንብ ዙሪያ ከአምስት ሺህ ሜትር ስኳየር በላይ የአረንጓዴ አካባቢ መገንባቱን ጠቅሰው፣ በጀጎል ውስጥ በአንደኛ እና በሁለተኛ ዙር የኮሪደር ልማት ሰባት ሺ100 ሜትር ስኬየር በላይ መሬት የማስዋብ ሥራዎች መጠናቀቃቸውን አስታውቀዋል።
በሶስተኛው ዙር የኮሪደር ልማት አምስት ሺ 500 ሜትር ስኳየር ያህል ቦታን የማስዋብ ስራ እየተካሄደ መሆኑን ገልጸዋል። እነዚህ ሁሉ ሥራዎች ከመንግስት በጀት ተመድቦባቸው እንዳልተሰሩ ጠቅሰው፣ ህብረተሰቡ እና የተለያዩ ተቋማትን በማስተባበር የተሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን ባስጀመሩት የኮሪደር ልማት ክልላችንን በቱሪዝሙ ዘርፍ ስም ያላት እንድትሆን ሁሉም እየሰራ ይገኛል ሲሉም አስታውቀው፣ በዓለም የቅርስ መዝገብ ላይ የተመዘገቡት የክልሉ ቅርሶች የሁሉም መሆናቸውን ታሳቢ በማድረግ የኔ በሚል ስሜት ሁሉም አካል አስተዋጽኦ እያደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
ለቱሪዝሙ ልማቱ የሚውል ገንዘብ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የመደመር ትውልድ መጽሐፍ እንደተገኘ ተናግረው፣ ከመጽሐፉ ሽያጭ በተገኘ ገቢ የተሠራ እንዳለም ገልጸዋል። የሀረር ኢኮ ፓርክ ዘመናዊ እና ምቹ ሆኖ ለመስህብነት እንዲውል ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን ጠቁመው፤ ኤኮ ቱሪዝሙ የካፍቴሪያ እና የእደ ጥበብ ሥራዎች ለጎብኚዎች ክፍት የሚደረጉባቸው ክፍሎች እንዳሉትም ተናግረዋል፡፡
እሳቸው እንዳሉት፤ ሙዚየሞች ላይ እሴት ለመጨመር እየተሰራ ሲሆን፣ በክልሉ የገጠር አካባቢዎች ያሉ እስከ አንድ ሺህ አመት ያስቆጠሩ ታሪካዊ ቦታዎችን ከፌደራል ቅርስ ባህል ባለስልጣን ጋር በመተባበር የእድሳት ሥራ እየተሰራ ይገኛል። በቀጣይ እነዚህ ቦታዎች እንደአንድ የቱሪስት መስህብ ለቱሪዝሙ ዘርፍ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በአሁኑ ወቅት በከተማዋ ሰፊ የኮሪደር ልማት እየተካሄደ መሆኑን አመልክተው፣ ይህ የኮርደር ልማት ለክልሉና ለከተማዋ ትልቅ እድል ይዞ መምጣቱን ገልጸዋል። በቱሪስት ፍሰቱ ላይ ከፍተኛ እመርታ ማምጣቱን ጠቁመው፣ በዘጠኝ ወራት ውስጥ ለተመዘገበው የቱሪስት ፍሰት የከመታ ማስዋብ ሥራው ከፍተኛውን ድርሻ ይወስዳል ብለዋል፡፡
የቢሮ ኃላፊው ያለፉት ዘጠኝ ወራት የቱሪስት ፍሰት ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በሀገር ውስጥ ቱሪስቶች በሰባት ነጥብ አራት በመቶ ብልጫ ማሳየቱን አስታውቀዋል። የውጪ ቱሪስት ፍሰት ደግሞ 30 ነጥብ ስምንት በመቶ ብልጫ ማሳየቱን ገልጸዋል።
የኮሪደር ልማቱ ቱሪስቶችን ከመሳብ ባለፈ ቆይታቸው እንዲራዘም በማድረግ በኩልም ድርሻው ከፍተኛ መሆኑን አስታውቀዋል። ከክልሉ ባለፈ በአቅራቢያው ለሚገኘው ማህበረሰብ መነቃቃትን የፈጠረ ትልቅ ስኬታማ ሥራ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
በዘጠኝ ወራቱ ከሀገር ውስጥ ቱሪስቶች 122 ሚሊዮን ብር መገኘቱን አቶ ተወለደ ተናግረው፤ ክልሉን ከጎበኙ የውጪ ቱሪስቶች ደግሞ 14 ሚሊዮን ብር እንደ ተሰበሰበ ገልጸዋል። ክልሉ ሰባት ሺ 877 የሚሆኑ የውጪ ሀገር ቱሪስቶችን ተቀብሎ ማስተናገዱን አስታውቀው፣ ይህም ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲተያይ በ31 ነጥብ ስድስት በመቶ ብልጫ እንዳለው ተናግረዋል።
123 ሺ 713 የሀገር ውስጥ ቱሪስቶች ክልሉን መጎብኘታቸውን ጠቅሰው፣ ይህም ካለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በዘጠኝ ነጥብ አራት በመቶ እድገት ማሳየቱን ገልጸዋል፡፡
እሳቸው እንዳሉት፤ በዘጠኝ ወራቱ በሀገር ውስጥ ቱሪስት 121 ሺህ 863 ጎብኚዎችን ለማስተናገድ ታቅዶ፣ 123 ሲህ 713 ቱሪስቶችን ማስተናገድ ተችሏል። እስከ ሰባት ሺህ የሚደርሱ የውጪ ሀገር ጎብኚዎችን ለመቀበል ታቅዶ ሰባት ሺ 877 ቱሪስቶችን ተስተናግደዋል። ከእቅድ አኳያ በሁለቱም ጎብኚዎች ከመቶ በመቶ በላይ አፈጻጸም ተመዝግቧል።
ከገቢ አኳያም በሀገር ውስጥ ጎብኚዎች 103 ሚሊዮን ብር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ፣ 122 ሚሊዮን ብር ገቢ ተገኝቷል ሲሉ ገልጸዋል። ይሄም በመቶኛ ሲሰላ ሰባት ነጥብ አራት በመቶ ብልጫ እንዳለው ተናግረዋል።
የውጪ ሀገር ቱሪስቶችን በሚመለከት 11 ነጥብ ዘጠኝ ሚሊዮን ብር ገቢ ለማስገኘት ታቅዶ እንደነበር አስታውሰው፣ 14 ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ብር እንደተገኘ ገልጸዋል። ይሄም በመቶኛ ሲሰላ በ30 ነጥብ ስምንት በመቶ ብልጫ እንዳለው አስታውቀዋል፡፡
እሳቸው እንዳብራሩት፤ ባለፉት አመታትም በቱሪዝም ዘርፉ መነቃቃት እየታየ መጥቷል። የቱሪዝም ዘርፉ እንደ አንድ የኢኮኖሚ ዘርፍ ተወስዶ በርካታ ስራዎች እየተሰሩበት ይገኛል። በተለይ ከኮረና ወዲህ ባሉት ባለፉት አመታት እንደ ሀገርም ሆነ እንደ ክልል ቱሪዝሙ ላይ ለውጥ መጥቷል።
የክልሉን የ2014 የሀገር ውስጥ እና የውጪ የቱሪስት ፍሰት እንደማሳያ ጠቅሰው ሲያብራሩ እንዳሉት፤ በክልሉ የውጪ ሀገር የጎብኚዎች ቁጥር አንድ ሺ 400 የነበረ ሲሆን፣ የሀገር ውስጥ ጎብኚዎች ቁጥር ደግሞ ከ65 ሺህ የማይበልጥ ነበር። በእዚህ አሀዝ ላይ በ2017 በጀት አመት ባለፉት ዘጠኝ ወራት ብቻ አስደናቂ ለውጥ ታይቶበታል፡፡
65 ሺህ የነበረው የሀገር ውስጥ ጎብኚዎች አሀዝ ወደ 123 ሺህ አሻቅቧል፤ አንድ ሺ 400 የነበረው የውጪ ሀገር የቱሪስት አሀዝም እንደዚሁ በዘጠኝ ወራቱ ብቻ ወደ ሰባት ሺ 877 አድጓል። ልዩነቶቹን ከቃል ባለፈ በተግባር የታየ፣ የቱሪዝሙ ዘርፍ በከፍተኛ ሁኔታ እየተነቃቃ ስለመሆኑ ምስክር የሚሆን ሲሉ ጠቅሰዋቸዋል።
በቀጣይ እንደ ክልል የጎብኚዎችን ቁጥር ለመጨመር እና ገቢን ለማሳደግ እየተከናወነ ስላለው ተግባርም ሃላፊው ገልጸውልናል። የገጽታ ግንባታ ለአንድ ቱሪስት ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው፣ በቀጣይ ከነበረው የተሻለ አካባቢያዊ እና ክልላዊ የገጽታ ግንባታ እንደሚሰራም ጠቁመዋል። ክልሉን ማስተዋወቅ፣ ያለውን ሰው ሰራሽ እና የተፈጥሮ ሀብቶች በማስተዋወቅ ቱሪስቶችን የመሳብ እንቅስቃሴ እንደተጀመረ ገልጸዋል፡፡
እሳቸው እንዳሉትም፤ ከእዚህ ተልዕኮ ጋር በተገናኘ ከሁለት ሳምንት በፊት በሆንግ ኮንግ በተደረገ ውይይት ሀረርን የአለም የቱሪስት ከተሞች ፌደሬሽን አባል እንድትሆን ተደርጓል። ከእነዚህ የፌደሬሽን አባል ሀገራት ጋር በመነጋገር እና የልምድ ልውውጥ በማድረግ ቀጣይ የስኬት አቅጣጫዎችን ተቀምጠዋል። ውይይቱ የቴክኒካል ድጋፎችን በማፈላለግ፣ ኢትዮጵያንም ሆነ ሀረር ከተማን በአለም አቀፍ መድረክ በቱሪዝሙ ዘርፍ ለማስተዋወቅ የተደረገ ጥረት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ከሰሀራ በታች ካሉ ሀገራት የአለም ቅርስ ከተሞች አባል በመሆን ሀረር ቀዳሚ መሆኗን ኃላፊው ጠቅሰው፣ ይሄ እድል እንደሀገርም ሆነ እንደክልል ፋይዳው የላቀ መሆኑን ተናግረዋል። እንደክልል የጀመርነው እንቅስቃሴ ከከተማ አልፎ አለም አቀፍ መልክን እየያዘ መጥቷል፤ ይህም ለቀጣይ ስኬታችን የአንበሳውን ድርሻ በመያዝ ይጠቀሳል ሲሉ አመላክተዋል፡፡
አቶ ተወለደ ባለፉት ጥቂት አመታት የታዩት ለውጦች መጪውን በተሻለ እንድንመለከት እድል የሰጡ ናቸው ሲሉም ጠቅሰው፣ የቱሪዝሙ ዘርፍ ከዋና ዋና የኢኮኖሚ ምሰሶዎች እንደአንዱ ተወስዶ በመንግሥት በኩል እየተሰራበት መሆኑ አዲስ የለውጥ ምዕራፍ እንደሚከፍት ይታመናል ሲሉ አስረድተዋል። ኢትዮጵያ እስከ አሁን ያልተጠቀመቸባቸውን ሰው ሰራሽ እና የተፈጥሮ ጸጋዎቿን እንድትጠቀም እድል እንደሚሰጥ ተናግረዋል።
ኃላፊው በሀገር አቀፍ ደረጃ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት እየተሠሩ ያሉ የቱሪዝም እንቅስቃሴዎችን አድንቀው፣ እነዚህ ሥራዎች ከኢኮኖሚ ተጠቃሚነት፣ ከገጽታ ግንባታ፣ ከውበት እና ከዘመናዊነት አኳያ አስተዋጽኦአቸው ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል። የእነዚህ ሥራዎች አድማሳቸው እያሰፋ ሲሄድ ከሀገር ባለፈ አለም አቀፍ እውቅና እንደሚያገኙ እምነታቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡
እንደ እሳቸው ማብራሪያ፤ የቱሪዝሙ ኢንዱስትሪ ጭስ አልባ ኢንዱስትሪው የመባሉ ነገር ዝም ብሎ አይደለም። ከኢትዮጵያ ያነሰ ጸጋ ያላቸው በርካታ ሀገሮች በውስን የቱሪዝም ሀብታቸው በሚገባ እየተጠቀሙ ናቸው።
ኢትዮጵያውያን በእዚህ በተፈጠረብን ቁጭት በዘርፉ እየተከናወኑ ባሉ ስራዎች በርካታ ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴዎችን እያየን እንገኛለን ሲሉም ገልጸው፣ በቀጣይ ከዘርፉ የበለጠ ተጠቃሚ የምንሆንበትን እድል ለመፍጠር የሁላችንም ንቃት፣ ግንዛቤ እና እንቅስቃሴ ወሳኝ ነው ብለዋል፡፡
የሀረሪ ክልል በሀገር አቀፍም ሆነ በአለም አቀፍ ደረጃ ለሚደረጉ ለየትኛውም የገጽታ ግንባታ ስራዎች ዝግጁ መሆኑን ጠቅሰው፣ የክልሉ ባህል ቅርስ ቱሪዝም ቢሮ በአወዚህ ለመሳተፍ ዝግጁ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
የክልሉ የቱሪዝም ዘርፍ ተግዳሮት የሚነሳ ነገር ካለ በሚል ተጠይቀው፣ ሲመልሱ የሀረሪ ክልል ቅርሶች ተጠብቀው፣ ተከልለው የሚቀመጡ ቅርሶች አይደሉም ሲሉም ጠቅሰው፤ ቅርሱ ባህላዊ ይዘቱን እና እሴቱን ጠብቆ እንዲቆይ ለማድረግ ነገሮች ትንሽ ውስብስብ መሆናቸውን ገልጸዋል። እንዲያም ሆኖ ግን በቅንጅት እና በውይይት በመተሳሰር ቅርሶቹን ለመጠበቅ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል። ህብረተሰቡም የእዚህ ትስስር አንድ አካል እንዲሆን በእዚህ አጋጣሚ ጥሪ አቅርበዋል።
ዘላለም ተሾመ
አዲስ ዘመን እሁድ ሚያዝያ 26 ቀን 2017 ዓ.ም