የህልውና ዘመቻውን በማበረታት የአንድ ሰሞን የማህበራዊ ሚዲያ መነጋገሪያ ነበሩ። ጦርነቱ ጋር በትኩሱ ደርሰው የማህበረሰቡን ችግር፣ የዘማቹን ሁኔታ ያዩና በቅርባቸው ያሉ ባለሀብቶችን ጭምር ያሳዩም ናቸው። ከዚህም በላይ የድጋፍ ማሰባሰብ ሥራዎችን በመስራትና ከዚያ በላይ መስራት እንደሚገባም ማስገንዘባቸው ያስመሰግናቸዋል። እንደ ‹‹ የዘመን ጣይቱ እንሁን›› አይነት አዳዲስ ንቅናቄዎችን በመፍጠርም ዛሬ ድረስ ዘማቹ እንዲታገዝ እያደረጉ የሚገኙ ጠንካራ አመራር እንደሆኑ ይነገርላቸዋል።
በሚመሩት ተቋም ላይ ሳይቀር ግብር ከፋዩን በደረጃው ህልውና ዘመቻው ላይ እንዲሳተፍ ያደረጉም ናቸው። በትምህርታቸው ደግሞ ከሰርተፍኬት እስከ ሁለተኛ ድግሪ ድረስ የዘለቁ ናቸው፤ እኛም ይህንን ተሞክሯቸውን ለአንባቢዎቻችን እንዲያጋሩልን በማሰብ ለዛሬ የ‹‹ ህይወት ገጽታ›› አምድ እንግዳችን አድርገናቸዋልና ከሲስተር ብዙአየሁ ቢያዝን ህይወት ተማሩ ስንል ጋብዘናችኋል።
ጭምቷ ግን ተወዳጇ ልጅ
የአርሶአደር ልጅ ናቸው። አባታቸው ደግሞ ካህን ሲሆኑ፤ የመማርን ጥቅም ጠንቅቀው ያውቁታል። ስለዚህም በነጻነት የሚማሩበትን ሁኔታ አመቻችተውላቸዋል። እርሳቸው ጨዋታ ወዳድ ባይሆኑም የሚጫወቱበት ጊዜም አይነፈጉም። እንዲያውም ተጫወቺ እየተባሉ ይጎተጎታሉ። በእርግጥ ብዙ ጊዜ ጨዋታ ላይ የማያሳልፉት ዝምተኛና ማንበብ ብቻ የሚወዱ በመሆናቸው ነው። ይሁን እንጂ ፋታ ሲያስፈልጋቸው ክረምት ላይ ከእድሜ እኩዮቻቸው ጋር ተጫውተዋል። ከጨዋታዎች የሚያስታውሱትም የልጅነት ህልማቸው የአሁኑ ደግሞ ውጤታቸው የሆነውን ህክምና ተግባራዊ በማድረግ ነው። በተለይም ነርስ መሆን ለእርሳቸው ልዩ ትኩረት የሚሰጠው ነበርና እንጨቱን ቀርጸው መርፌ በማስመሰል ህመምተኛውን ለማከም ይጥራሉ። ይህ ፍላጎታቸው የመነጨው ደግሞ የተቸገረ ማየት ስለማይሆንላቸው የተፈጠረ ነው። በዚህም ዛሬ ሰው ከተጠቀመበትና ከዳነ ነገ እኔ ሌላ አገኛለሁ ብለው ያምናሉና ያላቸውን ሁሉ ይሰጣሉ፤ በሙያ ጭምር ማገዝ እንደሚቻልም የተረዱት ገና ልጅ ሆነው እንደነበርም ይናገራሉ።
ሲስተር ብዙአየሁ ተወልደው ያደጉት በምስራቅ ጎጃም ዞን ስናን ወረዳ ገዳማዊት ቀበሌ ኮኛት ሰፈር ሲሆን፤ በዚህ ስፋራ ልጅነታቸውን በሚገባ አሳልፈዋል። ቤተሰቡን በቻሉት ሁሉ አግዘዋልም። በእርግጥ ቤተሰቡ ትልቅ የሚባል ሥራ ሰጥቷቸው አያውቅም። በዚህም እንደገጠር ልጅነታቸው ብዙዎቹን የገጠር ሥራዎች አልሰሩም። ዋናው ሀላፊነታቸውና ሁሌ እሰራው ነበር የሚሉት አንድ ነገር ብቻ ነው። ይህም ቤት መለቅለቅ ፣ ማጽዳትና ቄጤማ ጎዝጉዞ ቡና ማፍላት ነው። በእጣን ጢሱ ቡና አፍሊው ማን እንደሆነ ካልተለየ እርሳቸው መሆናቸው ግልጽ ነው። ስለዚህም በልጅነታቸው ከዚህ ውጪ የሰሩትን ሥራ እንደማያስታውሱት አጫውተውናል። ሰው ቢበድልህ አትበድለው አስተምረው እንጂ የሚል ብሂል ያላቸው ልጅም እንደነበሩ ይናገራሉ። ይህ ደግሞ የማማከር ችሎታቸውን ያጎላላቸው እንደነበር ያስታውሳሉ።
ሰርተፍኬቱ ወደ ሁለተኛ ድግሪ
የአባታቸው ወኔ ሰጪነት ትምህርታቸውን ያለማቋረጥ እንዲማሩ አድርጓቸዋል። በተለይም በልጅነታቸው ጭምር ሚኒስትር እንደሚሆኑ ቤተመንግስት እንደሚገቡ እየነገሩ ማሳደጋቸው ጠንክረው ተምረው የአመራርነት ቦታን ጭምር እንዲፈናጠጡት የረዳቸው ነበር። ከሌሎች የሰፈር ልጆች ጭምር ውጤታቸው ታይቶ ውጪ ላይ ሻይ መጋበዛቸውም እንዲሁ የውጤታማ ተማሪነታቸው መሰረት ነበር።
ሲስተር ብዙአየሁ መጀመሪያ ከትምህርት ጋር የተዋወቁት በስናን ወረዳ ሮብ ገበያ ከተማ ሮብ ገበያ ትምህርትቤት ነው። ከአንደኛ ክፍል እስከ ስምንተኛ ክፍልም በዚህ ትምህርት ቤት ትምህርታቸውን መከታተል ቀጠሉ። ቁጭት ነበረባቸውና ወገባቸውን ታጥቀው መማር በመቻላቸውም በማዕረግ ትምህርቱን እንዲያጠናቅቁ ሆኑ።
ቀጣዩ የትምህርት ጉዟቸው የሚወስደን አዲስ አበባ ላይ ሲሆን፤ ይህም ሁለት የትምህርት መስኮችን የያዘ እድል ያገኙበት ነው። የመጀመሪያው አሁን በሚሰሩበት የጤና መስክ ነው። በጥቁር አንበሳ አማካኝነት የተሰጣቸው የትምህርት እድልም ነበር። ሁለተኛው ደግሞ በዴቨሎፕመንታል ማኔጅመንት የተሰጣቸው የትምህርት እድል ሲሆን፤ ሁለተኛውን በመምረጥ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲን እንዲቀላቀሉ ሆነዋል። የመጀመሪያ ድግሪያቸውንም በማዕረግ አጠናቀዋል።
ከአምስት ዓመት የሥራ ላይ ቆይታ በኋላ ሌላኛውን የትምህርት ምዕራፍ የጀመሩ ሲሆን፤ ይህም የትምህርት እድል አግኝተውበት የተማሩት ነው። በሁለተኛ ድግሪ በፐፕሊክ ማኔጅመንት የቀጠሉ ሲሆን፤ በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርስቲ በመግባትም ተምረውታል። እዚህም ቢሆን እንደተለመደው በወርቅ ሜዳለያ ተሸላሚነት ነው ትምህርቱን ያጠናቀቁት። አሁንም ቢሆን መማር የሁልጊዜ ፍላጎታቸው ነው። መማር በሥራም የሚቆም ባይሆንም ገብቶ መማርም የሚጨምረው ብዙ ነገር አለ ብለው ያምናሉ። ስለዚህም የተሸለ አቅም ያለው አመራር ለመሆን የመጡ የትምህርት እድሎችን ያልሞከሩበት ጊዜ የለም። ግን አልተሳካላቸውም። ይሁንና ሙከራቸው የሚቋረጥ እንደማይሆን በወጋችን መካከል አንስተውልናል።
ከወረዳ የተሻገረው ሥራ
የሥራ ጅማሮአቸው በአስረኛ ክፍል ውጤታቸው ተወዳድረው ሰርተፍኬት በያዙበት የጤና ረዳትነት ሲሆን፤ በደብረወርቅ ክሊኒክ ለዓመት ያህል የሰሩበት ነው። ከዚያ በላይ በቦታው መስራት ያልቻሉት ሴት በመሆናቸው የማይደርስባቸው ፈተና አልነበረምና ነው። ስለሆነም ከጓደኞቻቸው ጋር ምንም እንኳን የፈለግነው ላይ ከመድረሳችን በፊት በጋብቻ አንተሳሰርም ተባብለው ቢማማሉም ፈተናውን ግን መቋቋም አልቻሉትምና ከእነርሱ ጋር ተመካክረው የዛሬውን ባለቤታቸውን አገቡ። በዚህም ቀጣዩን የሥራ ቦታቸውን ደብረማርቆስ ላይ አደረጉ።
ባለቤታቸውን ሲያገቡት እንደሚያስተምራቸውና የፈለጉት ላይ እንደሚያደርሳቸው ውል አሲዘው እንደነበር የሚያነሱት ሲስተር ብዙአየሁ፤ ቃል አክባሪው ባለቤታቸውም ወደ ከተማ ሲገባ ተከትለውት እንዲገቡ ገቡ። በዚያም ዓመት ከመንፈቅ መስራት ችለዋል። ዲፕሎማቸውን ከተማሩ በኋላ ደግሞ በደጀን ጤና ጣቢያ በክሊኒካል ነርሲንግ ሰርተዋል። ጎን ለጎንም የማማከር ሥራ ይሰሩ ነበር። ይህ ሁኔታ ደግሞ ሌላ አማራጭና የሥራ እድልን እንዲያዩ ያደረጋቸው እንደነበር ያስታውሳሉ።
አብሯቸው የሰራ አንድ ዶክተር በሥራቸውና በአመራርነት ብቃታቸው እንዲሁም በአንደበተ ርዕቱነታቸው በጣም ይደሰት ስለነበር ማህበራዊ ሳይንሱን ተቀላቅለው ቢማሩና ቢሰሩበት የበለጠ ለአገር እንዲሚያበረክቱ ይመክራቸዋል። ከምክርነቱ ባለፈም ይገፋፋቸው ጀመር። በዚህም እርሳቸው እንዲያስቡበትና እንዲሆኑት አድርጓቸዋል። በእርግጥ የአመራርነት ቦታውም ቢሆን በአጋጣሚ የተፈጠረ እንጂ እርሳቸው ፈልገውት የሆነ አልነበረም። ደጀን ወረዳ ላይ ገና ሲመጡ የሀላፊነት ቦታ ነበር ተሰጥቷቸው የሰሩት። ይህም በሹመት የተሰጣቸውና የጤና መምሪያ ሀላፊ በመሆን የሰሩበት ነው።
መጀመሪያ አካባቢ ሹመቱን እንቢ ብለው ነበር። ምክንያቱም እርሳቸው መስራት የሚፈልጉት በሙያቸው ብቻ ነው። የድርጅት አባልም አይደሉም፤ መሆንም አይፈልጉም። ነገር ግን የጤና ሥራ ላይ መሰረት ያለው በአቅምና በችሎታ የተሸለ ከአንቺ በላይ ማን ይምጣ በመባላቸው ተቀበሉት። ሁለት ዓመት ከመንፈቅ ያህልም በቦታው ላይ ሰሩ። በዚህ ቆይታቸው ደግሞ በከተማና በገጠር ጤና ኤክስቴንሽን ፤ በእናቶችና ህጻናት ጤና ዙሪያ በፌደራልም ሆነ በክልል ደረጃ ሞዴል የሆኑ ሥራዎችን መስራት ችለዋል። ይህ ሥራቸውም ለሌላ ሹመት አሳጭቷቸዋል። ይህም የሴቶችና ወጣቶች መምሪያ ሀላፊነት ነው።
ዞን ላይ ደብረማርቆስ ከተማ የሴቶችና ወጣቶች መምሪያ ሀላፊ ሆነው መስራት የጀመሩት ሲስተር ብዙአየሁ፤ ከአንዱ ቦታ አንዱ ቦታ መዘዋወራቸውን በፍጹም አልወደዱትም። ምክንያቱም ባሉበት ቦታ ላይ ገና ብዙ የምሰራቸው ሥራዎች አሉ ብለው ያምናሉ። በዚያ ላይ አዲስ ቦታ ሲዛወሩ እንደአዲስ ስራውን መማር ይኖርባቸዋልና ለመስራት ይስተጓጎላሉ። ስለዚህም ወደዚህ ቦታ ሲዛወሩ ሹመቱን አጥብቀው ተቃውመው እንደነበር ያስታውሳሉ። ነገር ግን የሚሰማቸው ስላላገኙ ተቀብለውት ከነበሩት ሰራተኞችና የሥራ ሂደት አስተባባሪዎች እየተማሩ፤ አስፈላጊውን ነገር ከሌሎች አገራት ተሞክሮ እያነበቡ ቦታውን ለሁለት ዓመት ከአራት ወር በብቃት መርተውታል።
የሚያምኑበትን መናገር እንጂ ምን ይመጣብኛልን ሳያስቡ የሚሰሩት ባለታሪካችን፤ ያላቸው ብቃትና ሀቀኝነት ከሹመቱ አላራቃቸውም። ይልቁኑም ተምረው ሲመጡ ሁልጊዜ በሹመት ይጠበቃሉ። ለዚህም ነው ሁለተኛ ድግሪያቸውን ሳይቀር ተመርቀው ሳይመጡ ደብዳቤው ቀድሞ ተጽፎ እዚያው ደብረማርቆስ ከተማ ላይ
የገቢዎች መምሪያ ሀላፊ ሆነው እንዲሰሩ የጠበቃቸው። ገብተውም ለዘጠኝ ወር እንደሰሩ ደግሞ ሌላ ሹመት ተከተላቸው። ለውጡ በመግባቱ የተነሳ የለውጥ አመራር በሚል ሌላ ቦታ ሄዱ። ይኸውም የምስራቅ ጎጃም ዞን ምክትል አስተዳዳሪነት ሲሆን፤ ሰባት ወራትን በቦታው ላይ ከሰሩ በኋላ ደግሞ በቀጥታ ወደ ክልል ተዛውረው አሁን ያሉበትን በአማራ ክልል የገቢዎች ቢሮ ሀላፊነትን እንዲይዙ ሆነዋል። ረጅም ዓመት ያገለገሉበት ቦታም ይህ እንደሆነ ነገርውናል።
የአገር አበርክቶ የሚጀምረው ከአስተሳሰብ ለውጥ የሚሉት ሲስተር ብዙአየሁ፤ አስተሳሰቡ የተስተካከለ ሰው ከጉልበቱም ሆነ ከእውቀቱ የሚቆጥበው ነገር የለም። ለሥራም መከፈል ያለበት ዋጋ ይከፍላል። ማህበረሰቡም ሆነ አገር ማግኘት ያለባትን ነገር እንዲያገኙ ወደኋላ የሚሉበት ነገር አንድም ነገር አይኖረውም። በተለይም የአገር ጥቅም ጉዳይ ከራሱ በላይ ነው። አሁን አገር እየተረፈች ያለችውም በዚህ እሳቤ ውስጥ ያሉ ሰዎች በመኖራቸው ነው። የአስተሳሰብ ቀናነት ለራስም ቢሆን ሞገስ ነው። በየአቅጣጫው መልካም እድልን ያቀዳጃል። ወደመልካም ጎዳናም ይመራል። ከሁሉ በላይ ታሪክ ያጽፋል። ተጋድሎው የሚነገርለት ሰው ያደርጋል። እምነት የሚጣልበት ሰውም ለመሆን ያስችላል ባይናቸው።
‹‹በየጊዜው ሹመት በሹመት ላይ ሲደራረብልኝ የኖረውም ቀናነት መለያዬ ፣ ለአገሬ የምሰስተው ጉልበት የሌለኝ በመሆኔ ነው። እናም ሰዎች በዚህ መልኩ ቢጓዙ ራሳቸውን፤ አገርንና ሰዎችንም ይጠቅማሉ›› የሚሉት ሲስተር ብዙአየሁ፤ በሥራቸው ሙሉ እንዳልሆኑና ብዙ ያደሩ የቤት ስራዎች እንዳሉባቸው አንስተዋል። እነዚህን ለማድረግ ደግሞ መልካምና ውጤታማ ስራ መስራታቸውን እንደሚቀጥሉ አጫውተውናል።
እርሳቸው የገቢዎች ቢሮን ሲቀላቀሉ ዘጠኝ ቢሊዬን ብር ገቢ አስገብተው በዓመቱ አስር ለማስገባት አቅደው ጠበቋቸው። ይህንን አሳክተው በዓመቱ ሁለት ቢሊዬን ጨምረው በማቀድ 93 በመቶ ማሳካት ችለዋል። በዚህ ዓመት ደግሞ 20ነጥብ 5 ቢሊዬን በማቀድ 20 ነጥብ 22 ቢሊዬን መሰብሰብ ችለዋል። ይህ የሆነውም ችግር ውስጥ የገቡ አራት ዞኖች በወቅቱ ሪፖርት ባለማድረጋቸው የተከሰተ ነው። እናም ከማህበረሰቡ ጋር ጥብቅ ግንኙነት መፍጠሬና መነጋገሬ ለአገሬ ውጤታማ ስራ እንድሰራ አድርጎኛልም ብለውናል።
ባለታሪካችን በማስተባበር ስራ የሚዋጣላቸው አይነት ሰው በመሆናቸው የስናን ወረዳ የብልጽግና ተወካይ ለመሆን የበቁና በክልል ደረጃ ምክርቤትን የተቀላቀሉ ናቸው። ከዚህ በተጓዳኝ ለዘመቻው የሚሆኑ ተግባራትን በማስተባበር ላይ ይገኛሉ።
ዘመቻን በሞራል
ውትድርና በወኔ ብቻ የሚቀላቀሉት አይደለም። ተራራ መውጣትና መውረድ ያለበት፤ ስልትና ሙያን ያነገቡ መሆንን ይጠይቃል። ነገር ግን ከዚህ የሚበልጠው ለሰራዊት ደጀን፣ ለወገን አጋር መሆን ነበርና ያንን መርጠው ሲሰሩ እንደቆዩና አሁንም እየሰሩ እንዳሉ አጫውተውናል። በዘመቻ መሳተፋቸው ከጦር ውጊያ በተለየ መልኩ እንደሆነም ነግረውናል። ዘመቻ ዘርፈ ብዙ ተግባራት ያሉበት ሲሆን፤ የመጀመሪያው ማበረታታት ነው። ይህም በብዙ መልኩ ይተረጎማል። አንዱና ዋነኛው መደገፍ ሲሆን፤ በርቀትም ሆነ ከጎኑ በመሆን አለሁ ማለት ወኔን መስጠት ነው።
በውትድርና ውስጥ ከመግባት ውጪ በምን መልኩ አስተማማኝ ደጀን መሆን ይቻላል ሲባልም ዘመቻው ዘርፈ ብዙ እድሎችን የሚሰጥ መሆኑን እናይበታለን። ለዚህም አሁን ጦር ሰብቆ የሚዋጋው እንዳለ ሆኖ ከዚያ በተጓዳኝ ምን ሌላም የምንሰራው አለ በማለት ከጎናቸው ሆነን እየሰራንና እየደገፍናቸው ያለነውም ይላሉ።
እርሳቸው ዘመቻውን ከመቀላቀላቸው በፊትም ቢሆን ብሬን ጭምር መተኮስ እንደተለማመዱና ግዳጅ ከመጣ እንደማይቀሩ ይናገራሉ። እስካሁን በነበረው የዘመቻ ጉዞ ገቢ በማሰባሰብና ግንባር ድረስ በመሄድ ድጋፉን በመስጠት ከመሳተፍ ያለፈ ተግባር አልሰራሁም ይላሉ። በደቡብ ጎንደር በደረሰው ድንገተኛ ጥቃት ህዝቡ በተደናገጠበት ወቅት የቁርጥ ቀን ልጅ መሆን የቻልኩትም ባለሀብቱን፣ አመራሩንና ተፎካካሪ ፓርቲዎችን በወኔ ቀስቅሼ በእኔ ሀሳብ ተስማምተው መሄድ በመቻላቸው እንጂ የተለየ ነገር አምጥቼ አይደለም ባይ ናቸው።
በወቅቱ ሰራዊቱ በጣም ተጎድቷል፤ ህዝቡም ካለበት ቀዬ ለቋል። ስለዚህም ገንዘብ ቢኖርም ገዝቶ ለመመገብ እድሉ አልነበረም። ይህ ደግሞ አይደለም አመራር ላይ ላለና አገርን እወዳለሁ ከሚል ዜጋ ያልሆነውን ጭምር የሚያሳስብ ነው። ስለሆነም ይህንን መፍታትና ፈጣን የሆነ ምላሽና ድጋፍ መስጠት ያስፈልገናል፤ ሀብት በማሰባሰብ ሦስት ጭነት መኪና መድሀኒትና ደራሽ ምግቦችን በመያዝ ከአስተባባሪዎች ውስጥ አንዷ በመሆን ከባህርዳር ከተማ ተነስተው ለወገኖቻቸው መድረስ ችለዋል።
ድጋፉን ደብረ ታቦር ላይ አድርሶ ለመመለስ ያሰቡና የተጓዙ ቢሆንም ደብረታቦር ላይ ሲደርሱ ግን ያለው ሁኔታ እንዲመለሱ አላስቻላቸውም ነበር። ሲገቡ ጣይቱ አዳራሽ ውስጥ የተወያዩና ምስጋና የተለዋወጡ ሲሆን፤ ከዚያ በኋላ ተመልሰው የሚሰሩትን ሥራ ሲያስቡና ከዚህ የባሰውን ቢያዩ ምን ያህል መጓዝ እንደሚችሉ ሲያመዛዝኑ የበለጠው ተጠግቶ ማየቱ እንደሆነ እንግዳችን አመኑበት። በዚህም ለታዳሚው ማሳረጊያውን እንዲህ ሲሉ አደረጉት። ‹‹እነ ጣይቱን የምናስታውሳቸው በመዘከር ብቻ ሳይሆን በተግባርም ነውና ጠጋ ብለን ወታደሩን እንመልከተው፤ ከጎኑ እንዳለን እንዲያስብም እናድርግ›› የሚል ነበር። ሁሉም በሀሳቡ ተስማማ። ጉዞ ተጀመረም። በእርግጥ መጀመሪያ ጀነራሎቹ ጋር ያለውን ሁኔታ ለመጠየቅ ደውለው ነበር። እነርሱ ግን መምጣታቸውን አልተቀበሉትም። ምክንያቱም ጦርነቱ ተፋፍሟል። እነርሱም ቢሆኑ ውጊያ ላይ ናቸው። ነገር ግን ሲስተር ብዙአየሁ አይሆንም መጠጋት አለብን በማለት ሌላውን አበረታቱት። እንዲያውም ሴት ሆና እንሂድ ካለችን ለምን ወደኋላ እንላለን በሚል ሁሉም ለመጓዝ ቆርጦ ተነሳ። ይህ ደግሞ የመሀል ግንባር ክምር ድንጋይ ችግሩንና የደረሰውን ጉዳት በስፋት እንዲያዩ ሆኑ።
ቦታው ላይ ሲደርሱ አሰሳ ላይ ነበሩ። ጁንታው እየተንጠባጠበ የሸሸበት ጊዜ ነው። በዚህም ትኩስ ጉዳቶችን እንዲያዩ ከመሆናቸውም በላይ ከእነርሱ ጋር በእግር እየተጓዙ አሳሾችም ነበሩ። በወቅቱ እንደወታደሩ ጥይት ይዞ በመዋጋት አልተሳተፉም እንጂ ያላዩትና ያልሰሙት ነገር አልነበረም። ለአብነት አልረሳውም የሚሉት የንግድ ባንኩን መዘረፍና መውደም፤ የተለያዩ ትልልቅ የሚባሉ ሆቴሎች መፈራረስና እንስሳት ሳይቀሩ ማለቃቸውን ነው። በጣም የገረመኝ ያሉን ደግሞ የቡድኑ ዝቃጭነት የዶሮ ላባ ከምሮ መሄድ ነበር። ምክንያቱም እንዴት እንደበላው ሳስበው ይዘገንነኛል ይላሉ። ማህበረሰቡን ያሰቃየበት ሁኔታም መቼም የሚረሳ አይደለም ባይናቸው።
ባለሀብቱን በመያዝ ድጋፍ እንዲደረግ በማስተባበርና ግንባር ድረስ በመሄድ የደረሰውን ጉዳት እንዲሁም ያሉበትን ሁኔታ በማየት ነው። በተለይም ጦርነቱ በተጧጧፈበት ወቅት ጋይንት ላይ ተገኝተው ያደረጉት ተግባር ብዙዎችን ያስገረመና ያነጋገረ ነበር። ከዚህ ጋር ተያይዞም ‹‹የእኛ ቡድን እዚያ ሄዶ ችግሮቹንና ሁኔታዎቹን ማየቱ የበለጠ ድጋፍ እንድናደርግና የችግሩን ክብደት እንድንረዳ በሚገባ አድርጎናል። በቋሚነት ሥራዎች መከናወን እንዳለባቸውም የቤት ስራ የሰጠን ነበር። እናም አትምጡ ብንባል በአካል መገኘታችን ብዙ ሥራ እንዳለብን ለእያንዳንዳችን ያስገነዘበ ነበርና ተደስቼበታለሁ። አዳዲስ ንቅናቄዎችንም እንድናደርግና ድጋፋችንን እንድናጠናክር መንገድ የጠረገው ጉዟችን ነው›› ብለውናል።
አሸባሪው ምንም አይነት ጦርነት ያደረገበት ቅጽበት የለም። ጦርነት የራሱ ስታንዳርድና ህግ ያለው ነው። እርሱ ግን ምንም ስብዕና ያልተሞላበትና ከአንድ ወታደር ያማይጠበቅ ተግባር ነው በማህበረሰቡ ላይ የፈጸመው። ለዚህም ማሳያው እንስሳትን በየመንገዱ ላይ ሳይቀር ገሎ ረፍርፎ መሄዱ፤ አገር ሊጠቅሙ የሚችሉ ሀብት ንብረቶችን ማውደሙ ሳያንሰው ሰዎችን በጭካኔ ገድሎ መሄዱ ነው።
ሲስተር ብዙአየሁ በሙያቸው ነርስ በመሆናቸውም በዘመቻው ላይ ከፍተኛ ተሳትፎ አድርገዋል። ከእነዚህመካከል በዋናነት የሚጠቀሰው ሰራዊቱ ተጎድቶ በሚመጣበት ጊዜ የተለየ እንክብካቤ እንዲደረግለት የሰሩት ነው። በባህርዳር ፈለገህይወት ሆስፒታል የተማሪዎችን ማደሪያ ብቸኛ ዋርድ፣ ክሊኒክና ፋርማሲ እንዲሁም የምግብ ማብሰያ እንዲኖረውም አድርገዋል። አምስት የህክምና ቡድን እንዲቋቋም ካደረጉት መካከል ግንባር ቀደም ናቸው። በተመሳሳይ ደብረታቦርም ይህ ችግር ሲፈጠር የህክምና ቁሳቁስ ዋነኛ አስፈላጊ ነገር እንደሆነ አስረድተው እንዲያዝ ያደረጉ ናቸው።
እንደ አመራር ወጣቱ ውትድርናውን እንዲቀላቀል ከማድረግና ከመመዝገብ ባለፈ ማሰልጠን ላይም ትልቅ ተሳትፎ አድርገዋል። በፊት አልመዘገብ ያለው ሁሉ ተመዝግቦ ተጠባባቂ ሀይልም እስከመፍጠር በተደረሰው ሥራ ላይ የእርሳቸው አሻራ ቀላል አልነበረም። ከዚህ በተጓዳኝ ግብዓቶችን በማቅረብም ተሳትፏቸው ላቅ ያለ ነው። በተለይም እርሳቸው የሚመሩትን ተቋም በደረጃ ግብር ከፋይ መዋጮ እንዲያደርጉ ያበረታቱ ናቸው። በዚህ ሳያበቁም የሴቶች ተሳትፎ ይታይ በማለት ‹‹የዘመን ጣይቱ እንሁን›› የሚል ጥምረት ፈጥረው ለህልውና ዘመቻው በአንድ ሳምንት ውስጥ ወደ 2 ነጥብ 7 ሚሊዬን ብር ማሰባሰብ ችለዋል። ይህንንም ለሚመለከተው አካል አድርሰዋል።
የዚህ ጥምረት አላማም አስተማማኝ ደጀን መሆን፣ ለተጎዱትና ለተፈናቀሉ እገዛ ማድረግና ማቋቋም፤ በጋራ ተሰብስቦ ለዘመቻው ድምጽ መሆንና ማጀግን የሚል ነው። እናም ይህንን በማድረግ ላይ በስፋት እየሰሩ ይገኛሉ።
መልዕክት
አሁን እየተደረገ ያለው ዘመቻ የአገርን ክብር፣ ህልውናን መመለስ ነው። ለዚህ ደግሞ ከሁሉም የማህበረሰብ ክፍል ቀድሞ ተጎጅም ሆነ ሁሉን የሚሰሩት ሴቶች ናቸውና በተለይ ቤተሰቡ ላይ በከፍተኛ ሁኔታ መስራት አለባቸው። አገር ወዳድ ትውልድ ፈጥሮ አገር ድል እንድታደርግ ከቤታቸው የጀመረ ስራ ሊሰሩ ይገባል። ማህበረሰቡን ጀግኖ በማጀገን የፊት ደጀንም ሊሆኑ ያስፈልጋል። ጉዳታቸው የሚታከመውም ይህ ሲሆን ብቻ ነው።
አሸባሪው ቡድን ከአባቶቹና ከአያት ቅድመአያቱ የወረሰው ባንዳነትን ነው። እያስቀጠለ ያለውም ይህንን ነው። ወጣቱ ደግሞ ከዚህ የተለየ የውርስ ባለቤት ነውና ከአሸባሪው መለየት አለበት። ከአባቶች የወረሰው ጀግኖ፤ አገር ወዶ ለአገር መሞትና ድልን ማቀናጀት በመሆኑ ይህንን በታሪክ ብቻ እያወሳ መኖር ሳይሆን የተግባር ሰው ሆኖ ውጤቱን ማሳየት ይኖርበታል። አገር የማዳን ግዴታውም የእርሱ ሀላፊነት ነው። ስለሆነም የነገ ታሪክ የሚነገርለት ሰው መሆን ይኖርበታል። የዘመኑ ጀብድ ሰሪ ለመሆን ደግሞ ዛሬ የተሰጠው እድል ትልቅ ነውና ይህንን አጋጣሚ መጠቀም ያስፈልጋል። ባንዳውን ከምድረገጽ የሚያጠፋውም በጀግኖቹ አባቶቹ ታሪክ መሆኑን መረዳት ይኖርበታል።
በእያነ ዳንዱ አገር ጦርነት ሳይኖር ቀርቶ አይደለም በሰላም እየተኖረ ያለው። ጦርነቱ የሚታከምበት ስልታዊ ሙያ እያንዳንዱ በመሰልጠኑ መድሀኒት እንዲያገኝ በመሆኑ ነው። እናም ኢትዮጵያዊያንም የውትድርና ሙያን መሰልጠን፤ መኖርና በዚያ ላይ የውዴታ ግዳጅ ተደርጎ ማገልገል የሚችሉበት አጋጣሚ ሊፈጠር ይገባል። ምንም እንኳን ሁኔታውና ችግሩ አስገድዶት የገባበት ቢሆንም የወጣቱ ርብርብና ለህልውና ዘመቻው መቀላቀል ያለው ተነሳሽነት ይበል የሚያሰኝ ነው። ነገር ግን ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል። አሁን በትንሽ ድል የምንረካበት ጊዜ ላይ አይደለንም። በመሆኑም አላማችን ረጅም ግባችን ሩቅ ነውና ይህንን እያሰብን መንቀሳቀስ አለብን።
ማንኛው አገሬን እወዳለሁ የሚል አካል ተቆጥሮ የተሰጠውን መስራት ብቻ ሳይሆን ያለውን የማህበረሰብ ችግር ተረድቶ ለስኬት ማብቃት ሲችል ነው። አንዳንዴ የሚወጡ መመሪያዎች ከተቋሙ ፍላጎት፣ ከግለሰቦች አተያይና ለእነርሱ በሚመቸው መልኩ እንዲሆን ብቻ ተደርገው ሊወጡ ይችላሉ። የቆለፍነው መመሪያ ደግሞ ራሳችንም ላንረዳበት የምንችልበት አጋጣሚ አለ። ስለሆነም ምንም አይነት ሥራ ለመስራት ከማህበረሰብ መጀመርና ችግሮቹን አውቆ ለመፍትሄ ተዘጋጅቶና ራስን ከማህበረሰቡ ውስጥ አካቶ መስራት ያስፈልጋል።
ይህ ጦርነት ኢትዮጵያንን እንድንጠነክርና ጉልበት እንዲኖረን አድርጎናል። ጉልበተኛ ሰው ደግሞ ከጥበብ ጋር ከተዋሀደ ግቡን በአጭር ቀን ያሳምረዋል። ስለሆነም እድሉን መጠቀምና ለውጤት ማብቃት የውዴታ ግዴታችን እንደሆነ ማሰብ አለብን የመጨረሻው መልዕክታቸው ነው።
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን መስከረም 9/2014