ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በርካታ ፈተናዎችን እየተጋፈጠች ያለችበት ወቅት ላይ ትገኛለች። የእነዚህ ተግዳሮቶች መንስኤ ደግሞ በዋናነት ከውስጥ የመነጨውና በህወሓትና በሱ ጋሻ ጃግሬዎች የሚደረገው ሀገርን የማፍረስ እንቅስቃሴ አንዱ ነው። ከዚህ በላይ ደግሞ ስውር እጃቸውን ዘርግተው ኢትዮጵያን ለማተራመስ የሚፈልጉ ኃይሎች ሴራም ሌላው ፈተና ነው።
ከዚህ አንጻር ከውስጥ በመሆን ኢትዮጵያን ለማፍረስ የተነሳው ህወሓት ካለፉት ሦስት ዓመታት ጀምሮ ኢትዮጵያን የማተራመስ አጀንዳውን በይፋ ተያይዞታል። ይህ ቡድን ላለፈው ግማሽ ምዕተዓመት የሚጠጋ ጊዜ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ባደረገው እንቅስቃሴ ኢትዮጵያ የሚመጥናትን የዕድገት ስፍራ እንዳትይዝ የራሱን ሚና የተጫወተ ቡድን ነው። ቡድኑ መነሻው በኢትዮጵያ የነበረውን ጭቆና በመቃወም ዴሞክራሲያዊ መንግሥትን እመሰርታለሁ የሚል ቢሆንም በዚህ ልክ የተንቀሳቀሰበት አንድም ጊዜ አለመኖሩን የኋላ ታሪኮቹ ያስረዳሉ።
ቡድኑ ገና በትጥቅ ትግል ውስጥ በቆየባቸው 17 ዓመታት እንኳን ዴሞክራሲያዊ ባህርይ ያልነበረው፤ ተቀናቃኞቹን ሁሉ በኃይልና በጠብመንጃ አፈሙዝ እያስገደደና ብዙዎችንም እያጠፋ የመጣ ሲሆን ከዚያ በኋላም በሥልጣን ላይ በቆየባቸው 27 ዓመታትም ኢትዮጵያን የመከፋፈልና የማዳከም አጀንዳ ቀርጾ ሲሰራ ኖሮ በመጨረሻም በሕዝብ ግፊት ከሥልጣን የተነሳ ነው።
ይህ ቡድን ገና ከመነሻው ወደሥልጣን ሲመጣ እነአሜሪካና አንዳንድ አውሮፓ ሀገራት በይፋም ሆነ በድብቅ ሲደግፉት ቆይተዋል። ከዚያ በኋላም በሥልጣን ላይ በቆየባቸው ዓመታት ቡድኑ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ እያደረሰ የነበረውን ግፍና መከራ አይቶ እንዳላየ በማለፍ ለቡድኑ ያላቸውን አጋርነት አሳይተዋል። ቡድኑ ግን በሕዝብ ግፊት ወርዶ አዲስ የለውጥ ኃይል ሲመጣ ከዚህ በተቃራኒ በመቆም የራሱን ጥቅም ለማስከበር ሲል ዳግም ኢትዮጵያን አደጋ ላይ የሚጥል ተግባር ውስጥ ሊዘፈቅ ችሏል።
አሸባሪው ህወሓት ላለፉት ሦስት ዓመታት በአንድ በኩል ገና ከመጀመሪያው የለውጥ ኃይሉን በመገልበጥ ዳግም ሥልጣን ለመቆናጠጥ ጥረት ሲያደርግ የቆየ ሲሆን ይህ አልሳካ ሲለውም ወደመቀሌ በመግባትና በመመሸግ ሀገርን የማፍረስ ሴራውን በተጠናከረ ሁኔታ ሲሰራ ቆይቷል። በነዚህ ሦስት ዓመታትም ሙሉ ትኩረቱን ሀገርን የማፍረስ ሥራ ላይ በማድረግ ጦር ሲያዘጋጅና ሲያስታጥቅ ቆይቶ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም የሰሜን እዝን በመውረር ሀገርን የማፍረስ ተልዕኮውን በይፋ የጀመረበት ጊዜ መሆኑ ይታወቃል።
ይሁን እንጂ ቡድኑ ለዘመናት በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ሲያደርግ የቆየው ግፍና መከራ ዳግም እንዳይመጣ ኢትዮጵያውያን በአንድነት በመቆም ቡድኑን ለመፋለም ጊዜ አልፈጀባቸውም። በዚህ የተነሳ ቡድኑ ለዓመታት ሲዘጋጅበት የቆየውን የጦርነት ድግስ በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ መና በማስቀረት የማይታመን ድል ሊቀዳጁ ችለዋል። በዚህ ደግሞ የአሸባሪው ህወሓት አባላት ብቻ ሳይሆኑ ከኋላ ሆነው አይዞህ ሲሉ የነበሩት የውጭ ኃይሎችም ተደናግጠዋል።
ከዚያ በኋላ ግን ቡድኑ የኢትዮጵያ ጠላት በሆኑ የውጭ ኃይሎች ትብብር ጭምር ዳግም ኢትዮጵያን ለማፍረስ በአማራና በአፋር ሕዝብ ላይ ያደረሰው ጉዳት ቀላል አይደለም። በዚህ ጦርነትም በርካታ ዘግናኝና አረመኔያዊ ተግባራትን ፈጽሟል። ሲቪል ዜጎችን አርዷል፤ እንስሳትን ገድሏል፤ አዝርእትን አውድሟል፤ ንብረት ዘርፏል፤ በርካታ ዜጎችም ከቀየአቸው እንዲፈናቀሉ አድርጓል።
ይህንን ቡድን ለየት የሚያደርገው ሌላው ጉዳይ ደግሞ እታገልለታለሁ የሚለውና በችግር ጊዜ ጉያው እየገባ የሚደበቅበትን ትግራይ ሕዝብም ላይ የጭካኔ በትሩን ማሳረፉ ነው። በዚህ መሰረት ለትግራይ ሕዝብ የሚደርሰውን የእርዳታ ቁሳቁስ በአደባባይ ዘርፏል፤ ከዚህም በላይ የእርዳታ ቁሳቁስ ጭነው የሚሄዱ ተሽከርካሪዎች ዳግም ተመልሰው ሌላ የእርዳታ ቁሳቁስ እንዳይጭኑ በሄዱበት አስቀርቷል። ከዚህም በላይ ትግራይን ከተቆጣጠረ በኋላ እሱ ለጀመረው ጦርነት ልጃቸውን የማይገብሩ የቤተሰብ አባላት እርዳታ እንዳይደርሳቸው ከልክሏል፤ ሰላማዊ ዜጎችንም ከፌዴራል መንግሥት ጋር አብራችኋል በሚል ገድሏል፤ ብዙዎችንም አፍኗል።
በአጠቃላይ ይህ ቡድን የአሸባሪነት ተግባሩን በዚህ ልክ አጠናክሮ መቀጠሉ የአደባባይ ምስጢር ሆኖ ሳለ አሜሪካና በእሷ የሚዘወሩ ሌሎች አገራትና ዓለም አቀፍ ግብረሰናይ ድርጅቶችና ተቋማት ግን የዚህን ቡድን እኩይ ተግባራት ከማየት ይልቅ የውሸት ምክንያት ፈጥሮ መንግሥትን ለመክሰስ ጊዜአቸውን ሲያጠፉ መመልከት አዲስ አልነበረም። በዚህም መሰረት ሰሞኑን የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን በትግራይ ጦርነት ተሳታፊዎች ላይ ያነጣጠረ ያሉትን የማዕቀብ ትዕዛዝ ይፋ አድርገዋል።
ማዕቀቡም ሆነ ጫናው በተለይም በዚህ ወቅት መደረጉ እውነትም ለሰላም ታስቦ ሳይሆን ኢትዮጵያ በሰፊ የሕዝብ ምርጫ የተመረጠ መንግሥት ለመመስረት የምታደርገውን እንቅስቃሴ ለማደናቀፍ ታስቦ እንደሆነ ይታወቃል። ይሁንና በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ተግዳሮቶችን ለማለፍ በርካታ መንገዶችን ተጉዛለች። ከነዚህም መካከል አንዱ የአሸባሪው ህወሓት ኃይሎች እየተካሄደ ባለው ጦርነት ወደመወገዱ እየተቃረቡ መሆኑ ነው። ከዚህም ሌላ በመላ ኢትዮጵያውያን ተሳትፎ የተመረጠው መንግሥት ሥልጣን ሊይዝ ከጫፍ መድረሱ በዋናነት ይጠቀሳሉ። እነዚህ ጉዳዮች ደግሞ የኢትዮጵያን ችግሮች ሙሉ ለሙሉ በመፍታት ኢትዮጵያን ወደብልጽግና ለማሻገር የተያዘውን ዓላማ የሚያሳካ ነው።
በመሆኑም አሁን የተጀመረው ዘመቻ ከዚህ በተቃራኒ የቆመ መሆኑ ኢትዮጵያን የማዳከም አንዱ መንገድ ነው። ስለዚህ አሜሪካም ሆነች ሌሎች የምዕራባውያን ሀገራት በትክክል ስለኢትዮጵያ የሚቆረቆሩ ከሆነ ኢትዮጵያን በማገዝ የተረጋጋችና የበለጸገች አገር የመፍጠሪያው ጊዜ አሁን መሆኑን ሊረዱና ሊደግፉ ይገባል።
አዲስ ዘመን መስከረም 9/2014