በቶኪዮ 2020 ፓራሊምፒክ ውድድር ኢትዮጵያን ወክላ የተሳተፈችው አትሌት ትዕግስት ገዛኸኝ በኢትዮጵያ ፓራሊምፒክ ታሪክ ከፍተኛ የሆነ ሽልማት አግኝታለች። በቅርቡ በተጠናቀቀው የቶኪዮ ፓራሊምፒክ ውድድር በ1500 ሜትር T-13 አይነ ስውራን ጭላንጭል ተፎካክራ በውድድሩ ታሪክ የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳሊያ ያስመዘገበችው አትሌት ትዕግስት ሁለት ነጥብ ስምንት ሚሊየን ብርና አርባ ግራም የወርቅ ኒሻን ሽልማት ከመንግስት ተበርክቶላታል፡፡ የኢትዮጵያ ፓራሊምፒክ አትሌቶች ይህን ያህል ከፍተኛ ሽልማት ሲበረከትላቸውም በታሪክ ትልቁና የመጀመሪያው ሆኗል፡፡
በቶኪዮ 2020 ፓራሊምፒክ ጨዋታ የተሳተፉ የልዑካን ቡድን አባላት የእውቅናና የማበረታቻ ሽልማት መርሃ ግብር ከትናንት በስቲያ ምሽት በሸራተን አዲስ ሆቴል ሲካሄድ፣ አትሌት ትዕግስት ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች በተገኙበት ሽልማቱን ተረክባለች፡፡ አትሌት ትዕግስት ገዛኸኝ 04:23:24 በሆነ ሰዓት ውድድሯን በማጠናቀቅ ለኢትዮጵያ የወርቅ ሜዳሊያ በማስመዝገብ በፖራሊምፒክ ጨዋታ ታሪክ አዲስ ምዕራፍ መክፈቷ ከተበረከተላት ሽልማት አኳያ በርካታ አካል ጉዳተኞችና በስፖርቱ ውስጥ ነጥረው ለመውጣት ጥረት እያደረጉ በሚገኙ የፓራሊምፒክ ተወዳዳሪዎች ዘንድ ከፍተኛ ተነሳሽነትን ሊፈጥር እንደሚችል ታምኖበታል፡፡
አትሌት ትዕግስት በፓራሊምፒክ ውድድሩ ይህን ታላቅ ታሪክ እንድትሰራ በማድረግ ከፍተኛ ሚና የነበራቸው የቡድኑ ዋና አሠልጣኝ ንጋቱ ኃይለማርያም የአራት መቶ ሺ ብር ሽልማት ሲበረከትላቸው በውድድሩ የተሳተፉ አትሌቶችም የተለያየ መጠን ያለው የገንዘብ ሽልማት አግኝተዋል፡፡ በዚህም በ1500 ሜትር እጅ ጉዳት T-46 ውድድር አምስተኛ ደረጃን በመያዝ የዲፕሎማ ውጤት ያስመዘገበው አትሌት ገመቹ አመኑ የሁለት መቶ ሺ ብር ተሸላሚ ሆኗል። በተመሳሳይ በ1500 ሜትር አይነስውራን ጭላንጭል T-13 ውድድር ሰባተኛ ደረጃን በመያዝ ያጠናቀቀው አትሌት ታምሩ ከፍያለው የመቶ ሃምሳ ሺ ብር ተሸላሚ ሆኗል፡፡ የቡድኑ ሀኪምም የመቶ ሺ ብር ሽልማት አግኝቷል፡፡ በቶኪዮ 2020 ፓራሊምፒክ ጨዋታ ኢትዮጵያ በሦስት አትሌቶች የተወከለች ሲሆን አንድ የወርቅና ሁለት የዲፕሎማ ደረጃዎችን በማግኘት ከዓለም ሃምሳ ዘጠነኛ ከአፍሪካ ደግሞ ስድስተኛ ደረጃ በመያዝ ማጠናቀቋ ይታወቃል፡፡
በሽልማትና እውቅና መርሃግብሩ ላይ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶክተር ሂሩት ካሳውን ጨምሮ የኢፌዲሪ ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ኤሊያስ ሽኩር ፣ ምክትል ኮሚሽነር አቶ ዱቤ ጅሎ ፣የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሀብታሙ ሲሳይ ፣ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ፣የክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነሮች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል ።
ከሽልማቱ መርሐ ግብር አስቀድሞ በሸራተን አዲስ ሆቴል ታዋቂ አትሌቶች እና ታዋቂ የእግር ኳስ ተጫዋቾች እንዲሁም አሰልጣኞች በይፋ ተሰብስበው ‹‹የነጩ ፖስታ ጎርፍ ወደ ነጩ ቤተ መንግስት›› በሚል የሚደረገውን ዘመቻ ተቀላቅለዋል፡፡ የስፖርት ኮሚሽነሩ አቶ ኤሊያስ ሽኩር እንደተናገሩትም፣ ኢትዮጵያ የያዘችውን እውነታ ለዓለም የማስረዳትና የአሸባሪውን ህወሓት የጥፋት ድርጊት ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ማሳየትን አላማ ያደረገው ‹‹የነጩ ፖስታ ጎርፍ ወደ ነጩ ቤተ መንግስት›› የፊርማ ማሰባሰብ ንቅናቄን አስመልክቶ ከስፖርቱ ማህበረሰብ ጋር ይመክራሉ። ዘመቻው ይፋ ሲደረግ ሚኒስትሮች፣ የተለያዩ ታዋቂ
ግለሰቦችና በርካታ ወጣቶችም ተገኝተዋል። በኢትዮጵያ ላይ በተሳሳተ መልኩ የሚነዛው አሉባልታ ከእውነት የራቀ መሆኑን ለዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ ለማሳየትም ዘመቻው እንደሚካሄድ ተነግሯል፡፡ በዚሁ ንቅናቄ ኢትዮጵያ የያዘችውን እውነታ ለአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን እንዲደርስ ይሰራል ተብሏል። ከአምስት ሚሊየን በላይ ወጣቶች የሚሳተፉበት ይህ ዘመቻ እስከ መስከረም 15 ቀን 2014 ዓ.ም የሚካሄድ መሆኑ ታውቋል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን መስከረም 8/2014