ፍርድ ቤቱ ተጠርጣሪዎች በማረሚያ ቤት ስልክና ኮምፒዩተር ይሟላልን አቤቱታም ውድቅ አድርጓል፡፡
የባሕር ዳር እና አካባቢው ከፍተኛ ፍርድ ቤት በአቶ በረከት ስምዖንና አቶ ታደሰ ካሳ ጉዳይ ላይ የ14 ቀን ተጨማሪ የጊዜ ቀጠሮ ፈቀደ፡፡ ዐቃቤ ሕግ ከዚህ በፊት በተሰጡት የጊዜ ቀጠሮዎች ምርመራውን ማጠናቀቅ አለመቻሉንና የዐቃቤ ሕግ ምስክሮች በውጭ ሀገር ለሕክምና እንደሄዱ አለመመለሳቸው ገልጾ ነበር፡፡ በተጨማሪ የኦዲት ሥራዎች አለመጠናቀቃቸው እና የባለሙያ ክትትል የሚያስፈልጋቸው መሆኑን በመጠቆም የ14 ቀን ተጨማሪ የጊዜ ቀጠሮ ጠይቆ ነበር፡፡
አቶ በረከት ሥምዖን እና አቶ ታደሰ ካሳ በበኩላቸው የምርመራ ሂደቱ በይፋ እንደተጠናቀቀ መገለጹን፣ የማረፊያ ቤት ቆይታቸውም እየተራዘመ መሆኑን እና ሌሎች ምክንያቶችን በመዘርዘር የክርክር ሂደቱ እንዲጀመር እና ተጨማሪ የጊዜ ቀጠሮ መጠየቁ አላስፈላጊ መሆኑን ለፍርድ ቤቱ አቅርበው ነበር፡፡
በማረሚያ ቤት ቆይታቸው ጉዳያቸውን ለመከታተል እና መረጃ ለመሰብሰብ የግል የስልክ፣ ኮምፒውተር እና ኢንተርኔት አገልግሎት እንዲሟላላቸውም ጠይቀው ነበር፡፡
ፍርድ ቤቱ ዐቃቤ ሕግ ያቀረባቸውን የምርመራ አለመጠናቀቅ እና የምስክሮች አለመሟላት ከግምት ውስጥ በማስገባት የ14 ቀናት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ፈቅዷል፤ በዚህ መሠረት መጋቢት 2 ቀን 2011 ዓ.ም ምርመራ ተጠናቅቆ እንዲቀርብ ፍርድ ቤቱ ቀን ተቆርጧል፡፡
አብመድ እንደዘገበው ፍርድ ቤቱ የአቶ በረከት ስምዖንና የአቶ ታደሰ ካሳን በማረሚያ ቤት ስልክና ኮምፒዩተር ይሟላልን አቤቱታም ውድቅ አድርጓል፡፡
እንደማንኛውም በሕግ ጥላ ሥር ያለ ሰው በማረሚያ ቤቱ ውስጥ ያሉ ‹ዴስክ ቶፕ› ኮምፒዩተሮች እና መደበኛ ስልኮችን እንዲጠቀሙ አዝዟል፡፡ ማረሚያ ቤቱ ከከተማ የወጣ በመሆኑ የኢንተርኔት አገልግሎት እንደሌለው የማረሚያ ቤት ተጠሪው ለፍርድ ቤቱ ያቀረቡትን ሪፖርት ችሎቱ ለአቤቱታ አቅራቢዎች ገልጿል፡፡
አቶ በረከት እና አቶ ታደሰ የመገናኛ ብዙኃን በፍረድ ቤት ጉዳያቸው ላይ ቁንጽል መረጃ እየለቀቁ መሆኑንም ለችሎቱ በአቤቱታ መልኩ አቅርበዋል፡፡ ሙሉ መረጃዎችን ብዙኃን መገናኛዎች ለሕዝቡ እንዲያደርሱም ጠይቀዋል፡፡ ለአብነትም የአማራ ብዙኃን መገናኛ ደርጅት አንዱ መሆኑን አቶ ታደሰ በግልጽ ጠቅሰዋል፡፡
ፍርድ ቤቱ በተጠቀሰው መገናኛ ብዙኃን የተነሱ ጉዳዮች በችሎቱ የተነሱ መሆናቸውን አስታውሶ የተዛባ መረጃ የሚያደርሱ የመገናኛ ብዙኃን ካሉም ድርጊቱ ሕገ-ወጥ መሆኑን አስታውቋል፡፡ ለሕዝቡ ቁንጽል ያልሆነና ያልተዛባ መረጃ እንዲያደርሱም አሳስቧል፡፡