ከል ለኀዘን መገለጫነት የሚለበስ ጥቁር ልብስ ነው። በአብዛኞቹ የሀገራችን ባህሎች ለሞተ የቅርብ ዘመድ ወይንም ወዳጅ ከል ይለበሳል። ኀዘኑ በበረታባቸው ወራት ሙሉ ጥቁር ልብስ የሚለበስ ሲሆን እምባውና ምሬቱ እየቀዘቀዘና ቀን እየገፋ በሄደ ቁጥር ግን አለባበሱም ከሙሉ ከል ወደ ግማሽ፤ እያደርም ሙሉ ለሙሉ በነጭ ልብስ እየተተካ ኀዘንተኛው የኀዘን ፍራሹን ጠቅልሎ በማንሳት ወደ ወትሮው የሕይወት ዑደቱ ይመለሳል። በአንዳንድ ባህሎቻችንም ኀዘኑ ጠንከር ሲል ማቅ ይታከልበታል።ማቅ አብዛኛውን ጊዜ ከጥቁር በግ ጸጉር የሚሰራ ባና ወይንም ዝተት በመባል ይታወቃል።ተዘውትሮ ቢለበስም የተለምዶ ጉዳይ ሆኖ ይበልጥ ተምሳሌነቱ የሚጎላው በኀዘን ገላጭነቱ ነው፡፡
ይህ የሰው ወግና ባህል እንጂ ሀገር በሚገጥማት የፈተና ጊዜያት ሁሉ ተስፋዋ እንደተሟጠጠ በማሰብ እንደ ዜጎቿ ከል ለብሳ እያነባች ፀጉሯን በመንጨት ሙሾ አታወርድም፡፡ እርግጥ ነው የልጆቿ መከራ መከራዋ፣ ኀዘናቸውም ኀዘኗ መሆኑ ለማንም ዜጋ ይጠፋዋል ተብሎ አይገመትም፡፡ ደራስያንና የሌሎች የጥበብ ዘርፍ ባለሙያዎች ሀገርን በሰውኛ ዘይቤ እየወከሉ የመከራዋን ጫና “ማቅ በማልበስ” ሲገልጹ መኖራቸውም እውነት ነው፡፡
ከአሁን ቀደም ደጋግሜ ለማስታወስ እንደ ሞከርኩት በዘመነ ተማሪነቴ ከምናከብራቸው የኮሌጅ መምህራኖቻችን መካከል አንዱ የነበሩት ዶ/ር ኃይሉ አርአያ በሰውኛ የዘይቤ ስልት ኢትዮጵያን መከራ በወደቀባት አንዲት ምስኪን ሴት በመወከል ማቅ የለበሰች በማስመሰል የገለጹበት ግጥማቸው ዛሬም ድረስ ከብዙ ተማሪዎቻቸውና ዘመነ አቻዎቻቸው ትውስታ የደበዘዘ አይመስልም፡፡ የገጣሚው ዋና ዓላማ ዘመናቸውን ለመግለጽ እንደሆነ ይገባኛል፡፡ ዘለግ ካለውና በዘይቤዎች ከተኳለው ግጥም ውስጥ የሚከተሉትን ጥቂት ስንኞች ላስታውስ፡፡ አንዳንድ ቃላት አፈንግጠውብኝ ከሆነም የዘመኑ ርዝመት ትውስታዬን አደብዝዞት ሊሆን ስለሚችል ይቅርታ እጠይቃለሁ፡፡ የሙሉው ሃሳብ የይዘት ጭብጥ የሚከተለውን ይመስላል፡፡
እኔስ መስሎኝ ነበር ዘመድ የሞተባት፣
የእናት ሞት የአባት ሞት የልጅ ሞት ያጠቃት፣
ፊቷን ያጠቆራት ከል ያጎናጸፋት፣
ለካ እሷስ ኖራለች ዘመን የሞተባት፡፡
የእኒህ ጎምቱ መምህራችን ብዕር ኪነ ጥበባዊ ብርታቱና የሰባ መልዕክቱ እንደተጠበቀ መሆኑ ባይካድም ሀገር በተለያዩ ዘመናት ውስጥ ወቅት ወለድ ፈተናዎችና ተግዳሮቶች ከፊቷ ቢጋረጡም እንደ ልጆቿ ወግና ባህል “ፀጉሯን እየነጨችና ክል እየተጎናጸፈች” ተስፋዋ መንምኖ እዬዬ በማለት “ፍራሽ ጎዝጉዛ ኀዘን አትቀመጥም የምትቀመጥም አይደለችም፡፡” ይልቁንስ በቆራጥና ጀግኖች ልጆቿ ያላሰለሰ ተጋድሎና መስዋዕትነት ፀንታ በመቆም አሸናፊነቷን ታውጃለች እንጂ ገበርኩ ብላ እጅ የሰጠችባቸው ዘመናት እንደሌሉ ረጅም ታሪኳ ምስክር ነው፡፡ አንድ ሦስቱን የቅርብ ዘመናት ታሪኳን እናስታውስ፡፡
አንድ፡-
የኢጣሊያ ፋሽስት ወራሪ ሠራዊት ሀገራችንን በግፍ በወረረባቸው ዓመታት (ከ1928 – 1933 ዓ.ም) ብዙ እልቂትና ጥፋት ቢፈጸምም በአንጻሩም በቁርጥ ቀን ልጆቿ ጀግንነትና መስዋዕትነት የተመዘገቡትን ገድሎች ብዙው ዜጋ በሚገባ ስለሚረዳው ጠለቅ ያለ ትንተና ውስጥ አልገባም፡፡ ውቂያኖስ አቋርጦ ባህር ቀዝፎ ሀገሪቱን የወረረው ሠራዊት የግፍ ድርጊት አልበቃ ብሎ በውስጥ ባንዳዎችና “ሆድ አደሮች”፤ በተለይም ዛሬ “ኢትዮጵያን ለማፈራረስ በመሃላ ጭምር ቆርጦ የነተሳውን” የሽብርተኛ ቡድን ይመሩ የነበሩት ግለሰቦች አያት ቅድመ አያቶች እንደምን ከጠላት ጋር አብረው ሀገሪቱን ይወጉ እንደነበር የጥቁር ታሪካቸው ጠባሳ በጥቁር የታሪካችን መዝገብ ውስጥ ተሰንዶ ስለሚገኝ በጥልቀት ለመረዳት የፈለገ ዜጋ መዛግብቱን እንዲፈትሽ አስታውሳለሁ፡፡ የዛሬዎቹ ሀገር እናፈርሳለን ባዮች የእነዚያ አባቶቻቸው ውጤት ስለሆኑ “የማን ዘር ጎመንዘር” ብለን እንድንገረም ግድ ይለናል፡፡
በእነዚህ የተጋድሎ ዓመታት ውስጥ በስደት ላይ የነበሩት ንጉሠ ነገሥቱ ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በወቅቱ የመንግሥታት ማኅበር ጉባዔ ላይ ተገኝተው የፋሽስት ኢጣሊያን ግፍ ለማስረዳት በሞከሩባቸው ጊዜያት ብዙዎቹ “ወዳጆች ነን!” ሲሉ የኖሩ መንግሥታት ሀገሬን ፊት ነስተዋት ከጠላት ጋር ተባብረው እንደነበር አይዘነጋም፡፡ በዚህ ወቅት “የብጫና ነጭ ቀለማት ህዝቦች” ታሪካዊ ልዩነታቸውን ወደ ጎን ትተው በማስወገድ “ብጫዋ ጃፓንና ነጯ ኢጣሊያ በጥቁሯ ኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ የጋራ አቋም በመያዝ ተደጋግፈው እንደነበር አይዘነጋም፡፡ ኦስትሪያና ሀንጋሪም የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ክደው የጣሊያንን ወረራ በማጽደቅ ሀገሬን ሽምጥጥ አድርገው ክደው ነበር፡፡ የኋላ ኋላ ማጣፊያው ሲያጥር የጠቆረ ፊቷን መልሳ “በቃል ኪዳን ስምምነት ኢትዮጵያን ካልረዳሁ” ማለቱ እንደተጠበቀ ሆኖ በመጀመሪያው የወረራው ዓመታት ግድም “የእንግሊዝ መንግሥት የኢጣሊያንን ሃሳብ ለማጽደቅ” ዳር ዳር ማለቱ ይታወሳል።
ይህንኑ ገዳይ በተመለከተ ንጉሡ በግለ ታሪክ መጽሐፋቸው ሁኔታውን የገለጹት እንዲህ በማለት ነበር፡፡ “ምንም አንኳን የእንግሊዝ መንግሥት የኢጣሊያን ይዞታ ለማወቅ በመሰናዳቱ ብዙ የመንፈስ ኀዘን ቢሰማንም፤ ከእንግሊዞች አንዳንዶቹ በሁኔታችን ኀዘን እንደሚሰማቸው ስለምናውቅ እንጽናና ነበር” ብለዋል፡፡
በዚህን መሰሉ ወጀብና አውሎ ነፋስ ውስጥ እስከ መጨረሻው ድረስ የኢጣሊያን ወረራ አውግዘው በአቋማቸው ጸንተው ከቆሙት ሀገራት መካከል ሜክሲኮ፣ ሶቭዬት ህብረትና ቻይና በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ።ውለታ የዋለን ለማመስገን የዓመታት ርዝመት ገደብ እንደማይሆን የታወቀ ነው፡፡ በዚሁ ነባር መርህ መሠረት የኢትዮጵያ ጥንታዊ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር የኢጣሊያ ወራሪ ሠራዊት የሽንፈት ጽዋ ተጎንጭቶ ድል የተቀዳጀንበት 75ኛው የአልማዝ ኢዮቤልዩ በዓል በተከበረበት በ2008 ዓ.ም ለእነዚህ የሀገራችን የክፉ ቀን ወዳጅ ሀገራት በቀድሞ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት በክቡር ግርማ ወ/ጊዮርጊስ አማካይነት ለመንግሥታቱ ምሥጋና የተላለፈው የወርቅ ሜዳሊያ በአምባሳደሮቻቸው አንገት ላይ በማጥለቅና የአድናቆት መግለጫ ዲፕሎማ በመሸለም ጭምር ነበር፡፡ የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ይህንን ታላቅ ክብረበዓል በማስተባበርና በማስፈጸም የዜግነት ድርሻውን በመወጣቱ ደስታው እጥፍ ድርብ ነው፡፡
በዚያ አምስት የወረራ ዓመታት ውስጥ ኢትዮጵያ በፋሽስቶቹ እኩይ ተግባራት፣ በውስጥ ባንዳዎች የተቀናጀ ሴራና ወዳጅ ሲባሉ በኖሩ መንግሥታት እንኳን ሳይቀር ክህደት ቢፈጸምባትም ክብር ለጀግኖቹ ልጆቿ ይሁንና ተስፋ ቆርጣ የኀዘን ማቅ አልለበሰችም።በሽንፈት ገብራም ለወራሪው ኃይል እጇን አልሰጠችም፡፡
ሁለት፡-
ወታደራዊው ደርግ ገና ሥልጣን እንደያዘ ሰሞን የጠላትነት ሴራ መውጠንጠን የተጀመረው ከሶማሊያ መንግሥት በኩል ነበር፡፡ የወቅቱ የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት የነበሩት ዚያድ ባሬ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ሊቀመንበር ስለነበሩ የፖለቲካ ሜዳው ለተስፋፊዋ ጎረቤት ሀገር የልብ ልብ ሰጥቷት ነበር።በዚሁ ወቅት የመገንጠል ዓላማ ያቀነቅኑ ለነበረው አዲስ ውልድ ለህወሓትና ብጤዎቹ በሀገሪቱ ላይ የተቃጣው ሴራ የሠርግና የምላሽ ያህል አስፈንድቋቸው እንደነበር አይዘነጋም፡፡ ጀብሃና ሻዕብያም “ወጥር” ብለው ሀገራዊ ጡዘቱን ያከረሩበት ወቅት ክፉ ነበር። አብዛኞቹ ምእራባዊና ምዕራባዊያን ሀገራትም እንደለመዱት የአብዮት ቋያ እየተቀጣጠለ ፋታ በነሳት ሀገሬ ላይ ፊታቸውን አዙረው “የት አውቀንሽ!” ያሉባቸው ዓመታት ነበሩ፡፡ ውስጥ ለውስጥ ሲብላላ ሁለት ዓመታትን ያህል ያስቆጠረውና በሀገሪቱ ላይ ሲሸረብ የኖረው ሴራ ድንገት ገንፍሎ ኢትዮጵያን ለመዋጥ ርብርቡ የተጀመረው ሶማሊያ በ1969 ዓ.ም የከፈተችው የተስፋፊነት ጦርነት ገሃድ ከተገለጠ በኋላ ነበር፡፡
በዚሁ ክፉ ወቅት አሜሪካ ከሱማሊያ ወራሪዎች ጎን ቆማ ሀገሬ ቀደም ሲል የገዛችውን የጦር መሳሪያዎች ክዳ መከልከሏና ዳግም መሳሪያ እንዳትገዛም በሯን ጥርቅም አድርጋ መቸንከሯ ምን ያህል ዋጋ እንዳስከፈለን ያልመሸበት ታሪካችን ምስክር ነው፡፡ በዚህን መሰሉ ተስፋ ባጣ ምድረ በዳ ለቆመችው ሀገሬ ፈጥነው በመድረስ የታደጉን (ምንም እንኳን ርእዮተ ዓለማዊው የፖለቲካ ቅርርብ ሳይዘነጋና መገለባበጥ ቢታይበትም) ሲቪዬት ህብረትና ቻይና ነበሩ፡፡ ኩባና የመንም የደም ዋጋ ከፍለዋል፡፡ እንጂማ አሜሪካና “ቡና አጣጮቿ ምዕራባዊያን ሀገራት” በግልጽና በይፋ ክህደት ፈጽመውብን ስለነበር ያለወዳጅ ሀገራት ትብብር መከራው እንደምን ይገፋ ነበር?
ወጀቡ ያየለ ቢመስልም “ይህ ነው ምኞቴ እኔስ በሕይወቴ፤ ከራሴ በፊት ለኢትዮጵያ እናቴ” በማለት የተመመው ጀግናው የሀገር ሠራዊት በመስዋዕትነት ወድቆ እየጣለ ወራሪውን የሶማሊያ ጦር ብቻ ሳይሆን ፊት የነሱን መንግሥታት ሳይቀሩ አንገታቸውን እንዲደፉ ያስገደዳቸው ድል መመዝገቡ አይዘነጋም።ምክንያቱም ሀገሬ የኀዘን ማቅ ለብሳ እንድትቆዝም ጀግኖቹ ልጆቿ ክንዳቸውን አልተንተራሱምና፡፡
ሦስት፡-
ዛሬም ሀገሬ “ከል ለብሳ እና የኀዘን ፍራሽ ላይ ተቀምጣ ሙሾ እንድታሞሽ” የሚመኙላት ታሪካዊ ጠላቶቿ ቁጥራቸው ቀላል የሚባል እንዳልሆነ ይገባናል፡፡ አሸባሪው የትህነግ ቡድን በጠራራ ፀሐይ የፈጸማቸውና እየፈጸማቸው ያሉት የግፍ ዓይነቶችን እየተመለከቱ ዓይናቸውን በመጋረድ ክህደት እየፈጸሙ መሆናቸው የአደባባይ ምሥጢር ነው፡፡
ጀግናው የመከላከያ ሠራዊታችን የተካደበትና የተደፈረበት አሳፋሪ ተግባር ለእነርሱ ትርጉም አልባ ነው። የራሳቸው ጉዳይ ቢሆን ኖሮ የዓለምን ጆሮ እንደምን እንደሚያደነቁሩት አይጠፋንም፡፡ የንጹሐን ዜጎቻችን መጨፍጨፍም ስሜታቸውን አላስቆጣም።
የአማራና የአፋር ክልሎቻቸን በዚህ አሸባሪ ቡድን መወረር ደንታ አልሰጣቸውም፡፡ ለምን ቢሉ እነርሱ በዘመናት ውስጥ ሲመኙ የኖሩት ኢትዮጵያ የኀዘን ከል ለብሳ ስትፈራርስ በመጎምጀት እያስተዋሉ “ነፍስ ይማር!” ለማለት አቆብቁበው ስለኖሩ – ምላሹ ነው፡፡
የዐባይ ውሃ ተጋሪዎቻችን በቅንዓት የቀላ ዓይን፣ የአንዳንድ ምዕራባውያን ሀገራት የተደጋገመ ክህደት ዋና ዓላማ ኢትዮጵያ ደካማ ሆና እንድትቀጥል ከመሻት የመነጨ ነው፡፡ ለዚህም ነው ለሽንፈታችን “ነጋ ጠባ የሚጸልዩት”፣ ኢትዮጵያ ከል ለብሳ ለማየትም በሩቁና በቅርብ ሆነው እያጮለቁ በማየት የመፈራረሷን ሟርት የሚደግሙት፡፡ በእርዳታ ስም ዱቄት ካላቀበልን የሚሉት አንዳንድ ውላጆቻቸውም “መጀመሪያ የእርዳታ ዱቄታችሁን በወንፊት እናጥራው” ተብለው ሲጠየቁ እሪታ የሚያሰሙት “ምን ያለበት ዝላይ አይችልም” ሆኖባቸው ነው፡፡
ዛሬ ሀገሬ ያለችበት ሁኔታ የተወሳሰበ ስለመሆኑ አልጠፋንም፡፡ የአሸባሪውን ቡድንና የሚዜዎቹን የተስፋ መቁረጥ የጥፋት ዜና መዋዕልም ዕለት በዕለት እየተከታተልን ነው፡፡ በተለይም ትህነግ ይሉት ጉድ ጡጦ አጉርሶና በአንቀልባ አሳዝሎ ገና ከጠዋቱ ባህር ማዶ አሻግሮ ለዓላማ የፈለፈላቸው ጀሌዎቹ ፓስፖርት በገፍ ባደሏቸው ሀገራት አደባባይ ላይ እየተንከባለሉ እንደ ወደል አህያ ማናፋታቸውንም በሚገባ እየተከታተልን ነው። ቢሆንም ግን እነርሱም ሆኑ “አለሁላችሁ” ባዮቹ ታሪካዊ ጠላቶቻችን እንደሚመኙት ኢትዮጵያ በመከራ ትፈተን ካልሆነ በስተቀር የኀዘን ከል ለብሳ ተገዳዳሪዎቿ እንዲፈነጥዙት አይሳካላቸውም፤ በኀዘን ፍራሽ ላይ ተቀምጣም “እግዜር ያጠናሽ!” እየተባለች በፍጹም መሳለቂያ አትሆንም፡፡
በእንግድነት የተቀበልነው ይህ የ2014 ዓ.ም የመስከረም ወር አዲስነቱ የዘመን መሸጋገሪያ በመሆኑ ብቻ ሳይሆን የፈተናዎቻችን ማብቂያና መደምደሚያ ጭምር እንደሚሆን ተስፋችን ነው፡፡ ነገ ጠዋት አዲስ መንግሥት ከአዲስ የድል ብሥራት ጋር ልንመሠርት ቀጠሮ ተይዟል፡፡ ጠላቶቻችን ይህንን መራራ እውነት ቢመራቸውም ሊቀበሉት ግድ ነው፡፡ የህዳሴ ግድባችን የሚያመነጨው የብርሃን ፀዳልም ለነገው ብሩህ ተስፋችን ተምሳሌነቱ የጎላ መሆኑን የሚንጫጩት ሁሉ ረጋ ብለው እንዲያስተውሉ እንመክራቸዋለን። ያኔ ፊታቸውን ያጨፈገጉብን ሁሉ ማፈራቸው እንደማይቀር እርግጥ ነው፡፡ ሀገሬን የጥቁር ከል ሸማ ለማልበስ ሲያሴሩ የባጁት ጠላቶቻችን በሙሉ ነገ ጠዋት “ነጭ የሀር ጥበብ” ተጎናጽፋ እንደሚያዩዋት የምናረጋግጥላቸው ታሪኳ እንደዚህ ስለሆነ ነው፡፡
ኢትዮጵያ በጀግኖች ልጆቿ ተከብራ ከፍ ከፍ እያለች ሽቅብ ትገዝፋለች።በፈጣሪ ኃያልነት ተማምናም ወደፊት ትገሰግሳለች፡፡ መደምደሚያው ይህ ነው፡፡ ሰላም ይሁን!
(ጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን መስከረም 8/2014