አክቲቪስት (የማህበረሰብ አንቂ) አገራዊ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮችን በአጀንዳነት በመቅረፅ፤ ፖለቲከኞችንና ጉዳዩ የሚመለከታቸው ተቋማትን በመወትወት እና እረፍት መንሳት የፖሊሲና የአስተሳሰብ ለውጥ የሚያመጣ ተፅእኖ ፈጣሪ ትልቅ ሙያ ነው። ለዚህ ነው አንድ ፖለቲከኛ ከቀረፀው አጀንዳ ይልቅ በጉዳዩ ላይ ንቁ ተሳትፎ የሚያደርግ አክቲቪስት በፍጥነት ቀልብን የሚስበው።
በዓለማችን ተፅእኖ መፍጠር የቻሉ አክቲቪስቶች በርካቶች ናቸው። ከእነዚህ ውስጥ ማላላ የሱፍዛይ፣ ጄሲ ጃክሰን፣ሮዛ ፓርክ፣ዋንጋሪ ማታይና ጁሊያን ቦንድን ለምሳሌ ያክል መጥቀስ ይቻላል። እነዚህ ግለሰቦች ለቆሙለት ጉዳይ ከፖለቲከኞችና ከአስተሳሰብ ጋር ጉሮሮ ለጉሮሮ ተናንቀው በከፍተኛ ደረጃ ተከታዮችን በማፍራትና በአንድ መስመር በማሰለፍ የሚፈልጉትን ግብ መምታት የቻሉ ናቸው። አለፍ ሲልም ሃያላን ፖለቲከኞች በእነርሱ አስተሳሰብ እንዲቃኙና ዓለም አቀፍ ተቋማት ፍትህ፣ እኩልነት እንዲሁም ሰብአዊነትን የሚመለከቱ ጥብቅ ፖሊሲዎችን እንዲቀርፁ እስከ ማድረግ ደርሰዋል።
በአገራችን ኢትዮጵያ “አክቲቪዝም” ከመሬት ላራሹ ህዘብዊ ንቅናቄ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ የራሱ ድርሻ ቢኖረውም የተደራጀ ቅርፅ ያለውና “ይህ ነው” የሚባሉ ተፅእኖ ፈጣሪ “የማህበራዊ አንቂ” ግለሰቦች ጎልተው የተፈጠሩበት አይደለም።
ከቅርብ ግዜ ወዲህ ማህበራዊ ሚዲያ ይዞት የመጣውን የአክቲቪዝም “አብዮት” የተቀላቀሉና የሚያስመሰግን ስራ የሚሰሩ ግለሰቦችና ቡድኖች ቢኖሩም የቅንጅት ጉድለትና ተመሳሳይ አጀንዳ በአንድ ጉዳይ ላይ የመቅረፅ ችግር እየፈተናቸው ይገኛል። ከዚህ አኳያ “ማህበራዊ አንቂዎች” በተናጠልም ይሁን በቡድን የሚፈለገውን ውጤት አምጥተዋል ለማለት የሚያስቸግር ነው። ይህ ማለት ግን ከቀደሙት ግዜያት የተሻለ ስራዎችን የሚሰሩ የዘርፉ ሞጋቾች የሉም ማለት አይደለም።
የወቅቱ ሁኔታ ከአክቲቪዝሙ አንፃር ሲቃኝ
ኢትዮጵያ ለአስራ አንድ ወራት በቆየ ህግ የማስከበር ዘመቻ ላይ ትገኛለች። አሸባሪ ትህነግ አንድን ህዝብ እንደ ምሽግ ይዞ አገር ለማፍረስ መቅበዝበዝ ከጀመረ ሰነባብቷል። በቡድኑ እኩይ ተግባራትም በርካታ ህዝብ ከቀዬው ተፈናቅሎ ለረሃብ፣ ለጉስቁልናና ለሞት እየተዳረገ ነው። የትግራይ እናቶች ልጆቻቸውን ከጉያቸው እየተነጠቁ ለሽብርተኛው ቡድን ህይወታቸውን እንዲገብሩ እየተደረገ ነው። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ለርሃብ አደጋ ተጋልጠዋል ።
ይህ ተጨባጭ እውነታ አደባባዮችን በሞሉበት ሁኔታ የኢትዮጵያን ህዝብና መንግስት የሚከሱ እጃቸውን የሚጠቁሙ ምእራባውያን ከዚህም ከዚያም ብቅ ብለው ምጣችንን እያባባሱት ነው። ዓለም አቀፍ ተቋማት ከእውነታው የራቀ ድምዳሜ ላይ ደርሰው አሸባሪውን ትህነግን ለማዳን ከላይ እታች እየተራወጡ ነው። ቡድኑ ለሶስት አስርት ዓመታት የዘረጋው የውሸት መረብ ወጥመዱን ይዞ ውሸት በአደባባይ ላይ እየተንጎማለለች እያየን ነው።
“አይጥ በበላ ዳዋ ተመታ” ይሉት ብሂል ሰርቶ መከራው የበዛበት ህዝብ በተፈናቀለ፣ በጭካኔ ህይወቱን በተነጠቀና ሃብት ንብረቱ በወደመ መልሶ የሚከሰሰው ማእቀብ የሚጣልበት እራሱ መሆኑ ። ግራ የገባው ጉዳይ ሆኗል !
እዚህ ጋር ነው እንግዲህ እውነትን ፈልቅቆ የሚያወጡ ተፅእኖ ፈጣሪ “ማህበራዊ አንቂዎች” ሚና ጎልቶ መታየት ያለበት። በመግቢያችን ላይ ለመናገር እንደሞከርው አክቲቪስት ከእውነት ጋር ወግኖ ድምፁን በማሰማት የተዛባን ማረቅ የተዘባረቀን ውል ለማስያዝ መትጋት ይኖርበታል።
በእርግጥ በማህበራዊ ድረ ገፅ በተለይ በፌስቡክ፣ ቲውተር እንዲሁም መሰል መተግበሪያዎች ላይ በርካታ ተፅእኖ መፍጠር የቻሉና ያላቸውን አቅም አሟጠው የሚሰሩ ግለሰቦች አሉ። በተለይ በአሸባሪው ትህነግ ሴራ አገር አደጋ ውስጥ መሆኗን የተረዱ፣ ዜጎች በጭካኔ ለርሃብና ሞት መዳረጋቸው የሚያበግናቸው፣ ዜጎች ከሽብርተኛው ቡድን ግዞት ነፃ እንዲወጡ አጥብቀው የሚሹና ለዚያ የሚሰሩ አክቲቪስቶች አያሌ ናቸው።
ሰርተው ሰርተው “አመድ አፋሽ” ያደረጋቸው ዋናው ችግር ግን ወዲህ ነው። የመደማመጥና የቅንጅት ጉድለት። አዎ የአገራችን አክቲቪስቶች አንድ አላማና ግብ ይዘው ግን መደማመጥ ፍፁም የጎደላቸው እንደሆኑ የአደባባይ ሃቅ ነው። ይህ ደግሞ “ትልቁን ምስል” እንዳናይና በዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ ድምፃችን አሁን ካለው በተሻለ መንገድ ጎልቶ እንዳይሰማ አድርጎታል። ከሁሉ በላይ ግን አክቲቪስቶቹ ጉልበታቸውንና አቅማቸውን አሟጠው የሚጮሁለት አላማ በከንቱ ባክኖ እንዲቀር እያደረገው ነው።
መፍትሄውስ
ምንም እንኳን የራሱ የሆኑ ክፍተቶች የሚታይበት ቢሆንም መንግስት ሽብርተኛው ቡድን እያስከተለ ያለውን ጥፋት በመደበኛው የዲፕሎማሲ ስርዓት ለዓለም አቀፍ ተቋማትና ወዳጅ አገራት አጋልጦ ለመታገል ጥረት እያደረገ ነው። ይሁን እንጂ የጥፋት ቡድን በመላው ኢትዮጵያውያን ላይ ያወጀው ጦርነት ከመሆኑ አንፃር እውነታውን አፍረጥርጦ የዓለም አቀፍ ማህበረሰቡን ከኢትዮጵያ ጎን የማሰለፍ ስራ ለመንግስት ብቻ የሚተው አይደለም። ለዚያም ነው በዓለም አቀፍ ጎዳናዎች ላይ ሰላማዊ ሰልፎችን ከማዘጋጀት ጀምሮ በማህበራዊ ሚዲያ አማራጮች “እውነታውን በአክቲቪዝም” የማጋለጥ ስራ እየተሰራ ያለው።
ይሁን እንጂ ይህን እንቅስቃሴ በምእራባውያኑ “ጆሮ ዳባ ልበስ” ከመባል ጀምሮ በአገር ውስጥም ሆነ በውጪ የሚገኙ አክቲቪስቶች በቅንጅት አብሮ የመስራት ፍላጎት ማጣት የሚፈለገውን ውጤት እንዳያመጣ እያደረገው ነው።
ምንም እንኳን የተለያየ አመለካከትና ልዩነቶች ያሉን ቢሆንም “አንዲት አገር” ነው ያለችን። “ኢትዮጵያን” ከአዞዎች አፍ ነጥቆ ለማውጣት በሚደረገው የህልውና ትግል ላይ በጋራ የመስራት ሃሞት “አክቲቪስቶቻችን” ሊኖራቸው ይገባል። ጫፍና ጫፍ ይዘው በተናጠል ትግል ከማድረግ ሰብሰብ ብሎ ህዝቡን ማስተባበር “እውነታውን” አደባባይ ላይ በማውጣት አሸባሪውን ትህነግ እራቁቷን ማስቀረት ይገባል።
መፍትሄው ጠርዝ መያዝ ሳይሆን ወደ መሃል መምጣት ነው። በአንድ አጀንዳ ላይ ይሄን ያህል መገፋፋትና መለያየት ከታየ “በማያስማሙን ጉዳዮች ላይ እንዴት ተቀራርበን ልዩነታችንን ማጥበብ እንችላለን?” የሚለውን ጥያቄ “የአክቲቪዝሙ” ስራ ላይ የተሰማሩ ግለሰቦች ሊያሰላስሉት የሚገባ አሳሳቢ ጉዳይ ነው።
ሌላው በጥንቃቄ ሊታይ የሚገባው ጉዳይ መንግስት “ከማህበረሰብ አንቂዎች” ጋር የሚፈጥረው ግንኙነት ነው። በመደበኛው መዋቅር የሚሰራውን የዲፕሎማሲ ስራ አክቲቪዝሙ ያግዘዋል በሚል የመንግስት አካላት ይህንን ሚና ከሚወጡ ግለሰቦች ጋር ግንኙነት እንደሚፈጥሩ ይታወቃል። በዚህን ግዜ ለመንግስት ፍላጎት ይቀርባሉ በሚል ገሚሱን አግልሎ ገሚሱን ደግሞ አቅርቦ (መረጃን ከመስጠት ጀምሮ) ድጋፍ ለማድረግ የሚደረግ ጥረት ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ላቅ ያለ ይሆናል።
ተናብቦ ከመስራት ይልቅ የበለጠ ልዩነት የሚያሰፋ “የተቃዋሚና የመንግስት” የሚል ጎራ የሚለይ ነው። በዚህ ምክንያት አንድ አይነት አጀንዳ ያላቸው ነገር ግን ጠርዝና ጠርዝ የቆሙ የተከፋፈሉ የማህበራዊ አንቂዎችን እንፈጥራለን። ከዚህ ድርጊት ከታቀብንና ማህበራዊ አንቂዎች ተናበው መስራት ከቻሉ “የአሸባሪ ትህነግ በሬ ወለደ” ውሸት አደባባይ ላይ ለማስጣት፣ የምእራባዊያኑን እኩይ ህልም ለማክሸፍ ሌላ አዲስ ዓመት የሚጠይቅ አይሆንም። ሰላም!
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን መስከረም 8 ቀን 2014 ዓ.ም