“የማያጠግብ እንጀራ ከምጣዱ ያስታውቃል” እንዲሉ፤ መልካም ሀሳብና ተግባር የሌለው ግለሰብም ሆነ ቡድን ከጅምሩ ይለያል፡፡ ለዚህ ዓብይ ማሳያ የሚሆነው ትናንት በኢትዮጵያ ፈላጭ ቆራጭ የነበረውና የዛሬው አሸባሪና አጥፍቶ ጠፊው አሸባሪው ህወሓት ነው፡፡ ይህ የሽብር ቡድን ከስንዴ መካከል እንክርዳድ እንደማይጠፋ ሁሉ፤ በኢትዮጵያ ህዝብ መሃል ተወልዶ በምግባርም፣ በሀሳብም የጨነገፈ የጥፋት ሀይሎች ተላላኪ ባንዳ ሆኗል፡፡
አሸባሪው ህወሓት ገና ከፍጥረቱ ከፍተኛ የስልጣን ጥማት ባላቸው ግለሰቦች ተቋቁሞ በብዙ የትግራይ የለውጥ ሀይሎች መስዋዕትነትና በውጪ ኃይሎች ሁለንተናዊ ጣልቃ ገብነት ወደ ስልጣን የመጣ ቡድን ነው። በስልጣን ላይ በነበረባቸው 27 ዓመታትም ይህንን የስልጣን ጥማቱን ለማርካት ከፍያሉ በደሎችን በሀገርና በህዝብ ሲፈጽም የነበረና በዚሁ ተግባሩ በህዝብ ተገፍቶ ከስልጣን የወረደ፤ እንኳን ለሀገር እወክለዋለሁ የሚለውን ህዝብ ከውልደቱ ጀምሮ ዋጋ እያስከፈለ ያለ የራስ ወዳዶች ስብስብ ነው።
ቡድኑ በተዛባ የአስተሳሰብ መሰረቱ ገና ከጅምሩ ታላቋን ትግራይ የመመስረት ህልም ይዞ የተነሳ ቢሆንም፤ የትግራይ ህዝብ ለኢትዮጵያዊነቱ ካለው ቀናኢነት አንጻር ሊገፋበት አልቻለም። ከዚያ ይልቅ ከመጋረጃ በስተጀርባ የማኩረፊያ አቅም አድርጎት ቆይቷል።
በስልጣን ዘመኑም ለአገር ሳይሆን ለቡድናዊ ፍላጎቱ ፣ ለህዝብ ሳይሆን ለቡድኑ አመራሮች የግል ጥቅም በስፋት ተንቀሳቅሷል። ለምዕራባውያኑ ታማኝ ሆኖ ለመገኘትም በሀገርና በህዝብ ጥቅሞች ሲያመነዝር ኖሯል። የታሪካዊ ጠላቶቻችንን ፍላጎት በሚያረካ መልኩ ኢትዮጵያውያንን በመከፋፈልና እርስ በርስ እንዳይተማመኑ የጥላቻና የመለያየት ትርክቶች ፈጥሮ በስፋት በመተረክ ሀገርን እንደ ሀገር አደጋ ውስጥ በሚከቱ ተግባራት ተጠምዶ ቆይቷል።
በንጹሃን መስዋዕትነት ለስልጣን የበቃው ይህ አሸባሪ ቡድን የትግራይ ህዝብ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ወንድሞቹ ጋር አብሮ እንዳይኖርና በስጋትና በጥርጣሬ እንዲታይ በሚያደርጉ የሴራ ትብታቦች ከወንድሞቹና እህቶቹ እንዲገለል ለማድረግም ብዙ ሰርቷል።
እነዚህ የቡድኑ የተላላኪነትና የጥቅመኝነት እኩይ ተግባራት ውለው አድረው በኢትዮጵያውያን እንዲጠላ፤ ኋላም በህዝብ ተገፍቶ ከስልጣን እንዲወገድ አድርገውታል፡፡ ይህ በሆነ ማግስትም ምዕራባውያኑና ግብጽ ክስተቱ በኢትዮጵያ ውስጥ ተላላኪ የሚያሳጣቸው በመሆኑ ቡድኑን ዳግም ወደስልጣን ለመመለስ የሚችሉትን ሁሉ ለማድረግ እየሞከሩ ነው፡፡
በዚህ ረገድ አንዳንድ አገራት በተራድኦ ድርጅታቸው አማካኝነትም ሆነ በሌሎች መንግስታዊ ተቋሞቻው አማካኝነት ስለ አሸባሪው ህልውና ሲሞግቱና በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማሳደር ሲሰሩ ቆይተዋል፤ አሁንም ከዚሁ ባህሪያቸው ለመላቀቅ ተቸግረው ይታያሉ፡፡
ሌላኛዋ የአሸባሪ ቡድኑ መመሪያ ሰጪና የህልውና መሰረት የሆነችው ግብጽም በአሸባሪ ቡድኑ አማካኝነት ሀገር የማፍረስ ዘመናት ያስቆጠረ ህልሟን እውን ለማድረግ ባለ በሌለ ሀይሏ እየተንቀሳቀሰች ትገኛለች፤ ከሰሞኑም በመሪዋ በሚደጎም መገናኛ ብዙሃኗ የአሸባሪው ህወሓትን አፈቀላጤ አቅርባ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ያላቸውን ውጥንና ህልም አደባባይ አውጥታለች፡፡
አሸባሪው ህወሓት በዚህ መልኩ በአደባባይ ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላት ጋር በመቀናጀት ሀገር ለማፍረስ ያለውን ጽኑ ፍላጎት ማስታወቁ ኢትዮጵያ- ጠል መሆኑን በግልጽ ከማሳየቱ በላይ የቱን ያህል ተስፋ መቁረጥ ውስጥ እንደገባ ያሳየበት ነው።
በተበላሸ አስተሳሰብ ተወልዶ ያደገው ይህ አሸባሪ ቡድን፣ የተበላሸ አስተሳሰቡ በጊዜ ሂደት ውስጥ ራሱን በልቶ ጨርሶት ዛሬ ላይ ወደ ተራ አሸባሪነት ቀይሮታል፡፡ አጠቃላይ ጉዞውም የተሸናፊነት ቁልቁለት ውስጥ የጨመረው በመሆኑ የመጨረሻ አማራጩ “እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል” እንዳለችው አህያ አይነት ወደ አጥፍቶ ጠፊነት ተቀይሯል፡፡
ይህንን አይቀሬ የቡድኑ ፍጻሜ በመገንዘብ መላው የትግራይ ህዝብ ጊዜ ወስዶ ከተጨባጭና ተገላጭ ባህሪዎቹ በመረዳት ራሱን ከዚህ አጥፍቶ ጠፊ ቡድን ሊታደግ ይገባል።ይህንን የማድረግም ዜጋዊ ኃላፊነት አለበት!
አዲስ ዘመን መስከረም 8 ቀን 2014 ዓ.ም