ለአገር መከላከያ ሰራዊት ድጋፍ ለማድረግ በታሰበው ‹‹እግር ኳሳችን ለሰላማችን›› የተሰኘ መርሃግብር ነገ በታዋቂ የኪነ ጥበብ ሰዎችና በመከላከያ አመራሮች መካከል በአበበ ቢቂላ ስታዲየም የእግር ኳስ ውድድር ይካሄዳል። አስራ አምስት ሺ ተመልካች ውድድሩን ለመመልከት በስቴድየም ይገኛል ተብሎ በሚጠበቅበት ከሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ጎን ለጎን በእለቱ ሴት ሚኒስትሮችና በተለያየ ሙያ ላይ ያሉ ተጽዕኖ ፈጣሪ ሴቶች የገመድ ጉተታ ውድድር እንዲሁም የደም ልገሳ መርሃ ግብር ይኖራቸዋል። በተመሳሳይ የፊታችን መስከረም 10/2014 ዓ/ም በስካይ ላይት ሆቴል የአገሪቱ ታዋቂ የኪነ ጥበብ ሰዎችና ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት ታላቅ የገቢ ማሰባሰብ መርሃ ግብርም እንደሚካሄድ አዘጋጆቹ አሳውቀዋል።
በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ለሚካሄደው መርሃ ግብር የመግቢያ ቲኬት የተዘጋጀ ሲሆን ትልቁን 1000 ብር ጨምሮ የ 500 ብርና የ 100 ብር መግቢያ ትኬቶች መዘጋጀታቸው ታውቋል። ከዚህም በተጨማሪ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ደጋፊዎች ማህበር ሙሉ የመግቢያ ትኬት ሽያጩን ለማስፈጸም ሃላፊነቱን የወሰደ ሲሆን ውድድሩ ቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭትም እንደሚኖረው ተገልጿል።
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የማርኬቲንግ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ኢሳያስ ታፈሰ፣ መስከረም 10/2014 ምሽት በስካይ ላይት ሆቴል በሚደረግ የእራትግብዣ ላይ የተለያየ መርሃ ግብሮች እንደተዘጋጁ በመግለፅ ጉዳዩ ለሚመለከታቸውም አካላት ጥሪ መደረጉን አስረድተዋል። ባለሀብቶች፣ የክልል የስራ ሃላፊዎችና በመር ሃግብሩ እንዲገኙ ጥሪ የሚደረግላቸው አካላትም ለመርሃ ግብሩ ትኩረት እንዲሰጡ ጠይቀዋል።
በእለቱ ገጣሚዎችና ሰአሊያን ስራዎቻቸውን የሚያቀርቡ ሲሆን ጨረታዎችና የተለያዩ የገቢ ማሰባሠቢያ ፕሮግራሞችም ተይዘዋል። ለዚህ ፕሮግራም 2 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር ወጪ የሚጠይቅ ሲሆን፣ ከአገር መከላከያ ጎን መቆሙንና እያደረገ ያለውን ትግል እንደሚደግፍ ለማሳየት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በሰጠው ውሳኔ መሠረት ዋቢ ኢቨንትስ ያቀረበውን እቅድ ሙሉ ወጪ ለመሸፈን መወሰኑን የፌዴሬሽኑ ዋና ጸሃፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን ገልጸዋል። ዋና ጸሃፊው አክለውም፣ የፕሪሚየር ሊግ ሼር ካምፓኒ አባል ክለቦች 8 ሚሊዮን ብር ለአገር መከላከያ ድጋፍ መስጠታቸውን ገልጸዋል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዋልያዎቹ ለአገር መከላከያ ያላቸውን ድጋፍ ለመግለጽ በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ የዚምባቡዌ አቻቸውን ባህርዳር ላይ አንድ ለዜሮ በረቱበት ማግስት የደም ልገሳ ማድረጋቸው ይታወሳል። አቶ ባህሩ ‹‹አገርን ከመፍረስ ለማዳን የማይጥር እግር ኳስ ጥንቅር ይበል›› ሲሉ የፌዴሬሽኑን አቋም አስረድተዋል።
የመከላከያ እግር ኳስ ክለብ የስፖርት ክፍል ሃላፊ ኮሎኔል ደረጀ መንግስቱ በበኩላቸው ‹‹እንደ ሰው ሊደረግ የሚችለው ሁሉ የሚፈጸመው ኢትዮጵያ ሰላም ሆና እንደ አገር ስትቆም ነው›› ሲሉ ተናግረዋል። በዚህ መርሃ ግብር ለአገር ሰላም በማሰብ ከመከላከያ ጎን የሆኑ አካላትንም በመከላከያ ስም አመስግነዋል። ኮሎኔል ደረጀ አክለውም ‹‹እግር ኳሱ የሰላም ጦርነት ነው፣ ያኛው ደግሞ ዋጋ የሚከፈልበት ነው ፣ በጦርነቱ መከላከልና ማጥቃት እንዳለ ሁሉ በኳሱም ማጥቃትና መከላከል አለ፣ እናጠቃለን ፋታ ለመስጠት እንከላከልና ግጥሚያውን ለመርታት እናጠቃለን፣ በስፖርቱ መሸነፍም እንዳለ ተጋጣሚዎቻችን ሊያውቁ ይገባል›› በማለት ተናግረዋል፡፡
አርቲስት ሰለሞን ተካ በበኩሉ ‹‹ያሰባሰበን ትልቁ ጉዳይ ሰላማችን ነው፣ ሰላማችንን ለማስከበር እየሰራ ላለው መከላከያ ሰራዊታችን ድጋፍ ለማድረግ የኪነ ጥበብ ባለሙያ በዚህ መርሃግብር እንዲካፈል ጥሪ በመደረጉ ኮርቻለሁ፣ መከላከያ ወንድም፣ እህት፣ አባትና እናት ሆኖልን በመገኘቱ ኮርቼበታለሁ፣ የአንድ አገር እድገቷ የሚለየው በኪነጥበብ እድገቷ ነው ሲል ዊሊያም ሼክስፒር ይናገራል፣ ይህን ለመፈጸም ሰላም ወሳኝ በመሆኑ ለሰላማችን መከላከያ እየከፈለው ላለው ዋጋ ሙሉ ድጋፍ ለመስጠት ተዘጋጅተናል›› ብሏል። ሁለቱ ቡድኖች ለሚያደርጉት የእግር ኳስ ውድድር ባለፉት ሳምንታት ልምምዳቸውን አጠናክረው ቀጥለዋል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን መስከረም 7/2014