(የመጨረሻ ክፍል)
ለውጡ እስከ ባዕተበት መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም ያልዘመመ እና ውሀ ልኩን ያልሳተ የልቦና ውቅር አልነበረም። የፖለቲካ፣የአስተዳደር፣የኢኮኖሚ፣የማህበራዊ፣ወዘተረፈ የልቦና ውቅራችን ዘሞ ነበር ማለት ይቻላል። ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ ተቋማዊና መዋቅራዊ ሆኖ የቀጠለው የማንነትና የዘውግ ፖለቲካ የዘመመ የልቦና ውቅር አዋቅሯል። በዚህ የተነሳም በዜጎቿ መካከል ጥላቻ፣ልዩነትና መጠራጠር በመጎንቆሉ ላለፉት ጥቂት አመታት ሁላችንንም ያሸማቀቁ፣ አንገታችንን ያስደፉና ያሳፈሩ፤ ለማየት የሚዘገንኑ ለመስማት የሚሰቀጥጡ ጥቃቶችና ግፎች ተፈፅመዋል።
98 በመቶ የሚሆን ዜጋ የተለያዩ ዕምነቶች ተከታይ በሆነባት ሀገር የቻርለስ ዳርዊን ዝግመት ለውጥ አማንያን፤ ፈጣሪ የለም በሚሉ ጉግ ማንጉጎች ማለትም በእነ ማርክስ፣ ኤንግልስ፣ ሌኒን፣ ስታሊን፣ ማኦ፣ ፓል ፓት፣ ወዘተረፈ የተተወረ የሶሻሊስት ርዕዮተ አለም(አይዶሎጂ)ተከታይ የሆን ጊዜ የልቦና ውቅራችን ዘሟል። ከኢትዮጵያውያን የስነ ልቦና ውቅር የተናጠበ የግማሽ ክፍለ ዘመን ማህበራዊ ወረታችንን፣እሴታችንንና ትውልዶች ከማሳጣቱ ባሻገር የከሸፉ ሁለት አብዮቶችን አስታቅፎን፤ ዛሬ ድረስ የራስ ምታት ታማሚ ላደረገን ፖለቲካዊ ሀንጎቨር አሳልፎ ሰጥቶናል።
ሀገራችን ለ50ና ከዚያ በላይ አመታት በድቅድቅ ጨለማ እንድትደናበር አድርጓል። ይህ ብቻ አይደለም ህልመኛና ሀገር ወዳድ የሆነ ትውልድ አሳጥቶናል። የትውልድ ክፍተት እንዲፈጠር አድርጓል። ለብልፅግና መሰረት የሆነ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንዳንገነባ፤ ተቋማትን እንዳንከተል አድርጎናል። በተለይ በዘመነ ትህነግ/ኢህአዴግ ተጠያቂነት ባለመኖሩ ሀገር በጠራራ ስትዘረፍ ፤ የዜጎች መብት በአደባባይ ሲጣስ በመኖሩ ዛሬ ለምንገኝበት ፈተና ዳርጎናል። ዳፋው ገና ለአመታት እንደ ጥላ ይከተለናል። ከ50 አመታት በላይ እየተፈራረቀ ተጭኖብን የኖረው የሶሻሊስትና የማንነት ፖለቲካ እንደ ሀገርም እንደ ሕዝብም የልቦና ውቅራችንን ከመሰረቱ አናግቶታል።
አዛብቶታል። በተለይ የሶሻሊዝም አይዶሎጂ የሀይማኖት ተቋማትን አዳክሟል። የሀይማኖት አባቶችን፣የሀገር ሽማግሌዎችን ሆን ብሎ ማህበራዊ ቦታቸውን እንዲያጡ አድርጓል። ከፈጣሪያቸው ይልቅ እነ ማርክስን እንዲያመልኩ እስከ ማስገደድ ደርሶ ነበር። እንደ ባህላዊ ሽምግልና፣ገዳ ያሉ እሴቶች እንዲደበዝዙ ፤ ለዘመናት አጋምደው በአብሮነት ያኖሩን ዘመን ተሻጋሪ ባህላዊ ትስስሮችን አንድ በአንድ አቋርጧቸዋል።
በዚህም ለባህሉ ለእሴቱ ግድ የማይለው ትውልድ ተፈጥሯል። ታላላቆቹን የሚያንጓጥጥ፣ የሀገር ሽማግሌዎችንና የሀይማኖት አባቶቹን ቁልቁል የሚያይ ትውልድ መጥቷል። በአናቱ ለአመታት ሲነዛና ሲቀነቀን የነበረው የተዛባ የማንነት ፖለቲካ ሲጨመር ፤ “ ኢትዮጵያ ትውደም!“ የሚል ፤ የተፈጥሮ ሀብት ብሔርተኝነትን በመፍጠር ዜጋን በማንነቱ የሚነቅል የሚያፈናቅል ጽንፈኛ ትውልድ ተፈጥሯል። በሀገሪቱ እዚህም እዚያም ጥላቻ፣ቂም በቀል ተንሰራፍቷል። የጋራ ታሪክና ጀግና ከመቀዳጀት ይልቅ በፈጠራ ትርክት እየተጓተተ ይገኛል።
በሶሻሊዝምና በአብዮታዊ ዴሞክራሲ ሲንጠራወዝ የኖረው የኢኮኖሚ መዋቅር ድህነትን፣ኋላቀርነትን፣ስራ አጥነትን፣የኑሮ ውድነትንና የዋጋ ግሽበትን አስታቅፎ ጥቂት ባለጊዜዎችን ደግሞ ባለጠጋ አድርጎ እንደ ደራሽ ጎርፍ አልፏል። ይህም ኢፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል ፈጥሯል። በዚህ የተነሳ ወጣቱ በትንሹም በትልቁም ሆድ እንዲብሰው ከማድረግ አልፎ ለተለያዩ የፖለቲካ ኃይሎች መጠቀሚያ ሆኗል። ሀገርም ሕዝብም ለጉስቁልና ተዳርጓል።
በዚህ አጭር መጣጥፍ የዘመሙ የልቦና ውቅሮች ያስከተሉትን ዳፋ ፤ እያስከፈሉን ያለውን ውድ ዋጋ ሁሉማውሳት አይቻልም። ይሁንና የዘመሙ የልቦና መዋቅሮች ለማቃናት የለውጥ ኃይሉ በተለይ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ፤ አንዳንድ ሚዲያዎችና እንደ ዶ/ር ምህረት ደበበ ያሉ ሀገር ወዳድ ዜጎች ጥረት እያደረጉ ቢሆንም የዘመሙ የልቦና ውቅሮች የትየለሌና ለዘመናት ሲንከባለሉ የኖሩ ስለሆኑ የሚፈለገውን ያህል ውጤታማ መሆን አልተቻለም።
በነገራችን ላይ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ መንግስት እየወሰዳቸው ያሉ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ማሻሻያዎች ማለትም የኢትዮ ኤርትራ የሰላም ስምምነት፣የተቋማት ግንባታ፣የመደመር ጽንሰ ሀሳብ፣ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ፣ አረንጓዴ አሻራ፣ ሸገርን የማስዋብ ፕሮጀክት፣ የእንጦጦ ፓርክ ልማት፣ የቤተ መንግስት ልማት፣ ከሸገር ወደ ሀገር፣ የአረጋውያን ቤት ጥገና፣ ችግኝ መትከልና ውሃ ማጠጣት፣ ከተማ ማፅዳት ለአካል ጉዳተኞችና ለችግረኞች የሚደረግ እርዳታ፣ ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር የሚያደርጓቸው ተከታታይ ውይይቶች፣ በየበዓላት የሚያስተላልፏቸው መልዕክቶች፣ በፌስ ቡክ ገጻቸው የሚያወጧቸው ጹሑፎች፣ የቀዳማዊ እመቤት የትምህርት ቤት ግንባታዎች፣ ወዘተረፈ የዘመሙ የልቦና ውቅሮች ለማቃናት የሚካሄዱ ወካይ/ ሲምቦሊክ / ጥረቶች ናቸው።
እነዚህ ወካይ ጥረቶች እንዲሰፉና እንዲጠልቁ ግን ተቋማዊ የማድረጉ ጥረት ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል። ሌላው ሊጤን የሚገባው ጉዳይ የዘመሙ የልቦና ውቅሮች በአንድ ግለሰብ ወይም በለውጥ ኃይሉ ጥረት ብቻ የሚቃኑ ስላልሆኑ በአዲሱ አመት የራሳችንን፣ የማህበረሰባችንን፣ የምንሰራበትን ተቋም፣ የሀገራችንና የሕዝባችንን የዘመመ የልቦና ውቅር ለማቃናት እጅ ለእጅ ተያይዘን እንድንተጋ ቃል እንግባ። የሀገሪቱን የዜጋውን የተቋማቱን የተዛመሙ የልቦና ውቅሮች ቀና ለማድረግ የተቋማት ግንባታ ወሳኝ ሚና አለው ። የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ መሠረተ ልማት ወይም ተቋማት ማለትም ገለልተኛ የምርጫ ቦርድ፣ብዙኃን መገናኛ፣የሰብዓዊ መብት እና የእንባ ጠባቂ ኮሚሽን ፤ የፍትሕ፣የዳኝነት፣የጸጥታ፣የደህንነት፣የትምህርትና ሌሎች ተቋማት ግንባታ እየተካሄደ ነው። በዚህም በዚያም የዘመመውን የልቦና ውቅር ለማቃናት ጥረት ተጀምሯል። ለውጡን ተቋማዊ ለማድረግ እየተከናወኑ ያሉ ተስፋ ሰጭ ጅምር ስራዎችም ይበል የሚያስብሉ ናቸው።
ተቋማቱን ከሞላ ጎደል ገለልተኛ ለማድረግ የሚያግዙ ማሻሻያ እርምጃዎችም ውጤት ማሳየት ጀምረዋል። የዳኝነት አካሉን፣ምርጫ ቦርድን፣ሚዲያውንና ሌሎች የዴሞክራሲ ተቋማትን ነፃና ገለልተኛ ለማድረግም በአሰራርና በአደረጃጀት የታገዙ ለውጦች እየተተገበሩ ይገኛል። ከለውጡ በፊት የነበረው አገዛዝ ለጭቆና ለአፈና ይጠቀምባቸው የነበሩ አዋጆች ተሻሽለዋል። በመሻሻል ላይም ናቸው። አዳዲስ አዋጆችና ሕጎችም በሒደት ላይ ይገኛሉ።
ተቋማዊ የግንባታ ሂደቱን የሚያግዙ በርካታ አዋጆችና ውሳኔዎች ፀድቀው ስራ ላይ ውለዋል። ከፀደቁት መካከል የምርጫ ቦርድ የማቋቋሚያ እና የሲቭል ማህበራት አዋጆች ይገኝበታል። ለሽግግር ሂደቱ አጋዥ ከሆኑ ውሳኔዎች የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት መዓዛ አሸናፊ፣የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ክብርት ብርቱካን ሚደቅሳ፣የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ዳንኤል በቀለ (ፒኤችዲ) እና የመንግስት መገናኛ ብዙኃን የስራ አመራር ቦርድ አባላት ምደባን በአብነት መጥቀስ ይቻላል። እነዚህ ሹመቶች መንግስት ነፃና ገለልተኛ የዴሞክራሲ ተቋማትን በመገንባት ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለመሸጋገር ያለውን ቁርጠኝነት ያሳያል።
ከሶስት አመታት በፊት በተለያዩ ወንጀሎች ተፈርጀው እና የፖለቲካ ምህዳሩ በመከርቸሙ በእስር፣በስደትና በትጥቅ ትግል ለነበሩ ዜጎች፣ድርጅቶችና ሚዲያዎች ይቅርታና ምህረት የተደረገው የዘመመውን የልቦና ውቅርቀና ለማድረግ ነው። አንዳርጋቸውን፣አንዷለምን፣እስክንድርን፣ተመስገን፣እማዋይሽን፣ንግስትን ጨምሮ በመላ ሀገሪቱ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ የፖለቲካ እና የህሊና እስረኞች ተፈተዋል። አርበኞች ግንቦት 7፣ የኦሮሞ ነፃ አውጭ ግንባር እና የኦጋዴን ነፃ አውጭ ግንባር የፖለቲካ ድርጅቶች በምህረትና በይቅርታ ወደ ሀገር ተመልሰው ሰላማዊ ትግሉን ተቀላቅለዋል።
እንደ ኢሳት ያሉ ከ200 በላይ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች፣ ድረ ገጾች፣ ጦማሮች፣ ጋዜጦችና መፅሔቶች እንደገና ወደ ስራ ተመልሰዋል። ፍትሕን፣ ኢትዮጲስን፣ ዘሀበሻን፣ ሳተናውን ለአብነት ማንሳት ይቻላል። የዘመመው የሀገር የሕዝብና የመንግስት የልቦና ውቅር ቀና የሚለው በአንድ ጀምበር ባይሆንም አበረታች ለውጦች መታየት ጀምረዋል። ሁለት አመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በመከላከያና በሌሎች የጸጥታና የደህንነት ተቋማት፤ በኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ፤ በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ፤ በብዙኃን መገናኛ፤ በሶስቱ የመንግስት አካላት ማለትም በሕግ አውጭው ተርጓሚውና አስፈጻሚው ለአመታት ይስተዋል የነበረውን መደበላለቅ በአሰራርና በአደረጃጀት ለመለየት የተጀመሩ ጥረቶች የዘመመውን የልቦና ውቅር ለማቃናት ለሚደረገው ጥረት እሴት ጨምረዋል።
እንደ መውጫ
በአዲሱ አመት የዘመሙ የልቦና ውቅሮችን የማቅናቱ ጥረት መቀጠል አለበት።መንግስት ለውጡን ተቋማዊ የማድረግ ጥረቱን አጠናክሮ ይቀጥል። ዜጋ ተቋማቱ ውጤታማ እንዲሆኑ ድርሻውን ይወጣ።ተቋማት የተጣለባቸውን ኃላፊነት በአግባቡ ይወጡ።የለውጥ ኃይሉ ምርጫ ቦርድ ነጻ ገለልተኛና ተአማኒ እንዲሆን የሄደበትን ርቀት ልብ ይሏል። ሕግ አሻሻለ፣ክብርት ብርቱካን ሚደቅሳን ሰብሳቢ አደረገ።የቦርዱን ውሳኔ ያለምንም ማቅማማት ተቀበለ።በተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ሆነ በዜጋው ተአማኒ የሆነና ተቀባይነት ያለው ተቋም በመሆኑ ዘመም የነበረው ነጻ ተአማኒና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ የማካሄድ የልቦና ውቅር ቀና ማለት መጀመሩን በ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ አረጋግጠናል።
የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ዘብ የነበሩት የደህንነት የጸጥታና የሰላም ተቋማት በተደረገ ማሻሻያ ከፓርቲ ቃፊርነት ወጥተው የሕገ መንግስቱ የሀገርና የሕዝብ ምሽግ ሆኑ።የመከላከያ ሰራዊት ከአንድ ፓርቲ መሳሪያነት ወጥቶ ሁለት አመት ባልሞላ ጊዜ እጅን በአፍ የሚያስጭን አንጸባራቂ ድል በማስገንዘብ የሀገርን ህልውና ያስቀጠለው እያስቀጠለ ያለው የዘመመው የልቦና ውቅር ማለትም የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ዘብነቱ ወደ ሕገ መንግስት የመጨረሻ ምሽግነት ቀና በማለቱ ነው።
በፍትሕ መዋቅሩ በሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ ተቋማት፣በኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተቋማት የተደረጉ ማሻሻያዎች ያመጡት የልቦና ውቅር ለውጦች ተስፋ የሚጣልባቸው ናቸው።
የተፈጠረው ሀገራዊ አንድነትና መተሳሰብ የልቦና ውቅር ለውጡ ትሩፋቶች ናቸው።
ለ27 አመታት ተቋማዊና መዋቅራዊ ሆነው የተሰራባቸው የጥላቻ የልዩነት የቂም በቀል የሁከት የሀሰተኛ ትርክት የስግብግብነት የውሸት የአቅላይነት የሌብነት የመጠላለፍና የሴራ ፖለቲካ ወዘተረፈ ከለውጡ ማግስት ጀምሮ መዋቅራዊና ተቋማዊ መሆናቸው ስለቀረ እንደ ኩይሳ በቁማቸው እየፈረሱ ቢሆኑም በአዲሱ አመት የቀሩትን የልቦና ውቅሮች በማቃናት ፍቅር ሰላም አንድነት ይቅር ባይነት እርቅ መነጋገር መደማመጥ መቀባበል ወዘተረፈን ቤተኛ ለማድረግ እንደ ካችአምናው ሌት ተቀን እንስራ።ተቋሞቻችንን እንጠብቅ። እናክብር። የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ቤተመቅደሶች ናቸውና።
አዲሱ አመት የሰላም፣ የጤና፣ የብልፅግና እና
የአንድነት ይሁን !አሜን ።
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን መስከረም 7/2014