አሮጌ ያልነው ዓመት አልፎ አዲስ ዓመት ከተተካ እነሆ ቀናት ተቆጥረዋል። ባሳለፍናቸው አዳዲስ ቀናት ብዙ የአዲስ ዓመት ስጦታዎችን ተቀብለን አልያም አቀብለን ይሆናል። በግለሰቦችና በቤተሰብ መካከል ከሚደረገው የስጦታ ልውውጥ ባለፈ ሀገርም ከልጆቿ ስጦታን የምትሻበት ጊዜ አለ። በተለይም ያለንበት ወቅት ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ሀገር የልጆቿን ስጦታ በእጅጉ ትናፍቃለች። ከልጆቿ በሚበረከትላት ውድ ስጦታም በታላቅነቷ ጸንታ የመቆሟን ሚስጥር ታረጋግጣለች እያረጋገጠችም ትገኛለች።
ቀደም ባለው ጊዜ ሙዚቀኞቻችን አዳዲስ የሙዚቃ ሥራዎቻቸውን ሲያወጡ ከሙዚቃቸው መካከል ስለ ሀገር የሚያቀነቅን ቢያንስ አንድ ሙዚቃ በመጫወት ስጦታ ያበረክታሉ አሉ። አብዛኞቹ ሙዚቀኞቻችንም በጥበብ ሥራዎቻቸው መካከል ሀገራዊ ስሜት ያላቸውን ዜማዎች ጣል ማድረጋቸውም ለዚሁ ነው። በተለያየ ጊዜና ምክንያት ሀገር ሲያተኩሳት ለመጽናናትም ሆነ ለመቆዘም እንዲሁም በጽናት ለመቆም ሙዚቀኞች የጎላ ድርሻ አላቸው። በተለይም እንዲህ እንዳሁኑ ሀገር የህልውና አደጋ ሲያጋጥማት ድምጻውያኑ የውስጣችንን ጥልቅ ስሜት አውጥተን ለሀገር ያለንን ወገንተኝነት እንድናሳይ ጉልበት ይሆናሉ።
ወገንተኝነት ከሚገለጽባቸው መንገዶች መካከል ፉከራና ቀረርቶ አንደኛው ሲሆን ሙዚቃ ደግሞ ዋነኛውና ስሜት ኮርኳሪ ሆኖ እንመለከታለን። ለአብነትም በቀደመው ጊዜ ከተዜሙት ሀገራዊ ዜማዎች መካከል የክቡር ዶክተር አርቲስት ጥላሁን ገሰሰ ዘመን ተሸጋሪ የሆኑና ወኔ ቀስቃሽ ዜማዎች ይጠቀሳሉ።
‹‹ዘማች ነኝ ቆራጥ እኔም ለሀገሬ፤
አልሻም ማየት ተደፍራ ድንበሬ፤
አልሳሳም ጭራሽ እኔም ለህይወቴ
ለሀገሬ ቢባል ቢጎድል አካላቴ ልሰዋ ለውዲቷ እናቴ…››
እንዲሁም በሌሎች በርካታ ዜማዎች ኢትዮጵያውያን ለሀገራቸው ያላቸውን ጥልቅ ፍቅር በዕንባ እየተራጩ ሲገልጹ መመልከት የተለመደ ነው። ኢትዮጵያ ጥላሁን ገሰሰን ጨምሮ በርካታ የጥበብ ፈርጦቿን በአካለ ነብስ ብታጣም ህያው ስራቸው ግን ለትውልድ ሲተላለፍ ይኖራል። ኢትዮጵያ ማህጸነ ለምለም በመሆኗም በየዘመኗ በኪነ ጥበብም ሆነ በሌሎች ዘርፎች ጀግኖቿን ታፈራለች።
ኪነ ጥበብ በፍስሃም ሆነ በመከራ ጊዜ ሀሳብና ስሜትን የወደፊት ተስፋና ስጋትን የምንገልጽበት ሁነኛ መሳሪያ ነው። በተለይም ሀገር ከገባችበት ቀውስ ውስጥ መውጣት እንድትችል ኪነጥበብ ብርታትና ጥንካሬ እንዲሁም ጽናትና ተስፋን ታጎናጽፋለች። የኪነ ጥበብ ሥራ ግለሰብንና ማህበረሰብን ከማረጋጋት እንዲሁም ከማነሳሳት ጀምሮ ሀገርን ማረጋጋትም ሆነ ሀገርን የማፍረስና የማተራመስ እምቅ ጉልበት እንዳለው ይታመናል። ሀገር አደጋ በተደቀነባት ወቅትም ሆነ በደስታዋ ጊዜ እያንዳንዱ ዜጋ በተሰማራበት ዘርፍ ጀግኖ ውጤታማ መሆን ከቻለ ከችግሮቹ ማትረፍ ይቻላል።
ከሰሞኑን የሀገር ባለውለታ ለሆነው ጀግናው የኢትዮጵያ ሠራዊት በተለያየ ዘርፍ ድጋፍ እየተደረገ ይገኛል። ሙዚቀኞችም እንዲሁ ግንባር ድረስ ሄደው ሠራዊቱን ደግፈዋል፤ አበረታተዋል፤ የሞራል ስንቅም ሆነዋል፤ በጋራ እንዲሁም በተናጠል ሆነውም ሀገራዊ ስሜትን የሚቀሰቅሱ በቁጥር የበዙ ዜማዎችንም አበርክተዋል። ከድምጻውያኑ የጥበብ ሥራዎች መካከል የድምጻዊት ራሔል ጌቱ ‹‹ኢትዮጵያዬ›› የተሰኘው ሙዚቃ ትልቅ ዋጋ ያለውና ለሀገር የተሰጠ የአዲስ ዓመት ስጦታ ነው ለማለት ያስደፍራል።
ድምጻዊቷ በዜማ እያንጎራጎረች ካስተላለፈችው መልዕክት በበለጠ በአካላዊ እንቅስቃሴዋ አትንኩኝ ባይ ጥልቅ ኢትዮጵያዊ ስሜቷን አሳይታለች። ሀገር መውደድ ማለት የት ድረስ እንደሆነም ጥጉ ድረስ ሄዳለች። ድምጻዊቷ ለተሰማራችበት ሙያ ያላትን እምቅ ችሎታ አሟጣ መጠቀም በመቻሏ ሙዚቃው የብዙዎችን ቀልብና ጆሮ ይዟል ብንል ማጋነን አይሆንም።
‹‹…ኧረ ጎራው ኧረ ዱሩ ›› እያለች ዱር ገደሉን አቋርጠን ለሀገር ዘብ እንድንቆም ታጀግናለች።
‹‹አረገኝ አረገኝ ንቢቷን
ቀፎዋን የነኩባት ቤቷን
አረገኝ አረገኝ ፍም እሳት
ተባይ ሀገሬን ሲንቃት
ባይ ካንገት በላይ በላይ
ሁሉ ካንገት በላይ በላይ
ያለ ሀገር ኑሮ ስቃይ
ማን ኢትዮጵያን መሳይ ሲሳይ
ሲሳይ ነች እሷ ሲሳይ…››
በሚል ዜማዋም እኛነታችንን ሲሳያችን ከሆነችው ኢትዮጵያችን ጋር ታስተሳስራለች። ኢትዮጵያውያን ከኢትዮጵያ ውጭ ከባህር የወጣ አሳ እንደሆኑም በሚንተገተገው ስሜቷ ገልጻለች። ከንቱ እንደሆነና ያለ ሀገር መኖር የማይቻል መሆኑን፤ መኖር ከተቻለም የስቃይ ኑሮ እንደሆነ አመዳይ በመሰለው ገጿ ላይ አስነብባናለች። እንጉርጉሮዋም ቢሆን የፍቅሯንና የቁጭቷንና ጥግ በጉልህ ማሳየት የቻለና ‹‹ያለ ሀገር›› የሞላ ቢመስልም መጉደሉን ሁሉም ከንቱ መሆኑን በአዲሱ ዓመት ለሀገር ባበረከተችው ስጦታ አጋርታናለች።
ታዲያ ከሙዚቃው በሻገር ሀገር አሁን ከገባችበት ቀውስ መውጣት የምትችለው እንዲህ ባለ ከልብ በመነጨ ሥራ ነው። እያንዳንዳችን የምናበረክተው አስተዋጽኦ ከልብ በመነጨ የሀገር ፍቅር እና ታማኝነት ከሆነ የማንሻገረው ችግር አይኖርም። እርግጥ ነው ከሰሞኑ የተሰናበትነው 2013 ዓ.ም በውስጥም ሆነ በውጭ በብዙ ፈተናዎች ተፈትነን አልፈናል። ከበርካታ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ክስተቶቹ በተጨማሪ በሰዎች ኑሮ ላይም ቢሆን ቀላል ግምት የማይሰጠው የዋጋ ንረት ተመዝግቧል።
ለዋጋ ንረቱም ሆነ ለሰላም እጦቱ በሰሜኑ የሀገሪቷ ክፍል የተጀመረው ህግ የማስከበር ዘመቻ በምክንያትነት ይጠቀሳል። ችግር ብልሃትን ይወልዳል እንዲሉ ኢትዮጵያውያን ለችግሮቻቸው ሁሉ በእጃቸው ያለን መፍትሔ ተጠቅመው ሲሻገሩ ኖረዋል። ምንም እንኳን በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያን የገጠማት ፈታና በአይነቱ ለየት ያለና የማይታለፍ እጅግ ውስብስብ መስሎ ቢታይም ቅሉ አሸባሪው የህውሓት ቡድን በንጹሃን ዜጎች ላይ እያደረሰ ባለው የጭካኔ በትር ቁጭት ያልገባው ኢትዮጵያዊ የለም።
ይሁንና ቡድኑ በለኮሰው እሳት ከመቃጠሉ ባለፈ የክፋቱ ጥግ ያስከፋው ህዝብም በአንድነት እንዲቆም ወርቃማ የሆነውን ዕድል ሰጥቶታል። ህዝቡ ችግሮችን ወደ ዕድል መቀየር እንደሚባለውም ለዓመታት ተነፍጎት የነበረውን አንድ የመሆን አጋጣሚ በመጠቀም ሀገር የገጠማትን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት፤ ዕድገት ብልጽግናዋን ለማረጋገጥ በሚያስችል ቁመና ላይ በሆነ ማግስት አዲስ ዓመትን ተቀብሏል።
በአዲሱ ዓመትም ትናንት የተነፈገውን አንድነት መሰረት አድርጎ በተሰማራበት የሥራ ዘርፍ ሁሉ በእልህና በቁጭት ለለውጥ እየተጋ ይገኛል። አሁን የተጀመረውን ከፍተኛ የህዝብ ንቅናቄና መነሳሳት በማስቀጠል በአዲሱ ዓመት ሰላማዊና የተረጋጋች ኢትዮጵያን ለማየት ኢትዮጵያውያን ትልቅ ተስፋ አላቸው። ተስፋቸው እውን እንዲሆንም በ2013 ዓ.ም የተከሰቱት አሰቃቂ ነገሮች ሁሉ በአዲሱ ዓመት 2014 እንዳይደገም ከምኞት ባለፈ በሥራ ሊተጉ ቆርጠው ተነስተዋል።
ድምጻዊቷ እንዳለችው ‹‹ያለ ሀገር ኑሮ ስቃይ›› መሆኑን አውቀውም ከምንጊዜውም በበለጠ ለሀገር ዘብ መቆምን የሠራዊቱ አባል ከመሆን ጀምሮ በቁሳቁስ ድጋፍ በማድረግ ጭምር አሳይተዋል። በአዲሱ ኣመትም በሁሉም ዘርፍ ተጠናክሮ የቀጠለው ይኸው ለሀገር ዘብ የመቆም ወገንተኝነት ተቀጣጥሎ አጥፊዎች የሚጠፉበት ኢትዮጵያ የምታሸንፍበት ዓመት እንዲሆን በመመኘት በተሰማራንበት የሥራ ዘርፍ ሁሉ ከምንጊ^ዜውም በበለጠ በብርቱ አንትጋ!
ፍሬህይወት አወቀ
አዲስ ዘመን መስከረም 7 ቀን 2014 ዓ.ም