ኢትዮጵያውያን ለብዙ ሺ ዓመታት አብሯቸው የቆዩ ከፍ ያሉ ማህበራዊ እሴቶች ባለቤት ናቸው። እነዚህ እሴቶች በያንዳንዱ ብሄር፣ ብሄረሰብና ህዝብ ውስጥ ገዥ ማህበራዊ እሴቶች ሆነው የመገኘታቸው እውነታ ደግሞ እሴቶችን እንደ ሀገር ለመቀበልና ለመጠበቅ ትልቅ እቅም ፈጥሯል።
ከነዚህ ከፍ ያሉ ማህበራዊ እሴቶቻችን መካከል አንዱና ትልቁ ውሸትን መጠየፍ ነው። ኢትዮጵያውያን ሃይማኖታዊ ሆኑ ባህላዊ አሴቶቻቸው ለእውነት ትልቅ ስፍራ የሚሰጡ ናቸው። ከዚህም የተነሳ እውነት በህዝባችን ውስጥ ያለው ስፍራ ከፍ ያለ ነው።
ይህ እሴት በማህበረሰባችን ውስጥ ለመጎልበቱ አንድም አብዛኛው ህዝባችን ሃይማኖተኛ የመሆኑ እውነታ ፣ ከዚህም በላይ እንደ ህዝብ ያለን ማህበራዊ መስተጋብር ጠንካራ መሆኑ ይታወቃል። የቀደመው ዘመን የሞራል አስተምህሮ የፈጠረው ተጽእኖ ቀላል እንዳልሆነ ይታመናል።
ይህ ማህበረሰባዊ አሴታችን ከሀገር ቤት ውጭም በተቀረው ዓለም እንደ አንድ የኢትዮጵያዊነት መገለጫ ተደርጎ ይወሰድ እንደነበር የተለያዩ የታሪክ መዛግብት ይመሰክራሉ። የጨዋነታችን መገለጫ ተደርጎ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ይወሰድ እንደነበርም ይነገራል። ይህ እውነታ አሁንም ቢሆን መታደስ የሚፈልግ እንጂ የነጠፈ እንዳልሆነም ብዙዎች ይስማማሉ።
ባለፉት 50 ዓመታት እንደ ሀገር የሄድንባቸው የተቀዱ የፖለቲካ አስተሳሰቦች በአንድ በኩል፤ በሌላ በኩል ደግሞ አስተሳሰቦቹ በማህበረሰባችን የሞራል ስብእና ላይ የፈጠሩት ፅልመት ህዝባችን በሚጠየፈው የውሸት ትርክቶች ሰለባ እንዲሆን ተደርጓል።
በተለይም ባለፉት 27 ዓመታት ሀገርና ህዝብን ለመከፋፈል በተጠና መልኩ በተደረገው ከፍ ያለ የሴራ ፖለቲካ ህዝባችን ከሚጠየፈው እውነታ ጋር ፊት ለፊት ተጋፍጧል ፤ ከፍ ያለ ዋጋም ለመክፈል ተገድዷል። በከፈለውም ዋጋ ሀገሩን ከጥፋት ታድጎ ለማስቀጠል ችሏል።
ይህንን ከጥቂት ቡድኖች እና ግለሰቦች የተዛባ የአስተሳሰብ ስሌት የመነጨ ሞራል አልባነት ወደ ህዝቡ ለማጋባት የተሄደበት ርቀትም ረጅም እንደሆነ፤ መላው ህዝባችን በዘመናት ውስጥ ለሞራላዊ እሴቶቹ ከነበረው ከፍ ያለ መታመን የተነሳ ማህበረሰባዊ ቁመናው ብዙ መዛነፍ ሳይደርስበት ቆሞ መሄድ ችሏል።
ከሁሉም በላይ የሚያሳዝነው ህዝብ እወክላለሁ የሚሉ ቡድኖችና ግለሰቦች በራሳቸው የሴራ መንገድ ተጠልፈው ህዝባችን እንደ ህዝብ በሚጠየፈው ውሸትና የውሸት ትርክት አደባባዮችን ሞልተው መታየታቸው፤ ይህንንም እውነታ ለማስተዋልና ለመመለስ ጊዜና የሞራል አቅም ማጣታቸው ነው።
በተለይም አሸባሪው ህውሓት ከውልደቱ ጀምሮ የተነሳበት የፖለቲካ አስተሳሰብና አስተሳሰቡ የፈጠረው የተበላሸ የአእምሮ ውቅር በትግራይ ህዝብ የሞራል እሴቶች ላይ ከፍ ያለ ተግዳሮት መፍጠሩ ይታመናል፤ እውነታው እንኳን ተራውን ህዝብ የሃይማኖት ተቋማትን የሚያገለግሉ አገልጋዮችን ጭምር በእጅጉ የተፈታተነ ነበር።
ቡድኑ ገና በበረሀ ትግል ውስጥ እያለ በትግሉ አሸናፊ ሆኖ ለመውጣት የፈጠራቸው የውሸት ትርክቶች ሀገርን እንደ ሀገር ለማስቀጠል ከፍ ያሉ ስጋቶች እንደነበሩ የቅርብ ጊዜ ትዝታዎች ናቸው። እነዚህ ስጋቶች ዛሬም ቢሆን ጥላቸው ከሀገሪቱ ፖለቲካ ላይ ሙሉ በሙሉ አልተገፈፈም።
ዛሬ ላይ ደግሞ ወቅታዊ ፖለቲካን በአግባቡ ካለመረዳት እና በተሳሳተ የማንነት ትርክት ስካር በተፈጠረበት ቀውስ ራሱንና ሀገርን ወዳልተገባ መንገድ በመውሰድ ከሁሉም በላይ የትግራይ ህዝብ ያልተገባ ዋጋ እንዲከፍል እያደረገው ነው። የትግራይን ህዝብ ትውልድ አልባ በሚያደርግ የጥፋት መንገድ ውስጥ ከገባም ሰነባብቷል።
ከሁሉም የሚከፋው ደግሞ ቡድኑ ዛሬም ወቅታዊ ፖለቲካን በአግባቡ ካለመረዳት እና በተሳሳተ የማንነት ትርክት ስካር ከተፈጠረበት ቀውስ ለመውጣት ውሸትንና የውሸት ትርክቶችን እንደ ዋንኛ የፖለቲካ አቅም አድርጎ የመጠቀሙ እውነታ ነው። ይህ ከቀደመው ታሪክ ስህተት ያለመማር እርግማን ነው።
ይህ ኃይል በ21ኛው ክፍለ ዘመን በመረጃ ዘመን ውስጥ ሆኖ ከዛሬ 40 እና 50 ዓመታት በፊት የነበረውን ተሞክሮዎችን ዳግም ለመተግበር የሚያደርገው ጥረት አንድም ቆሞ ቀር መሆኑን በተጨባጭ የሚያመላክት ሲሆን ከዚህም በላይ ቡድኑ እወክለዋለሁ ለሚለው ህዝብ ንቃተ ህሊና ያለውን ንቀት የሚያሳይ ነው።
ቡድኑ ለሥልጣን ከነበረው ከፍ ያለ ጥማት የተነሳ በቀደመው ዘመን በፈጠራቸው የውሸት ትርክቶች የትግራይን ህዝብ የቱን ያህል ዋጋ እንዳስከፈለ ከሁሉም በላይ የትግራይ እናቶች የሚያውቁት የአደባባይ ሚስጥር ነው። በስልጣን በነበረባቸው 27 ዓመታትም የትግራይ እናቶች ከከፈሉት ዋጋ ያተረፉት ምንም እንደሆነ ለማንም የተሰወረ አይደለም ።
የበለጠ አሳፋሪና አሳዛኝ የሆነው ደግሞ አሁንም ቡድኑ በሚፈጥራቸው የውሸት ትርክቶች የትግራይ እናቶች ልጆቻቸውን እየገበሩ የመገኘታቸው እውነታ ነው። ዛሬም መሳሪያ ለመሸከም የስነ ልቦናም ሆነ የአካል ዝግጁነት የሌላቸውን ልጆቻቸውን ከጉያቸው እየነጠቀ የቡድኑ ቀብር ማድመቂያ እያደረጋቸው ይገኛል።
ቡድኑ ተፈጥሯዊ ሞቱን ሞቶ ከተቀበረበት ጉድጓድ ለመውጣት በሚያደርገው ውጤት አልባ ድካም የትግራይን ወጣት ወደ ሞት እየነዳ ነው። የዚህ ችግር ዋነኛ ባለቤት የትግራይ ህዝብ ከመሆኑ አንጻር ህዝቡ ወደ ቀልቡ በመመለስ በቃ ሊለው ይገባል። በዚህም ትውልዱን ካልተጋባ እልቂት መታደግ ይጠበቅበታል። ለዚህ የሚሆን የሞራል እሴት ባለቤት ነው !
አዲስ ዘመን መስከረም 7 ቀን 2014 ዓ.ም