ጎንደር፡- በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ጎንደር ከተማ በቀን ከ10 ሺ ሊትር በላይ ዘይት የሚያመርት ፋብሪካ ዛሬ ተመርቆ ስራ ጀመረ፡፡
የፌደራል ህብረት ስራ ኤጀንሲ ዋና ዳሬክተር አቶ ኡስማን ሱሩር በምረቃው ወቅት እንደተናገሩት በፀሀይ ሁለገብ የገበሬዎች ኅብረት ስራ ዩኒዬን የተገነባው የዘይት ማምረቻ ፋብሪካ በአመት 80ሺህ ኩንታል የቅባት እህል በግብአትነት የሚጠቀም ሲሆን በቀን ከ10 ሺህ ሊትር በላይ የምግብ ዘይት ማምረት ይችላል፡፡
ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገበት ፋብሪካው ኑግ፣ ለውዝ፣ ሱፍና ሰሊጥን ጨምሮ ሰባት አይነት የቅባት እህሎችን አበጥሮ፣ ፈጭቶና ራሱ በሚያመርታቸው ከግማሽ ሊትር እስከ ሀያ ሊትር በሚይዙ የፕላስቲክ መያዣዎች አሽጎ ለሀገር ውስጥና ለውጪ ገበያ ያቀርባል፡፡ ፋብሪካው በሀገሪቱ የሰሊጥ ዘይት በማምረት የመጀመሪያው ሲሆን ለ52 ቋሚና 24 ግዚያዊ ሰራተኞች የስራ እድል ከፍቷል፡፡
የፀሀይ ሁለገብ የገበሬዎች ኅብረት ስራ ዩኒዬን ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ እንዳልካቸው አቤ በበኩላቸው ፋብሪካው በሙሉ አቅሙ ወደ ማምረት ስራ ሲገባ በዘይት ምርቶች ግብይት ረገድ የሚታየውን ያልተመጣጠነ አቅርቦትና የተጋነነ ዋጋ በማስተካከል መፍትሔ እንደሚሆንና አብዛኛውን ግብአት በአካባቢው ካሉአርሶአደሮች የሚጠቀም በመሆኑ በአካባቢው ላሉ የቅባት እህል ምራቾችም የተረጋጋ ገበያ ለመፍጠር እንደሚጠቅም ተነግሯል፡፡
በራስወርቅሙሉጌታ