የቅድመ ውድድር አካል የሆኑት የሲቲ ካፕ ጨዋታዎች በተያዘው ወር አጋማሽ እንደሚካሄዱ ታውቋል። የአዲስ አበባ እና ሲዳማ ሲቲ ካፕ ጨዋታዎች የፕሪሚየር ሊጉን ተሳታፊ ክለቦች እንዲሁም የጎረቤት አገር ክለቦችን በመጋበዝ የሚካሄዱም ይሆናል።
በኢትዮጵያ የሊግ ውድድሮች ዓመታዊ መርሃግብር ከመጀመሩ አስቀድሞ ክለቦችን ወደ ውድድር ሊያንደረድራቸው የሚችልና ዝግጅታቸውንም የሚመለከቱባቸው ከተማ አቀፍ ውድድሮችን ማካሄድ የተለመደ ነው። ይኸው ልምድ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ከመጀመሩ አስቀድሞ የሚካሄድ ሲሆን፤ የዘንድሮ የውድድር ዓመት ከመጀመሩ አስቀድሞም ሁለት የሲቲ ካፕ ውድድሮች በተያዘው ወር አጋማሽ (በቀጣዩ ሳምንት መጨረሻ) የሚጀመሩ መሆናቸውን ሶከር ኢትዮጵያ በዘገባው አስነብቧል።
በሲቲ ካፕ ውድድር ታሪክ ከፍተኛ ልምድ ያካበተውና ለዓመታት ሲካሄድ የቆየው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ትልቅ ትኩረት የሚሰጠው መሆኑ ይታወቃል። በአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የሚዘጋጀው ይህ ውድድር በዋናነት ከተማውን ወክለው በፕሪሚየር ሊጉ ተሳታፊ የሚሆኑ ክለቦችን በቅድመ ውድድር ራሳቸውን እንዲገመግሙ ለማገዝ የሚካሄድ ነው። ከከተማዋ ክለቦች ባሻገር ሌሎች የሊግ ተሳታፊ ክለቦችም በተጋባዥነት በሚሳተፉበት በዚህ ውድድር ክለቦች ከፍተኛ ፉክክር የሚያደርጉበትና ሳቢ ውድድር የሚታይበት መሆኑን ባለፉት ዓመታት ውድድሮች መታዘብ ተችሏል። ከሳምንት በኋላም ፌዴሬሽኑ ይህንን ውድድር ለማካሄድ ዝግጅቱን በማጠናቀቅ ላይ እንደሚገኝም አሳውቋል።
በዚህ ዓመትም በተመሳሳይ የአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የቅድመ ውድድር ጨዋታ ያዘጋጀ ሲሆን፤ ከአገር ውስጥ ክለቦች በተጨማሪ ከጎረቤት አገራትም የእግር ኳስ ክለቦችን ለማሳተፍ ጥሪ የቀረበ መሆኑ ታውቋል። በውድድሩ ላይ እንዲካፈሉ ጥያቄ የቀረበላቸው ሁለቱ ተጋባዥ ክለቦች የኤርትራ እና ደቡብ ሱዳን ክለቦች ናቸው። በዚህም ሙኑኪ ኤፍ ሲ የተባለው የደቡብ ሱዳኑ ክለብ በውድድሩ መሳተፉን ማረጋገጫ ሲሰጥ የኤርትራው ክለብ በቅርቡ ምላሹን እንደሚሰጥ ታውቋል።
ከጎረቤት አገራት ተጋባዥ ክለቦች ባለፈ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ተሳታፊ የሆኑ ሰባት ክለቦች በአዲስ አበባ ዋንጫ ተሳታፊዎች ናቸው። ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ኢትዮጵያ ቡና፣ አዲስ አበባ ከተማ፣ መከላከያ፣ ወልቂጤ ከተማ፣ አዳማ ከተማ እና ባህር ዳር ከተማ ከፌዴሬሽኑ የቀረበላቸውን የተሳትፎ ጥያቄ እንደተቀበሉ ተጠቁሟል። በውድድሩ የሚሳተፉት ክለቦች በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የመሰብሰቢያ አዳራሽ ተገኝተው የደንብ ውይይት የሚያደርጉም ይሆናል። ውድድሩን ከመስከረም 15 እስከ 30/2014ዓ.ም ድረስ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ለማካሄድም ነው የታቀደው።
ሌላኛው ሲቲ ካፕ ውድድር ለመጀመሪያ ጊዜ በሲዳማ ክልል የሚካሄድ ሲሆን፤ በሃዋሳ ከተማ በቤት ኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ተሳታፊ ክለቦች መካከል ይደረጋል። ከመስከረም 16 እስከ መስከረም 25/2014ዓ.ም ድረስ በሚደረገው ውድድር ላይ ስምንት ክለቦችን ለማሳተፍ በታቀደው መሰረት ጥሪ የቀረበላቸው ክለቦች ምላሽ መስጠታቸውን የክልሉ ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አንበሴ አበበ ማረጋገጣቸውን የሶከር ኢትዮጵያ ዘገባ ያመላክታል። ተሳታፊዎቹም የክልሉ ክለቦች የሆኑት ሀዋሳ ከተማ እና ሲዳማ ቡናን ጨምሮ ወላይታ ድቻ፣ ሀድያ ሆሳዕና፣ ባህርዳር ከተማ፣ ወልቂጤ ከተማ፣ ሰበታ ከተማ እና ድሬዳዋ ከተማ ናቸው። ይሁን እንጂ ወልቂጤ እና ባርዳር ከተማ ክለቦች በአዲስ አበባ ሲቲ ካፕ ተሳታፊ እንደሚሆኑ በመጠቀሱ በትክክል በየትኛው ውድድር እንደሚሳተፉ በቅርቡ የሚለይ ይሆናል።
በሁለት ምድብ ተከፋፍሎ የሚካሄደው ይህ ውድድር፤ አሸናፊ ለሚሆነው ክለብ ከሚዘጋጀው የዋንጫ ሽልማት በተጨማሪ ለኮከብ ተጫዋች፣ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ፣ ምርጥ ግብ ጠባቂ እና አሰልጣኝነት ለሚመረጡ ሽልማት መዘጋጀቱንም ታውቋል። ከተቋቋመ አንደኛ ዓመቱን በቅርቡ ያከበረው የሲዳማ ክልል እግር ኳስ ፌዴሬሽን በአጭር ጊዜ ውስጥ በርካታ የውስጥ እና አገር አቀፍ ውድድሮችን በማዘጋጀት መልካም የሚባል ሥራ እያከናወነ ይገኛል። ከአመርቂ ሥራዎቹ መካከል አንዱ የሆነውን የሲቲ ካፕ ውድድርም እንደሌሎች አካባቢዎች ሁሉ ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ ማዘጋጀቱ ተጠቃሽ ነው።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን መስከረም 6/2014