የትግራይ ምድር እንደ ሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎች ሁሉ በቀላሉ ታርሶ ፍሬ የሚሰጥ አይደለም። መሬቱ ለምነቱን ያጣ፣ ድንጋያማና እርጥበት አጠር በመሆኑ አርሶ አደሩን ብዙ ያደክማል። ዳሩ ‹‹ላይችል አይሰጥ›› ነውና ተረቱ ጠንካራው የትግራይ አርሶ አደር ጾም አያድርም። ብዙ ኪሎ ሜትሮችን በባዶ እግሩ ተጉዞ ወንዝ ካለበት፤ ደለልና ውሃ በጫንቃው ተሸክሞ በማምጣት ድንጋዩ ላይ እየደለደለ ጭምር ከተፈጥሮ ጋር ታግሎ ያመርታል።በዚህም የአርሶ አደሩን ጥንካሬና ብርታት መመስከር ይቻላል።
እንዲህ ባለ ትግል ውስጥ የሚታረሰው መሬት እንዲታረስና አጠቃላይ የግብርና ሥራው በወቅቱ እንዲከናወን በሚል መንግስት በክልሉ እየወሰደ ያለውን ህግ ማስከበር ዘመቻ ገታ ማድረጉ ይታወሳል። መንግስት ይህን ውሳኔ ሲያሳልፍ ለአሸባሪው ቡድን የጽሞና (የንሰሀ) ጊዜ ከመስጠት ባሻገር በዋናነት አርሶ አደሩ የጀመረውን የእርሻ ሥራ የሚያጠናቅቅበትን ዕድል መቸርን ታሳቢ አድርጎ ነበር።
የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ከክልሉ ጓዙን ጠቅልሎ እስከ ወጣበት ጊዜ ድረስ ያልታረሰና በዘር ያልተሸፈነ መሬት በአካባቢው መኖሩ ሳይዘነጋ 700 ሺ ሄክታር መሬት መታረሱን እና 200 ሺ ሄክታር መሬት ደግሞ በዘር መሸፈኑን የግብርና ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል። ታዲያ ይሄ ቡቃያ አብቦ ፍሬ ሲያፈራ የጎሞራውን ፍሬም በቅርቡ ሊከሰት ከሚችል አንበጣ መታደግና ለውጤት ማብቃትን ታሳቢ ተደርጎ በመንግስት በኩል የተናጠል ተኩስ አቁም ተደርጓል፡፡
‹‹በጥባጭ ካለ ማን ጥሩ ይጠጣል›› እንዲሉ አሸባሪው ህውሓት በፍፁም አርሶ አደሩ ተረጋግቶ እርሻውን እንዲያርስ አላስቻለውም። በዚህ ምክንያት ሕዝቡም አርሶ አደሩም የረሃብ አደጋ እየተጋረጠበት ይገኛል። ከዚህም በላይ አርሶ አደሩ እርሻውን ትቶ ለጦርነት እንዲሰለፍ መገደዱን በመረጃዎች ይጠቁማሉ። ሁኔታው በትግራይ ክልል ካለው አንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ሄክታር አጠቃላይ የሚታረስ መሬት ጋር ሲደመር በቀጣይ ችግሩን የከፋ እንደሚያደርገው በግብርና ሚኒስቴር የሰብል ልማት ዳይሬክተር አቶ ኢሳያስ ለማ ይናገራሉ።
ትግራይ በዓመት አንዴ በመህር ምርት ብቻ ተሳታፊ ከመሆኑ አንፃር ጉዳዩ አብዝቶ የሚያሳስብ ነው። ክልሉ በምግብ ራሱን የሚችል ካለመሆኑና አሸባሪው ህውሓት ካስገባው የጦርነት አጣብቂኝ ጋር ተያይዞ ይበልጥ ለተረጂነት ያጋልጠዋል። ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የወጣው መረጃ እንደሚያመለክተው በሰላማዊ ጊዜ 1/3ኛ የሚሆነው የክልሉ ህዝብ በሴፍትኔት ድጋፍ የሚደረግለት ነው። ባለፈው የምርት ወቅትም በአንበጣ መንጋና በኮሮና ምክንያት ህዝቡ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ጉዳት አግኝቶታል። በዚህ ላይ የመህር የእርሻ ወቅት በባህርይው በጎተራው ያለው እህል የሚሟጠጥበት የተዘራው ያልደረሰበት ወቅት ነው።
በትግራይ ከተጀመረው ህግ የማስከበር ዘመቻ በኋላ አርሶ አደሩ የግብርና ሥራውን ሳይረጋጋ እያሳለፈው ይገኛል፡፡ በመሆኑም በክልሉ ሊከሰት የሚችለው ቀውስ መንግስትን አብዝቶ ሲያሳስበው ከርሟል። የተናጥል የተኩስ አቁም አድርጎ መከላከያን ከትግራይ አካባቢዎች እንዲወጣ የወሰነውም ለዚሁ ነው የሚሉት የአማራ ክልል ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተርና ተመራማሪ ዶክተር ኤርሚያስ አባተ ናቸው፡፡ እንደሳቸው ገለጻ፤ ውሳኔው የተቀደሰ፣ ትክክለኛና የሚደገፍ ነው። ከክልሉ ተጨባጭ ሁኔታ ጋር በሚገባ መገናዘቡንም ማየት ይቻላል። 83 ከመቶ ህዝብ በግብርና ተሰማርቶ በገጠር በሚኖርበት ሁኔታ ግድና ተገቢም ነው። የውጭ ኃይሎች ይህን ዕውነታ ተረድተው ሊደግፉት ይገባል።
ከምንም ነገር አስቀድሞ መሬት ላይ ያለውን እውነታ ማገናዘብ ያስፈልጋል። ከአማራ ክልል በመነሳት ዋግ ህምራን ይዞ ትግራይ ሲዘለቅ ትውልድ ለረጅም ዘመን የሰፈረበትና የኖረበት ነው። በመሆኑም ለረጅም ዘመናት ሲታረስ ቆይቷል። በዚህም አካባቢው የአፈር ለምነቱን አጥቷል። በክልሉ ያለው የዝናብ ስርጭት መጠንም አነስተኛ ነው። በመሆኑም ድርቅ በሌለበት ጊዜ እንኳን በትግራይ የሚገኘው ምርት አነስተኛ ነው። በአካባቢው ላይ የህዝብ ቁጥሩ እየጨመረ በመሄዱ የነፍስ ወከፍ መሬት ይዞታውም እጅግ አነስተኛ ነው። በአካባቢው የሚመረተው የግብርና ምርት የአርሶ አደሩን የቤተሰብ ምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ ያስቸግራል።
ጥሪቱ የተሟጠጠ በመሆኑ ድርቅም ሆነ ጦርነት ሳይኖር ከፍተኛ ቁጥር ያለው የክልሉ ነዋሪ በምግብ እህል እየተረዳ ነው ህይወቱን የሚያስቀጥለው። የአንበጣ ወረርሽኝ በሚከሰትበት ጊዜ፣ በሰላም እጦት፣ በተለያየ ምክንያት መደበኛ የእርሻ ሥራው በማይከናወንበት ጊዜ የምግብ ዋስትና እጥረት ከፍተኛ ደረጃ ስለሚያደርሰው የአርሶ አደሩ ቤተሰብ በአጠቃላይ ህዝቡ በረሀብ ይጎዳል። ባለማምረቱ የረሃብ ተጋላጭነቱ በአምናና ዘንድሮ ብቻ ሳይወሰን በመጪዎቹ ዓመታት የሚቀጥል መሆኑን መረጃዎች ያመላክታሉ።
‹‹አርሶ አደሩ መኖር አለበት›› የሚሉት ዶክተር ኤርሚያስ አርሶ አደሩ ሥራውን እንዳይሰራ እንቅፋት የሆነበት ኃይል እውነት ከአብራኩ ወጥቻለሁና አስብለታለሁ የሚል ከሆነ ጦርነቱን አቁሞ እርሻውን እንዲያርስ በማድረግ ወገንተኝነቱን ማሳየት አለበት። ቢያንስ አርሶ አደሩን የእርሻ ሥራው ሳይስተጓጎል እርሻው ላይ እንዲቆይ ማድረግ ይኖርበታል። ህዝቡ ለረሀብና ተያያዥ ለሆኑ ችግሮች ተጋላጭ እንዳይሆን ማድረግ ተገቢም ሰብዓዊም ነው። ኃይሉ እታገልለታለሁ ለሚለው ህዝብ የሚያስብ ከሆነ የተናጥል ተኩስ አቁሙ መቀጠል ነበረበት።
አብዛኛው የትግራይ አካባቢ፣ ሰሜን ጎንደር፣ ዋግ ህምራ አካባቢዎች አምና በበረሃ አንበጣም የተጠቁበት ሁኔታ መኖሩን ኃይሉ ሊያገናዝብ ይገባ እንደነበርም ያወሳሉ። እንደ ዶክተር ኤርሚያስ ማብራሪያ በአካባቢው የበረሀ አንበጣ እንቅስቃሴ ሊከሰት እንደሚችል የሚያሳዩ ትንበያዎችን ጨምሮ የምግብ ዋስትናን አደጋ ውስጥ ከመክተት ጋር የተያያዙ ብዙ ስጋቶች አሉ። እንደ ትንበያው አንበጣው መራባት ደረጃ ላይ ደርሷል። የክረምቱን ዝናብ ተጠቅሞ ሀገር ውስጥ የሚፈለፈልበት ሁኔታ መኖሩን ማሰብ አይከፋም። ደግሞም በባህርይው በነፋስ ኃይል የሚመጣበት ሁኔታ መኖሩንና በተለምዶ ይታወቃል፡፡ እናም የተዘራውን በከፍተኛ ሁኔታ ለጥፋት ሊዳርገው ይችላል። የፀጥታው ችግር አንበጣ ቁጥጥሩ ላይም ተፅዕኖ ስለሚያደርግ መከላከሉ ሊያስቸግር ይችላል።
በመሆኑም መንግስትና የእርዳታ ድርጅቶች በተቀናጀ ሁኔታ ሊገቡበት ይገባል። ሌላው ቀርቶ በክረምቱ ወቅት ምርት ከጎተራ የሚያልቅበት፣ የተዘራው ያልደረሰበት በመሆኑ በውሃና በምግብ ዋስትና ችግር በተደጋጋሚ ለሚጠቃው ትግራይ ክልል ቀርቶ ትርፍ አምራች ናቸው በሚባሉ የሀገሪቱ ክልሎችም የምግብ እጥረት ሊገጥም መቻሉን ማሰቡ ብልህነት ነው።
ጦርነቱ በክልሉ ያለውን የምግብ ዋስትና በእጅጉ ሊያባብሰው ይችላል፡፡ ህዝቡ ለረሃብ እንዳይጋለጥም መንግስት በአካባቢው የማዳበሪያ፣ የምርጥ ዘርና ሌሎች ችግሮች እንዳያጋጥሙ ሥራ ሲሰራ እንደነበር ተናግረዋል። መንግስት የተናጠል የተኩስ አቁሙን ከማድረጉ በፊት ህዝቡ ለአስከፊ ረሃብ እንዳይጋለጥና እንቅስቃሴው እንዳይስተጓጎል መቐለ ውስጥ አራት መቶ ሺ ኩንታል የእርዳታ እህል፣ 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሊትር የምግብ ዘይት፣ 14 ሚሊዮን ሊትር ነዳጅ፣ 536 ሺ 979 ኩንታል ማዳበሪያና 37 ሺህ 599 ኩንታል ምርጥ ዘር ለህዝቡ ደህንነት ሲል በራሱ ገንዘብ ገዝቶ ማቅረቡም ይታወቃል።
ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የተገኘው መረጃም መታረስ ከሚችለው መሬት 70 በመቶው እንዲታረስም ያደረገበት ሁኔታ አለ። በተጨማሪም አንድ ሺ 79 ሜትሪክ ቶን ምግብ፣ 664 ቶን ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶችና 47 ሺ 740 ሊትር ነዳጅ በአጋር አካላት በኩል መቐለ እንዲገባ ያደረገበት ተጠቃሽ ነው። መንግስት መከላከያ ከወጣም በኋላ መንገዶችን በማመቻቸት የእርዳታ አቅርቦት እንዳይቋረጥ በመስራቱ የሚወቀስበት ምክንያት የለም። ለሰብዓዊ እርዳታም የሚሆን የአውሮፕላን በረራም ፈቅዷል። ይህን ሁሉ ያደረገው በትግራይ ክልል ያለው ህዝብ እንዳይቸገር በማሰብ ነው።
ዶክተር ኤርሚያስ አያይዘው ሁሉም ሊተገበር የሚችለው ሰላም ሲኖር እንደሆነ በማንሳት በተለያየ መረጃ እንደሚሰማው አሁን ላይ ኃይሉ ለዚህ ሰላም እንቅፋት በመሆኑ በተለይ ህጻናትና ሴቶች በከፍተኛ ሁኔታ ለጥቃት እየተጋለጡ ይገኛሉ። በመሆኑም መንግስት እንደወሰነው አርሶ አደሩ ከእርሻ ውጪ መሆን የለበትም። የምግብ እጥረቱ አርሶ አደሩ ምርታማ ሆኖ የግብርና ሥራውን ማከናወን እንዳይችል ማድረግ የለበትም። የምግብ እርዳታ ሊደርስ የሚችልበት መንገድ መመቻቸት ይኖርበታል። የቤተሰብ ምግብ ዋስትናው ለአደጋ ተጋላጭ እንዳይሆን ማድረግም ያስፈልጋል። በቅንጅት የአርሶ አደሩን ሕይወት ለመታደግ የሚያስችሉ ሥራዎችም መሰራት አለባቸው።
በቀጣይ አካባቢውን የተላመዱና ለችግር ጊዜ የተሻለ ምርት የሚሰጡ የሰብል ዝርያዎችን ለማሳያነት የጠቀሱት ዶክተር ኤርሚያስ፤ እነዚህን ዝርያዎች በአሁኑ የመኽር ምርት ዘመን መጠቀም አይቻልም። ምክንያቱም አሁን የመኽሩ ምርት ወቅት አልቋል። ሆኖም በዘንድሮ መኽር መመረት ባይችሉም እነዚህን ዘሮች ከአርሶ አደሩ ሰብስቦና በመስኖም ቢሆን አባዝቶ መልሶ ለሰፊው አርሶ አደር ተደራሽ ማድረግ ያስፈልጋል። በአካባቢው የሚበቅሉና በቶሎ የሚደርሱ ማሽላ፣ ስንዴ፣ ዳጉሳ፣ ጤፍ በልዩ ትኩረት ተደራሽ መሆን አለባቸው፡፡ በቀጣይነት በአርሶ አደሩ ዘንድ በስፋት የሚመረቱ የአካባቢ ዝርያዎችን የግብርና ተቋም ምርምርና የኤክስቴንሽን ዘር አባዥ አካላትም በልዩ ትኩረት መኽሩ ስላለፈ በመስኖም ቢሆን በማባዛት እነዚህ አካባቢዎች ላይ ከሌላ አካባቢ በተለየ ሁኔታ መታየት አለበት፡፡
ብዙ ጊዜ መደበኛ ዘር አባዥዎች የሚያባዙትና የሚያሰራጩት ዝርያዎች በምርምር የተረጋገጡ፤ በምርምር የወጡና፣ ውጤታማነታቸው የተመሰ ከረላቸውን ዘሮች ብቻ ነው፡፡ ሆኖም ከእነዚህ በተጨማሪ የዝናብ እጥረትና አፈር ለምነት ባለባቸው እንደ ትግራይ ባሉ አካባቢዎች ከትውልድ ትውልድ እየተወራረሱ የመጡና በአካባቢው የተለመዱ፤ ድርቅንና የአፈር ለምነትን የሚቋቋሙ፣ ዝርያዎች አሉ። እነዚህን ዝርያዎች የዘር አባዥዎች አያባዟቸውም። በመሆኑም እነዚህን ዘሮች በመሰብሰብ በቀጣይ መኽር የዘር ችግር እንዳይደርስ በመስኖ በማባዛት ለአርሶ አደሩ እንዲደርስ ማድረግ ያስፈልጋል።
በተጨማሪም ለእነዚህ አካባቢዎች ተብለው በምርምር የተለቀቁ ዝርያዎች አሉ። ለምሳሌ፦ ከመካከላቸው የገብስ፣ የስንዴ፣ የማሽላና የዳጉሳን ዘር መጥቀስ ይቻላል። እነዚህ ለድርቅ ተጋላጭ ለሆኑና የአፈር ለምነታቸው ለተሟጠጠ አካባቢዎች የሚቀርቡ ዝርያዎች ናቸው። መደበኛው የግብርና ኤክስቴንሽን ከሚሰጣቸው ድጋፍ በተጨማሪ አርሶ አደሩ የራሱ የሆኑ ለዘመናት በመጠቀም ሲያመርታቸው የቆዩ ናቸው። ድርቅን መቋቋምና የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ያስችሉታል። አርሶ አደሩ እነዚህን ዝርያዎች በቀጣይ ለዘር መጠቀም ካልቻለ ዘሮቹ ይጠፉበታል። በመሆኑም እነዚህን የሰብል ዝርያዎች እንዳያጣም ሰፊ ሥራ መሰራት አለበት።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 13 ቀን 2013 ዓ.ም