ክፍል አንድ
እኛ ኢትዮጵያውያን እንደ ግለሰብ ፣ ቤተሰብ ፣ ማህበረሰብ ከፍ ሲልም እንደ ሀገር ከክርስቶስ ልደት ወዲህ አዲስ ዓመትን ስንቀበል ስንሸኝ ፣ ስናከብር ስንዘክር፣ ለለውጥ ቃል ስንገባ ቃል ስናጥፍ ፣ ስናቅድ ስንፈፅም ፣ ስናቅድ ስንከሽፍ ፣ ተስፋ ስንሰንቅ ፣ ተስፋ ስንቆርጥ ፣ ስናልም ስንቃዥ ፣ ወዘተረፈ ቅዳሜ መስከረም 1 ቀን ሁለት ሺህ አስራ አራት/2014 /ዓመት ሞላን።
እንደ ሀገርም ሆነ ህዝብ ለዚህን ያህል ዓመት እንደ ሀምሌ አኝኝ…በሚል ሁኔታ አልፈን ለአደይ አበባ፣ ለጠራ ሰማይ ፣ ኩልል ላለ ምንጭ ፣ ብሩህ ለሆነ ቀን፣ ለጠባ መስከረም ደርሰናል። የዘንድሮው አዲስ ዓመትም ከዚህ ብዙም የተለየ አይደለም። ኡደቱ ከርሞም ይቀጥላል። ክረምት ይገባል። ክረምት ይወጣል። አደይ ያብባል። አደይ ይረግፋል።
ከዛሬ 2014 ዓመታት በፊት የባተ አዲስ ዓመትን እንደ አዲስ ዓመት ብቻ ካየነው ከዘንድሮው ያን ያህል የተለየ አይደለም። የዛን ጊዜም አደይ አብቧል። ዘንድሮም አብቧል። እንደ ጥንቱ ነዝናዛው ሀምሌ ሄዶ ፍልቅልቁ መስከረም ገብቷል። የዳመና ቡልኮውን ገፎ የጠራ ሰማይ ዘርግቷል። ተፈጥሮ የኡደት ምህዋሩን አልቀየረም።
በመሬት መራቆት ፣ በደን መጨፍጨፍ ፣ በአየር መበከልና በከባቢ አየር ሙቀት መጨመር የመጣው መዛነፍ እንዳለ ሆኖ። የሰው ልጅና ለውጥ ግን ከዚህ ተፈጥሮአዊና መደበኛ ኡደት የተለየና ፈጣን ነው። ዳሩ ግን ይህ ለውጥ እንደየ ሀገራቱና ሕዝቡ ውቅር ይለያል።
ከእንግሊዝ ፣ ከፈረንሳይ እና ከዩናይትድ ስቴትስ አብዮቶች በኋላ በተለይ ከእንግሊዝ የኢንዱስትሪ አብዮት መባት ጋር ተያይዞ በአውሮፓና በሰሜን አሜሪካ ፈጣን የኢኮኖሚ ፣ የፖለቲካና የማህበራዊ ለውጥ ተመዝግቧል። ከ30 ዓመታት ባልበለጠ ጊዜ ቻይና ወደ 20 ትሪሊዮን ዶላር በሚጠጋ ጥቅል የሀገር ውስጥ ምርት በምድራችን ግዙፉንና ሁለተኛውን ኢኮኖሚ መገንባት ችላለች።
ለዴንግ ዣውፒንግ ምስጋና ይግባቸውና። ጃፓንና ደቡብ ኮሪያ ከግማሽ ክፍለ ዘመን በፊት በሁሉም ዘርፍ ከሀገራችን ብዙም የተሻሉ አልነበሩም። ዛሬ የጃፓን ኢኮኖሚ ከአሜሪካና ቻይና ለጥቆ ሶስተኛውና ግዙፉ አኮኖሚ ነው። ደቡብ ኮሪያ ደግሞ በዓለማችን ግዙፍ ኢኮኖሚ ካነጹ 20 ሀገራት አንዷ ሆናለች ።
ታዲያ አህጉራችን በተለይ ሀገራችን እንዲህ ላለ ሁለንተናዊ ድህነት ለምን ተዳረገች ? በፈጣሪ ቁጣና እርግማን … ? አፍሪካዊ ስለሆነች … ? ከሰሀራ በታች ስለምትገኝ … ? ቀውስ በማይለየው የአፍሪካ ቀንድ ስለኖረች … ? እረ በፍጹም። ታዲያ ለምን ከእነ ሴራሊዎን፣ ማላዊ ፣ የመን ፣ ደቡብ ሱዳን ፣ ሶማሊያ የድህነት ተርታ ጋር ተዳበለች … ? ከታላቁ የአክሱማይት ስልጣኔ እንዴት ተንኮታኮተች … ?
ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ” ጃፓናይዘርስ “/ የጃፓን መንገድ ተከታዮች / የሚሏቸው ፤ ነጋድራስ ገብረህይወት ባይከዳኝ የ” መንግስትና የህዝብ አስተዳደር “ እንዲሁም “ የ” አጤ ምኒልክና ኢትዮጵያ “ ደራሲ የሀገራቸው የኋላ ቀርነት ቁጭት ቢያንገበግባቸው ከ100 ዓመታት በፊት ለልጅ እያሱ አገዛዝ የልማት ፍኖተ ካርታ እንዲሆን ያሰናዱት ንድፈ ሃሳብ የፍላጎታቸውን ያህል ባይሳካም ግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ሃይለስላሴ ግን የተወሰነውን ለመተግበር መሞከራቸውን የኢኮኖሚክስ ምሁር የሆኑት ዶ/ር አለማየሁ ገዳ ይናገራሉ።
የደራሲ ከበደ ሚካኤል እና የሌሎች ለሀገራቸው እድገት ቀናኢ የሆኑ ኢትዮጵያውያን የጃፓንንም ሆነ የሌሎች ሀገራትን ስልጣኔ ወደ ሀገራቸው ለማምጣትና ለማላመድ ጥረት ሲያደርጉ ለምን እምዬ ኢትዮጵያ በጀ እንዳላለች ፣ ከዚህ ሲብስም ለምን ልበ ድንጋይና አንገተ ደንዳና ሆነች … ? ማገዶዋን ሁሉ ቆስቁሳ ቆስቁሳ ታዲያ የእድገት ገበር ምጣዷ ለምን አልሰማ አላት ? ከአክሱም ፍርስራሽ ተፍገምግሞ ለመነሳት ጉልበቷን ምን ያዘው …? ዘመናትን በጥልቅ ድባቴና እንቅልፍ ለምን አሳለፈች?
እነዚህ ጥያቄዎች በእያንዳንዳችን ህሊና የሚብላሉ ወደ ፊትም ሲብላሉ የሚኖሩ ናቸው። ግን ምን ነክቶን ነው … ? ምንም። ቀኝ አክራሪ የነጭ ለፋፊዎች/ ኋይት ሱፐርማሲስትስ / ፣ ናዚዎችና ፋሽስቶች እንደሚሉን ደደብ ስለሆን ነው … ? እረ በጭራሽ ፤ ታዲያ ምንድን ነው … ? የብልፅግናን አውራ ጎዳና ለምን ? ፣ መቼ ? ፣ እንዴት ? ፣ የት ? ፣ ማን ? አሳተን … ? ለአነኝህና እነኝህን መሰል ጥያቄዎች የጋራ መልስ ስናገኝ ነው ሚስጥሩ የሚመሰጠረው ፣ አይናችን የሚከፈተው ፣ ርዕያችን የሚገለጠው ፣ ቋጦራችን የሚፈታው ፣ ትብታባችን የሚፍታታው ፣ የጠፋው ውሉ የሚገኘው።
የድህነትን ቀለበት ሰብረን የምንወጣው ፣ የጥላቻንና የልዩነትን መጋረጃ የምንቀደው ፣ የዘውጌያዊነትን ባቢሎን የምናፈርሰው ፤ የመጠፋፋትና የደባ ፖለቲካን እርም የምንለው ፣ ወደ ቀደመው ከፍታችን የምናሰራራው፣ በድህነትና በኋላ ቀርነት የጠለሸውን ሉዓላዊነት የምናነጻው ፣ ከሁሉም በላይ እንደ ሀገሬ ጉብል ስፌት መለማመጃ በጅምር በውጥን የቀረውን የሀገረ መንግስት ግንባታ ለመጨረስ ፤ በአጠቃላይ ለሁለንተናችን መክፈቻ የሆነውን እና ለጊዜው የተሰወረብን ቁልፍ / ማስተር ኪይ / ሀገራዊ የልቦና ውቅራችን ነው። በስሩ ንዑሳን የልቦና ውቅሮች አሉ። የፖለቲካ ፣ የአስተዳደር ፣ የኢኮኖሚ ፣ የባህል፣ የስነ ልቦና ፣ የታሪክ ፣ ወዘተረፈ ውቅሮች። ለመሆኑ የውልጠት ሀዲድ የሆነው የልቦና ውቅር/ ማይንድሴት/ ምንድን ነው ?
በተለይ ከለውጡ ማግስት ጀምሮ ጽንሰ ሃሳቡ በልሒቃንና በሚዲያዎች ትኩረት ያገኘ ይመስላል። ሆኖም ሀረጉ ሲወሳ ቀድሞ ወደ አእምሮአችን የሚመጣው የሥነ አእምሮና ሥነ ልቦና አንሰላሳዩና ሃሳቡን በቀላሉ የማጋባት ተሰጥኦ የታደለው ዶ/ር ምህረት ደበበ ነው። ብዙዎቻችን ግን የፅንሰ ሃሳቡን ወሳኝነት በውል የተገነዘብነውና ያጤነው አይመስልም። ሀገራችን ለተያያዘችው ለውጥ የማዕዘን ራስ መሆኑን በቅጡ ልብ አላልነውም ።
ለእልፍ አእላፍ ዓመታት በአእምሯችን የተሰገሰገውን አሉታዊ የልቦና ውቅር መዋቅር በሒደት አፍርሰን በአዲስ ካልተካነው በዚች ሀገር ሀቀኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት፣ ፍትሐዊ ብልፅግናን ፣ ብሔራዊ እርቅና መግባባትን ፣ አንድነትን ፣ የመንግስትና የሀገረ መንግስት ግንባታችን ፣ ህዳሴን ፣ ወዘተረፈ በሙላት እውን ማድረግ አንችልም።
የተቀየረ የልቦና ውቅር እነዚህን ግቦች ለማሳካት መስፈንጠሪያ ሰሌዳ / ስፕሪንግ ቦርድ / ነውና። ለዚህ ነው ጽንሰ ሃሳቡ ከetv የቴሌቪዥን መርሀ ግብሮች በአንጻራዊነት የ” ልቦና ውቅር “ በተመልካች ተወዳጅ የሆነው። እንደ ዶ/ር አጥላው አለሙ ያሉ ልሒቃን ወደፊት በመምጣት የልቦና ውቅራችን የነገውን እጣ ፈንታችንን የመወሰን አቅም ያለው ወሳኝና ንኡድ ጽንሰ ሃሳብ መሆኑን መለፈፍ የጀመሩት። አስፈላጊነቱ የማያጠያይቅ መሆኑን ከማስገንዘብ ተሻግረው የአስተዳደር ወይስ የኢኮኖሚ ውቅራችን ነው መቅደም ያለበት ብለው መሞገት የወደዱት።
ምንም እንኳ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ሁሉንም የልቦና ውቅሮች በተመሳሳይ ጊዜ መሳ ለመሳ ለመቀየር የሚያደርጉትን አካሄድ ብደግፍ ዶ/ር አጥላው ያነሱት የቅደም ተከተል ጉዳይም ችላ የሚባል አይደለም። ለመሆኑ ይህ የችግሮቻችን ሁሉ መፍቻ የሆነው የልቦና ውቅር ምን ማለት ነው።
የሀረጉን ስረወ – ቃል / ኤቲሞሎጂ /ልቦና (ልቡና) እና ውቅር የሚሉ ቃላት ተዋህደው የፈጠሩት ነው። የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጥናትና ምርምር ማዕከል በ1993 ዓ.ም ባሳተመው የአማርኛ ቋንቋ መዝገበ ቃላት ልቦና ፦ ህሊና ወይም አእምሮ ፣ ውቅር ደግሞ ፦ የጣራ ውጥን፣ ጅምር ፣ የተወቀረ ማለት ነው ይለናል። ስለዚህ የልቦና ውቅር ፦ የአእምሮ ውጥን ፣ ጅምር ማለት ነው።
ዛሬ ላይ እጃችን የገባችው ሀገረ ኢትዮጵያ የአእምሮ፣ የህሊናና ልቦና ውቅር ወይም ውጥን ፣ ጅምር እንዴት ቢሆን ነው አሁን ለምትገኝባት ሁኔታ የዳረጋት? ገና ከውጥኑ ፣ ከጅምሩ ህሊናችንና አእምሯችን ውጥኑ ምን ያህል ውሽልሽል ፣ ስሁት ወይም ፈር የለቀቀ ቢሆን ነው ዛሬ ላይ ለምንገኝበት ቀውስ ፣ ውድቀትና ውርክብ የተዳረግነው። ከአክሱም ከፍታ ፣ ኃያልነት ፣ ዘመናዊ ስልጣኔ ምን ፣ ማን ፣ አወረደን ? ወደ አክሱም ከፍታ ለማንሰራራት ምን ምን ውጥኖች ናቸው እንደገና መወጠን ያለባቸው ? የመጣጥፉ አስኳል የሆነውን ይህን ጥያቄ ለመመለስ ከመሞከር በፊት የውጭ ድርሳናት ስለ ማይንድሴት ምን ይላሉ የሚለውን በስሱ ላንሳ ።
የእንግሊዝኛ ቋንቋ መዝገበ ቃላት ሜሪያም ዌብስተር የልቦና ውቅር በሆነ ጉዳይ ላይ የማሰብ ፤ የሰዎች ዝንባሌ ወይም ስለ ሆነ ነገር ያላቸው አስተያየትና አዝማሚያ በሚል በአጭሩ ይበይነዋል። ጄዲ የተባለ ጦማሪ ደግሞ፣ የአስተሳሰብ ስልት ፣ የአእምሮ ዝንባሌ ፣ መረዳትና አስተሳሰብ በሚል ይተረጉመዋል።
የልቦና ውቅር የአስተሳሰብ ልምምድ የሚታነጽበት የሃሳቦች ጡብ ነው። የአስተሳሰብ ልምምድ እንዴት እንደሚታሰብ ፣ ምን እንደምታሰብና ምን እንደሚሰራ ይወስናል። ራሳችንን ከፍ ሲልም ዓለምን የምናይበት መነጽርም ነው። ስለ አንድ ጉዳይ አስቀድሞ ለመወሰን ወይም ለመተንተን ቀድሞ የተያዘ ሃሳብ ነው በሚልም ተበይኗል።
በይደር ወደ አቆየሁትና የዚህ መጣጥፍ ማጠንጠኛ ወደሆነው ጥያቄ ልመለስ ፤ ወደ ቅድመ አክሱም ከፍታ ለማንሰራራት ምን ምን ውጥኖች ናቸው እንደገና መወጠን ያለባቸው? የሀገራችንን ህልውና እና የሀገረ መንግስቱን ቀጣይነት ጥያቄ ላይ የጣለው ፤ ለእርስ በርስ ግጭት ፣ ለአጠቃላይ ፖለቲካዊ ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ቀውስና ትርምስ ሊዳርገን የነበረው ፤ ሀገራችን ትገኝበት ለነበረው መስቀለኛ መንገድ ያደረሳት የትኛው የልቦና ውቅር ውሃ ልክ ቢዘም ነው ?
በመጣጥፌ የመጨረሻ ክፍል የዚህን ጥያቄ መልስ ለመስጠት እሞክራለሁ። ምክረ ሃሳቦችንም ለማመላከት እሞክራለሁ። ሀገራችን ኢትዮጵያ በሀቀኛና ጀግኖች ልጆቿ ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር !!!
አሜን ።
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን) fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን መስከረም 6/2014