በአምቦ የልማት ፕሮጀክት ተሰማርተው ለመስራት የሚመጡ ኢንቨስተሮች የጸጥታ ስጋት ሊኖርባቸው እንደማይገባ ተገለጸ።
የምዕራብ ሸዋ ዞን መንግስት ኮሚኒኬሽን ጽ/ቤት ኃላፊ ዶክተር መንግስቱ ቱሉ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደተናገሩት በአምቦ ከተማ ፍጹም ሰላም የሰፈነበት እንቅስቃሴ መኖሩን ጠቅሰው ኢንቨስተሮች ያለምንም የጸጥታ ስጋት መዕዋለ ንዋያቸውን ማፍሰስ ይችላሉ።
ሀላፊው የአምቦ ከተማና አካባቢዋ ነዋሪ ከመንግስት ጎን በመቆም ከለውጡ ማግስት ጀምሮ ሰላምን ለማስፈን ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን አስታውሰው ህዝቡ በሶስት መንግስታት ከልማት ርቆ የቆየ በመሆኑ አሁን የመጣውን ለውጥ ተከትሎ ለመልማት ራሱን አዘጋጅቷል ብለዋል።
በአምቦ ከተማና አካባቢው በኢንቨሰትመንት ለመሳተፍ ከየትኛውም የሀገራችን ከፍል የሚመጣ ባለሀብት ያለምንም የጸጥታ ስጋት በመሳተፍ አትራፊ መሆን እንደሚችል የገለፁት ዶ/ር መንግስቱ የአምቦ ከተማና አካባቢዋ የወርቅ ማዕድን፣ የአሸዋ አፈር ፣ውሀ እና የተፈጥሮ አየሯ በፀጋነት ይጠቀሱላታል ብለዋል።
በመሆኑም በአምቦ ልማት ፕሮጅክት ቀድመው የሚሳተፉ ባለሀብቶች በአንድ ብቻ ሳይሆን በብዙ መልኩ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ አስረድተዋል።
በአምቦ ልማት ፕሮጀክት ስር 12ሺ ተማሪዎች ማስተናገድ የሚችል በሃገሪቱ የመጀመሪያው የሚሆን ደረጃውን የጠበቀ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣20ሺህ ሰው የሚያሰተናግድ አለም አቀፍ ስታድየም እና የሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድህን የአርት ጋለሪ እንደሚጠቃለሉ ይታወቃል።
አምቦን ለመደገፍ በአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ አስተባባሪነት ባሳለፍነው አርብ በሀያት ሬጌንሴይ /hyatt regengey /ሆቴል በተደረገ የገቢ ማሰባሰቢያ የእራት ፕሮግራም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ከሃገር መሪ በስጦታ የተሰጣቸውን የእጅ ሰዓት ለጨረታ ባቀረቡት የተገኘ 5 ሚሊየን ብር መነሻ ከሁሉም የሃገሪቱ ክፍል ባለሃብቶች በጥቅሉ 350 ሚሊየን ብር ለመሰብሰብ ተችሏል። የእርዳታ የባንክ ሂሳብ ቁጥርም ይፋ መደረጉ ይታወሳል።
በዳንኤል ዘነበ