በየትኛውም የዓለም ክፍል ያሉ ሀገራት ዜጎች በሀገራቸው ጉዳይ መደራደር የሚያስችል የሞራል መሰረት ይኖራቸዋል ተብሎ አይታሰብም። ይህ ማለት ግን ስለ ሀገር ብዙ የማያሳስባቸው እንዲያውም ሀገርን ከራሳቸው ጥቅም አሳንሰው የሚያዩ ባንዳዎች የሉም ማለት አይደለም። እንዲያውም በባንዳ ያልተፈተነ ሀገር ስለመኖሩ ማረጋገጫ መስጠት ከባድ እንደሚሆን ይታመናል።
ሀገር በዜጎቿ ካላት ከፍ ያለ ትርጉም አንጻር የትም እና መቼም የሀገር ጉዳይ ለዜጎች ትልቁ አጀንዳ እንደሚሆን ይታመናል። ከዚህ የተነሳም በየትኛውም የዓለም ክፍል የሚገኝ ሀገር ዜጎች ከሀገራቸው አስበልጠው የሚያዩት ነገር ስለመኖሩ በርግጠኝነት ለመናገር የሚከብድ ነው።
በተለይም ለእኛ ለኢትዮጵያውያን የሀገር ጉዳይ አልፋና ኦሜጋችን ነው። ከዚህ ተጨባጭ እውነታ በመነሳትም አብዛኛው ታሪካችን ከሀገር ጋር የተሳሰረ የነጻነትና የተጋድሎ ታሪክ ነው። ለዚህም እልፍ አእላፍ ዜጎቻችን በየዘመኑ ስለሀገር ሰማእት ሆነው አልፈዋል። ዛሬም ቢሆን ሰማዕት ለመሆን ራሱን ያዘጋጀ ጀግና ሕዝብ ባለቤት ነች።
ለኢትዮጵያውያን ለሀገር መሞት ክብር ነው፤ ስለ ነጻነት የሚከፈል ከፍ ያለ ዋጋ ነው። ይህ ከትውልድ ትውልድ ሲቀባበል የመጣ ከሁሉም ከፍ ያለ ትውልድ ተሻጋሪ ማህበራዊ እሴታችን ነው። እሴቱ በየዘመኑ በሚከፈል መስዋዕትነት እየታደሰ ዛሬ ላይ የደረሰ፤ ዛሬም በተመሳሳይ የመስዋዕትነት ክቡር ደም እየታደሰ የሚገኝ ነው።
እውነታው በዓለም አቀፍ ደረጃ ሳይቀር የኢትዮጵያውን የጋራ ማንነት መገለጫ ተደርጎ የሚወሰድ ነው፤ ነጻነቱ ለእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ክብሩና ኩራቱ ስለመሆኑ ብዙ የታሪክ ጸሐፊዎች ተጨባጭ የታሪክ ማስረጃዎችን በማጣቀስ በስፋት ጽፈውበታል፤ በአደባባይም ምስክርነታቸውን ሰጥተውበታል።
ሕዝባችን በየዘመኑ ካደረገው የነጻነት ተጋድሎ በመነሳትም ኢትዮጵያ የነጻነት ቀንዲል ከመሆን ባለፈ ከፍ ያሉ በብዙ ጀብዱ የተሞሉ የነጻነት ትርክቶች ባለቤት መሆን የቻለች ሀገር ነች። ስለነጻነት ሲነሳም ምሳሌ ተደርጋ የምትወሰድ ሀገር ነች። ዜጎቿ ስለነጻነታቸው በየትኛውም ዘመን አንገታቸውን ያስደፋ ታሪክ አላስተናገዱም። ለማስተናገድ የሚችል ስብእና ኖሯቸውም አያውቅም።
ይህ እውነታ ዛሬም ቢሆን የሕዝቦቿ መገለጫ ስለመሆኑ ሀገር ችግር ላይ ወድቃለች የሚለው የክተት ጥሪ ከታወጀ ማግስት ጀምሮ የሀገሪቱን አደባባዮች የሞላ እውነታ ሆኗል። በተለይም አሁንም ወጣቱ ትውልድ ሀገርን ለመታደግ ሆ ብሎ የተነሳበት መንገድ ስለ ሀገር የነበረው የአባቶች የአገር ፍቅር ስሜት በአዲስ ትውልድ ላይ ህያው ሆኖ ስለመታተሙ ተጨባጭ ማሳያ ሆኗል።
ሀገር አደጋ ውስጥ ገብታለች፤ የሀገር ህልውናን የሚፈታተን ችግር ተፈጥሯል በተባለበት ቅጽበት ቀናትን በዝምታ ማሳለፍ ያልቻለው አዲሱ ትውልድ ራሱን ለመስዋዕትነት በማዘጋጀት «ሁሉም የሚሆነው ሀገር ስትኖር ነው» በሚል የቀደመ የአባቶቹ ብሂል ሁሉን ትቶ ሀገሩን በሕይወቱ ለመታደግ ወደ ማሰልጠኛ ጣቢያዎች እየተመመ ነው።
ትውልዱ ለሀገሩ ለመሞት እያሳየ ያለው ቁርጠኝነት፤ በየማሰልጠኛ ጣቢያዎች የሚታየው ለሀገር የመሞት ኩራትና መነሳሳት፤ ከዚህም በላይ በየአውደ ውጊያው እየታየ ያለው ጀግንነትና እየተሰራ የሚገኘው ገድል የአባቶቹ ልጆች ስለመሆኑ ተጨባጭ ማስተማመኛ እየሆነ ነው።
ባለፉት 27 ዓመታት ስለ ሀገር እንዳያስብ፤ ከዚህ ይልቅ መንደርተኛ እንዲሆን በብዙ የተሰራበት ይህ ትውልድ ከመንደርተኝነት ወጥቶ ከፍ ባለው የአባቶቹ መንፈስ የመገለጡ እውነታ ብዙዎችን ያስደነገጠና «ይች ሀገር አበቃላት» ያሉትን ሁሉ እጃቸውን በአፋቸው ያስጫነ ታሪካዊ ክስተት ሆኗል።
የትውልዱ በዚህ ደረጃ ስለ ሀገሩ ያሳየው መነቃቃት ለእኛ ለኢትዮጵያውያን የትናንት ታሪካችን ቀጣይ ምዕራፍ ቢሆንም ለጠላቶቻችን ግን ፍርሀትና ድንጋጤ ከዚያም በላይ የተስፋ መቁረጥ ምንጭ እየሆነ መጥቷል።
መነቃቃቱ ኢትዮጵያውያን እንደ ሀገር ላሰብነው የብልጽግና ጉዞ የተሻለ መደላድል መፍጠር የሚችልና በብልጽግና ጉዞው በቀጣይ ሊያጋጥሙት የሚችሉ ተግዳሮቶችን በድል መሻገር የሚያስችል አቅም ፈጥሯል። ከዚህም ባለፈ ለወዳጅም ሆነ ለጠላት ከፍ ያለ መልዕክት ያስተላለፈ ነው።
ኢትዮጵያውያን እንደ ትናንቱ ሁሉ ዛሬም ከሀገራቸው በላይ አስበልጠው የሚያዩት አንዳች ነገር እንደሌለ፤ ለሀገር መሞት ክብር መሆኑን ዳግም ለመላው ዓለም ለማሳየት ዕድል የፈጠረ ታሪካዊ ክስተት ነው። ትውልዱም የአባቶቹ ልጆች ስለመሆኑ በተጨባጭ መስዋዕትነት ማስተማመኛ እየሰጠ ነው!
አዲስ ዘመን መስከረም 6 ቀን 2014 ዓ.ም