ትውልደ ኢትዮጵያውያን ተጫዋቾችን በኢትዮጵያ ዋናው ብሔራዊ ቡድን(ዋልያዎቹ) ስብስብ ውስጥ ለማካተት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በይፋ ስምምነት አድርጓል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንና የኢትዮጵያ ቡና የቀድሞ ተጫዋች ዴቪድ በሻህ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ተጫዋቾችን በብሔራዊ ቡድኑ ለማካተት ያቀረበው የስካውቲንግ(ምልመላ)እንዲሁም ከፌዴሬሽኑ ጋር አብሮ የመስራት እቅድና ሃሳብ በፌዴሬሽኑ ተቀባይነት በማግኘቱ ፌዴሬሽኑ በይፋዊ የስምምነት ደብዳቤው ጀርመን ለሚገኘው ዴቪድ በሻህ ማሳወቁን የኢትዮ ኪክ ዘገባ ያመለክታል።
ለረጅም ዓመታት ሲጠበቅ የነበረው የትውልድ ኢትዮጵያውያን ተጫዋቾችን በብሔራዊ ቡድኑ የማካተት ሥራዎችን ለማስጀመር በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በኩል ፕሬዚዳንቱ አቶ ኢሳያስ ጅራ እንዲሁም የፌዴሬሽኑ ዋና ጸሐፊው አቶ ባህሩ ጥላሁን ከፍተኛ ፍላጎትና ጥረት መሳካቱ ታውቋል። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዋና ጸሐፊው አቶ ባህሩ ጥላሁን ፊርማ ባረፈበት የውሳኔ ደብዳቤ መሠረትም ዴቪድ በሻህ በስካውቲንግ ለብሔራዊ ቡድኑ ሥራውን በይፋ የሚጀምር ይሆናል፡፡
ከኢትዮጵያውያን ወላጆች የተገኙና ኢትዮጵያዊ ደም ያላቸው በርካታ እግር ኳስ ተጫዋቾች በተለያዩ አገራት ሊጎች ይጫወታሉ፡፡
ቁጥራቸው ትንሽ የማይባሉ ትውልደ ኢትዮጵ ያውያንም በተለያዩ የዓለማችን ስመ ጥር የእግር ኳስ አካዳሚዎች እየሰለጠኑ ይገኛሉ። በተለያዩ ደረጃዎችዓለም አቀፍና አህጉር አቀፍ ውድድሮችን የሚያደርጉና በተለያየ ደረጃ የሚገኙ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድኖች ግን ይህን እምቅ አቅም በአግባቡ ሲጠቀሙ አይስተዋልም፡፡
ዋልያዎቹ ከ31 ዓመታ በኋላ ለደቡብ አፍሪካው የአፍሪካ ዋንጫ ማለፋቸውን ተከትሎ የሱፍ ሳህለ፣ ፉአድ ኢብራሂምና ዋሊድ አታን የመሳሰሉት ትውልደ ኢትዮጵያውያን ተጫዋቾች ከያሉበት አገር መጥተው በተለያዩ ውድድሮች ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተሰልፈው የመጫወት ዕድል ቢያገኙም ሌሎች በርካታ ተጫዋቾች ይህን ዕድል ማግኘት እንዳልቻሉ ይታወቃል።
አብዛኞቹ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ተጫዋቾች ኢትዮጵያን የመወከል ፍላጎት ቢኖራቸውም ‹‹ለማንና እንዴት ለአገሬ ልጫወት›› የሚለውን ጥያቄ በየትኛው መንገድ ማቅረብ እንዳለባቸው ባለማወቅ ብሔራዊ ቡድኑን ማገልገል ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡
ይሁን እንጂ ይህ ችግር በጀርመን አገር ተወልዶ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንና በኢትዮጵያ ቡና ክለብ ለሁለት ዓመታት በመጫወት የሚታወቀውና መጫወት ካቆመ በኋላም በእግር ኳስ የማማከርና የተጫዋቾች ወኪል በመሆን እያገለገለ በሚገኘው ዴቪድ በሻህ አማካኝነት ተቀርፏል፡፡
ዴቪድ ከብዙ ልፋት በኋላ በውጭ አገራት የሚጫወቱ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ተጫዋቾችን አድራሻ አሰባስቦ ለብሔራዊ ቡድኑ ተሰልፈው እንዲጫወቱ በርካታ ሥራዎችን በራሱ ተነሳሽነት አከናውኖ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አድራሻቸውን የያዘ ዝርዝር ካስገባ የቆየ ቢሆንም ምላሽ ሳያገኝ ረጅም ጊዜ ተቆጥሯል፡፡
ፌዴሬሽኑ ይህን ጉዳይ ችላ እንዳለው በመግለፅ ትችቶች ሲሰነዘሩበትም ቆይተዋል፡፡
ለዚህ ደግም እንደ ሌሎች አገራት ሁሉ የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት የሁለት ዜግነት(ጥምር ዜግነት) ፍቃድ አለመስጠቱ ሁልጊዜ እንደ ችግር ሲነሳ ቆይቷል፡፡
ይሁንና ፊፋ ጥምር ዜግነትን ለማይፈቅዱ አገራት (Sport Passport) በሚል መፍትሄ አምጥቷል። ሆኖም ይህንን ተግባር በትክክል ለፊፋ የሚጠይቅና የሚያስፈፅም ባለመኖሩ ሁልጊዜም ችግሩ የዜግነት እንደሆነ ተደርጎ ይነገራል።
የዋልያዎቹ ዋና አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ግን ይህን ችግር ለመቅረፍ የሌሎች አገራትን ተሞክሮ ወስደው በብሔራዊ ቡድናቸው ትውልደ ኢትዮጵያውያን ተጫዋቾችን ለማካተት እንዳሰቡ የተለያዩ ዘገባዎች ቀደም ብለው ሲወጡ ቆይተዋል። የምሥራቅና መካከለኛው አፍሪካ አገራት(ሴካፋ) ከ23 ዓመት በታች የእግር ኳስ ውድድር ከሰኔ 26/2013 እስከ ሐምሌ 11/2013 ዓ.ም በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት በባሕር ዳር ከተማ በተካሄደበት ወቅት አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በውድድሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ተጫዋቾችን በቡድኑ ማካተትን በተመለከተ ታላቅና ሲጠበቅ የነበረውን ሃሳብ ተግባራዊ ሊያደርጉ ሞክረው አልተሳካም ነበር። አሠልጣኝ ውበቱ አባተ በውጭ የሚገኙ ተጫዋቾችን በቡድኑ ለማካተት ይረዳ ዘንድ ከፌዴሬሽኑ ጋር በጋራ በመሆን በውጭ ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች ጋር አብሮ ለመሥራት ጥረቶችን ሲያደርጉ ቆይተዋል። በተለይም በጀርመን የሚገኘውና ለበርካታ ጊዜያት የውጭ ተጫዋቾች በብሔራዊ ቡድኑ እንዲካተቱ በሙያው የስካውቲንግ (ምልመላ) ሥራ ለመስራት ሁሌም ፍላጎቱ ከሆነው የቀድሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድኑና የኢትዮጵያ ቡና ተጫዋች ዴቪድ በሻህ ጋር በጥምረት ለመስራትና አዲስ ነገር ለመተግበር ሲንቀሳቀሱ እንደነበር መረጃዎች ያመለክታሉ።
የውጭ ተጫዋቾችን በኢትዮጵያ የማካተት ተግባር በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ እንዲሁም በፌዴሬሽኑ መታሰቡ ታላቅ ለውጥና ተስፋ በመሆኑ በርካታ የስፖርት ቤተሰቦች ደግፈውታል፡፡
ከውጭ የሚመጡት ተጫዋቾች ከአገር ውስጥ ተጫዋቾች ጋር በመጫወት የተሻለው የማግኘት ሂደቱ መታሰቡ በመጪው ዓመት በካሜሩን የአፍሪካ ዋንጫ ኢትዮጵያ ጠንካራ ቡድን ይዛ ለመቅረብ ትልቅ አስተዋፅኦ ሊያበረክት እንደሚችል ታምኖበታል፡፡
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን መስከረም 5/2014