በሰላም፣ በልማት፣ በዴሞክራሲና በመልካም አስተዳደር ግንባታ ዙሪያ ዲያስፖራው የራሱን አስተዋፆኦ እያበረከተ ይገኛል። በተለይ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያን ከገጠማት ውስጣዊ እና ውጫዊ ፈተናዎች አኳያ እየተጫወተ ያለው ሚና ከፍተኛ ነው። ከሀገር ውጭ በተለያዩ ዓለም ሀገራት የሚኖረው የዲያስፖራ ማህበረሰብ አባላት ባሉበት ሆነው ስለሀገራቸው ያላቸውን ነባራዊ እውነታ ተገንዝበው ከሀገራቸው ጎን በመሰለፍ ድጋፍ እያደረጉ ይገኛሉ።
ምዕራባውያኑ በኢትዮጵያ ውስጥ ጉዳይ ጣልቃ በመግባት የሚያደርጉትን ጫና ለመመከት ዲያስፖራው በርካታ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ጥረቶችን እያደረጉ ነው። የተለያዩ ሚዲያዎችን በመጠቀም የሚወጡ የተዛቡ አመለካከቶችና መረጃዎች በማረምና በማስተካከል ነባራዊ ሁኔታዎች ላይ በመመስረት ትክክለኛውን መረጃ በመስጠት አበረታች ሥራዎች መሥራት ተችሏል።
በሀገር ውስጥ ለሚደረጉ የልማት ሥራዎችና በተለያዩ ጊዜያት ለተከሱቱት ችግሮች እጃቸውን በመዘርጋት ለወገኖቻቸው ከሚያደርጉት ድጋፍ ባሻገር ባህር ውቅያኖሱን አቋርጠው ወደ ሀገራቸው ተመዋል። እንደሀገር ያጋጠመውን የህልውና አደጋ በመመከት የመፍትሔ አካል ለመሆንና ከወገኖቻቸው ጎን በመሰለፍ አብሮነታቸውን ለማሳየት ችለዋል።
ዲያስፖራዎች ሁልጊዜም ከሀገራቸው ጎን በመቆም አስፈላጊውን ሁሉ እያደረጉ ነው። ሀገር ለዜጎቿ ያደረገችውን ጥሪ ተከትሎ ሀገርን በማዳን ዘመቻው ተሳታፊ ለመሆን ጨርቄን ማቄን ሳይሉ ፈጣን ምላሽ በመስጠት የህልውና ዘመቻውን የተቀላቀሉም እንዳሉ ተመልክተናል።
ከዚህም ባሻገር ደም በመለገስ እና የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ የሀገር አለኝታነታቸውን እየገለጹ ነው። ምንም እንኳን በውጭ ሀገር በተመቻቸ ሁኔታ እየኖሩ ቢሆንም የሀገር ጉዳይ ከምንም በላይ ነውና መሠዋዕትነት እስከ መክፈል ያላቸው ፍቅርናተቆርቋሪነትን ማሳየት ችለዋል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ኢትዮጵያ ከድህነት ተላቅቃ በእድገት ጎዳና ለመራመድ የምታደርገው ተስፋ ሰጪ ጥረት ለመደገፍ ጥረቶች ሲደርጉ ይስተዋላሉ። በተለያዩ አጋጣሚዎች የሀገራቸውን ስምና ክብር ከፍ በማድረግ በዓለም አደባባይ ስለሀገራቸው ድምጻቸውን እያሰሙ ለወገኖቻቸው መከታ እየሆኑ ነው።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ ዲያስፖራው በውጭ ምንዛሬ በኩል የሚያደርገው ተሳትፎ ለትውልድ ሀገሩ የኢኮኖሚ ልማት የሚያበረክተው አዎንታዊ አስተዋፅኦ ከፍተኛ እንደሆነ ይታመናል። በዚህም በተለያዩ ዓለም ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንም ሆኑ ትውልደ ኢትዮጵያውያን የውጭ ምንዛሬን ወደ ሀገራቸው በመላክ ለተለያዩ የልማት ሥራዎች ሲያውሉ ይስተዋላል።
በተመሳሳይ ወደ ሀገር ውስጥ የሚልኩትን ለተለያዩ ድጋፎች የሚውል ገንዘብ ህጋዊ በሆነ መንገድ በመላክ ኃላፊነታቸውን እየተወጡ ያሉ የመኖራቸውን ያህል በተቃራኒው ህጋዊ ባልሆኑ መንገዶች የተሰለፉም እንዳሉ መረጃዎች ይመላክታሉ። ለበጎ ዓላማ የተሰለፉ ህጋዊ መስመርን ተከትለው ለሀገራቸው ድጋፍ የሚያደርጉ ዲያስፖራዎች እንዳሉ ሁሉ ሀገር ለማፍረስ ለሚደረግ እኩይ ሤራ እና ለተለያዩ ዓላማ ህገወጥ በሆነ መልኩ ዶላር ወደ ሀገር ውስጥ የሚያስገቡ መኖራቸው ይታወቃል።
ህገወጥ የሆነው ተግባር ሀገር ከውጭ ምንዛሬ ማግኘት የሚገባትን ያህል ገቢ እንዳታገኝ በማድረግ ሀገርን መጎዳትና ለከፍተኛ ኪሳራ የሚዳርግ ነው። በመሆኑም ዲያስፖራው ወደ ሀገር ውስጥ የሚልከውን የውጭ ምንዛሬ ህጋዊ በሆነ መልኩ መላክ እንዳለበት በተለያዩ ጊዜያቶች በሚደረጉ የምክክር መድረኮች ያሉ ሲሆን፤ በዚህም በየጊዜው መሻሻሎች እየመጡ እንደሆነ ይነገራል።
የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሰላማዊት ዳዊት እንዳስታወቁት፤ በ2013 በጀት ዓመት በውጭ ምንዛሬ ፍሰት ከሌላ ጊዜ እየተሻለ መምጣቱን የሚያሳይ ነው። ለዚህ በበጀት ዓመቱ የውጭ ምንዛሬ ፍሰት 3 ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር ገቢ የተገኘ ሲሆን፤ ይህም ሀገራችን በውጭ ኤክስፖርት ከምታገኘው የውጭ ምንዛሬ የተሻለ ገቢ እንደሆነ ተጠቁሟል።
የዲያስፖራ የውጭ ምንዛሬ በውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በአገራቸው ባንክ በውጭ ምንዛሬ የሚከፍቱት ነው። በዚህም 6ሺ 914 የዲያስፖራ አባላት በሀገር ውስጥ የውጭ ምንዛሬ አካውንት በመክፈት የሚያንቀሳቅሱ መሆኑን ጠቅሰው፤ 7 ሚሊዮን 542 ሺህ 231 ዶላር ተቀማጭ የሆነበት ወይም የተንቀሳቀሱበት ሁኔታ መኖሩ ተመላክተዋል።
ይህም ሆኖ በሚፈለገው ልክ ማግኘት የሚገባ የውጭ ምንዛሬ እየተገኘ አይደለም የሚሉት ወይዘሮ ሰላማዊት፤ በጣም ከፍተኛ አቅም ያለን በመሆኑ ብዙ ሥራዎች መስራት ይጠብቅበናል ብለዋል። ዲያስፖራው ገንዘቡን በህጋዊ መንገድ ብቻ በመላክ በኢትዮጵያ ላይ እየተፈጠሩ ያሉ ጫናዎችን ለመቋቋም የጀመረውን ተግባር አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ጠቁመው፤ በዚህ ረገድ ሁሉም የበኩሉን ድርሻ በመወጣት ሊሰራበት የሚገባው ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል። አያይዘውም በአዲሱ ዓመት ዲያስፖራው ለቤተሰቦቹ የሚልከውን ገንዘብ ልክ ህጋዊ በሆነ መንገድ መላክ ይገባዋል ሲሉ አሳስበው እንደነበር ይታወሳል።
ይሁን እንጂ ሰሞኑን ዲያስፖራው ገንዘቡን ወደ ሀገር ቤት በህጋዊ መንገድ የሚልክበትን ሁኔታ የሚያመቻች ከመንግስትና የግል ባንክ ከፍተኛ አመራሮች ጋር የበይነ መረብ ውይይት የተካሄደ መሆኑን የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ኤጀንሲ አመላክቷል።
ወይዘሮ ሰላማዊት ዳዊት እንደገለጹት ፤ ውይይቱ ከወቅታዊ ሀገራዊ ሁኔታዎች ጋር በተያያዘ በዲያስፖራው ዘንድ እየታየ ያለውን በህጋዊ መንገድ ገንዘብ የመላክ ከፍተኛ ፍላጎት ማርካት የሚችሉ የአጭርና የረዥም ጊዜ ስልቶችን መንደፍ በሚቻልበት መንገድ የሚያመላክት መሆኑ ገልጸዋል። የመንግስትና የግል ባንኮች የስራ ኃላፊዎችም በበኩላቸው ከዲያስፖራው ሊገኝ የሚችለውን የውጭ ምንዛሬ ግኝት ከማሳደግ አንጻር ያሉ ተግዳሮቶችንና የመፍትሔ ሃሳቦችን ያመላክቱበት ነው።
የብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥ አቶ ፍቃዱ ድጋፌ በበኩላቸው መንግስት በዘርፉ ያለውን ችግር ተረድቶ ልዩ ልዩ የህግ ማዕቀፎችን ማበጀቱን ገልጸው፣ ከችግሩ ስፋትና ውስብስብነት እንዲሁም ከባለድርሻ አካላት ትብብር ማነስ ጋር በተያያዘ በቀላሉ መፍትሔ ማግኘት እንዳልተቻለ ገልጸዋል። በቀጣይም በጥቁር ገበያና በመደበኛው የባንክ ምንዛሬ መካከል ያለውን ልዩነት በዘላቂነት ማጥበብ እንዲቻል ሁሉም ባለድርሻ አካላት የየበኩላቸውን ድርሻ ሊወጡ እንደሚገባ አሳስበዋል።
በዘርፉ የሚታዩ ችግሮችን ከመፍታት አንጻር በአጭርና በረዥም ጊዜ መሰራት ያለባቸውን ጉዳዮች ለይቶ የሚያቀርብና የሚመለከታቸው አካላት የተካተቱበት ኮሚቴ መቋቋሙን ጠቅሰው፣ በቅርቡ ኮሚቴውን ወደ ስራ ሊያስገቡ የሚችሉ የውሳኔ ሃሳቦቹን ይዞ ወደ ሥራ እንደሚገባ መግለጻቸውን ከኤጀንሲው የተገኘው መረጃ ያሳያል።
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን መስከረም 5/2014