(የመጨረሻ ክፍል)
አሸባሪው ህወሓት በሀገሬ በሕዝቤና በወገኔ ላይ እየፈጸመ ያለው ማለቂያ መቋጫ ያላገኘው ግፍ እንባዬን አድርቆታል። ሀዘኔ ከል በመልበስ ጸጉር በመንጨት ፊት በመፍጀት ትቢያ በመነስነስ ደረት በመድቃት በእዝልና በአራራይ ምህላ በማድረግ አይወጣም። አዎ ! ሀዘኔ የሚወጣው፣ የተሰበረው ቅስሜ የሚቃናው ሀገሬን እያደማ፤ ሕዝቤን የሚያሰቃየው አሸባሪ እንደ እብቅ ተጠርጎ ለንፋስ ሲሰጥ ብቻ ነው።
የሀገሬና የምድሪቱ መስክ ጋራ ሸንተረር ተራራ ወንዝ ሸለቆና ሰርጣ ሰርጥ ሳይቀሩ በፈሰሰው የንጹሐን የሕፃናት፣ የእናቶች፣ የአረጋውያንና የካህናት ደም፤ በጠፋው ባድማ ፤ በተፈጸመው ህልቆ መሳፍርት የሌለው ግፍ፤ ከትግራዋይ እናት ጉያ ተነጥቆ ለሽብር ኃይሉ ሥልጣን ለእሳት በተማገደው ትውልድ ወደ ላይ በተረጨው እንባ ሀዘናቸው ቅጥ ስላጣ እየቃተቱ ጥርስ እያፋጩ ነው።
ሐዋርያው ጳውሎስ «ምድር በሀዘን ብዛት የተነሳ ትቃትታለች»ያለው ቃሉ እየተፈጸመ ይመስላል። የኢትዮጵያ ምድር መልክዓና መንፈስ እየቃተተ ነው። ከሀገሬ ከወገኔ መቃተት በኋላ ድል አድራጊነት ተስፋና አዲስ ቀን ስለሚመጣ በእሱ እጽናናለሁ። በዋሻው ጫፍ ጭል ጭል የሚል ብርሃን ስላለ በእሱ ተስፋ አደርጋለሁ።
በዚህ ስምንት ወራት በሰሜን ዕዝ በማይካድራ በጋሊኮማ በአጋምሳ እና ለጊዜው ባላወቅናቸው በሌሎች ቦታዎች በወገኖቼ ላይ በተፈጸመ ግፍና ውርደት ሀዘኔን ሳልጨርስ በወጉ ሳልጽናና ይህን መጣጥፍ እያጠናቀርሁ እያለ ሌላ ልብንና ቅስምን በሀዘን የሚሰብር ከመርግ የከበደ መርዶ ከወደ ሰሜን ጎንደር ዞን ዳባት ወረዳ ጭና ተክለሃይማኖት የገጠር ቀበሌ 203 አረጋውያን ካህናት ሴቶችና ሕፃናት በአረመኔው በላዔሰቡና አሸባሪው ህወሓት በግፍና በጭካኔ የተጨፈጨፉ ንጹሐን የጅምላ መቃብር በቴሌቪዥን ተመለከትሁ።
ሌላ የደም መሬት፤ ሌላ አኬልዳማ። ሌላ አጋምሳ ሌላ ማይካድራ በኢትዮጵያ ምድር። ዛሬም የንጹሐን ደም ይጮሀል። ይጣራል። የንጹሐን እንባ ወደ ላይ ወደ ፈጣሪ ይረጫል። ለግማሽ ክፍለ ዘመን ያህል በኢትዮጵያ ሕዝብ በተለይ በአማራ የሆነው ይህ ነው ። ለዚህ ሽብር ቡድን በወገንተኝነት ሽንጣቸውን ይዘው የሚሟገቱ አካላት ዛሬስ ወዴት ይሆኑ! ?።
በእርግጥ ከአንጀትም ባይሆን ከአንገት ጭፍጨፋውን በሹክሹካ መዘገብ ጀምረዋል ። የመንግሥታቱ ድርጅት በማይካድራ የጦር ወንጀል ሳይፈጸም እንዳልቀረ እንደገለጸው፤ አመነስቲ ኢንተርናሽናልም የዘር ማጥፋት ወንጀል ሳይፈጸም እንዳልቀረ የሚያመለክቱ መረጃዎች ማግኘቱን እንደጠቆመው፤ በጭና ተክለሃይማኖት የተፈጸመውን ዘር ማጥፋት፣ በሰብዓዊ ፍጡር ላይ የተፈጸመ የጦር ወንጀል ሊያወግዙና ተጠርጣሪዎች ለሕግ እንዲቀርቡ ጫና ሊያደርጉ ይገባል። ይህን የምለው እይታቸው ሸውራራ መሆኑ ጠፍቶኝ አይደለም። በሁመራና በትግራይ ያወጧቸው የነበሩ ሀሰተኛና የተዛቡ መግለጫዎች ውሸት መሆኑን ተገንዝበዋል በሚል ሞኝነት እንጂ።
«በጀግኖቻችን የተቀናጀ ጥቃት ሲፈጸምበት በየጫካው እየተፋለሙት ያሉትን አናብስት ምት መቋቋም ያልቻለው ወራሪ በየቤታቸው የነበሩ አዛውንቶችን፣ ሕፃናትንና እናቶችን በያሉበት መንደርና ሠፈር በመግባት፣ ቀሳውስትን ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ገብቶ የፊጥኝ በማሰር ጨፍጭፏቸዋል፤»ሲል የአማራክልል ኮሙዩኒኬሽን ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ግዛቸው ሙሉነህን ጠቅሶ ሪፖርተር ዘግቧል።
ከአንድ ቤት ስድስት ሰዎችን ጨፍጭፏል። የስድስት ወር ሕፃን የታቀፈች የካህን ሚስት ከእነ ልጇ በግፍ ከተጨፈጨፉ ንጹሐን ውስጥ ይገኙበታል። ሕፃናትን ልጃ ገረዶችንና ሴቶችን አስገድዶ ደፍሯል። 100 የቀበሌው ሰዎች እስከ ዛሬ የደረሱበት አልታወቀም። ንጹሐንን አሰልፎ ረሽኗል። የአርሶ አደሩን ንብረት ዘርፏል። በሬውን ላሙን በጉንና ዶሮውን አርዶ በልቷል። የተረፉትን እንስሳት በግፍ በጥይት ደብድቧል።
የነሐሴ 26 እና 27፣ 2013 ዓ.ም የጭና ተክለሃይማኖት ለማየት የሚዘገንን ለመስማት የሚሰቀጥጥ ጭፍጨፋ ማይካድራን ጋሊኮማንና አጋምሳን እንድናስታውስ ያስገድደናል። እግረ መንገዳችንን አሸባሪው ህወሓት አሁን የያዛቸውን አካባቢዎች ሲለቅ ከእነዚህ አካባቢዎች የከፋ ጭፍጨፋ መፈጸሙ ስለማይቀር ራሳችንን ለማዘጋጀት እና ለታሪክና ለትውልድ ፍርድ መለስ ብለን በወፍ በረር እንቃኛለን።
በማይካድራ ከተማ የተፈጸመው ጥቃት በአካባቢው መስተዳድር የጸጥታ መዋቅርና ‘ሳምሪ’ በተባለኢ-መደበኛ የወጣቶች ገዳይ ቡድን ነው። የማይካድራ ጥቃት፣ ግድያ፣ ጉዳትና ውድመት ጠቅላላ ድርጊቱና ውጤቱ ግፍና ጭካኔ የተሞላበት በሰላማዊ ሰዎች ላይ የተፈጸመ የጭፍጨፋ ወንጀል ነው። ይህ ከፍተኛ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት በሰብአዊነት ላይ የተፈጸመ ወንጀል እና የጦር ወንጀል ሊሆን እንደሚችል ለዚህም የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን/ኢሰመኮ/ ዝርዝር ማስረጃዎቹን እና ወንጀሉን የሚያቋቁሙትን የሕግና የፍሬ ነገር ትንተና በሙሉ ሪፖርቱ ላይ በዝርዝር አጣርቶ አጠናቅሯል።
በማይካድራ የነበረው የሚሊሽያና የፖሊስ መዋቅር የፌዴራሉ ሠራዊትን እርምጃ ሸሽቶ አካባቢውን ለቆ ከመውጣቱ በፊት «ሳምሪ» ከተባለ መደበኛ ያልሆነ የትግራይ ወጣቶች ቡድን ጋር በመተባበር በተለይ “አማሮችና ወልቃይቴዎች ላይ «ጥቃት» ፈጽሟል። በዚህም ቡድኑ ከቤት ቤት እየዞሩና በየጐዳናው ላይ ያገኙትን ሰው በገመድ በማነቅ፣ በስለት በመውጋት፣ በመጥረቢያ በማጥቃት፣ በዱላ በመደብደብ ገድለዋል። የአካል ጉዳት አድርሰዋል። እንዲሁም ንብረት አውድመዋል።
«ሳምሪ» የሚባለው የትግራይ ወጣቶች ቡድን በዚህ ከባድ ወንጀል ላይ ቢሰማራም፤ በአንጻሩ የትግራይ ብሔረሰብ ተወላጆች የሆኑ አንዳንድ የአካባቢው ነዋሪዎች አጥቂው ቡድን ሲያሳድዳቸው የነበሩ ሰዎችን በቤታቸው፣ በቤተክርስቲያንና በእርሻ ቦታ ደብቀው እንዳተረፏቸው የኢሰመኮ የምርመራ ቡድን ያነጋገራቸው የአካባቢው እማኞች ገልፀዋል። ይህ ዛሬም ሰብዓዊነትና ኢትዮጵያዊ ማንነት ቢደበዝዝም ጨርሶ አለመጥፋቱን ያሳያል።
እንዲሁም በአፋር ክልል በፈንቲ ረሱ ዞን በጋሊኮማ ጊዜያዊ መጠለያ ተጠልለው የነበሩ በአሸባሪው ህወሓት በተተኮሰ ከባድ መሣሪያ 107 ሕፃናት፣ 89 ሴቶች፣ 44 አዛውንቶች ተገድለዋል። 30ሺህ ኩንታል የእርዳታ እህል የያዘ መጋዘንም በጥቃቱ ወድሟል። በወረራው በብዙ አስር ሺህዎች የሚገመቱ ንጹሐን ከቀየአቸው ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል።
በተመሳሳይ በሐምሌ ወር መጨረሻ የሀገር ቤት ሚዲያዎችና ዘ ቴሌግራፍ የተባለው የእንግሊዝ ጋዜጣ፤ አሸባሪው ህወሓት በሰሜን ወሎ ራያ ቆቦ ወረዳ አጋምሳ በተባለ የገጠር ቀበሌ በከባድ መሣሪያ በርካታ ቤቶችን በማቃጠል የጅምላ ጭፍጨፋ መፈጸሙን በአስር ሺህዎች የሚገመቱ ቤት ንብረታቸውንና ቀዬአቸውን ጥለው መፈናቀላቸውን መዘገባቸው ይታወሳል። አሸባሪው ህወሓት ከሦስት ዓመታት በላይ እንደ ፈረስ የሚጋልባቸውን እንደ ውሻ ቻዝ የሚላቸውን ተላላኪዎች በማሰማራትና ስፖንሰር በማድረግ በሀገሪቱ አራቱ ማዕዘናት ንጹሐንን ሲያስጨፈጭፍ፤ ከቀዬአቸው ሲያፈናቅል ሲዘርፍ፤ የሃይማኖትና የማንነት ግጭት ሲቀፈቅፍ ቆይቷል።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ከማሽና መተከል ዞኖች ጥቃቶች፤ የአማራ ክልል የአጣዬና አካባቢው ጭፍጨፋዎች፤ የኦሮሚያ ክልል የአራቱ ወለጋ ዞኖች ጥቃቶችና ተደጋጋሚ ግፎች፤ በደቡብ ክልል የኦሮሚያ አዋሳኝ አካባቢዎች የሚታዩ የታጠቁ አካላት ጥቃቶች፤ ከቤንች ሸኮ ዞን ጉራፈርዳ ግፎች ጀርባ የአሸባሪው ረጅም እጅ ነበር። ከዚህ ባለፈም የሶማሊና ኦሮሚያ፣ እንዲሁም የሶማሊና የአፋር ክልሎች የድንበር አካባቢ ግጭቶች ሀገርን የማተራመስ ዕቅዱ ፕሮጀክት አካል ነው ።
ራሱን«የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት» ብሎ የሚጠራው ሸኔ ከህወሓት ጋር በወታደራዊ ጉዳዮች በትብብር ለመስራት መስማማቱን የአሸባሪው ሸኔ መሪ ኩምሳ ድሪባ/ጃል መሩ/ ለአንዳንድ ዓለምአቀፍ መገናኛ ብዙኃን መገለጹና ህወሓትም ጋብቻቸውን በአደባባይ እወቁልን ማለቱ ድሮውንም አብረው ሲያሸብሩ እንደነበር አረጋግጦልናል። ስዬ አብርሀ የኢትዮጵያ ማጎሪያ ቤቶች የሥራ ቋንቋ ኦሮሚፋ እስኪመስል በኦሮሞ ወጣቶች ተጥለቅልቀዋል እንዳለው አሸባሪው ህወሓት ኦነግ እያለ የኦሮሞን ወጣት ለ27 ዓመታት በግፍ ሲገደል በጅምላ ሲያጉር ሲያሰቃይ ሲያንኮላሽ እግር ሲቆርጥ ፤ የኦሮሞ ሕዝብን ሲዘርፍ ሲንቅ አንገት ሲያስደፋና ሲያንኳስስ መኖሩ የተዘነጋ ይመስል ከሸኔ ጋር ለማሸበር ውል መፈጣጠሙ ይቺን ሀገር ለማፍረስ ሲኦልም ቢሆን እወርዳለሁ ያለውን በተግባር ማዋሉን አረጋግጦልናል።
ሸኔም በኦሮሞ ሕዝብ ላይ ያን ሁሉ ሕልቆ መሣፍርት የሌለው ግፍ ከፈጸመ አሸባሪ ጋር ታክቲካዊ ትብብር ማድረጉ የኦሮሞ ሕዝብ አንቅሮ እንዲተፋው አድርጓል። የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ከማሽና መተከል ዞኖች ጥቃቶች፤ የአማራ ክልል የአጣዬና አካባቢው ጭፍጨፋዎች፤ የኦሮሚያ ክልል የአራቱ ወለጋ ዞኖች ጥቃቶች፤ በዚያ ሰሞን እንኳ በምሥራቅ ወለጋ ዞን ጊዳ ኪራሙ ወረዳ ወደ 200 የሚጠጉ ንጹሐን ማንነት ላይ ባነጣጠረ ግፍ መገደላቸውና በሺዎች የሚቆጠሩት ደግሞ መፈናቀላቸውን ይታወሳል።
በደቡብ ክልል የኦሮሚያ አዋሳኝ አካባቢዎች የሚታዩ የታጠቁ አካላት ጥቃቶች፤ የቤንች ሸኮ ዞን ጉራፈርዳ ግፎች፤ እንዲሁም የምዕራብ ኦሞ የፀጥታ ችግሮች የአሸባሪው ህወሓት የእጅ ሥራ ናቸው። በጅግጅጋና አካባቢው ከሐምሌ 28 እስከ 30 ቀን 2010 ዓ.ም በአብዲ ኢሌ በሚመራው ሄጎና በክልሉ ልዩ ኃይል አባላት ታቅዶ ማንነትን ኢላማ አድርጎ የተፈፀመው ዘግናኝ ግፍና ሰቆቃ፤ በቅርቡም በጉሙዝ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ታጣቂ ቡድን አባላት በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ካማሺ ዞን በሎ ጅጋንፎይ ወረዳ ከ50 በላይ ንፁኃን ዜጎች የተጨፈጨፉት በታሪካዊ ጠላቶቻችንና በአሸባሪው ህወሓት ስምሪትና ፋይናንስ መሆኑን በጀብደኝነት አረጋግጦልናል።
አሸባሪው ህወሓትም ሆነ ሸኔ እንዲሁም በቅማንት ማንነት ስም የሚንቀሳቀሰውን ጨምሮ ሌሎች የጉምዝና የጋምቤላ ግልገል አሸባሪዎች ፖለቲካዊ ሥልጣንን የሞት ሽረት ጉዳይ ያደረጉት የማይነጠፍ የሥልጣንና የሀብት ወይም የኢኮኖሚ ምንጭ ስለሆነ እንጂ እንወክለዋለን ለሚሉት ሕዝብ መብት ተቆርቁረው ወይም አስበው አይደለም። ፖለቲካዊ ሥልጣን መያዝ የሀገሪቱን ሀብትና በጀት የመቆጣጠር ጉዳይ ስለሆነ ነው፤ ህወሓትንም ሆነ ጀሌዎቹን እንዳበደ ውሻ የሚያዛክራቸው።
ለችግሮቻችን ዘላቂ መፍትሔው የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥና ጠንካራ የደህንነትና የጸጥታ ተቋማትን መገንባት ብቻ አይደለም። ዘላቂው መፍትሔ በመንግሥት መዳፍ ስር የሆነውን ኢኮኖሚና ሥልጣን ለሕዝብና ለተቋማት ማደላደል ነው ። ሀብታምና ትልቅ መሆን ያለበት ሕዝብ እንጂ መንግሥት አይደለም። የእኛ መንግሥት ነጮች ትልቅ መንግሥት “big government “ የሚሉት ዓይነት እንጂ አገልጋይ አለመሆኑ ነው ከፍ ብዬ እንደገለጽሁት ሥልጣን መያዝ የሞት ሽረት ጉዳይ የሆነው። በአጭር ጊዜ የኑሮ ውድነቱን የዋጋ ግሽበቱንና ሥራ አጥነቱን በአስቸኳይ ማስተካከሉ እንዳለ ሆኖ። ሀገራችን ኢትዮጵያ በሀቀኛና ጀግኖች ልጆቿ ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር !!!
አሜን።
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)
fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን መስከረም 5/2014