2013 ዓ.ም. አገራዊ ምርጫው በሰላም የተጠናቀቀበት እና የሁለተኛው ዙር የህዳሴ ግድብ ውሃ ሙሊት የተከናወነበት ነው። ከዚህም በተጨማሪ በከተማዋ የተጀመሩ ትልልቅ ፕሮጀክቶች በወቅቱ ተጠናቅቀው በፕሮጀክት አፈጸጸም ዙሪያ ተስፋዎች የታዩበት ጭምር ነው።
የተሰናበተው ዓመት ለኢትዮጵያ ከባድ የፈተና ዓመት ሆኖ ያለፈ ነው ። በኮቪድ-19 ወረርሽኝ፤ ብዙ ኢትዮጵያውያን የተሰቃዩበትና ከ4ሺህ 857 ያላነሱ ሰዎች የሞቱበት ዓመት ነው። በዚህም ትጉህ የህዝብ አገልጋዮች የነበሩ የኪነጥበብ ሰዎች በጎ አድራጊዎችና የፖለቲካ ልሒቃን በሞት የተለዩን ዓመት ነው ።
ኮቪድ ብቻ አይደለም፤ የአንበጣ መንጋ፣ የጎርፍ መጥለቅለቅ ጉዳቶች፣ ብሔርንና ሃይማኖትን ሽፋን ያደረጉ ግጭቶችና ሁከቶች፣ በሌላ በኩል ገደብ የለሽ ሆኖ የቀጠለው የኑሮ ውድነት በርካታ ዜጎች በተለይም በዝቅተኛ ገቢ ለሚተዳደረው ኢትዮጵያውያን ዓመቱን ፈታኝ ዓመት አድርጎታል።
ከየትኛውም በላይ ደግሞ ከሰላም ይልቅ ጦርነትን የሙጥኝ ያለው አሸባሪው ህወሓት ፤ የሀገርን ዳር ድንበር ሲጠብቅ የነበረውን የመከላከያ ሠራዊት ከጀርባ በማጥቃት በታሪክ ሊዘነጋ የማይችል ክህደት የሰራበት ዓመት ነበር።
የሀገርን ህልውና አደጋ ውስጥ የከተተው ክህደት ተፈፅሞ የታየ ቢሆንም፤ ጥቃቱን በመመከት የመከላከያ ሰራዊቱ ከፍ ያለ ገድል መስራት ችሏል። በዚህም በሀገሪቱ ላይ ተደቅኖ የነበረውን የመበተን ስጋት ማክሰም ተችሏል።
መንግስት ለትግራይ ህዝብ እና ለቡድኑ አመራሮች የጥሞና ጊዜ በመስጠት ችግሩን በተሻለ መልኩ ለመፍታት ከዛም ጎን ለጎን አርሶአደሩ የእርሻ ስራውን እንዲያከናውንና ከጠባቂነት እንዲወጣ ለማስቻል የደረሰበትን ውሳኔ በመጣስ በአጎራባች ክልሎች ወረራ በማካሄድ ለሰላም ቅንጣት ታህል ሃሳብ እንደሌለው አሳይቷል።
በአፋርና በአማራ ክልል ባካሄዳቸውም ወረራዎች የወሮበላነት ባህሪው በተጨባጭ የታየ ሲሆን በዚህም አንድም ተስፋ መቁረጡን ከዚህም በላይ የቱን ያህል ጸረ ህዝብና ጸረ ኢትዮጵያዊ እንደሆነ በግልጽ በተግባር አሳይቷል።
ቡድኑ በሃይል በያዛቸው አካባቢዎች ታጣቂዎቹ ዜጎችን በማሰቃየት አልፎ ተርፎም በጅምላ በመፍጀት የአገሪቱን ህልውና ለመፈታተን ሞክረዋል። ሊሰሩ የሚችሉ የአገር ተስፋ ወጣቶችን ብቻ ሳይሆን ነገ አድገው አገር የሚገነቡ ህፃናትን ጨርሰዋል። መጦር ያለባቸው ለመከላከል የሚያዳግታቸውን አረጋውያንን ከመግደል አልፈው አንደበት የሌላቸውን እንስሳት በጥይት በየጎዳናው አንጋለዋል። ንብረት ዘርፈዋል።
በደቡብ ጎንደር ዞን የተለያዩ አካባቢዎች ብቻ የአሸባሪው ቡድን አባላት ከ60 በላይ ንፁሃንን በከባድ መሳሪያና በጥይት ገድለዋል። ከ111 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የግለሰቦችን ንብረት መዝረፋቸውንና ማውደማቸውን በደብረታቦር ዩኒቨርሲቲ የጉዳት መጠኑን ለማጥናት የተቋቋመው አጥኚ ኮሚቴ አሳውቋል።
የአሸባሪው የህወሓት ቡድን አባላት ባካሄዱት ዝርፊያ በርካታ ዜጎች ለችግር ተዳርገዋል። በዛው በደቡብ ጎንደር ዞን ብቻ 120 ያህል ተቋማት ላይም ጉዳት አድርሰዋል። ይህ ለምሳሌ ያህል ቢጠቀስም በአማራ ክልል እና በአፋር ክልል ያስከተሉት ጥፋት አገርን ፈተና ውስጥ መጨመሩ አይካድም። ቁም ነገሩ ፈተናው መታለፉ እና ከጉድጓድ መውጣት እንደሚቻል መታየቱ ነው።
ፈተናዎቹ ኢትዮጵያን ተራራ ላይ የሚያስቀምጣትን መልካም ዕድል እየፈጠሩ ነው። ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ከዳር እስከ ዳር እያነገሱ ነው። የኢትዮጵያዊነት ስሜት ከፍ ብሎ ወጥቷል። ጦርነቱ መጥፎ ችግሮች እንደፈጠረ ሁሉ ያመጣውን ይህንን መልካም አጋጣሚ መጠቀም ከተቻለ ከጉድጓድ ወጥቶ የታላቁን ተራራ አናት መቆናጠጥ እንደሚቻል አያጠራጥርም።
ምንጊዜም የማይተኙ የውጭ ጠላቶች በተደራጀ ሁኔታ በተለያየ መልኩ ቢሰማሩም፤ እነርሱን ለመቆጣጠር በአንድነት ኢኮኖሚውን ማጠናክር ላይ አተኩሮ መስራት ይገባል። ለዚህ ደግሞ አሁን ላይ ኢኮኖሚውን ለማጠናከር የሚያስችል መሰረት ተጥሏል።
ወቅታዊ ችግሮችን ተቋቁሞ መንግሥት ጠንክሮ ሲሄድና ተዓማኒነት ያላቸው ፍትሃዊ መንግሥታዊ ተቋማትን የመፍጠር ግዴታውን ሲወጣ፤ በደመነፍስ የሚሰሩ ሞያኞችና የተቋማት ሃላፊዎች ቆም ብለው ራሳቸውን በማየት በአዲስ ጎዳና ለመራመድ ጥረት ሲያደርጉ፤ አሁን እየታዩ ያሉ መነሳሳቶች ተጠናክረው ሲቀጥሉ፤ ኢትዮጵያ በእርግጠኝነት ትለወጣለች። ማንም ወደ ታች የሚጎትታት ሳትሆን ተንጠራርቶ የማይደርስባት አይኑን ሰቅሎ የሚያያት ትሆናለች። ለዚህ አሁን ትልቅ የኢትዮጵያዊነት መንፈስ እየነፈሰ ነው።
ከመንግስት ተቋማት በተጨማሪ በአጠቃላይ ህዝቡ የሚጎዱ አካሔዶችን በማስተካከል፤ እያንዳንዱ ዜጋ አዕምሮውን ተጠቅሞ በራሱ ቁሳቁስ ራሱን ለመለወጥ ከተነሳ ኢትዮጵያ ጠንካራ የኢኮኖሚ መሰረት መገንባት አያዳግታትም።
ሁሉም ወደ ራሱ በማየት ‹‹ከእኔ ምን ይጠበቃል›› በሚል የሥራ መንፈስ በመነሳሳት ከተጋ የኢትዮጵያ የብልፅግና ጊዜ ሩቅ አይሆንም። ዜጎች አሮጌ የማይጠቅሙ አካሔዶችን በመተው፤ ለአንድ ለራስ እና ለራስ ቤተሰብ ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም የሚመች መንገዶችን በመፍጠር በህብረት ለአገር መስራት ከተቻለ፤ ጥላቻና ንቀትን በመተው በምትኩ ፍቅርና መከባበር ከተዘራ በእርግጥም ኢትዮጵያ ካደጉት አገራት ተፅዕኖ ትላቀቃለች።
ሁሉም ዜጎች እኩል ታይተው፤ የመላው ኢትዮጵያውያን ባህሎቻችን፣ መብቶቻችንንና ቋንቋዎቻችን ተከብረው፤ ህብረ ብሔራዊ አንድነት ፀንቶ፤ ዜጎች መሰፈሪያቸው ሃይማኖት እና ብሔራቸው ሳይሆን ብቃታቸው ላይ ብቻ ከተመሰረተ በእርግጥም የተራራውን አናት መቆጣጠር ይቻላል። በእብሪት ከመጋጨት ይልቅ ችግሮችን ተነጋግሮ መፍታት እንደባህል ከተወሰደ ሁሉም መንገድ ቀና ይሆናል። ለዚህ ሁሉም ሃላፊነቱን መወጣት አለበት።
የራስ ለውጥ ተደምሮ አገር ይለውጣል፤ ሰው ካልተለወጠና ራሱን ካላደሰ የትናንትናው ቀን እና ያለፈው ዓመት ከዛሬው አይለይም። ዛሬ አዲስ ዓመት ነው። የተጀመረው ዓመት ደግሞ እንዳለፈው ዓመት ዜጎች የሚሰቃዩበት ሳይሆን የሚሰሩበት፤ ሰርተው በበረከት የሚትረፈረፉበት እና የሚደሰቱበት ይሆናል።
ባለፉት ጊዜያት ኢትዮጵያ እንድትጠፋ ብዙ ተሰርቷል። ያ አልሆነም። ኢትዮጵያ አልጠፋችም። ከዚህም በኋላ በምንም ሁኔታ አትጠፋም። ከዚህ ከ2014 ዓ.ም ደግሞ ኢትዮጵያን ለማጥፋት የሚያቅዱ በሙሉ ህልማቸው ዕውን እንደማይሆን የሚያረጋግጡበት ይሆናል። ኢትዮጵያ ዳግም ቁልቁል ላትታይ በሩጫ ተራራውን ለመውጣት እየተንደረደረች ነው። የተራራው አናትን ለመቆናጠጥ ጉዞ ጀምራለች። እኛ እውነተኛ የኢትዮጵያ ልጆች ደግሞ ጉዞዋ የተሳካ እንዲሆን አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ በማድረግ ሃላፊነታችንን እንወጣ እላለሁ። ሰላም!
ምህረት ሞገስ
አዲስ ዘመን መስከረም 5 ቀን 2014 ዓ.ም