ሽብርተኛው ህወሓት ጥቅምት 24/2013 ዓ/ም በሰሜን ዕዝ የመከላከያ ሰራዊት ላይ ጭካኔ የተሞላው፣ ዘግናኝና አረመኔያዊ የክህደት እርምጃ ከፈጸመ ጊዜ ጀምሮ በተለያዩ የሀገሪቱ ክልሎች ከፍተኛ ሰብአዊና ቁሳዊ ጉዳት አድርሷል። ሀገርን ማፍረስ ዋነኛ ዓላማው አድርጎ ከውስጥ እና ከውጭ ቅጥረኛ ሃይሎች ጋር በመተባበር በህዝብና በሀገር ላይ ያልፈጸመው ወንጀል የለም።
ለእኩይ የክፋት ግቡም ቅጥረኛ የዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃንና አክቲቪስቶችን በማደራጀት በሬ ወለደ ዘመቻው በሀገርና በህዝብ ላይ ከፍቷል። ቅጥረኞቹም ይሄንን ሴራና አሰቃቂ ተግባሩን አይተው እንዳላዩ ፤ ሰምተው እንዳልሰሙ ሆነው አለባብሰውና ሸፋፍነው አልፈውታል። አንዳንዶቹም የሽብርተኛውን አጸያፊ ተግባር ሌላ ባለቤት ሲፈልጉለት ከርመዋል።
መገናኛ ብዙሃን በየትኛውም ዓለም ለቆመለት ዓላማ ታማኝ መሆን አለበት። ሙያተኛውም ለሙያው ስነምግባርም ሆነ መርሆዎች መገዛት ይጠበቅበታል። የሚሰራቸው ዜናዎች የሚያሰራጫቸው ዶክመንተሪዎች ሙያውንና ሥነምግባሩን ያከበረ፣ ለህዝብ የወገነ ፣ እውነተኛ እና በየትኛውም ዘመን ተአማኒነት ያለው ታሪክ ሊሆን የሚችል ዘገባዎችን መስራት ይጠበቅባቸዋል። የሚቀርቡ ዘገባዎች እውነት ስለመሆናቸውም ጉዳዩ የሚመለከታቸውን የሁለተኛ ወገን አካላትን ጠይቆ በማረጋገጥና ሚዛኑን በጠበቀ መልኩ ማቅረብ ላይ የተመሰረተ ሊሆን ይገባል። ይሁን እንጂ አሁን አሁን በአንዳንድ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን የሚሰራጩ ወሬዎች ከእውነታው ያፈነገጡ፣ ወደ አንድ ወገን ያጋደሉ ፣ ሚዛኑን ያልጠበቁና ከሙያው ስነምግባር ያፈነገጡ ናቸው።
ሰሞኑን መቀመጫውን በአሜሪካ ጆርጅያ ያደረገው ሲኤንኤን የተባለው መገናኛ ብዙሃን ያሰራጨው ዘገባ ይሄንኑ የሙያውን ስነምግባር የጣሰ ነው። በሌላ ሁለተኛ ነፃ ወገን ያልተረጋገጠ፣ ተጨማሪ ሳይንሳዊ መንገዶችን ወይም የህክምና መረጃዎችን ያላካተተ ዘገባ በኢትዮጵያ ላይ አውጥቷል። በዘገባው ለምንጭነት የተጠቀመበት የአሸባሪው ህወሓት አባል የሆነና በማይካድራ ንጹሃንን የጨፈጨፈ ግለሰብ መሆኑ ትልቅ ስም አለው ተብሎ ከሚጠራ መገናኛ ብዙሃን በፍጹም የሚጠበቅ አይደለም። ይህም ዘገባ ቀደም ሲል በሰዎች አእምሮ ያሉትን ጥርጣሬዎች በተግባር ያረጋገጠና መገናኛ ብዙሃኑንም ግምት ውስጥ የከተተ ነው። በእርግጥ የሀገሬ ሰዎች “አውቆ የተኛን ቢቀሰቅሱት አይሰማም” የሚል አባባል አላቸው ።
እውነታውን ክደውና ደብቀው የሚሰሩ መገናኛ ብዙሃን በአንድ በኩል የተቋቋሙበትን ሀገርና መንግስት ፍላጎት ለማሟላት በሌላም በኩል እንደ ህዝብ ስልክ በተሞላላቸው ሳንቲም ልክ ሙያውን አሳልፈው የሚሸጡ ናቸው። አሸባሪው ህወሓት በኢትዮጵያና በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ የሚፈጽመውን ግፍ እና ጭካኔ ፣ የሰብአዊነት ጥሰት፣ ሀብትና ንብረት ዘረፋና ውድመት የመሳሰሉትን አሰቃቂ ተግባራት አይተው እንዳላዩ ሲያልፉ አይተን ታዝበናቸዋል። ለምሳሌ ያህል አሸባሪው ህወሓት በአማራ ክልል በማይካድራ አሰቃቂ የጅምላ ጭፍጨፋ ፈጽሟል።
አጋምሳና ጭና እንዲሁም በአፋር ክልል ጋሊኮማ ላይ ንፁሃን ዜጎችን በመጨፍጨፍ አሸባሪነቱን በተግባር አረጋግጧል፤ አሁን ደግሞ በሰሜን ወሎ ዞን ወረባቡ አካባቢ ንጹሀንን ገድለው የአውሬ ሲሳይ እንዲሆኑ አድርጓል። በርካታ ህጻናት ፣ሴቶችና አረጋውያን በሚያሳዝን መልኩ ባልጠበቁት ሁኔታ ህይወታቸውን አጥተዋል። እንዲሁም ሴቶች ሲደፈሩ ፣ ህጻናት ሰብሳቢ ወላጅ አጥተው ለከፋ አደጋ ሲጋለጡ ዓለም አቀፉ መገናኛ ብዙሃን ሰምተው እንዳልሰሙ አይተው እንዳላዩ አይናችንን ግንባር ያድርገው ብለው አልፈውታል።
ከዚሁ ጎን ለጎን ደግሞ ለከፋያቸው በሚወግንና እውነታን በዘነጋ መልኩ እንዳውም ያልነበረ ወይም ሀሰተኛ ፎቶ ጭምር ማስረጃ አድርገውና ዜና ፈብርከው ዓለም አቀፉን ማህበረሰብ በሚያሳስት መልኩ ሲዘግቡ አይተናል ፤ አንብበናል። በሁለተኛ ወገን ያልተረጋገጠ መንግስትና ህዝብን በመረጃነት ያላካተተ፣ ሳይንሳዊ መንገዶችን ያልተከተለ፣ የአንድ ወገን ለዚያውም የሽብርተኛ ቡዱኑ አካል ከሳሽም መስካሪም የሚሆንበትን ሀሰተኛ መረጃ ብቻ ያነገበ ዘገባን አውጥተዋል።
አሸባሪው ህወሓት ዓለም አቀፍ ህግጋትን በመጣስ ህጻናትን በጦርነት እየማገደ ፣ ቆሜልሀለሁ የሚለውን የትግራይን ህዝብ እርዳታ የመጣን እህል አንድም የግዳጅ ማስፈጸሚያ ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ላሰማራው ጦር ስንቅ እያዋለና ህዝቡን በረሀብና በችግር እየቆላ ባለበት በዚህ ወቅት ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ጉዳያቸው ሳያደርጉት አልፈው ዛሬ ለሽብርተኛው ቡድን አፈቀላጤ ሆነው መቆማቸው ያስተዛዝባል።
ዓለም አቀፉ መገናኛ ብዙሃን የሚያቀርቡትን ዘገባ አይቶና አድምጦ ማንነታቸውን መገመት አእምሮ ላለው ሰው ከባድ አይሆንም። ለከፋያቸው በማጎብደድ ላይ መሆናቸውን በማስረጃ ያረጋግጣል ። በእርግጥ እውነት ትቀጥን ይሆናል እንጂ አትበጠስም። ታፍና እና ተዳፍና አትቀርም። ያኔ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን በሰራቸው ሀሰተኛ ዘገባዎች ይጋለጣሉ ፤ ደግሞም ያፍራል!
አዲስ ዘመን መስከረም 5 ቀን 2014 ዓ.ም