ግዙፉ የስፖርት ትጥቅ አምራች ኩባንያ አዲዳስ ‹‹አዲዜሮ›› በሚል ስያሜ ስፖንሰር የሚያደርጋቸው አትሌቶቹን በአዲሱ ዓመት ማግስት በጀርመን በተለያዩ የጎዳና ላይ ውድድሮች አፎካክሯል። በ5 እና 10 ኪሎሜትሮች እንዲሁም በግማሽ ማራቶን ርቀቶች ፈጣን ሰዓት ለማስመዝገብ በተደረጉት የጎዳና ላይ ውድድሮች ሃያ ሦስት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ተሳታፊ ሆነዋል።
የ2015 የዓለም ቻምፒዮና የ5 ሺ ሜትር የብር ሜዳሊያ አሸናፊዋ አትሌት ሰንበሬ ተፈሪ በ5ኪሎ ሜትር ባደረገችው የጎዳና ላይ ውድድር የዓለም ክብረወሰን አሻሽላ በማሸነፍ አዲሱን ዓመት ተቀብላለች። በኢትዮጵያውያን የበላይነት በተጠናቀቀው በዚህ ውድድር ሰንበሬ ርቀቱን 14:29 በሆነ ሰዓት በአስደናቂ ጥረት ስትፈፅም፣ ከሦስት ሳምንት በፊት በኬንያ በተካሄደው የዓለም ከ20 ዓመት በታች ቻምፒዮና በ3 እና በ5ሺ ሜትሮች የብርና የነሐስ ሜዳሊያ ያጠለቀችው አትሌት መልክናት ውዱ በ25 ሰከንድ ልዩነት ሁለተኛ ሆና አጠናቃለች። ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት አትሌት ንግስቲ ሃፍቱ 14:54 በሆነ ሰዓት ሦስተኛ ሆና አጠናቃለች።
ከስድስት ሳምንት በፊት በቶኪዮ ኦሊምፒክ በአምስት ሺ ሜትር ስድስተኛ ደረጃን ይዛ ያጠናቀቀችው ሰንበሬ በአዲስ ዓመት ማግስት ባደረገችው አንድ የጎዳና ላይ ውድድር ሁለት የዓለም ክብረወሰኖችን በእጇ አስገብታለች። የመጀመሪያው ክብረወሰን በርቀቱ በኬንያዊቷ ቢትሪስ ቺፕኮይች በ14:44 ተይዞ የቆየውን የሴቶች ብቻ የዓለም ክብረወሰን ሲሆን ሌላኛው በትውልደ ኢትዮጵያዊቷ የኔዘርላንድስ አትሌት ሲፋን ሃሰን በወንድ አሯሯጮች ታግዛ የሰበረችው 14:43 ሰዓት ነው።
ከዚህ በተጨማሪ ሰንበሬ ያስመዘገበችው ሰዓት በርቀቱ ታሪክ በየትኛውም አጋጣሚ ከተመዘገቡ ፈጣን ሰዓቶች ቀዳሚው ሆኗል። ይህም ከዚህ ቀደም የርቀቱ የዓለም ክብረወሰን መመዝገብ ከመጀመሩ በፊት ኬንያዊቷ ጆይስሊን ጂፕኮስጌ ከሮጠችው 14:32 ሰዓት ሁሉ የፈጠነ ሰዓት መሆኑ ነው። «በጣም ተደስቻለሁ» በማለት ከድሉ በኋላ አስተያየቷን ለመገናኛ ብዙኃን የሰጠችው ሰንበሬ ከቶኪዮ ኦሊምፒክ በኋላ ይህን የዓለም ክብረወሰን ለማሻሻል ተዘጋጅታ እንደነበረ ተናግራለች።
በተመሳሳይ ዕለት በተካሄደው የወንዶች 10 ኪሎ ሜትር ውድድር የዓለም ክብረወሰን ባለቤት የሆነው ኬንያዊው አትሌት ሮኔክስ ኪፕሩቶ 26:43 በሆነ ሰዓት አሸናፊ ሆኗል። ይህም በርቀቱ ታሪክ አራተኛው ፈጣን ሰዓት ሆኖ ተመዝግቧል። በኬንያው ከ20 ዓመት በታች የዓለም ቻምፒዮና በ3ሺ ሜትር ወርቅ ያጠለቀው ኢትዮጵያዊ አትሌት ታደሰ ወርቁ 26:56 በሆነ ሰዓት ሁለተኛ ሆኖ ሲያጠናቅቅ ያስመዘገበው ሰዓት የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ክብረወሰን ሆኗል። ኬንያዊው ኬኔዲ ኪሙታይ 27:09 በሆነ ሰዓት ሦስተኛ ሆኖ ፈፅሟል።
በወንዶች 5ሺ ሜትር ውድድር ጃኮብ ክሮፕ 13:06 በሆነ ሰዓት ቀዳሚ ሆኖ ሲያጠናቅቅ፣ የሁለት የዓለም ቻምፒዮናዎች አሸናፊው አትሌት ሙክታር ኢድሪስ ሦስት ሰከንድ ዘግይቶ ሁለተኛ ሆኖ ፈፅሟል። ዩጋንዳዊው ሆሴ ኪፕላንጋት ደግሞ 13:13 በሆነ ሰዓት ሦስተኛ በመሆን ውድድሩን ጨርሷል። በዚህ ውድድር ኢትዮጵያዊው ኦሊምፒያን ዮሚፍ ቀጄልቻ አቋርጦ ወጥቷል።
ኬ ንያውያን አትሌቶች በበላይነት ባጠናቀቁበት የሴቶች 10 ኪሎ ሜትር ውድድር አግኒስ ቲሮፕ የሴቶች ብቻ የሆነውን የዓለም ክብረወሰን በሃያ ስምንት ሰከንድ በማሻሻል ስታሸንፍ 30:01 የሆነ ሰዓት አስመዝግባለች። ሼላ ቺፕኪሩይ 30:17 እና ናንሲ ጄላጋት 30:50 በሆነ ሰዓት ተከታትለው በመግባት ውድድሩ በኬንያውያን የበላይነት ተጠናቋል። በተመሳሳይ የኬንያውያን የበላይነት በተንፀባረቀበት የግማሽ ማራቶን ውድድር በሴቶች ብሬንዳ ጂፕሌቲንግ 1:06:52 በሆነ ሰዓት ቀዳሚ ሆና ስታጠናቅቅ ኢትዮጵያዊቷ በሱ ሳዶ 1:08:15 በሆነ ሰዓት ሁለተኛ ሆናለች።
ብሪሊያን ጂፕኮሪር 1:08:28 በመግባት ከኬንያ ሦስተኛ ሆናለች። በወንዶች መካከል በተካሄደውም ተመሳሳይ ውድድር ኬንያውያን ከአንድ እስከ አምስት ባለው ደረጃ ውስጥ ማጠናቀቅ ችለዋል። አቤል ኪፕቹምባ 58:48፣ አሌክስአንደር ሙቲሶ 59:20፣አሞስ ኪቢዮት 59:34 በሆነ ሰዓት የሜዳሊያ ደረጃውን ይዘው ያጠናቀቁ አትሌቶች ናቸው።
አትሌት ሰንበሬ ተፈሪ የ5ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ የዓለም ክብረወሰን ሰብራለች፣
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን መስከረም 4/2014