ከዓለም ሕዝብ አምስት በመቶ የሚሆነው በመስማት ችግር እንደሚሰቃይ የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ ያመላክታል። አምስት በመቶ ማለት በመቶኛ ሲገለጽ ትንሽ ቢመስልም በቁጥር ሲገለጽ ግን ከፍተኛ ቁጥር ነው። ከ430 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ በዓለም አቀፍ ደረጃ በመስማት ችግር ውስጥ ይኖራል እንደማለት ነው። ይህም የብዙ ሀገራት አጠቃላይ የሕዝብ ድምር እንደማለት ነው።
የዓለም የሕዝብ ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መሆኑን ተከትሎ በቀጣይ ጊዜያት መስማት የተሳናቸው ሰዎች ቁጥር እየጨመረ እንደሚሄድ የሚያሳየው ዓለም ጤና ድርጅት መረጃ ጉዳዩን የበለጠ አሳሳቢ እንደሆነ ይገልጻል። እንደ ድርጅቱ መረጃ ከሆነ እ.አ.አ በ2050 መስማት የተሳናቸው ሰዎች ቁጥር ወደ 700 ሚሊዮን ይደርሳል። ይህም ማለት ከአስር ሰው አንዱ የመስማት ችግር ያጋጥመዋል ማለት ነው።
እነዚህ መስማት የተሳናቸው የኅብረተሰብ ክፍል የምልክት ቋንቋን በመጠቀም እርስ በእርሳቸው እንዲሁም የምልክት ቋንቋን ከሚችሉ የመስማት ችግር ከሌለባቸው ጋር መግባባት ቢችሉም፤ አብዛኛው የመስማት ችግር የሌለባቸው ሰዎች የምልክት ቋንቋን ስለማይችሉ ለመግባባት ያዳግታቸዋል። በዚህም ምክንያት ለተለያዩ ችግሮች ይጋለጣሉ።
የዓለም ጤና ድርጅት መረጃዎች እንደሚያሳዩት መስማት የተሳናቸው ሰዎች እንደ ድብርት እና ጭንቀት ባሉ የስነልቦናዊ ችግሮች የመሰቃየት ዕድላቸው የመስማት ችግር ከሌለባቸው ሰዎች በሁለት እጥፍ ከፍ ያለ ነው። መስማት የተሳናቸው ሰዎች የሚያጋጥማቸው ድብርት እና ጭንቀት ከመገለል ስሜት የመነጨ ነው። ለእነዚህ ዓይነቶች ጉዳዮች በጣም ውጤታማው መፍትሄ የቴራፒ ህክምና ሲሆን ብዙውን ጊዜ ከህክምና ባለሙያው ጋር መነጋገር ስለሚከብዳቸው ሁኔታውን የከፋ ያደርገዋል።
መስማት የተሳናቸው ሰዎች የመስማት ችግር ከሌለባቸው ሰዎች ጋር የመግባባት ክፍተትን ለመሙላት ከዚህ ቀደም የተለያዩ ጥረቶች ሲደረግ የነበረ ቢሆንም ይህ ነው የሚባል ውጤት ማግኘት አልተቻለም ነበር። ሰሞኑን ግን ከሀገረ አሜሪካ አዲስ ብስራት አዲስ ቴክኖሎጂ ይፋ ተደርጓል። በአሜሪካ በኒውዮርክ የሚገኘው ቡፋሎ ዩኒቨርሲቲ የተመራማሪዎች ቡድን የጆሮ ማዳመጫን ከስማርት ስልክ ጋር በማገናኘት የምልክት ቋንቋን ወደ ድምፅ መተርጎም ወደሚችል መሳሪያ መቀየራቸው ሰሞኑን ይፋ ተደርጓል።
መሳሪያው ‹‹ዶፕለር›› የተባለውን ቴክኖሎጂ ጥቅም ላይ በመዋል የድምጽ ሞገድን በመልቀቅ የምልክት ቋንቋን ከሚያሳየው ሰው እጅ ላይ ነጥረው የሚመጡ የድምፅ ሞገዶችን ቅርፅ መተርጎም ማስቻሉን ቴክ ኤክስፕሎር የተሰኘው አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሰራ ድረ ገጽ አስነብቧል።
‹‹ሶኒክ ኤ.ኤስ.ኤል›› በሚል ስያሜ በተጠራው በዚህ መሳሪያ ለጊዜው የአሜሪካን የምልክት ቋንቋ ተጠቅሞ በቤት ውስጥ በተደረገ ሙከራ መሳሪያው የምልክት ቋንቋዎችን ወደ ድምጽ በመቀየር ረገድ 93 ነጥብ 8 በመቶ ውጤታማ መሆን መቻሉን ነው ድረ ገጹ ያስነበበው።
42 ቃላትን ያካተተ በቤት ውስጥ እና ከቤት ውጪ በተደረጉ ሙከራዎች አዲሱ ቴክኖሎጂ 93 ነጥብ ስምንት በመቶ ውጤታማ መሆኑ የተረጋገጠ ሲሆን፤ ሙከራው ከተደረገባቸው የቃላት ምሳሌዎች መካከል «ፍቅር» ፣ « ስፔስ» እና «ካሜራ» የሚሉት ይገኙበታል።
በተመሳሳይ 30 ቀላል ዓረፍተ ነገሮች ላይ በተደረገው ሙከራ ቴክኖሎጂው 90 ነጥብ ስድስት በመቶ ውጤታማ መሆኑ ተረጋግጧል። ሙከራው ከተደረገባቸው ቀላል አረፍተ ነገሮች መካከል እራስዎትን በመገናኘቴ ደስ ብሎኛል የሚል ይገኝበታል።
ምርምሩ ከዚህ ቀደም በአጋዥ ቴክኖሎጂዎች አሊያም በተጨማሪ የሰው ኃይል የምልክት ቋንቋዎችን ለመተርጎም የሚደረገውን ጥረት ወደ አዲስ ምዕራፍ እንደሚወስድ ይጠበቃል። ከዚህ በኋላ በዘርፉ ለሚሰሩ ሥራዎችም መሠረት እንደሚሆን በርካቶች ከአሁኑ እየተናገሩ ነው።
መሣሪያው መስማት በተሳናቸው እና በሌሎች ሰዎች መካከል የሚደረግ ተግባቦትን በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚያቃልል ተመራማሪዎቹ እምነት እንዳላቸው ነው ቴክኖሎጂውን ይፋ ባደረጉበት ወቅት አብራርተዋል።
በቡፋሎ ዩኒቨርሲቲ የኮምፒዩተር ሳይንስና ኢንጂነሪንግ ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት ዣንፔንግ ጂን « ‹ሶኒክ ኤ ኤስ ኤል› መስማት የተሳናቸው እና መስማት በሚችሉ ሰዎች መካከል ያለውን ግንኙነት በከፍተኛ ሁኔታ ማሻሻል እንደሚቻል በጽንሰ ሀሳብ ደረጃ ተይዞ የነበረውን በተግባር ማረጋገጥ ያስቻለ ነው» ብለዋል።
ነገር ግን እንዲህ ዓይነቱ ቴክኖሎጂ ለንግድ ከመቅረቡ በፊት ብዙ ሥራ መሰራት አለበት ሲሉ ተነናግረዋል። ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት ዣንፔንግ ጂን ለምሳሌ የሶኒክ ኤ ኤስ ኤል መዝገበ ቃላት በከፍተኛ ሁኔታ መስፋፋት አለበት ብለዋል። እንዲሁም፣ ሥርዓቱ የአሜሪካ የምልክት ቋንቋ ዋና አካል የፊት ገጽታዎችን ማንበብ መቻል አለበት ብለዋል። የምርምር ውጤቱ እ.አ.አ ከመስከረም 21 እስከ 26 በሚካሄደው የ ኤ ሲ ኤም ኮንፈረንስ ላይ ይቀርባል ተብሎ እንደሚጠበቅም ተነግሯል።
የዓለም መስማት የተሳናቸው ፌዴሬሽን ባወጣው መረጃ መሰረት ሦስት መቶ የተለያዩ የምልክት ቋንቋዎችን የሚናገሩ 72 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች በዓለም ዙሪያ ይገኛሉ።
ምንም እንኳን የተባበሩት መንግሥታት የምልክት ቋንቋዎች የመስማት ችግር በሌላቸው ከሚነገረው ቃል ጋር እኩል መሆናቸውን እውቅና የሚሰጥ ቢሆንም፣ ይህ አመለካከት በብዙ ሀገሮች ገና እውን አልሆነም። መስማት የተሳናቸው ወይም የመስማት ችግር ያጋጠማቸው ሰዎች አሁንም በርካታ የመግባባት መሰናክሎች ያጋጥማቸዋል።
በተለምዶ መስማት በተሳናቸው የአሜሪካ የምልክት ቋንቋ ተጠቃሚዎች (ኤ ኤስ ኤል) ተጠቃሚዎች እና መስማት የተሳናቸው ሰዎች የሚጠቀሙትን ቋንቋ በሚያውቁ መስማት በሚችሉ ሰዎች መካከል መግባባት የሚከናወነው በምልክት ቋንቋ አስተርጓሚ ወይም በካሜራ ቅንብር በኩል ነው።
ተባባሪ ፕሮፌሰር ዣንፔንግ ጂን እንደሚሉት የምልክት ቋንቋን ለመተርጎም ሥራ ላይ የሚውሉ ካሜራዎች አጠቃቀምን በተመለከተ በርካቶች ስጋት እንዳላቸው ሲገልጹ ሰንብተዋል። ዘወትር ከሚደመጡ የስጋት ድምጾች መካከል እነዚያ የካሜራ ቀረጻዎች አላግባብ ጥቅም ላይ መዋል አለመቻላቸውን በምን ማረጋገጥ ይቻላል የሚለው ነበር። በተጨማሪም የምልክት ቋንቋ አስተርጓሚዎች አጠቃቀም ይበልጥ እየተለመደ የመጣ ቢሆንም፤ አንድ አስተርጓሚ ሰው በተፈለገበት ሰዓት ሊገኝ እንደሚችል ምንም ዋስትና የሌለ መሆኑ ካሜራም ሆነ አስተርጓሚዎች ላይ ሙሉ እምነት ለመጣል አስቸጋሪ ሆኖ ነበር።
ሶኒክ ኤ ኤስ ኤል እነዚህን ጉዳዮች ለመፍታት ያለመ መሆኑን ያብራሩት ተባባሪ ፕሮሰሩ፤ በተለይም በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ ምንም ቅድመ ዝግጅት እና እቅድ ሳያስፈልገው ለሌሎች አገልግሎቶች ሊውሉ የሚችሉ የጆሮ ማዳመጫዎች ላይ ማሻሻያ በማድረግ ብቻ ይህንን አገልግሎት እንዲሰጡ የሚቻል መሆኑ ቴክኖሎጂውን ልዩ እንደሚያደርገው ተናግረዋል።
በሰሜን ምዕራብ ዩኒቨርሲቲ የድህረ ምረቃ ምሁር ከመሆናቸው በፊት በተባባሪ ፕሮፌሰር ጂን ላብራቶሪ ውስጥ ምርምሩን ያጠናቀቁት የምርምሩ ተባባሪ መሪ ያንግ ጋኦ «እኛ ሶኒክ ኤ ኤስ አልን በተለያዩ አካባቢዎች ማለትም ቢሮ፣ አፓርታማ፣ ኮሪደር እና የእግረኛ መንገድ ሥፍራዎችን ሞክረናል» ብለዋል። ምንም እንኳን አጠቃላይ የአካባቢያዊ ድምፆች ሲጨመሩ ትንሽ የትክክለኛነት ችግር ቢታይም፣ አብዛኛው የአካባቢያዊ ድምፆች በሶኒክ ኤ ኤስ ኤል በሚፈለገው ድግግሞሽ ክልል ላይ ሁሌም ጣልቃ ስለማይገቡ አጠቃላይ ትክክለኝነት አሁንም በጣም ጥሩ ነው።
ዋናው የሶኒክ ኤ ኤስ ኤል አልጎሪስም (ስልተ ቀመር) በማንኛውም ስማርትፎን ላይ ሊተገበር እና ሊሰራ ይችላል ያሉት ያንግ ጋኦ፤ ሶኒክ ኤ ኤስ ኤል ከአሜሪካ የምልክት ቋንቋ ባሻገር በሌሎች የምልክት ቋንቋዎች ላይም በማመቻቸት ሊተገበሩ የሚችሉ መሆናቸውንም አረጋግጠዋል።
ከዚህ ቀደም መስማት የተሳናቸው እና የመስማት ችግር የሌላቸው መካከል የሚፈጠረውን የተግባቦት ክፍተቶችን ለመሙላት ጥረት የማድረግ ኃላፊነት መስማት ለተሳናቸው ብቻ ተትቶ የነበረ መሆኑን የሚጠቁሙት ተመራማሪዎቹ በቅርቡ ሥራ ላይ የሚውለው ሶኒክ ኤ ኤስ ኤል ግን በተቃራኒው የመስማት ችሎታ ያላቸው ሰዎች መስማት ከተሳናቸው ሰዎች ጋር ለመግባባት ጥረት እንዲያደርጉ የሚያስችል ነው ብለዋል።
«የተለያዩ የምልክት ቋንቋዎች የራሳቸው አጠራር፣ የቃላት መፈጠር እና የቃላት ቅደም ተከተል ያላቸው እንዲሁም የተለያዩ ባህሪዎች አሏቸው» ያሉት ተባባሪ ፕሮፌሰር ጂን፤ «ለምሳሌ፣ ተመሳሳይ ምልክት በተለያዩ አገሮች ውስጥ የተለያዩ የምልክት ቋንቋ ቃላትን ሊወክል ይችላል። ሆኖም፣ የሶኒክ ኤ ኤስ ኤል ቁልፍ ተግባር በምልክት ቋንቋዎች ቃላትን እና ዓረፍተ ነገሮችን የሚወክሉ የተለያዩ የእጅ ምልክቶችን መለየት ነው፣ እነሱ አጠቃላይ እና ሁለንተናዊ ናቸው። ምንም እንኳን የአሁኑ ቴክኖሎጂ በኤ ኤስ ኤል ላይ ያተኮረ ቢሆንም፣ የአልጎሪዝም (የስልተቀመር) ሞዴሉን በትክክል በማሰልጠን ፣ ከሌሎች የምልክት ቋንቋዎች ጋር በቀላሉ ሊላመድ ይችላል።» ብለዋል።
ምርምሩን የበለጠ ውጤታማ ለማድረግ እና ለሁሉም ተደራሽ ለማድረግ በቀጣይ የተለያዩ እርምጃዎችን ለመውሰድ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የገለጹት ተባባሪ ፕሮፌሰር ጂን እንደሚሉት ከቀጣዮቹ እርምጃዎች መካከል በሶኒክ ኤ ኤስ ኤል ሥራ ላይ ሊውሉ፣ ሊታወቁ እና ሊለዩ የሚችሉ የምልክት ቋንቋ መዝገባ ቃላትን ማዘጋጀት እና ማስፋፋት እንዲሁም የምልክት ቋንቋ ዋነኛው አካል የሆነውን የፊት ገጽታዎችን የማንበብ ችሎታን ለማካተት እንደሚሰራ ጠቁመዋል።
«ተመራማሪዎች በ ሶኒክ ኤ ሴስ ኤል ላይ በቀጣይ ለመስራት ያቀዷቸው ሥራዎች መስማት በተሳናቸው እና መስማት በሚችሉ ሰዎች መካከል ተግባቦትን ለማሳለጥ እና ለማመቻቸት ለተጠቃሚ ምቹ፣ ለአጠቃቀም ምቹ እና ቀላል የሆነ የጆሮ ማዳመጫ ዘይቤን ለማዳበር ያለመ ነው» ይላሉ ተባባሪ ፕሮፌሰር ጂን።
ከቡፋሎ ዩኒቨርሲቲ በተጨማሪ በዩናይቲድ ኪንግደም የሚገኘው የሳውዝሃምፕተን ዩኒቨርሲቲ እና የዋሽንግተን ዩኒቨርሲቲን የሚወክሉ የተለያዩ ተመራማሪዎች ለምርምሩ ስኬታማነት አስተዋጽኦ ማበርከታቸውም ነው የተነገረው::
መላኩ ኤሮሴ
አዲስ ዘመን መስከረም 4/2014