የሰው ልጅ ሰዓታትን ቀናትንና ዓመታትን ከፋፍሎ እንደ እምነቱ፣ ባህልና የሥልጣኔ ደረጃው የራሱን የቀን መቁጠሪያ አዘጋጅቶ ይጠቀማል። ኢትዮጵያ ከሌላው ዓለም በተለየ የራሷ የዘመን ስሌትና ቀመር ያላት ጥንታዊት አገር ናት። ለኢትዮጵያውያን መስከረም የዓመት መጀመሪያ ወር ናት፡፡ ከአንዱ ዘመን ወደ ሌላው የመሸጋገር ምልክት ናት፡፡ ክረምት አልፎ መስከረም ሲጠባ፣ አሮጌ ዓመት ሄዶ አዲሱ ይገባል፡፡
በወርሃ መስከረም የሐምሌ ጨለማ፣ የነሐሴ ዝናብ ይሻራል፡፡ የደፈረሰ ጅረት፣ የጠገገ ሰማይ ይሰናበታሉ፡፡ የክረምት ጭለማ አልፎ ብርሃን ይመጣል፡፡ ወንዞች ኮለል ይላሉ፡፡ ሰማዩ ይጠራል፡፡ አበቦች ይፈካሉ፡፡ በአዲሱ ዓመት መባቻ በወርሃ መስከረም ሜዳው፣ ጋራው፣ ሸንተረሩ በአደይ አበባ ይለመልማል። በአረንጓዴ ነገሮች ከመከበቡም ሌላ ነፍስን የማለምለም ሀሴትን የመፍጠር አቅም አለው፡፡
የዘመን በዘመን የጊዜ በጊዜ መተካት የማያቋርጥ ሂደት ቢሆንም አዲስ ዓመት ሰው ከራሱ ጋር ይታረቅ ዘንድ፣ እቅዱ ከግቡ እንዲስማማ፤ ውጫዊና ውስጣዊ ሕይወቱ እንዲጣጣም ወሳኝ ድርሻ አለው፡፡ አዲስ ዓመት የሰው ልጅ ራሱን የሚያሻሽልበት፣ ያለፈውን ሕይወቱን ገምግሞ ደካማውን ሽሮ ጠንካራውን ይዞ እንዲቀጥልበት ለራሱ የፈጠረው የቀን ቀጠሮ ነው፡፡
አዲስ ዓመትም ራስን ለመለወጥ፣ አስተሳሰብን ለማደስ፣ አኗኗርን ለማስተካከል፣ ለማሰብና ለማሰላሰል ዕድል ይሰጣል፡፡ ዘመን አልፎ ዘመን ሲተካ ሰው ባሰመረው የጊዜ ድንበር ለአዲስ ዓመት ሁሌም አዲስ ያስባል፡፡ ኢትዮጵያውያንም አሮጌውን ዘመን ሸኝተው አዲሱን ዘመን ተቀብለዋል፡፡
አዲስ ዓመትም፣ በአብዛኛው ኢትዮጵያውያን ዘንድ አዲስ ቃል የሚገቡበት ዕለቱ ነው፡፡ ሁሉም በየፊናው መጪው ጊዜ መልካም እንዲሆን፤ ኑሮው እንዲሳካ፣ ጎጆው እንዲሞላ፣ መንፈሱ እንዲረካ፣ አዕምሮው እንዲሰላ፣ ነፍስያው እንዲጠግብ፣ የውስጡም የውጪውም ሕይወቱ እንዲያምር ያቅዳል፡፡
ለአብዛኞቻችን ኢትዮጵያውያንም እውነተኛው የአዲስ ዓመት ትርጉሙም አዲስ ሰውነት፣ አዲስ አስተሳሰብ፣ አዲስ ለውጥ፣ አዲስ የሕይወት መንገድ የምናበጅበት፣ ለራሳችን ቀና አስተሳሰብ የምንቀይስበት በአጠቃላይ አዲስ የምንሆንበት የአዲስነት የጅማሮ ቀን ነው፡፡
አዲስነት የትናንቱን ድካም፤ ያለፈውን አጉል ልማድ መድገም ሳይሆን አዲሱን ኑሮ በአዲስ ሰውነት፣ በሰለጠነ አስተሳሰብና በቀናነት መጀመር ነው፡፡ አዲስነት በግንዛቤ መበልጸግ፣ በጥበብ መጎልመስ፣ ራስን በመቆጣጠር መርቀቅ ጭምር ነው፡፡
ዓመቱ አዲስ እንዲሆን ደግሞ አዲስ ሰው መሆን ይጠይቃል፡፡ አዲስን ወይን ጠጅ በአሮጌ አቁማዳ ውስጥ እንደማይጨምሩት አዲሱና አሮጌው እንደማይስማሙ ሁሉ ሰው በአዲስነት ካልተቀበለው አዲስ ዓመት አይጠቅመውም፡፡
በዘመን ሂደት፣ በትውልድ ቅብብል የማይጠቅምን አስተሳሰብ ማራመድ ለፖለቲከኛውም፣ ለሕዝቡም ለኢትዮጵያም የሚያመጣው በጎ ነገር የለውም። ከዚያ ይልቅ የማይድን ቁስል ሆኖ ሁሌ በበሽታው የሚያሰቃይ ገዳይ በሽታ ይሆናል። አንድ ከማድረግ ይልቅ የሚነጣጥል፤ መሰብሰብን ትቶ የሚበትን፣ ከማዋሃድ ይልቅ የሚለያይ አስተሳሰብን ማራመድ ኪሳራ እንጂ ትርፍ የለውም።
አንዳንድ የአስተሳሰብ ቁስልን ገና በእንጭጭነቱ ማከም እየተቻለ ውሎ ያድርና ቁስሉ አመርቅዞ ወደ ካንሰር ይለወጣል። ወደካንሰር ያደገን ቁስል ማዳን አይቻልም። ቀውሱ ሁልጊዜም በቁስሉ ህመም ሲሰቃዩ መኖር ብቻ ነው። ማስታገሻ እንጂ መፈወሻ መድሐኒት የለውም። ሕመምን በቶሎ ማከም መቻል ከብልህ ሰው የሚጠበቅ አዋቂነት ነው። ቢቻል ሕመሙ እንዳይከሰት ቀድሞ መጠንቀቅ ነው። ጥንቁቅነት ከልባሞች የሚመነጭ ቅድመ መከላከያ ነው። ጥንቁቅነት ፍራቻ አለመሆኑን የሚረዱት አስተዋዮች ብቻ ናቸው።
አንድ መታወቅ ያለበት ወሳኝ ጉዳይ ቢኖር ማሰብ መቻል ልዩ ፀጋ ነው። መልካም ሃሳብን መርጦ መተግበር ደግሞ ሰው በራሱ ላይ የሚያመጣው በረከት ነው። ማንም ለሆዱ የሚስማማውን ምግብ እንደሚመርጠው ሁሉ ለአዕምሮውም የሚመጥን ሃሳብን መመገብ ራስን መጥቀም ነው።
ንፁህ ምግብ ሰውን ከበሽታ እንደሚከላከለው ሁሉ ንጹህና መልካም ሃሳብም ሰውን አፍራሽ ተልዕኮ ካለው ተግባር ያቅበዋል። ሰው ሃሳቡን እያበጠረ ገለባ ሃሳቡን የሚያስወጣበትና ጠቃሚውንና ፍሬ ሃሳቡን የሚያስቀርበት የሕሊና ወንፊት መስራት ይገባዋል። ሃሳብ እንደስንዴ እንክርዳድ ካልተጣራ ንጹሁንም ሃሳብ ያበላሻል።
እኛ ኢትዮጵያውያን ትናንት በሃሳብ ቀድመው ከፍ ከፍ እንዳላልን ዛሬ ዝቅ ብለን ከሌሎች አገራት ጭራ ሆነን አንገት ደፍተናል። አዲስ ሃሳብ መስራት፣ ሃሳቡን ማርቀቅ፣ ሃሳቡን ማጎልመስ፣ ሃሳቡን በተሻለ ሃሳብ መጣል፣ ሃሳቡን በሃሳብ ማድመቅ የሚያስችል ባህል ጠፍቶብናል፡፡ ትናንትም ሆነ ዛሬ እየተመላለሰ የሚደቁሰንና አዙሪት ሆኖብን ወደፊት አላንቀሳቅስ ያለን ችግራችንን በአስተሳሰብ ልዕልና ተነጋግረንና ተወያይተን ፍቱን የሆነ መፍትሄ ማስቀመጥ አለመቻላችን ነው፡፡
ይህን ታሪክ በአዲስ ዓመት መለወጥ ይኖርብናል፡፡ ኢትዮጵያችን በአዲስ ዓመት አዲስ አስተሳሰብ ያለው ዜጋን ትፈልጋለች፡፡ የሚክሳት እንጂ የሚከሳት አያስፈልጋትም፡፡ ዘመን የሚዋጅ፣ ትውልድን እንደ አዲስ የሚቀርፅ ትውልድ ትሻለች፡፡ ትንሳኤዋን የሚሻ፣ ወደ ኋላ የሚጎትትና የማይጠቅም አስተሳሰብ በአዲስና በተሻለ አስተሳሰብ መለወጥ የሚችል ዜጋን ትናፍቃለች፡፡ ሊገነባ፣ ትውልድ ከፍ ከፍ ሊያደርግ የሚችል አስተሳሰብ ትሻለች፡፡
በአዲስ ዓመት ለመናቆር ሳይሆን ለመፋቀር ቦታ እንስጥ፡፡ ፀጉር ከመንጨት፣ ሃሳብ ማመንጨት
እናስቀድም፡፡ ከመቆላለፍ መተላለፍን፣ ከመተናነቅ፣ መደናነቅን እንምረጥ፡፡ ከአቧራ ምኞት ከአቧራ ሕይወት እንውጣ፡፡ የአምናውን ዕዳ እንውረስ፡፡ የአምናውን ክፋት አንጨርስ፡፡ አዲስ ጎዳና ይተለም፡፡ አዳዲስ ፈትል
ይቀለም፡፡ ተከፋፍሎ መፍረስ ይብቃ፡፡ ለቆጡ ተንጠራርተን የብብቱ አያምልጠን፡፡
የእብደቱ መንገድ ቁልቁለቱ፣ በዘር ሀረግ መለቃቀም፣ በእምነት ጥላ መጠቃቀም ይብቃን፡፡ በሰውነት እንከባበር፡፡ ማድላት ማግለል እንቅበር፡፡ ቅን እናስብ፡፡ ቅን እንናገር፡፡ አፍና ልባችን አንድ ይሁን፡፡ ወጥመዱን ሁሉ እንበጥስ፡፡ተንኮሉን ሁሉ እናፍርስ፡፡
በአዲስ ዓመት በአስተሳሰብ ለውጥ ‹‹እኛ እነሱ››፣ ‹‹የእኛና የእነርሱ›› የሚል ዘረኛ ቀይ የጎጥ መስመር ከማጋደም እንቆጠብ፡፡ በብሔር መነፅር ተሸፍነን ‹‹እንዲህ ነን›› ስላልን ‹‹እንዲያ›› እንደማንሆን እንገዘብ፡፡ የባንዲራ ክብር ይታየን፡፡ የዘረኝነት ዋሻ ሊውጠን አይገባም፡፡ ‹‹እኔ ብቻ ልኑር!›› አያዋጣንም፡፡
በጎጥና መንደር የጠበበ ሰው አስፍቶ ማሰብ ያሳንሳልና ከጎጥ አስተሳሰብ እንገነጠል፡፡ ምግባርና ተግባር የጎደለን፣ የሚጨበጥና የሚያዝ የሌለን ልንሆን አይገባም፡፡ ህሊና ሊያድስ፣ ሰውነት ሊመልስ፣ ሃይማኖት ሊፈውሰን ይገባል፡፡
የሀገር ፍቅር ድምጽ ሰማን፡፡ ሁሉንም ወቃሽ ከመሆን እንቆጠብ፡፡ ተጠቅቻለሁ ከሚል በደል ቆጣሪነት እንፋታ፡፡ ከተገፊነት ተረክ እንላቀቅ፡፡ ከሚያነቃቅፈን ይልቅ የሚያስተቃቅፈንን እንምረጥ፡፡ ቃልና ተግባራችን ይመጣጠን፡፡
ባለፈውና ባሳለፍነው አጉል ጊዜ መቆጨትን ማቆም እና ለወደፊቱ መሻልን ማሰብ ልንጀምር ይገባል፡፡ ከማፍረስ ይልቅ መካብ ሊቀለን፣ ሃሳብ ልዩነት ሁሌም ሊቀለን ይገባል። ኋላቀርነት ሊማርከን፣መጥፎ ታሪክ ሊጎትተን፣ዘመን ሊያድሰን፣ክፉ ትናንት ሊቀይረን አይገባም፡፡ ከመጥበብ መስፋትን እንምረጥ፡፡ ለሕዝብ የማይበጅ የሴራ ፖለቲካ መጎንጎን ማቆም አለብን፡፡
በአዲስ ዓመት በዚህ አስተሳሰብ ለመቃኘና አስተሳሰቡን ተግባራዊ ለማድረግ ደግሞ ለዚህ የሚመጥን ጭንቅላት መፍጠር ግድ ይለናል። አስተዋይ ጭንቅላት አንድም ከመጽሐፍ ማሕፀን በንባብ ምጥ የሚወለድ፤ አንድም ትናንትን በማስተዋልና የኋላ ታሪክን ተጠቅሞ በበጎ እሳቤ በመለወጥ እውን የሚሆንን መረዳት ይኖርብናል፡፡ ይህ ማድረግ ከቻልን የተሻለችና በሁሉም መስኮች የተሳካላት ኢትዮጵያን ማየት ህልም አይሆንብንም፡፡
መልካም አዲስ ዓመት
አዲስ ዓመት፣ ሰላም የሞላበት፣ፍቅር የበዛበት ይሆን ዘንድ ከራሳችን ጋር ውል የምትፈፅምበት፣ በአዲስ ሰውነት ለራስ፣ ለወገን፣ ለአገር ቅን አስበህ በጎውን የምንከውንበት ይሁን፡፡
ታምራት ተስፋዬ
አዲስ ዘመን መስከረም 4 ቀን 2014 ዓ.ም