ያሳለፍነው 2013 ዓ.ም በአንድ በኩል መልከ ብዙ በሆኑ ጦርነቶች ውስጥ የነበርንበት እና በብዙ ፈተናዎች የተፈተንንበት፤ በሌላ በኩል ደግሞ ትላልቅ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች በስኬት በማጠናቀቅ የጀመርነው የብልጽግና ጉዞ ተስፋ ሰጪ እንደሆነ የተመለከትንበት ዓመት ነው።
በተጠናቀቀው ዓመት ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ. ም አሸባሪው ህወሓት በሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ ክህደት በመፈጸም ጥቃት አድርሷል። በዚህ የሀገር ክህደት ተግባሩ የሀገርን ልብ የሰበረ፤ በታሪክም መቼም ሊረሳ የማይችል ወንጀል ፈጽሟል። ጥቃቱን ተከትሎም በተካሄደው የህግ ማስከበር ፈጣንና አንጸባራቂ ድል ማስመዝገብ ተችሏል።
ከግንባር ጦርነቱ ባልተናነሰ ሁኔታ አሸባሪው ቡድን በዲጂታል ሰራዊቱ የመረጃ ጦርነት በመክፈት ለዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ የተዛቡ መረጃዎች በስፋት አሰራጭቷል። በዚህም ዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ በጉዳዩ ዙሪያ የተዛባ አመለካከት እንዲይዝ በስፋት ሰርቷል።
ቡድኑ በስልጣን ዘመኑ በፈጠራቸው መርህ አልባ ግንኙነቶችን መሰረት ባደረገ መልኩም አንዳንድ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃንን እና ዓለም አቀፍ ተቋማትን በመጠቀም በመንግሥት ላይ ጫና ለመፍጠር ረጅም ርቀት ሄዷል።
ቡድኑን የራሳቸው ፍላጎት ማስፈጸሚያ ለማድረግ የተንቀሳቀሱ ኃይሎች መሬት ላይ ያለውን ተጨባጭ እውነታ አይተው እንዳላየ በመሆን፤ የቡድኑን የሀሰት መረጃዎችና የፈጠራ ትርክቶች በማስተጋባት በመንግሥት ላይ ከፍ ያለ ጫና ፈጥረዋል። መንግሥት ለትግራይ ሕዝብ እና ለቡድኑ አመራሮች የጥሞና ጊዜ በመስጠት ችግሩን በተሻለ መልኩ ለመፍታት ከዚያም ጎን ለጎን አርሶአደሩ የእርሻ ሥራውን እንዲያከናውንና ከጠባቂነት እንዲወጣ ለማስቻል የደረሰበትን ውሳኔ በመጣስ በአጎራባች ክልሎች ወረራ በማካሄድ ለሰላም ቅንጣጥ ታህል ሀሳብ እንደሌለው አሳይቷል።
በአፋርና በአማራ ክልል ባካሄዳቸውም ወረራዎች የወሮበላነት ባህሪው በተጨባጭ የታየ ሲሆን በዚህም አንድም ተስፋ መቁረጡን ከዚህም በላይ የቱን ያህል ጸረ ሕዝብና ጸረ ኢትዮጵያዊ እንደሆነ አሳይቷል። ከዚህ በተጻራሪም 2013 ዓ.ም ሀገሪቱ የተሳካ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ያካሄደችበት፣ የታላቁ የህዳሴ ግድብ ሁለተኛ የውሀ ሙሌት የተካሄደበትና በግድቡ ዙሪያ የሚደረገው የሦስትዮሹ ድርድር ወደ አፍሪካ ህብረት የተመለሰበትና በዚህም ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ድል የተገኘበት ነው። በአጠቃላይ ለውጡን ተከትሎ በባለፉት ሦስት ዓመታት በውስጥና በውጭ ፀረ-ሰላም እና ጸረ ኢትዮጵያ ኃይሎች ምክንያት እንደ ሀገር ብዙ ፈተናዎችን በጽናት የተጋፈጥንበትና በአሸናፊነት የተሻገርንበት ነው።
ተስፋ ያረግናት የበለፀገች ኢትዮጵያ እውን ለማድረግ ሁለንተናዊ በሚባል ፈተና ውስጥ ያለፍንበት፤ አበቃላቸው ስንባል በብዙ ጽናት ቆመን ለመራመድ የቻልንበት፤ እያንዳንዷ ደቂቃ በብዙ ተግዳሮቶች ተሞልታ የመጣችበትን እና ከፍ ባለ ጽናት የተቋቋምንበት ዓመት ነው። ከገጠሙን ፈተናዎች ይልቅ ፈተናዎቹ የፈጠሩልንን መልካም አጋጣሚዎች በመጠቀም፤ የተገኙ ድሎችን ቀጣይና አስተማማኝ፤ ከዚህም በላይ ለጀመርነው የብልጽግና ጉዞ ተጨማሪ አቅም ለማድረግ የሄድንበት መንገድ ተስፋችንን ከፍ ወዳለ ደረጃ ማድረስ አስችሏል።
ይህንን የፈተና ወቅትና የስኬት ተሞክሮዎችን በአዲሱ ዓመት በለውጥ አስተሳሰቦች በማስፋት የጀመርነው የለውጥ ጉዞ የተሻለ ደረጃ ላይ ማድረስ፤ በዚህም ጠላቶቻችን እጃቸውን እንዲሰበስቡ ማድረግ ይጠበቅብናል። በአዲሱ ዓመት ከፍ ባለ የሀገር ፍቅር መንፈስ ወደ ብልጽግና የምናደርገው ፈተና የበዛበት እልክ አስጨራሽ ጉዞ በተሻለ ቁመና ላይ እንዲገኝ ማድረግ፤ ከትናንት ቀጣይ የሆኑ ድሎችን በማስመዝገብ የይቻላል መንፈሳችንን ማጎልበት ይኖርብናል።
አዲሱ የ2014 ዓመት በሰፊ ሕዝባዊ ምርጫ የተመረጠው አዲስ መንግሥት የሚመሰረትበት፣ ኢትዮጵያውያን ኅብረ ብሔራዊ አንድነታቸውን የሚያጸኑበት፣ ዴሞክራሲያዊ ዕሴቶቻቸውን የሚያጎለብቱበት፣ የተጀመረው ሀገራዊ ሪፎርም መልክ የሚይዝበት፤ለዚህም የሁሉም ተሳትፎ ወሳኝ የሚሆንበት ነው። በአዲሱ ዓመት እያንዳንዳችን ከጥላቻ ይልቅ ፍቅርን፤ ከመበቀል ይልቅ ይቅር ባይነትን፣ ከፀብ ይልቅ ውይይትን፤ ከመጣላት ይልቅ ወዳጅነትን የዕለት ከዕለት ተግባራችን ማድረግ ይኖርብናል።
አዲሱ መንግሥትም ትኩረት ሰጥቶ የሀገሪቱን ሰላም በአስተማማኝ መልኩ ማስጠበቅ፣ የህግ የበላይነትን ማስፈን፣ ዘላቂ ልማትና ዴሞክራሲ በሀገሪቱ ማስፈን፣ ጠንካራ ተቋማትን መገንባት፤ ኢኮኖሚው የሚያገግምበትን መንገድ ማፈላለግ ይጠበቅበታል።
በአጠቃላይ በአዲሱ ዓመት ያጋጠሙንን ተግዳሮቶች ለይቶ በመፍታት ወደ ስኬት የሚወስዱንን ጎዳናዎች በመጥረግ በአዲስ ተስፋ አዲስ ብርሃን የምናይበት እንዲሆን ሁላችንም በተሰማራንበት የሥራ መስክ ሁሉ ከፍ ባለ ኃላፊነት መንቀሳቀስ ይጠበቅብናል!
አዲስ ዘመን መስከረም 4 ቀን 2014 ዓ.ም