ሃገር በቀል እውቀትን የትውልድ መገንቢያ ለማድረግ የኪነ ጥበብ ዘርፍ ትልቅ ድርሻ እንዳለው የትምህርት ሚኒስትሩ ዶክተር ጥላዬ ጌቴ ተናገሩ።
በቀጣይ 15 አመታት በሚተገበረው የትምህርት ስልጠና እና ፍኖተ ካርታ ዙሪያ ከኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ጋር ምክክር እየተደረገ ነው።
በምክክር መድረኩ ላይ ሚኒስትሩ የኪነ ጥበብ ዘርፍ ሃገር በቀል እውቀትን የትውልድ መገንቢያ ለማድረግ ለሚደረገው ጥረት ትልቅ ድርሻ እንዳለው ተናግረዋል።
ሚኒስትሩ ባለፉት 24 አመታት በነበረው የትምህርት ፖሊሲ ላይ የኪነ ጥበብ ዘርፉን በአግባቡ ማሳተፍ እንዳልተቻለም ነው የተናገሩት።
ከዚህ አንጻርም ተማሪዎች ከዘርፉ ጋር ተዛማጅነት ባላቸው ትምህርቶች ውጤታማ እንዳይሆኑ ማድረጉን አንስተዋል።
በቀጣይም ዘርፉ በትምህርቱ መስክ የሚኖረውን ሚና ለማሳደግ መስራት ይገባልም ነው ያሉት።
የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች በበኩላቸው ባለፉት አመታት የነበረው የትምህርት ፖሊሲ ሃገሪቱን ወደፊት እንዳትራመድ አድርጓት መቆየቱን ጠቅሰዋል።
አሁን ላይም ኪነ ጥበቡን በመደገፍ ትምህርትን ጨምሮ በሌሎች ዘርፎች ያለውን ተሳትፎ ለማሳደግ መስራት ይገባል ብለዋል።
ለቀጣዮቹ 15 አመታት በሚተገበረው የትምህርት ስልጠና እና ፍኖተ ካርታ ላይ ካለፈው ሃምሌ ወር ጀምሮ የግብዓት ማሰባሰብ ስራ እየተሰራ መሆኑ ተጠቅሷል።
ኤፍ ቢ ሲ እንደዘገበው በፍኖተ ካርታው ላይ ከ750 ሺህ ሰዎች እንዲሁም ከ16 ተቋማት ጋር ምክክር ተደርጎበታል።