ስፖርት አካልንና አእምሮን በማቀናጀት የሚከወን የእንቅስቃሴ ዓይነት ነው፡፡ ይሁንና አካላዊ ጉዳት ሊያግደው የአእምሮ መታወክም ሊያስቀረው አይችልም፡፡ ይህም ስፖርት የሰው ልጅ የሚፈልገውን ለመከወን ኃያል መሳሪያ ስለመሆኑ የሚያረጋግጥ ነው፡፡ ስፖርት በሰዎች ላይ ሊደርስ ከሚችል አካላዊ ጉዳትና የጤና መጓደል ይከላከላል፣ ከየትኛውም ጉዳት ለማገገም ፍቱን የሆነ መፍትሄም ነው፡፡ ስፖርት አእምሮን ለማሳረፍ፣ ለአካል ጥንካሬ፣ ለበሽታ መከላከል፣ ጉዳትን ድል ለመንሳት፣ ለመዝናናትና ጊዜን ለማሳረፍ፣ ለገቢ ምንጭነት፣ መልካም እሳቤንና ወዳጅነትን ለማስፋፋት እንዲሁም ተዘርዝረው የማያልቁ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች እንዳሉት በሳይንስ ጭምር የተረጋገጠ ነው፡፡
በርካቶች በአካላዊ ጉዳታቸው ምክንያት ራሳቸውን አሳንሰው የሚሹትን ከማድረግ ሲቆጠቡ ማየት የተለመደ ነው፡፡ በተለይም እንደ ስፖርት ባሉ አካላዊ እንቅስቃሴ በሚፈልጉ ጉዳዮች ላይ እንደሚፈልጉት መንቀሳቀስ አዳጋች የሆነባቸው አካል ጉዳተኞች በብዛት ደፍረው ወደ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ለመግባት አይደፍሩም። አካል ጉዳተኞች ስፖርት ካለው እምሯዊና አካላዊ ጠቀሜታ አንጻር በዘርፉ መሳተፋቸው መልካም ቢሆንም፤ ግንዛቤው አናሳ በመሆኑ ደፍረው ወደ ዘርፉ በመግባት ጎልተው የወጡትና ከጥቅሙም ተቋዳሽ የሆኑት ጥቂቶች ብቻ ናቸው፡፡
አካላዊ ጉዳታቸው ያልበገራቸው ብርቱዎች በስፖርቱ ዘልቀው በመግባት ተወዳዳሪ ከመሆን አልፈው አገራቸውን እስከ ማስጠራት ደርሰዋል። በተጠናቀቀው ዓመት መጨረሻ በተካሄደው የፓራሊምፒክ ውድድር የታየውም ይኸው ነበር፡፡ በተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ አደጋዎች በደረሱባቸው ጉዳቶች ሳይበገሩ እንዲሁም በጉዳታቸው ምክንያት የሚፈጠሩ ስነልቦናዊ ሁኔታዎችን አልፈው ከታላቁ መድረክ ክብርን የተጎናፀፉ በርካቶች ናቸው፡፡ ከእነዚህ ብርቱ አካል ጉዳተኛ ስፖርተኞች መካከልም አስተማሪ የሆነ የህይወት ተሞክሮ ያላቸው ጥቂት ስፖርተኞችን በዛሬው የስፖርት ማህደር አምዳችን እንመልከት፡፡
ረያን ቦይል
አሜሪካዊው የፓራ-ብስክሌተኛ ረያን ቦይል ሲወለድ አካላዊና አእምሯዊ ጤናው የተሟላ ነበር፡፡ እስከ 9ዓመቱ ድረስም እንደ ጓደኞቹ እየቦረቀና ትምህርቱን እየተከታተለ ቢቆይም፤ ያልታሰበው አደጋ ግን ህይወቱን በድጋሚ ‹‹ሀ›› ብሎ እንዲጀምር ምክንያት ሆኖታል፡፡ ተወልዶ ያደገባት ኒው ሄቨን የተሰኘችው ከተማ የብስክሌት እንቅስቃሴ በአብዛኛው የተለመደባት በመሆኑ፤ ቦይልም ከልጅነቱ ጀምሮ ብስክሌትን ሊወዳጅ ችሏል፡፡ እድል ፊቷን ባዞረችበት በአንዱ ቀንም ትንሹ ቦይል የጓደኞቹን ልደት አክብሮ ሲመለስ በመኪና ይገጫል፡፡ አደጋውም እጅግ አስከፊ ከመሆኑ የተነሳ ህይወቱ ቢተርፍም ቦይል ግን ራሱን አያውቅም ነበር፡፡
ጭንቅላቱ ላይ ከባድ ጉዳት የደረሰበት ታዳጊ ኮማ ውስጥ ሆኖ (ራሱን ስቶ) ለሁለት ወራት ነፍስ ውጪ ነፍስ ግቢ ትግል ውስጥ ቆይቷል፡፡ የህክምና ባለሙያዎችም የታዳጊውን ህይወት ለማትረፍ ውስብስቡን የአንጎል ቀዶ ጥገና አደረጉለት፡፡ ቦይል ጉዳቱ የደረሰበት በጭንቅላቱ የኋላኛው ክፍል ሲሆን፤ ከወራት በኋላ ሲነቃም የቀኝ አካል ክፍሉን አንዲት ጣት እንኳን ማንቀሳቀስ አይችልም ነበር፡፡ ነገር ግን በተደረገለት ተከታታይ ህክምና ለውጥ በማሳየቱ አዲስ እንደተወለደ ህጻን ህይወትን እንደ አዲስ መለማመድ የግድ ሆነበት፡፡ ያለፈው ጊዜ ከትውስታው ማህደር በመሰረዙም በድጋሚ እንዴት መተንፈስ፣ መመገብ፣ መራመድ፣ መቀመጥና ወዘተ እንዳለበት
ተማረ፡፡
ከጊዜ በኋላም ወደ ትምህርት ቤት ተመልሶ ህይወቱን እንደ ቀድሞው መኖር ሲጀምር፤ አካላዊ ጥንሬውን ለመመለስ ይቻለው ዘንድ ስፖርትን የእለት ከእለት ተግባሩ አድርጎም ነበር፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ሳለም ለሌሎች መማሪያ ሊሆን የሚችለውን የህይወት ታሪኩን የሚዳስስና ‹‹ሁለተኛ የመኖር ዕድል የተሰጠው ልጅ›› በሚል ርዕስ የሰየመውን መጽሃፉን አሳተመ፡፡ ከስፖርቱ መራቅ የማይሆንለት ቦይል በዚያን ወቅት ውሃ ዋናን ያዘወትር ነበር፤ በአንድ አጋጣሚ ግን በድጋሚ ህይወቱን ሊለውጥ የቻለ ስጦታ
ደረሰው፡፡ ይኸውም ስጦታ ከአደጋው በፊት እንደ እኩዮቹ ይቦርቅበት የነበረው ብስክሌት ሲሆን፤ ወደ ስፖርተኝነት እንዲገባም ምክንያት ሆነው፡፡ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን አጠናቆ ወደ ዩኒቨርሲቲ ሲገባም ከትምህርቱ ጎን ለጎን ስልጠናውን እየወሰደ ለአሜሪካ ፓራሊምፒክ ብሄራዊ ቡድን አባልነት ታጨ፡፡ እአአ በ2016ቱ የሪዮ ኦሊምፒክ ተሳትፎውም ለአገሩና ለራሱ የብር ሜዳሊያ በማስመዝገብ ስኬቱን ማጣጣም ቻለ፡፡ በቶኪዮ ፓራሊምፒክም አገሩን ወክሎ ሜዳሊያ ማስመዝገብ ባይችልም በተለያዩ የዓለም ቻምፒዮናዎች ላይ ሜዳሊያዎችን ማስመዝገብ ችሏል፡፡ አስደናቂው የህይወት ተሞክሮውም በሰው ልጅ ህይወት ተስፋ መቁረጥ ቦታ የሌለው መሆኑን በተግባር ያሳየ
ነው፡፡
ዘሀራ ነማቲ
ይቺ ኢራናዊት የቀስት ስፖርት ተወዳዳሪ አካል ጉዳተኛ ከመሆኗ አስቀድሞ የቴኳንዶ ስፖርተኛ ነበረች። ይሁንና በአንድ ያልታሰበ ሁኔታ እኤአ 2004 ላይ በገጠማት የመኪና አደጋ የአከርካሪ አጥንቷ በመጎዳቱ ሰውነቷን ማዘዝ እንዳትችል(ፓራላይዝድ) እንድትሆን አደረጋት። ይሁን እንጂ አትሌቷ በገጠማት የአካ ጉዳት በቀላሉ ተስፋ የምትቆርጥና መንፈሷም የሚረብሽ ባለመሆኑ ከስፖርቱ ሳትርቅ በፓራሊምፒክ ስፖርቶች መሳተፍ ጀመረች። እአአ በ2012 የለንደን ፖራሊምፒክም ለመጀመሪያ ጊዜ በቀስት ውርወራ ተሳታፊ በመሆን አሸነፈች። ይህ ያጠለቀችው የወርቅ ሜዳሊያም ለራሷም ብቻ ሳይሆን ለአገሯም በኦሊምፒክም ይሁን በፓራሊምፒክ ውድድሮች የመጀመሪያው ሆኖ ተመዘገበላት። በቡድን ደግሞ የነሀስ ሜዳሊያ በማግኘቷ ስኬታማ ለመባል በቃች። በ2016 በተካሄደው ቀጣዩ የሪዮ ፓራሊምክም በድጋሚ ስትሳተፍ የአገሯን ባንዲራ በመያዝ ፊታውራሪ ለመሆን ችላለች። የወርቅ እና የብር ሜዳሊያዎችንም አጥልቃለች። የ 36 ዓመቷ አትሌት በሶስተኛ የፓራሊምፒክ ተሳትፎዋም ስኬቷን አስቀጥላ ሌላኛውን የወርቅ ሜዳሊያ አጥልቃለች። ይህም አትሌቷን የብዙ ሴትና የአካል ጉዳተኞች ምሳሌ አድርጓታል፡፡
ብራድ ስናይደር
አገሩ አሜሪካንን በውትድርና ሲያገለገል በቆየበት ወቅት ነበር ጉዳቱ የገጠመው። ስናይደር እኤአ በ2011 በአፍጋኒስታን ግዳጅ ላይ ሳለ በደረሰበት የቦምብ ፍንዳታ ዓይኖቹ የማየት አቅማቸውን ተነጥቀዋል። በዚህም ምክንያት አገሩን እንደቀድሞ ማገልገል ባለመቻሉ ፊቱን ወደ ስፖርት በመመለስ በውሀ ዋና ስፖርት አገሩን ከመወከል አልፎም ውጤታማ እስከመሆን ደርሷል። በሪዮ እና ለንደን ፖራሊምፒኮች ተሳትፏል: በዚህም ለንደን ላይ 2 ወርቅና1 ብር እንዲሁም በሪዮ 3 ወርቅና 1 ብር በጠቅላላው 5 ሜዳሊያዎችን አግኝቷል። ከዚህም ባለፈ በ100 ሜትር ነጻ ዋና የዓለም ክብረወሰን ባለቤት ለመሆን ችሏል። በሶስተኛው የቶኪዮ ኦሊምፒክ ተሳትፎውም አንድ ወርቅ ያስመዘገበ ሲሆን አጠቃላይ ለአገሩ ስድስት ሜዳሊያዎችን በማስመዝገብ ስኬታማ ነው። ወታደሩ ስናይር ስሙ እንዲነሳ ያደረገው አንዱ ደግሞ አዲስ ነገር ከመሞከር ወደኋላ የማይል በመሆኑ ሲሆን፤ በቶኪዮ ፓራሊምፒክ የተሳተፈው ከሚታወቅበት ውሀ ዋና ውጪ በትራይቶሎን ውድድር (ዋና፣ ብስክሌትና ሩጫን ያጠቃለለ) ተሳታፊ በመሆን ስኬታማነቱን ማረጋገጥ ነበር፡፡ ይህ የወታደሩ ስናይደር አይበገሬነትና አዲስ ነገርን የመሞከር ፍላጎትም በብዙዎች ዘንድ አድናቆትን ሲያተርፍለት፤ ብርታቱም ለብዙዎች ምሳሌ አድርጎታል፡፡
ፓርፌት ሀኪዚማና
ከአንድ አካል ጉዳተኛ ጉዳት በስተጀርባ ሰው ሰራሽ አደጋ አሊያም ተፈጥሯዊ ምክንያት መኖሩ እውን ነው። ሠው ሠራሽ ጉዳቶችን ከሚፈጥሩ ጉዳዮች መካከል አንዱ የሆነው ጦርነት ደግሞ የዛሬውን ስኬታማ ስፖርተኛ ሀኪዚማናን ሊፈጥር ችሏል። አሁን ላይ የዓለም ስደተኞችን ወክሎ የተሳተፈው ሀኪዚማና በብሩንዲ የተወለደ ሲሆን፤ የስምንት ዓመት ታዳጊ ሳለ በአገሪቷ በተነሳው ጦርነት ምክንያት በጥይት ተመታ። በወቅቱ እሱ እጁን ሲመታ ወላጅ እናቱ ላይመለሱ አንቀላፉ። ወታደር አባቱ እርሱን ለማዳን ወደ ሀኪም ቤት ቢወስዱትም ከሁለት ዓመት በላይ በህክምና ክትትል ስር ቆይቶ አንድ እጁን ለማጣት ተገደደ። በኋላም በስደተኝነት በሚኖርበት ሩዋንዳ በሚገኝ የስደተኛ ጣቢያ ወደ ቴኳንዶ ስፖርት በመግባት ውጤታማነቱን ከማስመስከር አልፎ የስደተኞች ቡድንን ወክሎ ለፖራሊምፒክ ውድድር መሳተፍ ከቻሉ 6 አትሌቶች መካከል አንዱ ሆኗል። በ61 ኪሎ ግራም ቶኪዮ ላይ የተሳተፈው ሀኪዚማና ለበርካታ አካል ጉዳተኞችና ስደተኞች አስተማሪ የሆነ ታሪክ አለው። ስፖርት በጉዳቱ እንዳይወሰን ያደረገው ሲሆን፤ ለስደተኝነት ህይወቱ አንዱ ማጣፈጫ እንዲሁም በልጅነቱ የተለዩት ቤተሰቦቹን ሃዘን መርሻ ሆኖታል፡፡ እንደ እርሱ አባባል ከሆነም “ስደተኞች ምንም አይኖራቸው ይሆናል፤ ነገር ግን ስፖርት ችግራቸውን ሁሉ ሊያስረሳቸው ይችላል” ይላል።
ኤሊ ኮል
በቶኪዮ አራተኛ የፓራሊምፒክ ተሳትፎዋን ያደረገች ውጤታማ አውስትራሊያዊት ዋናተኛ ናት። ኮል ለአካል ጉዳተኝነት የተዳረገችው በህመም ምክንያት ሲሆን፤ ገና በሶስት ዓመቷ ባደረባት የካንሰር በሽታ አንድ እግሯን አጥታለች። ታዲያ በወቅቱ የህክምናው አንድ አካልና ሠውነቷን በድጋሚ ወደ ብርታት እንዲመለስ የሚያደርጋት አካላዊ እንቅስቃሴ ነበር። በመሆኑም እግሯ በተቆረጠ በስምንተኛው ሳምንት በውሀ ዋና መሳተፍ ጀመረች። በሜልቦርን ውሀማ አካባቢዎች መወለዷ የጠቀማት ኮል ለሰውነቷ ጥንካሬና ማገገሚያ የጀመረችው ዋና አብሯት አድጎ በፓራሊምፒክ አገሯን እንድትወክል ያስቻላት ሆኗል። የ29 ዓመቷ ዋናተኛ በአራት ፓራሊምፒኮች የተሳተፈች ሲሆን፤ በ 100 ሜትር የጀርባ ቀዘፋ ቻምፒዮን ናት። 15 ሜዳልዎችን በስሟ ማስመዝገብ የቻለች ስፖርተኛም ናት። ከእነዚህም መካከል 6 የወርቅ ሜዳሊያዎችን ያገኘችው እአአ በ2008 በተካሄደው የቤጂንግ ፓራሊምፒክ ነው።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን መስከረም 2 ቀን 2013 ዓ.ም