የአዲሱ ዓመት መጀመሪያ መስከረም 2/2014 ዓ.ም ላይ እንገኛለን። መላው ኢትዮጵያውያን ዘመኑን በፍቅርና በአንድነት መንፈስ ተቀብለው መጪውን ግዜያት በብሩህ ተስፋ ይጠብቃሉ። ከቅርብ ዓመታት በኋላ ኢትዮጵያ “አስቸጋሪ” የሚባል ፈተና ውስጥ የገባች ቢመስልም ትንሳኤዋ ግን እሩቅ እንዳልሆነ ሁሉም ዜጎቿ በልበ ሙሉነት ያምናሉ። ለዚህም ነው ዓዲሱን ዓመት በፍፁም ቅንነትና አገር ወዳድነት እየተቀበሉት የሚገኙት።
ወርሃ መስከረም “አዲስ ዓመት” የምንጀምርበት ከመሆኑም በላይ እጅግ ብዙና አስደናቂ ታሪኮችንም ያስታውሰናል። አባቶች በተለያዩ መዛግብት እንዳሰፈሩልንም «መስከረም» ከግዕዙ «ከረመ» ከሚለው ግስ የተባዛ ነው። በተጨማሪነትም «መሰስ-ከረም» (ክረምቱ መሰስ ብሎ ማለፉን)፣ ወይም «መዘክረ-ዓም» (የዓመት መታወሻ) እንደሚባል ያስረዱናል።
ከላይ ለማንሳት እንደሞከርነው ወርሃ “መስከረም” በኢትዮጵያውያን ዘንድ ትልቅ ስፍራ ይሰጠዋል። የተፈጥሮ ኡደት ተቀይሮ ምድር በአሸብራቂው “አደይ አበባም” ከመሞላቷ ባሻገር ይሄ ግዜ በታሪክ፣ ፖለቲካና በትውስታ ማህደር ውስጥ አያሌ ትዝታዎችንም የሚጭር ነው። በተለይ ሁሉም ኢትዮጵያውያን የዛሬዋን እለት “መስከረም ሁለት” ቀንን በልዩ ሁኔታ ያስታውሱታል።
በዋናነት ኢትዮጵያውያን መስከረም ሁለትን የሚያስታውሱበት ምክንያት ግርማዊ ቀዳማዊው አፄ ሃይለስላሴ “በደርግ” ወታደራዊ መንግስት ከዙፋናቸው በመፈንቅለ መንግስት እንዲለቁ መደረጉን ምክንያት በማድረግ ነው። ከቤተ መንግስት እንዲወጡና ስልጣናቸውን እንዲያስረክቡ የተገደዱት ጃንሆይ ጥቂት ቆየት ብሎ ባልታወቀ ምክንያት ህልፈተ ህይወታቸው ተሰምቷል። ይሁን እንጂ ቀዳማዊ ዓፄ ሃይለስላሴ በደርግ ሴራ እንዲገደሉ መደረጉን የተለያዩ የታሪክ መዛግብትና የቅርብ እረዳቶቻቸው መስክረዋል።
ቅድመ ደርግ -የስርዓት ለውጥ ጥንስስ
በግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ሃይለስላሴ የአገዛዝ ዘመን በርካታ ቅሬታዎች ይነሱ ነበር። በተለይ የባላባቱና የሰራተኛው መደብ ፅንፍ የወጣ ልዩነትና የምጣኔ ሃብት በደል በአንዳንድ ተራማጅ ሃይሎች ዘንድ ከፍተኛ ማጉረምረም እንዲከሰት አድርጓል። የአስተዳደር በደሎች፣ የፍትህ መዛባት፣ ዲሞክራሲያዊ መንግስት ምስረታ መጓተት፣ የርእዮተ ዓለም ልዩነትና በምሁራኑ መካከል የተፈጠረ መከፋፈል አራት አስርት ዓመታት የዘለቀውን የንጉሱን ስርዓት እንዲነቃነቅ ትልቁን ድርሻ እንደተወጣ ይነገራል። ጃንሆይን ከዙፋናቸው ለማውረድና አዲስ ስርዓት ለመመስረት የተደረገው ከፍተኛ እንቅስቃሴ የተጀመረውም ደርግ በመፈንቅለ መንግስት ስልጣኑን “መስከረም ሁለት” 1967 ዓ.ም ከመቆጣጠሩ በርካታ ዓመታት በፊት ነበር። ከዋና ዋና እንቅስቃሴዎቹ መካከልም የታህሳስ ግርግር እየተባለ የሚጠራው በሁለቱ ወንድማማቾች (መንግስቱ ንዋይና ገርማሜ ንዋይ) የተመራውና ያለ ውጤት የተደመደመው ስሂረ መንግስት አንዱ ነበር።
በዋናነትም ገርማሜ ንዋይ እና የክቡር ዘበኛው አዛዥ ጄኔራል መንግስቱ ንዋይ የመፈንቅለ መንግስቱ ጠንሳሽ ሆኑ። ሁለቱ ወንድማማች ሌሎች ተባባሪዎችን ከጐናቸው አሰለፉ። ዋና ተባባሪያቸው የደህንነት ሹሙ ኮሎኔል ወርቅነህ ገበየሁና የፖሊስ ኮሚሽነሩ ጄኔራል ፅጌ ዲቡ ናቸው። ንጉሡ ለጉብኝት ወደ ብራዚል ማምራታቸውን እንደመልካም አጋጣሚ ተጠቅመው ታህሳስ 3 ቀን 1953 አብዛኛውን የአዲስ አበባ አካባቢና እንደ የገንዘብ ሚኒስቴር ፣ብሔራዊ ባንክና ሬዲዮ ጣቢያ ያሉ ዋና ዋና የመንግስት መስሪያ ቤቶችን ተቆጣጠሩ።
ንጉሠ ነገሥቱ ዜናውን በመስማታቸው በደቡብ አሜሪካ የሚያደርጉትን ጉብኝት አቋርጠው አደጋ ላይ የወደቀውን ዙፋናቸውን ለማዳን መገስገስ ጀመሩ። የንጉሱ ታማኞችም መፈንቅለ መንግስቱን ለማክሸፍ ተዘጋጁ። የጦር ኃይሎች ኤታማዦር ሹም ሜጄር ጄኔራል መርዕድ መንገሻ የሚመሩት የምድር ጦር ኃይል የክብር ዘበኞችን እንቅስቃሴ ለማኮላሸት ተንቀሳቀሰ። አየር ኃይሉን ከጐናቸው አሰልፈው የፓትርያርኩ የአቡነ ባስልዮስ የውግዘት ቃልን ጨምሮ መፈንቅለ መንግስቱን የሚያወግዙ በራሪ ወረቀቶች እንዲበተኑ አደረጉ። ከመፈንቅለ መንግስቱ በተጻራሪ የቆሙ ወታደሮች ከዳር አገር ወደ አዲስ አበባ ተሰበሰቡ። ይህን የተባባረ ኃይል ለመቋቋም የክብር ዘበኛና በብርጋዴር ጄኔራል ጽጌ ዲቡ የሚመራው የፖሊስ ሰራዊት በቂ አልነበረም።
እነ ጄኔራል መንግስቱ ንዋይ ሙከራቸው እየከሸፈ መሆኑን ተረዱ። በዚህ ጊዜ ከአገቷቸው ሹማምንት መካከል ታህሳስ 6 ቀን 15 ባለሥልጣኖችን ረሸኑ። መንግስቱ እና ገርማሜም ከአዲስ አበባ በመውጣት ሽሽት ጀመሩ። ወንድማማቾቹ ከተማውን ለቀው ሲወጡ ንጉሡ በድል ወደ ከተማዋ ገቡ። የደህንነት ክፍሉ የበላይ ኮሎኔል ወርቅነህ ገበየሁ ራሳቸውን አጠፉ። ገርማሜ ዝቋላ አካባቢ ከሚያድኑት ፖሊሶች እና ወዶ ዘማቾች ጋር ተታኩሰው ሞቱ። መንግስቱ ንዋይ ክፉኛ ቆስለው ወደ አዲስ አበባ ከመጡ በኋላ ለፍርድ ቀርበው በስቅላት ተቀጡ።
እንግዲህ ጃንሆይን ከስልጣን ለማውረድ የተደረገው የመጀመሪያውና ትልቁ ስሂረ መንግስት በተለምዶው “የታህሳስ ግርግር” እየተባለ የሚጠራው ነበር። ይሄ ሙከራ የስርዓት ለውጥ ሊመጣ እንደሚችል ንጉሱን ከመቃወም ጀምሮ አመፅ አስነስቶ ለማውረድ ጥረት መደረግ የመጀመሩ ትልቅ ምልክት ነበር።
ጃንሆይና የምሁራኑ ምክር
ሌላው በድህረ የደርግ ስርዓት የግርማዊ ቀዳማዊ ሃይለ ስላሴ የቅርብ ወዳጆችና ስርዓቱን በማገልገል ላይ የነበሩት ምሁራን “ስርዓቱ ከዓለም ፖለቲካና ርእዮተ ዓለም ጋር ሊመጣጠን አለመቻል፣ ከጃንሆይ ስር ስር በማለት በርካታ ጉድለቶች የሚፈፅሙና ህዝብን የሚበድሉ ባለሟሎች እየበዙ መምጣታቸው ፣ እንዲሁም ከሁኔታዎች ጋር እየተቀያየረ የሚሄድ የዲሞክራሲ ግንባታና አስተዳደር መዋቅር መገንባት አስፈላጊነት” ጠቅሰው እነዚህን ጉዳዮች በፍጥነት መርምረው “ንጉሰ ነገስቱ” የማሻሻያ ውሳኔዎችን የማያሳልፉ ከሆነ “ለስልጣናቸውም ሆነ ለአገር መተራመስ” ትልቅ ስጋት እንደሚፈጥር በተደጋጋሚ በበጎ መልኩ ምክር ለግሰው ነበር።
ከነዚህ ታላላቅ ምሁራንና የስርዓቱ አገልጋዮች መካከል ደግሞ ክቡር አምባሳደር ብርሃኑ ድንቄ ይገኙበታል። እርሳቸው ቀስ እያለ ከስር እየበሰበሰና ከያቅጣጫው ገፍተው ሊጥሉት የሚቋምጡትን ሴረኞች በመታዘባቸው እራሳቸውን “ከአምባሳደርነት” ስልጣናቸው ከማግለላቸውም በላይ “ትንቢታ” ምክራቸውን ቀጥታ ለጃንሆይ እንዲደርስ በማሰብ “በደብዳቤ” አድርሰዋል።
የየካቲት 1966 ዓ.ም አብዮት ፍንዳታን ተከትሎ መስከረም 2 ቀን 1967 ዓ.ም ዘውዳዊውን ሥርዓት ገርስሶ ሥልጣኑን የጨበጠው ወታደራዊ ደርግ ከ60 በላይ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት ከፍተኛ ሹማምንት፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩን፣ የአፄ ኃይለ ሥላሴን የልጅ ልጅና ከደርግ አባላት ጥቂቱን ጨምሮ መግደሉ የሚታወስ ነው። ታዲያ ይህ አምባ ገነናዊ ስርዓት ከመመስረቱ አስቀድሞ በዲፕሎማሲው ሜዳ ታላቅ ገድል እንደፈፀሙ የሚነገርላቸው አምባሳደር ብርሃኑ ድንቄ “የሪፎርም” መደረግ አስፈላጊነትና ያ ካልሆነ የሚከተለውን አደጋ ያመላከቱበት ከዚህ በመቀጠል ቀንጭበን የምናቀርብላችሁን ትንቢታዊ ደብዳቤ ለጃንሆይ ፅፈው ነበር።
“…ጃንሆይ! በኢትዮጵያ ወጣቱ ሽማግሌው ሴቱ ወንዱ የአኗኗሩ ዘዴ ውሉ
ተዘባርቆበታል፡፡ አምላካችን፣ፈጣሪያችን እያለ ቢደልልዎት
አይመኑት፡፡ ጨንቆት ነው፡፡ ከልብ የሚመርቅዎት ግን ራስህን አስተዳድር ብለው አርነት ሲያወጡትና ወደ ዴሞክራሲ ሲመሩት ነው፡፡ ይህንንም ስል ሕዝብ በራሱ ሲተዳደር ችግር አይገጥመውም ማለቴ አይደለም፡፡ እስከዚህ
አልሳሳትም፡፡ ነገር ግን ሌላው ለፍቶ ከሚጥለውና ላንሣህ ከሚለው፣ ራሱ ወድቆ በራሱ መነሣትን ይመርጣል፡፡ ይኽም በሥሕተት መማር ይባላል፡፡ ስለዚህ ጃንሆይም ተሳሳቱ እያለ ከሚከስዎት እርሱ ለሥሕተት እንዲጸጸትና እንዲማር ቢያደርጉት ትልቅ ውለታ ይቆጠራል፡፡
የዛሬው ሕገ መንግሥት ዴሞክራሲን ለማስገንባት የሚረዳ ካለመሆኑም በላይ ያንኑም ቅሉ አክብሮ ለመጠበቅ በአንቀጽ ፳፩ (21) እንደተመለከተው ከንጉሠ ነገሥቱ በመሐላ የተሰጠው ቃል ፈርሷል እያሉ አያሌ ኢትዮጵያውያን እንደሚያማርሩ ግርማዊነትዎ ሳይሰማው አይቀርም፡፡ መቸም ሕገ መንግሥቱን፣ ለመጣስ አንድ የጽሕፈት ሚኒስቴር ደብዳቤ ይበቃል፡፡ እንግዲህ ሕዝቡ ወይም ሹማምንቱ ለንጉሠ ነገሥቱ ታማኝ ነኝ እያሉ ቢምሉም፣ ንጉሠ ነገሥቱ በበኩሉ መሐላውን የሚጠብቅ ካልሆነ በመሐላቸው ታስረው እንደማይኖሩ በልጅ ኢያሱ ጊዜ የደረሰው ሁኔታ ምሳሌ ሊሆን ይችል ይመስለኛል፡፡
በአሁኑ ጊዜ የገጠመንን ፕሮብሌም (ችግር) እንደ መጠኑ ለመግለጥ ‹‹በግርማዊነታቸው መንግሥት ያገኘሁት ኤክስፔሪያንስ (ልምድ)›› የሚለው መጽሐፌ በሙሉ ታትሞ እስከወጣ ድረስ ፲፪ኛውን (12ኛውን) ምዕራፍ ከዚህ ጋር አያይዤ ለግርማዊነትዎ በትህትና አቀርባለሁ” የሚል መልክት ለንጉሱ አድርሰው ነበር። እስራቸው ከላይ በጥቂቱ ቀንጭበን ባስነበብናችሁ ምሁራዊ ምክርና የዲሞክራሲ ግንባታ በጃንሆይ ይሁንታ አንዲገነባ የሚጠይቅ ምክር ቢለግሱም ጆሮ የሚሰጣቸው ማግኘት አልቻሉም። ይህ እየገነገነ የመጣው ችግርም “የደርግ” ወታደራዊ ስርዓት እንዲወለድና ታሪክ በቁጭት የሚያነሳቸው ስህተቶች እንዲፈጠሩ ምክንያት ሆኗል።
የደርግ ስርዓት ጅማሮ-መስከረም ሁለት
ጃንሆይም ለአራት አስርት ዓመታትን ለዘለቀ ግዜ “በንጉሰ ነገስትነት” የስልጣን ዙፋን በአንባገነናዊ የወታደር ስርዓት እጅ ይወድቅ ዘንድ ግዜው ደረሰ። ከውስጥ ሆነው በሴራ ፖለቲካ ጃንሆይን ለመጣል እስከ አበሩትና በግልፅ በአደባባይ ተቃውሞ እስካስነሳው “የመሬት ላራሹ” የተማሪዎች እንቅስቃሴ ጀምሮ በርካታ ጉዳዮች ለስርዓቱ መፈራረስ የራሳቸውን ድርሻ ያዙ። ዋናው ግን ሳይታሰብ በአገሪቱ ከሚገኙ 42 የጦር ክፍሎች ሦስት ሦስት ወኪሎች ወደ አዲስ አበባ እንዲመጡ ከተወሰነ በኋላ መደበኛ ስብስባ በማድረግ በወታደሩ ሃይል “ደርግ” እንዲቋቋም መደረጉና አቢዮቱን በቀዳሚነት መምራቱ ነበር። በተለይ በአነጋገር ጥንካሬው፣ በፈጣን ውሳኔ ሰጪነቱ ታዋቂነት ያተረፈው መንግስቱ ኃይለማርያም “ኢትዮጵያ ትቅደም” የሚለውን መፈክር ካስተዋወቀ በኋላ ተቀባይነትን በማግኘቱ የዚሁ ኮሚቴ ሊቀመንበር ሆኖ ተመረጡ። 1967 መስከረም 2 ኮሚቴው “ግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ሃይለስላሴን” በይፋ ማሰናበቱን አወጀ። የእርሳቸውን ከዙፋን መሰናበት የሚያውጅ ፅሁፍ በጃንሆይ ፊት ያደረጉት ሻለቃ ደበላ ዲንሳ እንደሆኑ የተለያዩ መዛግብት ነግረውናል። የደርግ ስርዓት ለ17 ዓመታት መንበረ ስልጣኑን ሲቆጣጠር ፕሬዚዳንት መንግስቱ ሃይለማሪያም አገሪቷን ፊት መስመር ላይ ሆነው መርተዋል። መስከረም ሁለትም ብሄራዊ በዓል ሆኖ እንዲከበር ተወስኖ ነበር። ወያኔ 1983 ዓ.ም የደርግ ስርዓትን ጥሎ በዘር ፖለቲካ አገሪቱን መዘወር በጀመረበት ግዜም ይህ ቀን ተሰርዞ ትህነግ መራሹ ኢህአዴግ እስከወደቀበት 2010 ዓ.ም ድረስ በግንቦት 20 እንዲተካ ተደረገ። ይህን ፖለቲካዊ ክስተትም ታሪክ “በታላቁ ዶሴ” ከትቦት ትውልድ ሲያስታውሰው ይኖራል።
ዋቢ መፅሃፍት- ፍሰሃ ደስታ “አብዮቱና ትዝታዬ”፣ “ህይወቴና የኢትዮጵያ እርምጃ” አንደኛ መፅሃፍ፤ ፍሬ ከናፍር፤ አምባሳደር ብርሃኑ ድንቄ “ቄሳርና አብዮት”
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን መስከረም 2 ቀን 2013 ዓ.ም